በየዓመቱ የሚከበረው የሲዳማ ብሄር ፍቼ ጨምበላላ በዓል በሀዋሳ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።በበዓሉ የሲዳማ ወጣቶች፣ አባቶችና እናቶች ግርማ ሞገስ በሚሰጣቸው ባህላዊ አልባሳት ተውበውና ደምቀው ከየአቅጣጫው ወደ አዳባባዮች ብቅ ሲሉ የተለየ የደስታ ድባብ አለው፡፡
ከተለያዩ የሲዳማ ዞን ወረዳዎች ተወጣጥተው በዓሉን ከታደሙት የብሄሩ ተወላጆች ባሻገር በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከሚገኙና ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ ብሄሮችና ብሄረሰቦችም በየራሳቸው ባህላዊ አለባበስባና አጋጌጥ ደምቀው የበዓሉ ታዳሚ ሆነዋል።ከኦሮሚያ ክልል የመጡትም ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ሰጥተውታል።
የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ቃሬ ጫዊቻ እንደተናገሩት፤ ፍቼ ጨምበላላ ሲዳማ ለኢትየጵያና ለዓለም ህዝብ ያበረከተው ትልቁ ስጦታ ነው።በሰው ልጆች መካከል ልዩነት ሳይደረግ የሚከበር በዓል ነው።ሁሉን የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፍ መሆኑ ለየት ያደርገዋል።
በዓሉ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያጎለብትና ማህበራዊ ትስስርን የሚያስተሳስር ገመድ ነው ያሉት አቶ ቃሬ፤ በዓሉ በሲዳማ ውስጥ የተወለደና በዘመናት ውስጥ ያልተከለሰ በክብር የተጠበቀ ጥንታዊ የሰው ልጅ ጥበብ ውጤት ነው ይላሉ፡፡
ፍቼ ጨምበላላ በውስጡ የሰላም፣ የመቻቻል፣ የመከባበርና የአቃፊነት እሴቶችን ያቀፈ ነው ያሉት ደግሞ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ናቸው።በሲዳማ ባህል ቂም ይዞና ተኮራርፎ ከዓመት ዓመት መሸጋገር የተከለከለ ነው።ተኳርፈው የቆዩ ባልና ሚስት እንኳ ታርቀው አብሮነታቸውን የሚያስቀጥሉበት ታላቅ በዓል መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡
በፍቼ ጨምበላላ ከቄጣላና ከሌሎች ጭፈራዎች ባሻገር የሰላምን፣ የፍቅርን፣ የመቻቻልንና አቃፊነት እሴቶችን ጭምር ለማክበር የሚረዳ ነው ያሉት አቶ ሚሊዮን፤ በዓሉ ተራ የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን በውስጡ አብሮነትን፣ሰላምንና እርቅን የያዘ መሆኑን ይገልጻሉ።እንስሳትና እጽዋት ጭምር ክብር የሚያገኙበት ለሰላም የተለየ ቦታ የሚሰጥበት መሆኑንም ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ሚሊዮን ማብራሪያ፤ አባቶች ለዘመናት ባካበቱት ጥበብ ከዋክብትን በመመራመር፤ ለአንድ ወር ያክል በጾም ጭምር ራሳቸውን በማዘጋጀት ከዘመን ዘመን ለልጆቻቸው ያስተላለፉት ታላቅ በዓል ነው።
በበዓሉ መልዕክት ያስተላለፉት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፤ የሲዳማ ህዝብ የሰለጠኑ የሚባሉ ህዝቦች ያሏቸው ሁሉም ባህሎችና ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ስርዓት ያለው ከመሆኑም ባሻገር፤ ከዘመን ወደ ዘመን የሚሸጋገርበት የራሱ እውቀት ያለው፤ በዘመን መለወጫ ውስጥ በይቅርታ በሰላም፣ በአንድነት ከትናንት ይልቅ የወደፊቱን በማየት ምኞቹን የሚገልጽበት ትልቅ በዓል መሆኑን ነው የጠቀሱት።
የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳ በበኩላቸው፤ የዘመናት ውጣ ውረዶች ሳይበግራቸው፤ ሳይበረዙና ሳይከለሱ ተጠብቀው ለትውልድ ከተሸጋገሩ በዓሎች መካከል የሲዳማ ህዝብ የዘመን መለወጫ ፍቼ ጨምበላላ ለአብነት የሚጠቀስ በዓል ነው ይላሉ።በዓሉ ከሲዳማ አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን ብሎም ከዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ በመሆን የሀገሪቱን ስምና ዝና በዓለም እንዲተዋወቅ ካደረጉ ውብ ባህላዊ ገጽታዎች መካከል አንዱ መሆኑን ያነሳሉ።
እንደ ዶክተር ሂሩት ማብራሪያ፤ ባህል ህዝብን የሚያቀራርብ የስህበት ሀይል ነው።አንዱ ከሌላው ወገኑ ጋር በፍቅርና በመተሳሰብ እንዲኖር የሚያስችል ገመድ ነው።ፍቼ ጨምበላላም መላው ኢትዮጵያውያንና የዓለም ህዝብን በፍቅርና በጥበብ አስተሳስሮ ባማረና ባሸበረቀ ሁኔታ ሊያሰባስብ ችሏል፡፡
ፍቼ ጨምበላላን የመሳሰሉ ብርቅዬ ባህላዊ እሴቶች በሚገባ ተጠብቀውና ተሰንደው ለቀጣዩ ትውልድ ከነሙሉ ክብራቸው እንዲተላለፉ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ያሉት ዶክተር ሂሩት፤ በክልልና በፌዴራል ያሉ ተቋማት ፍቼ ጨምበላላን ጨምሮ ሌሎች ባህላዊ እሴቶችን ተጠብቀው ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፉበት ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን ሊያቀርቡ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባህላዊ እሴቶች እንዲጠበቁና እንዲቆዩ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር እንደሚሰራም ነው የገለጹት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 24/2011
መላኩ ኤሮሴ