ንጉሥ ላሊበላ እና የገና በዓል

ከዛሬ 896 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ልክ በገና በዓል ዕለት ታኅሣሥ 29 ቀን 1120 ዓ.ም አጼ ላሊበላ ተወለዱ:: የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ እነሆ 850 ዓመታት ሆናቸው:: ንጉሥ ላሊበላ እነሆ በዚህ ዓለም አቀፍ ንብረት በሆነው የላሊበላ ሚሊኒየም ተሻጋሪ ቅርስ ሲታወሱ ይኖራሉ:: በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 900 ዓመታትን ወደኋላ መለስ ብለን ንጉሥ ላሊበላን እናስታውሳለን:: ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች በዚህ ሳምንት የተከናወኑ ዓለም አቀፍ እና የሀገር ውስጥ ክስተቶችን እናስታውስ::

ከ99 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃንና የጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ የነበረው ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ ተመሰረተ (ለሕትመት በቃ):: አንጋፋው ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› መስከረም 3 ቀን 1914 ዓ.ም በንጉሥ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) መኖሪያ ግቢ ውስጥ ጨው ቤት በሚባለው ባለ ሁለት ክፍል ውስጥ ሥራውን ጀመረ:: ማተሚያ ቤቱም ታኅሣሥ 23 ቀን 1917 ዓ.ም “ብርሃንና ሰላም” የተባለውን ጋዜጣ ማተም ሲጀምር ስሙም ከዚሁ ጋዜጣ ወረሰና ‹‹ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት›› ተባለ:: ይህም ማተሚያ ቤቱ ጋዜጦችን እንዲያትም (የማተም አገልግሎት እንዲሰጥ) አስቻለው::

‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ በ500 ቅጂዎች ያህል በሳምንት አንድ ጊዜ (ሐሙስ ዕለት) ይታተም፤ የስርጭቱም በሁለት ፈረሰኞች አማካኝነት ይካሄድ እንደ ነበር ታሪክ ያስረዳል።

ጋዜጣው ሲመሠረት (ከ1917) ጀምሮ እስከ 1921 ዓ.ም ድረስ የጋዜጣው ዳይሬክተር (ዋና አዘጋጅ ለማለት ነው) የነበሩት አቶ ገብረክርስቶስ ተክለሃይማኖት የተባሉት የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሥራ አስኪያጅ ነበሩ:: በ1921 ዓ.ም አቶ ማኅተመወርቅ እሸቴ የጋዜጣው ዳይሬክተር ሆኑ::

ጊዜው ለኢትዮጵያ የብርሃንና የደስታ (ሰላም) እንዲሆን በመመኘት (በማሰብ) ንጉሥ ተፈሪ መኮንን የጋዜጣውን ስያሜ ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ብለው እንደሰየሙት ይነገራል።

ሌላኛው የዚህ ሳምንት ክስተት ከ27 ዓመታት በፊት ታኅሣሥ 23 ቀን 1989 ዓ.ም ጋናዊው ዲፕሎማት ኮፊ አናን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 7ኛው ዋና ፀሐፊ ሆነው ተሾሙ:: በተለይም በኢትዮጵያ ሚሊኒየም ዋዜማ የኮፊ አናን ስም በተደጋጋሚ ይጠራ ነበር:: ምክንያቱም ያ ወቅት ኮፊ አናን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊነቱን ያጠናቀቁበት ወቅት ነበር::

ከ6 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በዘመናዊ የኢትዮጵያ የሕክምና ታሪክ ጉልህ ስፍራ ያላቸው፣ ስለበሽተኞች የምርመራ ሪፖርት አያያዝ የሚያስረዳ በኪስ የሚያዝ መመሪያ (A Guide to Write Writing Medical Case Reports) አዘጋጅተው በሥራ ላይ እንዲውል ያደረጉት፣ ፕሮፌሰር ዶክተር ዕደማርያም ፀጋ አረፉ::

ከ121 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 24 ቀን 1895 ዓ.ም የፊደል ገበታ አባት የሚባሉት እና አርበኛው ቀኛዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ ተወለዱ:: ቀኝ አዝማች ተስፋ ገብረሥላሴ የአማርኛ ፊደል ሆሄያትን በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል ለማስተማር በእግራቸው ብዙ የዞሩ እና ያስተማሩና “የፊደል አባት” የሚል ማህበራዊ ማዕረግን ያገኙ ሰው ናቸው:: በጣሊያን ወረራ ወቅትም ከፍተኛ የአርበኝነት ሥራ ሰርተዋል::

ከ6 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ታኅሣሥ 26 ቀን 2010 ዓ.ም የመጀመሪያው አፍሪካዊ ‹‹የንግድ ጄት›› አብራሪ የሆኑት ኢትዮጵያዊው ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ አረፉ::

ካፒቴን ዓለማየሁ ገና ከአስር ዓመታቸው ጀምሮ አውሮፕላን በሰማይ ላይ ሲበር ሲያዩ አውሮፕላን አብራሪ የመሆን ሕልም እንደነበራቸው በተለያዩ ፀሐፊያን የተሰነደው ታሪካቸው ያሳያል:: ህልማቸውን ለማሳካት ጠንካራ ትጋትና ሥነ ምግባር የነበራቸው ካፒቴን ዓለማየሁ፣ በ1955 ዓ.ም የመጀመሪያውን ‹‹የንግድ (Commercial) ጄት›› በማብረር በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ኢትዮጵያዊ፤ እንዲሁም አፍሪካዊ ለመሆን በቅተዋል::

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ወደ ጄት ዘመን ሲሸጋገር ከፋና ወጊ አብራሪዎች ተጠቃሹ ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ነበሩ:: የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ‹‹ቦይንግ 720B›› አውሮፕላን በካፒቴንነት ያበረሩት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ በዚሁ ተግባራቸው ‹‹የመጀመሪያው›› አፍሪካዊም ናቸው:: በኅዳር 1955 ዓ.ም ቦይንግ ጄት ከሲያትል (አሜሪካ) ከቦይንግ ፋብሪካ አውሮፕላኑን እንዲያመጡ የተደረጉት ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ እና ካፒቴን አዳሙ መድኃኔ ነበሩ::

ካፒቴን ዓለማየሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመቀላቀል የቻሉት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በኩል በማለፍ ነው:: በወቅቱ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት ያጠናቀቁ ተማሪዎች ወደ አቪዬሽን ትምህርት እንዲገቡ ሲደረግ ከዕድሉ ተጠቃሚዎች መካከል አንዱ ካፒቴን ዓለማየሁ ነበሩ:: በ1943 ዓ.ም ምርጥ የሆኑ አብራሪዎች ከአየር ኃይል ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲዛወሩ በተወሰነው መሠረት፣ ካፒቴን ዓለማየሁ ከተመራጮቹ አንዱ መሆን ችለው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተቀላቀሉ::

በሦስት አስርታት ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገልግሎት ዘመናቸውም ከመጀመርያ የበረራ መኰንንነት እስከ ካፒቴንነት (ከየመጀመሪያው የቦይንግ 720B ጄት ካፒቴንነት) እስከ አየር መንገዱ የበረራ ዘርፍ ምክትልና ዋና ኃላፊነት (ከ1948 እስከ 1960 ዓ.ም) ድረስ ሠርተዋል:: ከ1961 እስከ 1972 ዓ.ም. ደግሞ የዓለም አቀፍ በረራዎች ዳይሬክተር፣ የበረራ ኦፕሬሽን ረዳት ጄኔራል ማኔጀር ሆነው አገልግለዋል:: በ1968 ዓ.ም. የመጀመሪያው አፍሪካዊ የቦይንግ 707 ጄት ካፒቴን ሆነው ሲሾሙ፣ በ1972 ዓ.ም የጄት ካፒቴኖች ፈታኝ በመሆን አገልግለዋል::

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎታቸውን በ1974 ዓ.ም ፈጽመው ከተሰናበቱ በኋላ፣ በኡጋንዳና በየመን አየር መንገዶች ውስጥ በአሠልጣኝነትና በአማካሪነት ለአምስት ዓመታት ያህል ሰርተው የበረራ ምዕራፋቸውን ቋጭተዋል::

ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሥራ አስፈፃሚ የነበሩትን ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ እንዳስተማሯቸው ታሪካቸው ያስረዳል::

በሦስቱ መንግሥታት ዘመን በከፍተኛ የሀገርና የሙያ ፍቅር ሀገራቸውን ያገለገሉት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ ባለትዳርና የአራት ሴቶችና የአራት ወንዶች ልጆች አባት፣ እንዲሁም የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ:: ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብም በ1997 ዓ.ም ‹‹ሕይወቴ በምድርና በአየር›› የሚል መጽሐፍ አሳትመዋል። የካፒቴን ዓለማየሁ አበበን ታሪክ ትንሽ ዘለግ ያደረግነው የእንዲህ ዓይነት ሰዎች ታሪክ መታወስ ስላለበት ነው::

አሁን ወደ ንጉሥ ላሊበላ እንሂድ:: አጋጣሚ ሆኖ እነሆ ዛሬ የገና በዓል ነው:: በገና በዓል ዕለት ሳምንቱን በታሪክ ገናን እና ንጉሥ ላሊበላን እናስታውሳለን ማለት ነው::

ስመ መንግሥታቸው ገብረመስቀል፤ አንዳንድ ሰነዶች ላይ ደግሞ ገብረክርስቶስ ይባል:: ይህ የ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን (1120 ዓ.ም) ታሪክ ነው:: እነሆ ወደ አንድ ሚሊኒየም (1000 ዓመታት) እየተጠጋ ነው:: አጼ ላሊበላ በላስታ ላሊበላ ታኅሣሥ 29 ቀን 1120 ዓ.ም እንደተወለዱ ታሪካቸው ያሳያል:: እነሆ በዚሁ ቅዱስ ቦታ ላይ የገና በዓል በየዓመቱ ታኅሣሥ 29 ቀን በድምቀት ይከበራል:: እንደ ዘንድሮ ባሉ አጋጣሚዎች (ጳጉሜን 6 ስትሆን) ደግሞ ታኅሣሥ 28 ቀን ይከበራል:: ምክንያቱ ሃይማኖታዊ ቀመር ስለሆነ እንለፈውና፤ ታሪካዊ ይዘቱን ምክንያት በማድረግ የዚህ ሳምንት አካል ስለሆነ ስለንጉሥ ላሊበላ ታሪክ ጥቂት እንቃኝ::

የዛግዌ ሥርዎ መንግሥት ንጉሥ ነበሩ:: ለ40 ዓመታት ያህል በንጉሠ ነገሥትነት የቆዩ ሲሆን፣ ታሪካቸው ከ12ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ እስከ 13ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድረስ ይዘልቃል::

የንጉሥ ላሊበላ ታሪክ በዋናነት የሚታወቀው የዓለም ሀብት በሆነው የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ነው:: ከባለቤታቸው እቴጌ መስቀል ክብራ ጋር በመሆን 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን አሰርተዋል:: እነዚህም፤ ቤተ መድኃኒያለም፣ ቤተ ማርያም፣ ጎለጎታ ሚካኤል፣ ኪዳነ ምህረት፣ ሥላሴ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ ሊባኖስ፣ ቤተ ገብርኤል፣ ቤተ መርቆሬስ፣ ቤተ ጊዮርጊስ እና ቤተ መስቀል ናቸው:: ከእነዚህ ውስጥ ቤተ ጊዮርጊስ በመስቀል ቅርጽ የተሰራ ነው::

ስለ አጼ (ንጉሥ) ላሊበላ ይህ ታሪክ ይነገራል:: ንጉሡ ላሊበላ የሚለውን ስም ያገኘው፣ ሲወለድ በንቦች ስለተከበበ ነው ይባላል። “ላል” ማለት በአገውኛ ቋንቋ ማር ማለት ሲሆን፤ “ላሊበላ” ማለትም ላል ይበላል (ማር ይበላል) ማለት እንደሆነ ይነገራል። ውቅር ቤተ ክርስቲያናቱን ንጉሡ ጠርቦ የሰራቸው ከመላዕክት እገዛ ጋር እንደሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ይነግራል።

በ16ኛው መቶ ከፍለ ዘመን አውሮፓዊው ተጓዥ ላሊበላን ተመልክቶ «ያየሁትን ብናግር ማንም እንደኔ ካላየ በፍጹም አያምነኝም» ሲል ተናግሮ ነበር።

ቅዱስ ላሊበላ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ሕንፃዎችን ለመገንባት አሰበ፤ ከዚያም በጊዜው ከነበሩት አባቶች በተለይ ቀይት ከምትባል ባለአባት የጠየቀውን 40 ጊደር ለመግዛት በሚያስችለው ወርቅ ቦታውን ገዝቶ በከርሰ ምድር ውስጥ ያሉትን ሕንፃዎች ሊያወጣ ተዘጋጁ:: ቅዱስ ላሊበላ የሚገነባባቸውን መሳሪያዎች ለ10 ዓመታት አዘጋጅቶ፤ በ1157 ዓ.ም ነግሶ በ1166 ዓ.ም ሕንፃውን ገንብቶ ጨረሰ:: ቅዱስ ላሊበላ ከ40 ዓመታት የንግስና ዘመን በኋላ በተወለደ በ97 ዓመቱ ሰኔ 12 ቀን 1217 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ:: ከ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ (1120 ዓ.ም) እስከ 13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ (1217 ዓ.ም) ድረስ የዘለቀው የላሊበላ ታሪክ አንድ ክፍለ ዘመን ይሸፍናል ማለት ነው::

ላሊበላ እነሆ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም ቅርስ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ‹‹ገናን በላሊበላ›› በሚል በድምቀት እየተከበረ ይገኛል::

መልካም የገና በዓል!

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You