ታላላቅ በዓላትን – ለላቀ ቱሪዝም ፍሰት

በኢትዮጵያ ታኅሣሥና ጥር በድምቀት የሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት እንዲሁም ባህላዊ ትዕይንቶች ይዘወተርባቸዋል:: በተለይም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በልዩ ድምቀት የሚከበሩት የገና እና የጥምቀት በዓላት ብዙ ሚሊዮኖች በአደባባይ ተገኝተው የሚሳተፉባቸው ከመሆናቸውም ባሻገር ለቱሪዝም መስህብነት የሚጠቀሱ ፌስቲቫሎች ናቸው።

በዚህ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ቱሪስቶች ከሌሎቹ ወቅቶች በተለየ ቁጥራቸው እንደሚጨምር መረጃዎች ያመለክታሉ። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በገና እና ጥምቀት የሚከናወኑት ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘት ያላቸው ክዋኔዎች እንደሆኑ ይጠቀሳል::

በዩኒስኮ የማይዳሰስ ቅርስ የተመዘገበው የጥምቀት በዓል፤ በታሪካዊቷና በውቅር አብያተ- ክርስቲያናቶቿ በምትታወቀው በላሊበላ ከተማ በዛሬው እለት በልዩ ድምቀት የሚከበረው የገና (የክርስቶስ ልደት) በዓል ሥነ-ሥርዓት ለቱሪስት ቁጥሩ መጨመር ምክንያት እንደሆኑም ይታመናል።

እነዚህ በዓላት ዘንድሮም በልዩ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቱሪስት ተገኝቶ እንደሚጎበኛቸው ይጠበቃል። ለዚህም በተለይም የአርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና የቱሪዝም ሚኒስቴር እንግዶችን ተቀብለው ለማስተናገድ ዝግጅታቸውን ስለመጨረሳቸው ከተቋማቱ በተለያየ ጊዜ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ዘንድሮ በድምቀት የሚከበሩትን እነዚህን በዓላት አስመልክተው የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ስለሺ ግርማ ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለጹት፤ ዛሬ የሚከበረውን የገና በዓል እና በጥር ወር የሚከበረውን የጥምቀት በዓል በደማቅ ሥነ-ሥርዓት ለማክበር በሚኒስቴሩ በኩል በቂ ዝግጅት ተደርጓል። ሁለቱ በዓላት ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በስፋት ይከበራሉ። በዚህም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጎብኚዎች ወደተለያዩ ቦታዎች በመሄድ መጎብኘት እንዲችሉ የቱሪስት መዳረሻዎቹ ክፍት ሆነው አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል።

ለአብነትም ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ወደ ላሊበላ ከተማ በርካታ ጎብኚዎች እንደሚሄዱ ጠቅሰው፣ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ ከከተማዋ ከንቲባና ከቤተክርስቲያናቱ አስተዳዳሪ ጋር ውይይት መደረጉን ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል:: ወደ አካባቢው የሚሄዱ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ለማስተናገድ በቂ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል::

የታኅሣሥ እና ጥር ወራት በርካታ ዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡባቸው ወቅቶች መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዋናነትም የገና እና የጥምቀት በዓልን ተከትሎ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ፍሰት እንደሚጨምርም ነው ያስረዱት።

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ ሁለቱ በዓላት በሌላው ዓለም በስፋት የማይከበሩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ጎብኚዎች ፍሰት እንደሚጨምር ይጠበቃል:: በተጨማሪም አብዛኛው የዓለም ሀገራት በአሁኑ ሰዓት አዲስ ዓመትን ተከትሎ እረፍት ላይ መሆኑ የጎብኚዎችን ቁጥር ይበልጥ ከፍ ሊያደርገው ይችላል።

በዓላቱን ምክንያት አድርገው ለሚመጡ ቱሪስቶችም አማራጭ የጉብኝት ጥቅሎች እንዲኖሩ መሠራቱን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ጠቁመዋል:: ከፀጥታ ጋር ተያይዞ ያለውን ስጋት ለማስቀረት ቱሪስቶች በኦንላይን መረጃ ማግኘት የሚችሉበትን የሞባይል መተግበሪያ በማልማት ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ክብሮም ተስፋይ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ማህበሩ የተመሠረተው በዘርፉ ኤክስፐርት በሆኑና በቂ የሙያ ትምህርትና ሥልጠና በወሰዱ አስጎብኚ ባለሙያዎች ነው። ማህበሩ 250 አባላት ያሉት ሲሆን፣ ከተመሠረተ አራት ዓመታትን አስቆጥሯል።

‹‹ከመስከረም እስከ መጋቢት ያለው በኢትዮጵያ የቱሪስት እንቅስቃሴ በስፋት የሚታይበት ነው›› የሚሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ የገና እና ጥምቀት በዓላት ዋንኛዎቹ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በየዓመቱ የውጪ ቱሪስቶች እንዲመጡ የሚደረግበት ስልት እንደሚለያይ በማንሳትም በዘንድሮው የታኅሣሥና ጥር ወራት የተለየ እቅድ ይዞ እየሠራ መሆኑን ያመለክታሉ::

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ተከትሎ የጎብኚዎች መጠን አንዳይቀንስ የሚያደርጉ የተለያዩ ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ናቸው:: በዋናነትም ሰላማዊና ደህንነታቸው በተረጋገጠ አካባቢዎች ላይ ቱሪስቱ እንዲጎበኝ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ ነው::

ይህ ዓይነቱ አሰራር በሌሎች ሀገራትም እንደሚተገበር ጠቅሰው፣ በየትኛውም የዓለም ክፍል ላይ ፍፁም የሆነ ሰላም እንደሌለም ይገልጻሉ:: በኢትዮጵያ ጎብኚዎች ደህንነታቸው ተጠብቆ በገና እና የጥምቀት ልዩ በዓላት ላይ እንዲታደሙ እንደ አስጎብኚ ማህበሩ አቅጣጫ ይዞ እየሰራ መሆኑን ይናገራሉ።

‹‹ቀደም ባሉት ዓመታት በታኀሣሥ እና ጥር ወራት ከፍተኛ የሆነ የውጭ ጎብኚ ወደ ሀገሪቱ ይገባ ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት ግን በኮቪድና በአንዳንድ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች መቀነስ ይታያል›› የሚሉት አቶ ክብሮም፤ አሁንም ግን ጥቂት የማይባል ቁጥር ያለው ቱሪስት በዓላቱ ላይ ለመታደምና ለመጎብኘት እንደሚመጣ ይገልፃሉ።

አቶ ክብሮም እንዳሉት፤ ባለፉት ሁለት ወራት የቱሪዝም ማኅበረሰቡ ባደረገው ከፍተኛ የማስተዋወቅ ሥራ ምክንያት ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ይሆናል:: ይህ ወቅት ከዚህ ቀደም በዚህ ወቅት ከሚመጣው ቱሪስት አንፃር ምንም እንኳን ዝቅ ያለ ቁጥር የሚመዘገብበት ቢሆንም፣ ካጋጠመው ችግር አንፃር ግን ተስፋ ሰጪ የጎብኚዎች ቁጥር ሊኖር ይችላል። እነዚህ ጎብኚዎችን የማህበራቸው አባላት የሆኑ አስጎብኚዎች በኢትዮጵያዊ ጨዋነት፣ በጥሩ መስተንግዶና ፍትሃዊ በሆነ ዋጋ ለማስተናገድ ዝግጅት አድርገዋል።

እንደ አቶ ክብሮም ገለፃ፤ በተለይ ከዚህ ቀደም የጎብኚዎች መዳረሻ የሆኑ ሥፍራዎችና ተዘግተው የቆዩ አካባቢዎች እንዲነቃቁ ለማድረግ እየተሠራ ነው። በተለይ ለጎብኚዎች ጥሩ የክፍያ ዋጋ በማቅረብ ፍላጎት እንዲያድርባቸውና በብዛት እንዲመጡ ለማድረግ፣ በመስህብ ሥፍራዎቹ የሚገኙ ሆቴሎች እንዲሁም አገልግሎት ሰጪዎች እንዲነቃቁና በተሻለ ቅልጥፍና እንግዶችን እንዲቀበሉ ውይይት ተደርጓል።

ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች በኢትዮጵያ የሚከበሩትን የገና እና የጥምቀት በዓላት ለማክበር የሚመጡ ቱሪስቶች የቆይታ ጊዜያቸውን ወስነው ላይመጡ ይችላሉ። ይህንን አጋጣሚ ተጠቅሞ ልዩ ልዩ አማራጮችን በማሳየት ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ማድረግ ይቻላል። ይህንን በተመለከተ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ከዋናው በዓል በተለየ ጎብኚዎች ቆይታቸውን አራዝመው ሌሎች መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ ለማድረግ እንደሚሰራ ይናገራሉ።

‹‹በዚህ ወቅት በዋናነት ከሚጎበኙት መስህቦች ባሻገር አዳዲስ መዳረሻዎች በቱሪስቱ እንዲታዩ እየሠራን ነው›› ሲሉ ገልጸው፣ አዳዲስ የተሰሩ መዳረሻዎች ምን ዓይነት ይዘት እንዳላቸው ለማየት የማህበሩ አባላት በአካል ተገኝተው በቅድሚያ መጎብኘታቸውን ያስረዳሉ።

ይህም ለዝግጅት እንደረዳቸውና ቱሪስቶችን ወደ ስፍራው እንዲያቀኑ ለማድረግ እድሉን እንዳመቻቸላቸው ያመለክታሉ። በልዩ ልዩ መዳረሻዎች በመገኘት መዳረሻዎቹን በፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስል በመውሰድ፣ ርቀታቸውን የመለየት ዝግጅት እንዳደረጉም አስታውቀዋል።

ቱሪዝም በርካታ ጉዳዮች በአንድ ላይ ተካትተው በጥቅል ለቱሪስቱ የሚቀርብ አገልግሎት መሆኑን አቶ ክብሩ ጠቁመው፤ በዚህ ውስጥ በርካታ ባለድርሻዎች በአንድ ላይ እንደሚሳተፉ ይናገራሉ። ስኬታማ መሆን የሚቻለውም አየር መንገዱ፣ ቱር ኦሬተሮች፣ አስጎብኚው፣ አገልግሎት ሰጪ ሆቴሎች፣ መዳረሻው የሚገኝባቸው ክልሎች፣ ሚኒስቴሩ እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሲሰሩ መሆኑን ይናገራሉ።

በመሆኑም በእነዚህ ትላልቅ በዓል በሚከበርባቸው ጊዜያት በጋራ ለአንድ ዓላማ መሥራት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። በዚህ ረገድ በተለይ የገና እና ጥምቀት በዓላት በስኬት እንዲጠናቀቁም ማህበሩ ከእነዚህ አካላት ጋር ለመሥራት መዘጋጀቱን ነው ያስረዱት።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ከፍተኛ የቱሪስት እንቅስቃሴ በሚደረግባቸው በእነዚህ ወራት በውጭ ሀገሮች ለሚኖሩት የ‹‹ሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን›› ወደ ሀገራቸው እንዲገቡና ከባህላቸው ከታሪካቸው ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ጥሪ ማድረጉን ይገልፃሉ። ይህም ለቱሪዝሙ ተጨማሪ እድል መሆኑን ነው ያመለከቱት። ስለ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም እውቀቱ የሌላቸው ዜጎች ወደ ሀገራቸው ገብተው ከማኅበረሰቡ ጋር እንዲገናኙ የማድረጉ ሃሳብ ጥልቅና አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። በተለይ ታላላቅ ክዋኔዎች የሚታዩበት የገና እና ጥምቀት በዓላት እንዲገኙ ጥሪ መደረጉም በራሱ አጋጣሚውን ልዩ እንደሚያደርገው ይናገራሉ።

‹‹ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ጥሪ የተደረገላቸው የሁለተኛው ትውልድ ዲያስፖራ ወጣቶች የዲጂታል ዘመኑን ጠንቅቀው የሚረዱ ናቸው›› ያሉት አቶ ክብሮም፤ በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ዓለምን ማዳረስ የሚያስችል እውቀት የታጠቁ መሆናቸውንም ይገልጻሉ። ይህ ወጣት ኃይል በዲጂታል አማራጭ የኢትዮጵያን ቱሪዝም ማስተዋወቅ እና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር የማድረግ አቅም ያለው ኃይል እንደሆነ ይናገራሉ። በተለይ በእነዚህ ልዩ ክብረ-በዓላት ላይ ሲገኙ በዲጂታል አማራጭ የሚያሰራጯቸው መረጃዎች ተፅዕኖ የሚፈጥሩና የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ የሚገነቡ እንደሚሆኑም ያስረዳሉ።

አቶ ክብሮም እንደሚሉት፤ በዚህ ወቅት ጥሪ የተደረገላቸው በውጭ ሀገሮቹ የሚኖሩ የሁለተኛው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን እውቀትና ሀብት በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ላይ ማዋል የሚችሉ ናቸው። ከዚህ የተነሳ ማህበሩ መንግሥት ያደረገው ጥሪ እንዲሳካና ወደ ሀገራቸው የሚገቡ ኢትዮጵያውያን የመጡበትን ዓላማ እንዲያሳኩ እንደ አንድ ባለድርሻ አካል ይሰራል። በተለይ የሀገራቸውን ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስና ተፈጥሮ ጠንቅቀው እንዲያውቁ በየመጡበት ሀገር ቋንቋ ለማስረዳትና ለማስጎብኘት ማህበራቸው ዝግጅቱን አጠናቋል::

አቶ ክብሮም ‹‹በዓሉ ለእምነቱ ተከታዮች ምህረት እና ፀሎት የሚያደርግበት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሲሆን፣ የእምነቱ ተከታይ ላልሆኑት ደግሞ የአብሮነት፣ የብዝሀነትና የውበታቸው ምልክት ነው›› ይላሉ:: በዓሉን አስመልክቶ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ጎብኚዎች የሃይማኖቱን ተከታዮች ብቻ ሳይሆን የሚጠቅሙት መላ ሀገሪቱን እንደሆነ አንስተው፤ ሁሉም እሴቶቹን በጋራ መጠበቅና የእኔነት ስሜት መፍጠር ይገባዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You