አብሮነት – ለኢትዮጵያዊ ብዝሀነት

ከሰው ልጅ ባህርያት መካከል አንዱ አብሮነት ነው። አብሮ መሥራት፣ አብሮ መንቀሳቀስ … አብሮ መኖር የሰው ባህርያትና ድርጊቶች ናቸው። የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ባለሙያዎችም ሰው በባህሪው ማኅበራዊ ፍጡር በመሆኑ ብቻውን ከመኖር ይልቅ አብሮ መኖርን እንደሚመርጥ በጥናት አስደግፈው ይገልፃሉ። የሃይማኖት መምህራንም ፈጣሪ ሰውን ፈጥሮ ብቻውን ሊተወው ስላፈለገ አጋዥ/አጋር እንደፈጠረለት በመናገር አብሮነት በፈጣሪም የሚደገፍ እንደሆነ ያስተምራሉ።

አብሮነት መቻቻልና መተባባር የጠነከረበት እንዲሁም ዘላቂ ሰላም የሰፈነበት ማኅበረሰብ/ሀገር ለመገንባት በጎ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያዎች ደጋግመው ያስረዳሉ። በአብሮነት ውስጥ ሰው መሆንንና የማንነት መገለጫዎቻችን ማክበር፣ መቀበልና ማድነቅ አለ። አብሮነት የተለያዩ ማንነቶችን ያስተናግዳል፤ ያከብራል። አብሮነት የሰዎችን መስተጋብር ያቀናጃል፤ ያጠነክራል። አብሮነት በሰላም አብሮ የመኖር መሠረት ነው።

በርካታ ግለሰቦችና ተቋማት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚስተዋሉት ግጭቶች እንዲሁም የጥላቻ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ለአብሮነት አስተሳሰብ ተገቢውን ስፍራ ያለመስጠት ውጤቶች አድርገው ይመለከቷቸዋል። በርግጥም የመቻቻልና የአብሮነት እሳቤና ተግባር ተገቢውን ትኩረት ቢያገኝ ኖሮ፣ ከባድና አሳዛኝ ዋጋዎችን ያስከፈሉት ብዙዎቹ አለመግባባቶችና ግጭቶች እንዳይከሰቱ ማድረግ ይቻል ነበር።

ስለሆነም ስለአብሮነትና መቻቻል በመነጋገርና ግንዛቤ በመፍጠር ግጭቶችን ለማስወገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበር ‹‹የመቻቻል ቀን›› እንዲኖር በቀረበ የመነሻ ሃሳብ መሠረት፣ እ.ኤ.አ ከ1995 ጀምሮ ‹‹ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን›› (International Day for Tol­erance) በየዓመቱ ኅዳር 6 ቀን (November 16) ይከበራል። ‹‹ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን›› የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) እ.ኤ.አ በ1995 ባቀረበው የመነሻ ሃሳብና የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ባፀደቀው ውሳኔ (የውሳኔ ሃሳብ 15/95) መሠረት፣ የድርጅቱ አባላት በሆኑ ሀገራት የሚከበር ሲሆን፣ የቀኑ መከበር ዋና ዓላማም ስለመቻቻል ምንነትና ፋይዳ ግንዛቤ መፍጠር ነው። በ‹‹መቻቻል ቀን›› በርካታ ልዩነቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ የመቻቻል እሳቤና ተግባር ስላለው ጥቅም በስፋት ይነገራል። የዘንድሮው ‹‹ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን›› ‹‹መቻቻል፣ የሰላምና የእርቅ መንገድ›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ ተከብሯል።

በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች መፍትሔ እንደሆነ የሚታመንበት አብሮነት፣ የኢትዮጵያውያን መገለጫ የሆነና የእርስ በእርስ ማኅበራዊ መስተጋብራቸውን አጠንክሮ የኖረ ተግባር ነው። የተራበን ማብላት፣ የታረዘን ማልበስ፣ ያዘነን ማፅናናት… የተቸገረን መርዳት ኢትዮጵያውያን የሚታወቁበት ባህርያቸው እንዲሆን ያደረገው የአብሮነት ባህል ነው። ደስታና ሐዘናቸው በአብሮነት ነው። ኢትዮጵያ ያለ ኢትዮጵያውያን አብሮነት ነፃነቷንና ሉዓላዊነቷን አስጠብቃ መቆየት አትችልም ነበር። በአጠቃላይ፣ አብሮነት ባይኖር ኖሮ አሁናዊ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የተለየ ይሆን ነበር።

ቴክኖሎጂው፣ የሕይወት ሩጫው፣ የእርስ በእርስ ፉክክሩ… የበዛበት ዘመናዊው ዓለም ግን ከአብሮነት ጋር የሚስማማ ሆኖ አይታይም። ‹‹አብሮነት ተዳከመ፣ መተባበርና መደጋገፍ ጠፋ …›› የሚሉ ድምጾች ደጋግመው ይደመጣሉ። በተለይም የኢትዮጵያውያን መገለጫ ተደርገው ከሚቆጠሩት ባህርያት መካከል አንዱ የሆነው አብሮነት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረና እየደከመ መሄዱ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውኑ ይስተዋላል።

የጳጉሜን ወር ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች ሲከበሩ ለቀናቱ ስያሜነት ከሚሰጡ ሃሳቦች መካከል አንዱ አብሮነት/መቻቻል/ ነው። ለአብነት ያህል ያለፈው ዓመት የጳጉሜን ወር ስድስተኛ ቀን ‹‹የአብሮነት ቀን›› ተብሎ ተሰይሞ ልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደተከናወኑበት ይታወሳል።

አብሮነት መገለጫዋ የሆነውና በየዓመቱ ‹‹ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን››ን ስታከብር የቆየችው ኢትዮጵያ፣ የዘንድሮውን ‹‹ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን›› ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማዛመድ ቀኑን የ‹‹አብሮነት ሳምንት›› በሚል ስያሜ አክብራለች። የዘንድሮው ‹‹የአብሮነት ሳምንት››፣ ‹‹ብዝሀነትን መኖር›› በሚል መሪ ቃል ከታኅሣሥ 20 እስከ 25 ቀን 2016 ዓ.ም ለ14ኛ ጊዜ የተከበረ ሲሆን፤ በኅብረተሰቡ መካከል የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የአብሮነት እና የሰላም ግንባታ አስተሳሰብ እንዲጎለብት የሚያስችሉ ተግባራት እንዲከናወኑ እና ሀገራዊ አንድነትንና አብሮነትን በሚያጎላ መልኩ እንዲከበር ጥረት ተደርጓል። ይህን ጥረት ስኬታማ ለማድረግም በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት የተመራ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ለዝግጅቱ ስኬት የሚረዱ ተግባራትን አከናውኗል።

በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ ‹‹የአብሮነት ሳምንት›› መከበር የኢትዮጵያ/ኢትዮጵያውያን/ መገለጫ የሆነውን የአብሮነት ባህል የበለጠ ለማጉላት ፋይዳ እንዳለው ይገልፃሉ። እሳቸው እንደሚሉት፣ አብሮነት ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያዳበሩት እሴት በመሆኑ፣ የሳምንቱ ስያሜ ለዚህ አስተሳሰብና ድርጊት የበለጠ ተስማሚና ገላጭ ይሆናል። አብሮነት በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በሌሎች የማንነት መገለጫዎች የተለያዩ ወገኖችን የሚያቀራርብና የሚያስተሳስር እሴት ነው። ቀደምት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ከትውልድ ትወልድ ለማስተላለፍ የተጠቀሙት ትልቁ እሴትና መሳሪያ አብሮነት ነው።

‹‹ኢትዮጵያ በብዙ የማንነት መገለጫዎች (እምነት፣ ብሔር፣ ቋንቋ…) የብዝሀነት ባለቤት ናት። ኢትዮጵያውያን በአብሮነት መንፈስ በአንድነት ቆመው ሀገርን ለማስቀጠል የከፈሏቸው መስዋዕትነቶችም አፍሪካንና ዓለምን ያስደመሙ ናቸው። የኢትዮጵያውያን መገለጫዎችና ድርጊቶች በአብሮነት የሚከወኑ ናቸው። ‹‹የአብሮነት ሳምንት›› እነዚህ መገለጫዎች ይበልጥ እንዲጎሉና እንዲደምቁ ያደርጋል›› ይላሉ።

‹‹የአብሮነት ሳምንት›› ሲከበር የአሁኑ ትውልድ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ከነበራቸው የአብሮነት ባህል ምን መማር እንዳለበት፣ ትውልዱ ያጎደላቸው የአብሮነት እሴቶች ምን እንደሆኑ እና ጠንካራ የአብሮነት መንፈስ ለመፍጠር ምን ማድረግ እንደሚገባ እንዲሁም ቀደምት ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን የአብሮነት መንፈስ መጠበቅና ወደተሻለ ደረጃ ማሸጋገር እንደሚያስፈልግ መገንዘብ እንዳለበትም ይናገራሉ።

እንደ ወይዘሮ ወርቅነሽ ማብራሪያ፤ ጉዳዩ የአንድ ግለሰብ ወይም ተቋም ብቻ ባለመሆኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ብሔራዊ ኮሚቴው በቴክኒክና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተደራጅቶ ዝግጅቱን ለማድመቅ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የሚያስተባብረው ብሔራዊ ኮሚቴ አባል ሆነው በቴክኒክና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተግባራት ውስጥ በንቃት ተሳትፈዋል።

በ‹‹አብሮነት›› ሳምንት አብሮነትን በተግባር ለማሳየት የታመሙ ሰዎችን የመጠየቅ፣ የተቸገሩ ወገኖችን የመርዳት፣ ደም የመለገስ፣ ስለአብሮነት ምንነትና ፋይዳ በመገናኛ ብዙኃን ገለፃዎችን የማቅረብ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ስለአብሮነት ያለውን እሳቤ እንዲናገር እድል የሚሰጡ የውይይት መድረኮችን የመፍጠር፣ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን በጋራ የመሥራት እና በአብሮነት ላይ ያተኮሩ መልዕክቶችን የመለዋወጥ ተግባራት ተከናውነዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ሹማምንት፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ ምሁራን፣ አምባሳደሮችና የኅብረተሰብ ተወካዮች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሽኔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የ‹‹አብሮነት ሳምንት›› መከበር አብሮነት በአሁኑ ወቅት አደጋ ውስጥ እንደገባና ለዚህም መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ለማስጨበጥ እንደሚያግዝ ይገልፃሉ።

‹‹የሰው ልጅ ስልጣኔ መሠረት አብሮነት ነው። በጥንት ጊዜ የሰው ልጅ ተበታትኖ በሚኖርበት ዘመን ሕልውናው ጭምር ለአደጋ የተጋለጠ ነበር። በአብሮነት መኖሩ ጥንካሬ ሆኖታል። በአሁኑ ጊዜ አብሮነት በቴክኖሎጂ ነክ ጫናዎችና በሌሎች ምክንያቶች እየተሸረሸረ ነው። አብሮነት ፈተና ውስጥ በገባበት ጊዜ ላይ ስለምንገኝ ስለአብሮነት ደጋግሞ መናገር ይገባል›› ይላሉ።

ዶክተር ኮራ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብሮነትን በእጅጉ የሚፈልግና በአብሮነት የኖረ ኅብረተሰብ እንደሆነ ጠቁመው፣ ሕዝቡ የአብሮነትን እሴት በሚገባ የሚያውቀውና የኖረበት ባህሉ በመሆኑ፣ ይህን እሴት ጠብቆ በማቆየት ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተለያዩ ባህርያትና የማንነት መገለጫዎች ባለቤት የሆኑ ተማሪዎች የሚገናኙባቸው ስፍራዎች ስለሆኑ፣ ጠንካራ የአብሮነት እሴት ሊታይባቸው የሚገቡ ቦታዎች መሆን አለባቸው። በተቋማቱ ውስጥ የሚታዩ የአብሮነት እሳቤዎችና ተግባራት ለሀገርም ጠቃሚ ይሆናሉ። ‹‹አብሮነት ከሌለ ሰላም፣ ልማት፣ ፍትህና እኩልነት አይታሰብም›› የሚሉት ዶክተር ኮራ፣ የልዩነትን ተፈጥሯዊነት ጠብቆ በአብሮነት ላይ ማተኮር ይገባል በማለት ይናገራሉ።

የአብሮነት እሳቤና ተግባር በሃይማኖት ተቋማት በእጅጉ የሚደገፍ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ተስፋዬ ውብሸት፤ አብሮነት በሁሉም የሃይማኖት አስተምህሮዎች ውስጥ የተካተተ የበጎ እሳቤ መገለጫ እንደሆነ ያስረዳሉ። ‹‹አብሮነት ጥንትም የነበረና ወደፊትም የሚኖር ነው። በአብሮነት ውስጥ ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅርና መተባበር አለ። የአብሮነት እሴቶችና ተግባራት በሁሉም ቤተ-እምነቶች አስተምሮዎች ውስጥ አሉ። አብሮነት የሁሉም ሃይማኖቶች ዕለታዊ ትምህርት አካል ነው›› በማለት ስለአብሮነት ፋይዳና አብሮነት በሃይማኖቶችም የሚደገፍ ተግባር እንደሆነ ያስረዳሉ።

አቶ ተስፋዬ እንደሚናገሩት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ባለፉት 13 ዓመታት አብሮነትን ለማጠናከር የሚያግዙ ተግባራትን አከናውኗል። ጉባዔው በመላው ኢትዮጵያ ባሉት መዋቅሮች፣ በተለይም አብሮነት ለሰላም መስፈን ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዳለው፣ በከፍተኛ ትኩረት ተንቀሳቅሷል። ስለአብሮነት ግንዛቤ የሚያስጨብጡ የማስተማሪያ ሰነዶች አዘጋጅቶ ስለእሳቤው ትምህርት ይሰጣል። እስካሁን የተከበሩ የአብሮነት ቀናት ሰላምን በማስፈን እና ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ቀላል የማይባሉ በጎ አስተዋፅኦዎችን አበርክተዋል። አብሮነትን የበለጠ ለማዳበር ተስማምቶ መሥራትን እንደሚጠይቅም አቶ ተስፋዬ ገልጸዋል።

 አንተነህ ቸሬ

 አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2016

Recommended For You