ባለፉት 30 ዓመታት ለ 7 ሺ 800 ህጻናት በነጻ የልብ ቀዶ ህክምና አገልግሎት ሰጥቷል። ይህ በዓለም ላይ ትንሽ ገንዘብ ነው የሚጠይቁት በሚባሉ ሆስፒታሎች ሂሳብ እንኳ ቢሰራ ከ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የሚያወጣ አገልግሎትን ለኢትዮጵያውያን የሰጠ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ።
ተማሪ ቤተልሔም ታምሩ የልብ ህመም እንዳለባት የታወቀው ገና በህጻንነቷ ነው። ተወልዳ ባደገችበት አዳማ እንዲሁም አዲስ አበባ እየመጣችም ለአስር ዓመት ያህል ያለማቋረጥ ህክምናን አድርጋለች። በነዚህ ሁሉ ዓመታት ደግሞ ለቀዶ ህክምና ወረፋ እየጠበቀች ነው የቆየችው። ቤተልሄም የቀዶ ህክምናውን ያገኘችው ከአራት ዓመት እልህ አስጨራሽ ጥበቃ በኋላ በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ውስጥም ቀዶ ህክምናው ተደረገላት።
እንደ እኩዮቿ ሮጣ መጫወት በክፍል ውስጥ ቁጭ ብላ መማር ያቃታት ቤተልሄም እንደገና የመኖር እድልን አገኘች። በዚህም ለአራት ዓመት ያቋረጠችውን ትምህርቷን እንደገና ጀመረች፤ ዛሬ ላይ እንደ ልቧ የፈለገችውን ታደርጋለች፣ ፎቅ ላይ ትወጣለች፣ ትወርዳለች፣ ትሮጣለች፣ ትጫወታለች የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷንም በጥሩ ሁኔታ ትማራለች።
ቤተልሄም « እኔ ቀዶ ህክምና ሳይደረግልኝ በፊት መሮጥ አይደለም መንቀሳቀስ አልችልም ነበር፤ ከታክሲ ወርጄ ወደ ሆስፒታል የምገባው እንኳን ታዝዬ ነበር፤ ዛሬ እኔ እድል ቀንቶኝ ድኛለሁ። መሰል የልብ ችግር ላለባቸው ህጻናት ግን ሊደረስላቸው ይገባል ፤ ኢትዮጵያውያን የመረዳዳት ባህላቸው ሊገለጽ ያስፈልጋል። የህክምና ባለሙያዎቹ ብቻ ምንም ሊያደርጉልን ስለማይችሉ ሁሉም ዜጋ ሆስፒታሉን ያግዘው» ትላለች።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ከሰኔ 1 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ 30ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን «ስለ ልብ ብላችሁ፤ ከልብ አድምጡን!» በሚል መሪ ሀሳብ ያከብራል።
ይህንን አስመልክቶም በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሄለን በፍቃዱ እንዳሉት ሆስፒታሉ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ህጻናት ተስፋ የሆነ ቢሆንም ያለበት የአላቂ እቃዎች እጥረት በሚፈለገው ልክ እንዳይሰራ አድርጎታል። እነዚህ አላቂ እቃዎች በባህሪያቸው ለልብ ህክምና በጣም አስፈላጊ፣ በቀላሉ የማይገኙ፤ በተለይም ደግሞ አገር ውስጥ የሌሉና በውጭ ምንዛሪ የሚመጡ መሆናቸው ችግሩን እንዳባባሰው ይናገራሉ።
ይህንን እቃ ለመግዛት ብዙ ብር ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ « እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ» ብሎ ማሰብ አለበት ያሉት ዶክተር ሄለን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አንዳንድ ብር አዋጥቶ ማዕከሉን እንደገነባው ሁሉ ዛሬም በዚህ መልኩ ገንዘብ መሰብሰብ ቢቻል ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይላሉ፡፡
በመሆኑም ማንም ሰው ግዴታ መድሀኒት መግዛት፣ መሳሪያ ማስመጣት አይኖርበትም ግን የሚችለውን በአቅሙ ድጋፍ በማድረግ ማዕከሉ በሚፈለገው ልክ ሰርቶ በወረፋ ምክንያት ከሞት ጋር ተፋጠው ያሉትን ህጻናትን ተስፋ መመለስ ይቻል ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በሌላ በኩልም በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በመደራጀት እነዚህ ለስራው እጅግ አስፈላጊ የሆኑ አላቂ እቃዎችን ከሚኖሩባቸው አገሮች ሆስፒታሎች እየሰበሰቡ በየስደስት ወሩ አልያም በዓመት እገዛ ቢያደርጉላቸው መልካም መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ሥራ አስኪያጅ አቶ ህሩይ አሊ በበኩላቸው፤ በ 1981 ዓ.ም በቅን ልቦና ተነሳስተው ምንም ደሀ ብንሆንም በልብ በሽታ መሞት የለብንም፤ በተለይም ህጻናት ተስፋቸው እንዳይጨልም በሚል ሀሳብ የተነሳሱ ሀኪሞች ከአገር ውስጥና ውጪ ባሰባሰቡት እርዳታ ማዕከሉን እውን ማድረግ ተችሏል ። የዛሬ 30 ዓመት ስራውን በይፋ ሲጀምርም በርካታ ህጻናትን ወደ ውጭ አገር በመላክ ያሳክም ነበር፤ በዚህ ስራም ከ 2 ሺ 300 ህጻናት በላይ የእድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል ይላሉ።
በወቅቱ ማዕከሉ አቅሙ ውስን የነበረ በመሆኑ ህጻናቱ ለህክምና ወደ ውጭ በሚሄዱበት ጊዜ አንድ የቤተሰብ አባል እንኳን አብሮ ለመላክ አይቻልም ነበር ያሉት አቶ ህሩይ፤ ይህ ደግሞ ህጻናቱ ቀዶ ህክምናቸውን ጨርሰው ከሰመመን በሚነቁበት ጊዜ የሚያዩት በመልክም በቋንቋም የማይመስሏቸውን የሌላ አገር ዜጎች ስለነበር በስነ ልቦና እጅግ ይጎዱ አንደነበር ያስታውሳሉ።
የኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህጻናት መርጃ ከ 10 ዓመት በፊት በህብረተሰቡ ድጋፍ እውን መሆን ከቻለ በኋላ ግን ቢያንስ ህጻናቱ በአገራቸው ላይ ከቤተሰቦቻቸው እቅፍ ሳይወጡ የህክምና አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህም ቢሆን ግን አሁንም ባለበት የአላቂ እቃዎች እጥረት ምክንያት መረዳት የሚገባቸው ህጻናት ረጅም ቀጠሮን ወስደው ወረፋ እንዲጠብቁ ተገደዋል ብለዋል።
‹‹ችግሩ ቢኖርም ቅድመ እና ድህረ ቀዶ ህክምና ላይ ያሉ ታካሚዎች ሁልጊዜ ክትትል ይደረግላቸዋል፤ ከሰኞ እስከ ረቡዕም ቀዶ ህክምና ይሰራል፡፡ በዚህም የብዙ ህጻናት የነገ ተስፋ እያለመለመ ይገኛል። በዚህ መልክ ስራውን ይስራ እንጂ ከፍተኛ በሆነ የገንዘብ እጥረት አለ ፡፡ በተለይም ደግሞ በአላቂ እቃዎች ችግር ውስጥ ነው፡፡ ማዕከሉ በገንዘብ ሲተመን ቀላል የማይባል አገልግሎትን እየሰጠ ያለ ቢሆንም እንደ አገልግሎቱ አስፈላጊነትና እንደ ህመሙ ስፋት የሚያድግበት መንገድ መፈለግ አለበት›› ይላሉ አቶ ህሩይ፡፡
በክብረ በዓሉ ላይም እስከ አሁን ሲደረግ ለነበረው ድጋፍ እውቅና ለመስጠት ፤ ባለፉት 30 ዓመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ማሳወቅና ማዕከሉ ያለበትን የፋይናንስ በተለይም የአላቂ እቃዎች ችግር ከሚመለከታቸው አካላት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመሆን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
እፀገነት አክሊሉ