አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም መሠረታዊ አገልግሎቶች ለማከናወን በአገሪቷ 500 ወረዳዎችን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ማህበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም ምዕራፍ ሦስት በይፋ መጀመሩን አስመልክቶ ትናንት የምክክር መርሐ ግብር ሲያካሂድ በመድረኩ የተገኙት የማህበራዊ ተጠያቂነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ሮልፍ ሁኒንግ እንደተናገሩት፤ የምዕራፍ ሦስት ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ግማሽ በሚሆኑት 500 ወረዳዎች ውስጥ ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ፕሮግራሙ የአይሪሽ ኤይድ፣ አውሮፓ ህብረት፣ ኦስትሪያን ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ፣ ዲፓርትመንት ፎር ኢንተርናሽናል ዴቨሎፕመንት፣ ኤምባሲ ኦፍ ስዊድን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በስፋት እንደሚተገበር፤ ፕሮግራሙን በወረዳ ደረጃ ለሚተገብሩ ከ100 በላይ ለሚሆኑ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች30 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚከፋፈል እንደሚሆን ሰብሳቢው አስታውቀዋል፡፡
ሮልፍ ሁኒንግ፤ የመሠረታዊ አገልግሎቶችን ጥራትና ተደራሽነት በማሻሻል ሁለተኛው የ‹‹ኢሳፕ›› ምዕራፍ ከ2003ዓ.ም እስከ 2010ዓ.ም በተሳካ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ 223 ወረዳዎች ውስጥ በአምስት የአገልግሎት ዘርፎች ማለትም በትምህርት፣ በጤና፣ በመጠጥ ውሃ፣ በገጠር መንገድና በግብርና ላይ መተግበሩን አስታውሰው፤ የተገኙ ውጤቶች ስኬታማ መሆናቸውንና በተለይም ማኅበረሰቡን ለድህንነት አጋላጫ የሆኑ ደካማ የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በማሟላት የማኅበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቀጣይነት እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አድማሱ ነበበ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ከማድረግ ባሻገር በአገሪቷ ፈጣን ለውጥ ለማምጣት፣ የልማትና ዴሞክራሲ አስተሳሰብን ለማስፈን አስተዋጽኦ እንዳለው በመጥቀስ ተጠያቂነትና ግልጸኝነትን በማረጋገጥ የመንግስትን የማስፈጸም አቅም በማሳደግ አገሪቷን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገውን እንቅስቃሴ ይደግፋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ተጠያቂነት ፕሮግራም መሠረታዊ አገልግሎቶች በፍትህ መልኩ ተደራሽ እንዲሆኑና ባልተማከለ ደረጃ የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ የሚሰራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
አዲሱ ገረመው