ጭንቅላታቸው ላይ ሻርፕ የጠመጠሙ ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን አዝለው በእጆቻቸው ቢጫ ውሃ መቅጃ ጀሪካን ይዘው የውጭ በር ያንኳኳሉ፡ ፡ ያንኳኩት የግቢ በር ሳይከፈት የሰፈር ሕፃናት እየተንደረደሩ ተመሳሳይ ጀሪካን ይዘው ከሴቶቹ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ከግቢው ውስጥ ጫጫታ ይሰማል፡፡
እነርሱ ያላቸውን አቅም ተጠቅመው በሩን ቢያንኳኩም ድምፁ ግቢ ውስጥ ካለው ድምፅ ባለመብለጡ ይሁን በሌላ ምክንያት በሩ አልተከፈተም፡፡ ፆም ያደከማቸው ሴቶች ባዶ ውሃ መቅጃ ጀሪካኖቻቸውን አስቀምጠው ካዘሏቸው ሕፃናት ጋር ተቀመጡ፡፡
በግቢው ውስጥ የነበረው ድምፅ ሲቀንስ በሩ ተከፈተ፡፡ አንድ ጎረምሳ በሁለቱም እጆቹ ውሃ የተሞሉ ጀሪካኖችን ይዞ ወጣ፡፡ ሴቶቹ እና ልጆቹ እየተጋፉ ወደ ግቢው ሲገቡ ውሃ አስቀጂው ረዘም ያለ ጎልማሳ ‹‹የውሃዋ ሃይል ቀንሷል፤ ቀድመው የገቡትም አይደርሳቸውም!›› በማለት ከንግግሩ ባሻገር ውጡ በማለት በእጁ ይገፋቸው ጀመረ፡፡ ‹‹ኸረ! በአላህ ለሾርባ መቀቀያ አንድ ጀሪካን ብቻ ልቅዳ›› እያሉ ተራ በተራ ቢለምኑትም ‹‹አልሰማችሁም ጭቅጭቃችሁ ሰልችቶኛል ውጡልኝ›› ብሎ ከነህፃናቱ ሰብስቦ አስወጣቸው፡
ወይዘሮ ዘቢባ ጀማል በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ጠሮ በሚባለው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ወትሮም ቢሆን የውሃ ችግር ያለበት መንደራቸው ከአንድ ወር ወዲህ ደግሞ ከራስ ግቢ ቧንቧ ውሃ መቅዳት ቅንጦት ሆኗል፡፡ ከአስፓልቱ በስተግራ በኩል ያሉት ቤቶች በተከታታይ ውሃ ሲያገኙ በስተቀኝ ያሉት ቤቶች ግን ውሃ ስለሌላቸው ‹‹የውሃ ለማኝ ሆነናል፡፡
ምንም እንኳ በከተማዋ እጥረት መኖሩ ቢገለፅም ለሁሉም በተመሳሳይ መልኩ በፈረቃ መሰጠት እያለበት አንዳንዱ ያለማቋረጥ ውሃ ሲያገኝ፤ ሌላው ደግሞ ጭራሽ በወርም ውሃ የማያገኝበት ሁኔታ መኖሩ እጅግ የሚያበሳጭ ነው›› ይላሉ፡፡ በተለይ ለሴቶች የውሃ አለመኖር ‹‹በኑሯችን ላይ ጫና እየፈጠረብን ይገኛል›› ብለውናል፡፡ ለጉለሌ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ አቤቱታ ቢያቀርቡም ‹‹እናስተካክላለን ብሎ ከመመዝገብ ውጪ መፍትሄ ሊሰጡን አልቻሉም›› ይላሉ፡፡
በዚያው አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ አባይነሽ ወልዴም በአካባቢያቸው የውሃ አቅርቦት ከተቋረጠ አንደኛ ወሩ አልፎ ሁለተኛ ወሩን እንደያዘ ይናገራሉ፡፡ ልብስም ሆነ ገላቸውን መታጠብ እንዳልቻሉ፤ ለምግብ ማብሰያ እና ለዕቃ ማጠቢያ ብቻ ከመንገድ ማዶ እየቀዱ መሆኑንና መፍትሄ ማጣታቸውንም ነው የሚናገሩት፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ አዲሱ ገበያ፣ ስድስት ኪሎ አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ ፈረንሳይ እና ቤላ አካባቢ በቦሌ ክፍለ ከተማ ሰሚት እና ጎሮ አካባቢ በከተማዋ ባለው የውሃ እጥረት ሳቢያ መቆራረጥ ቢኖርም በሳምንት አንድ አንድ ቀን፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ሁለትና ሶስት ቀን የውሃ አቅርቦት ያገኛሉ፡፡ ነገር ግን በብዛት ፈረቃዎች የሚዘበራረቁበት ሁኔታ መኖሩን ዛሬ ይመጣል ተብሎ ሲጠበቅ አልፎ አልፎ ውሃ ማግኘት የማይችሉበት ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ፡፡
በብዛት ለረጅም ጊዜ ውሃ ከሚያጡት አካባቢዎች መካከል የአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 07 አካባቢ ነዋሪዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በአብዛኛው ከቀን ይልቅ ሌሊት ዘጠኝ እና አስር ሰዓት ውሃ የሚያገኙ ሲሆን፤ ያም ቢሆን እየቆየ በአምስት ቀን አንዴ በመሆኑ እጅግ መቸገራቸውን የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ አረጋሽ ሽኩር ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ችግሩን በመረዳት በቦቴ ውሃ አምጥቶ ቢያከፋፍልም ቦቴው በሚመጣበት ጊዜ በአካባቢው የሌሉ ሥራ የሚውሉ ሰዎች ውሃ ስለማያገኙ ከጊዜያዊ ይልቅ ዘላቂ መፍትሄ የሚበጅበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል ይላሉ፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሳሪስ አካባቢ ነዋሪው አቶ አብረሃም ዘውዴ በበኩላቸው፤ ውሃ በተከታታይ ለ15 ቀናት እንደሚጠፋና ነዋሪዎችም እየተቸገሩ መሆኑን በመጠቆም ባለስልጣኑ የከተማውን ህዝብ ከውሃ ችግር የሚያላቅቅበትን ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደሚገባም ነው የጠቆሙት፡፡
በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ተወካይ አቶ ንጉስ ደሳለኝ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ ከፍተኛ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በመኖሩ የውሃ ፍላጎቱ በከፍተኛ መጠን አድጓል፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማዋ በቀን የሚያስፈልጋት 930ሺ ሜትር ኪዩብ ቢሆንም ባለስልጣኑ ማቅረብ የቻለው ግን 574ሺ ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ በከተማ ደረጃ የውሃ እጥረት በመኖሩ አቅርቦቱ በፈረቃ ተደርጓል፡፡ ሆኖም አንዳንዴ በሚኖሩት ተደራራቢ ችግሮች ሳቢያ የውሃ አቅርቦት ከፈረቃም በላይ ሰፊ ክፍተት እየተፈጠረበት ነው፡፡
አንደኛው ችግር ምንም እንኳ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ጋር በጋራ ኮሚቴ በማዋቀር በልዩ ትኩረት የውሃ መገኛዎችና ግፊት መስጫዎች አካባቢ ሃይል እንዳይቋረጥ ቢሰራም አልፎ አልፎ አሁንም መቆራረጡ ያጋጥማል፡፡ ይህ በፈረቃ በሚቀርበው የውሃ አቅርቦት ላይ የራሱን አሉታዊ ተፅዕኖ ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሌላው በአቶ ንጉሱ የተገለፀው፤ የከርሰ ምድር ውሃ ላይ የሚያጋጥመው የውሃ መሳቢያ ፓምፕ መበላሸት እየፈጠረ ያለው ችግር ነው፡፡ ፓምፑ ሲበላሽ ጉድጓዶቹ ጥልቅ በመሆናቸው ለማስተካከል ከሰባት ያላነሰ ቀናትን ይፈጃል፤ ይህም በአቅርቦቱ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡
ሌላው እና አሳሳቢው ችግር ደግሞ የከርሰምድር ውሃ ምርት መቀነስ ነው፡፡ ውሃው ከተገመተው ጊዜ ቀድሞ መጠኑ ሲቀንስ በዛ አካባቢ ያሉ ሰዎች ውሃ የማያገኙበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በተጨማሪ የውሃው ጥራትም እየተበላሸ ለማጣራት የሚፈጀው ገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ የሚሆንበት ጊዜም ያጋጥማል ይላሉ፡፡ ጨምረውም የውሃ ስርጭቱ ላይ ከፍተኛ እንቅፋት የሆነው የመስመር መሰበር ሲሆን፤ ባለስልጣኑ እነዚህን ችግሮች ለማቃለል ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
እንደ አቶ ንጉሱ ገለፃ፤ ባለስልጣኑ በአዲስ አበባ ስምንት ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፤ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ሁሉም እየሰሩ ናቸው፡፡ ከፈረቃ ውጪ ውሃ ሲቋረጥ ከ‹‹906›› ነፃ የስልክ አገልግሎት ባሻገር ሌሎችም የየቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶቹ የመስመር ስልኮችና የስራ አስኪያጅ ስልክ ሳይቀር ክፍት ሆነው የደንበኞችን ጥያቄ የሚያስተናግዱ ሲሆን፤ ከአቅም በላይ ያሉትን ችግሮች ደንበኞች እንዲያውቁት ይደረጋል፡፡ አንዳንዴ ከስነምግባር ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙ ችግሮች ሲኖሩ፤ ባለስልጣኑ የራሱ የሚያጣራበት ሁኔታ ቢኖርም በተጨባጭ ችግሮች የሚያስተውሉ ካሉ መክሰስና መጠየቅ ይችላሉ፡፡
የውሃ አገልግሎቱ በፈረቃ መሆኑ እጥረት በመፈጠሩ የተከሰተ መሆኑን ገልፀው፤ በተከታታይ በአንድ አካባቢ አገልግሎቱ የሚቋረጠው ከላይ በተገለፁት ምክንያቶች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ አያይዘውም አንድ ቦታ ያለምንም መቆራረጥ በተከታታይ የሚያገኘው ሆነ ተብሎ አድሎ በመፈፀም ሳይሆን ሌላው አካባቢ የሚያገኘው ከእነርሱ ሞልቶ ሲያልፍ በመሆኑና ከዚያ በላይ ምንም አማራጭ ስለሌለ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ለአብነት ከለገዳዲ የተነሳው ውሃ ቀጥታ መገናኛ ደርሶ ወደ ሌላ አካባቢ የሚሰራጭ ሲሆን፤ መገናኛ ሳይሞላ ሌላው አካባቢ ማግኘት ስለማይችል ያ አካባቢ በተከታታይ የሚያገኝበት ሁኔታ መኖሩን ነው ያመለከቱት፡፡
አቶ ንጉሱ ባለስልጣኑ ቀድመው በውጭ ምንዛሪ እጥረት ያልተጠናቀቁ የኮዬ ፈጬ አካባቢ የውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ወደ ስርጭት እንዲገቡ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ በተለያዩ የከተማዋ ኪስ ቦታዎችም ጉድጓድ በመቆፈር የውሃ አቅርቦቱን ለመጨመር ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
ምህረት ሞገስ