አዲስ አበባ፡-ሰላምና መረጋጋት ለአንድ አገር ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ መንግሥትና ህዝብ ተባብረው ሰላም እና መረጋጋትን ማምጣት እንዳለባቸው አቶ ልደቱ አያሌው አመለከቱ፡፡
ፖለቲከኛው አቶ ልደቱ አያሌው በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ተወደደምተጠላ በምርጫም ባይሆን አሁን ወደ ስልጣን የመጣ መንግስት አለ፡፡ ህዝብም የአሁኑ መንግሥት ወደ በጎ አቅጣጫ ያሸጋግረናል በሚል ዕውቅና ሰጥቷል፤ ሊደግፈውም ተዘጋጅቷል፡፡ ይህን ዕድል በመጠቀም መንግሥት ህዝቡን አሳምኖ በዙሪያው አሰባስቦ የለውጡ ባለቤት በማድረግ ህግና ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግ ይቻላል ብለዋል፡፡
« ለማመን በሚያዳግት መልኩ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሐ ማልማት የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፣ በአገሪቷ ታይቶ የማይታወቅ አሰቃቂ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች ሳይቀሩ በህግ ተጠያቂ እየሆኑ አይደለም፣ ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ የህግ የበላይነት አለመኖሩ አጠያያቂ ነው፡፡ ጉዳዩን በቸልተኝነት ማየት አይገባም፤ መንግሥት ያለው አቅም ሁሉ ተጠቅሞና ህዝብን አሳምኖ ሰላምን የማስፈን ግዴታ አለበት» ብለዋል አቶ ልደቱ፡፡
‹‹አሁን ላይ ስለምርጫ፣ ስለዴሞክራሲ፣ ስለሰብዓዊ መብት መነጋገር ቅንጦት ነው›› ያሉት አቶ ልደቱ፤ መጀመሪያ ለአንድ አገር መሰረታዊ ጥያቄ የሆነው የሰላም ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
ምህረት ሞገስ