አዲስ አበባ፣ የሥልጣኔ እና የታላቅነት ማሳያ አብነቶች ውስጥ አንዱ፤ ምናልባትም ዋነኛው – የማኅበረሰብ የዘመን ቀመር ዕውቀትቀዳሚ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ ፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምበላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ በዚህ ዋና ባልነው መለኪያ ስንመዝነው ደግሞ የሲዳማ ሕዝብ በፀሐይ፣ በጨረቃ እና በከዋክብት ድንቅ የተፈጥሮ ዑደት ውስጥ ያለውን ጥልቅ ፅንፈ ዓለም (ዩኒቨርስ) ምሥጢር በመመርመር ጊዜን እያሰላ ዘመንን የሚቆጥርበት ጥበብ እጅጉን የሚደንቅ የኩራት ምንጭ ነው፡፡
«ዘመን የሰው ልጆች የታሪክ፣ የማንነት፣ የባሕል፣ የሥነ ልቡና እና የህልውና መከተብያ፣ መሳያ፣ መበየጃ፣መንደፍያ እና ማቆያ ትንግርታዊ ሰሌዳ ነው፡፡ይህንን ድንቅ ሸራ በመቁጠር – በመቀመር – በማስላት እና በተፈጥሮ ዑደት ውስጥ የሚዘወርበትን ሥርዓት በመዘርጋት የሚጠቀምበት ማኅበረሰብ ደግሞ እርሱ ከዘመን ጋር የማይሄድ ከዘመንም ጋር የማይመጣ በዘመን ገላ ላይ ትናንት በአባቶቹ – ዛሬ በራሱ እና ነገም በልጆቹ ህያው የሚሆን ታላቅ ሕዝብ በመሆኑ የሲዳማ ሕዝብ ይህን ታላቅ የሥልጣኔ አበርክቶ አጥሮ፣ ጠብቆ አቆይቶልናል » በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የሰው ልጅ ከጊዜና ከቦታ ውጪ ለማሰብ፣ ለማሰላሰል፣ ለመፍጠር፣ እና ተፈጥሮን ለመመርመርም ሆነ እራሱን ለማረቅ እጅጉን ይቸገራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጊዜን የምናሰላበት መንገድ እና ዘመንን የምንቀምርበት ጥበብም እንደ ሰውም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ለሁለንተናዊ ሥልጣኔያችንና ራሳችንንም ሆነ ዙሪያችንን ለምንቀርጽበት ስብእና ብዙ ዐቅም እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
«በሲዳማ የዘመን አቆጣጠር ጥበብ ውስጥ እስከ ማይክሮ ሰከንድ ሽርፍራፊ የጊዜ ቅንጣት ድረስ የሚወርድ ጊዜን የመለኪያ ጥበብ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ለሲዳማ አባቶቻችን ያለንን ክብር እና ፍቅር እጅጉን ከፍ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ይሄንን የአዲስ ዓመት በዓል እና የዘመኑን አዲስነት ለማወጅ ጊዜን የሚቆጥርበትን ግሩም ዕሴት መላው ኢትዮጵያዊ ወገናችን ክብሩንም ሆነ በዓሉን ከልብ ይወደዋል እንደ ሁልጊዜው በጋራ ያከብረዋል» ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፡፡
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው « የሲዳማ ሕዝብ የራሱ የሆነ የዘመን አቆጣጠር ቀመር፣ “ወንሾ አምቦን” የመሰሉ የእርቅና የሽምግልና ስርዓት “ሉዋን” የመሰሉ ዴሞክራሲያዊ የስልጣን ሽግግር ስርዓት እና ሌሎች የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት የሆነ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪስት መስህቦች በዙሪያው አቅፎ የያዘ ሕዝብ ነው፡፡
የሲዳማዎች የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ ዘመን ከዘመን የሚለዋወጥበት ዕለት ብቻ ሳይሆን ፋይዳው ብዙ የሆነ ታላቅ ቀን ነው፡፡ ፍቼ ጫምባላላ ጉዱማሌ ላይ መገናኛ፣ መተጫጫ፣ መመራረቂያ፣መተሳሰቢያ፣ የወደፊት ተስፋ መሰነቂያ፣ ከአንደበት ክፉ ቃል የማይወጣበት ፣እንስሳቱ ሳይቀር ከሰው እኩል የሚከበሩበት ፣እንግዳ የሚከበርበት፣ ትውልድ የሚዘከርበት፣ለሀገር የሚበጀው ሁሉ የሚከወንበት ታላቅ በዓል ነው፡፡ በድጋሚ በእኔ እና በመላው የኦሮሞ ሕዝብ ስም እንኳን ለዚህ ታላቅ በዓል አደረሳችሁ- አደረሰን ለማለት እወዳለሁ» ብለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ወደ መኖሪያ ቀያቸው የተመለሱ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል።
በዞኑ ቀርጫ ወረዳ ጉራቹ ጀልዱ ቀበሌ በተለያዩ ግጭቶች ተፈናቅለው የነበሩ ከ3 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው የተመለሱ ሲሆን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ተፈናቅለው በጌዲኦ ዞን ገደብ ወረዳ ተጠልለው የነበሩት እና አሁን ወደ ቀድሞ ቀያቸው የተመለሱትን ተፈናቃዮች አነጋግረዋል።
ተፈናቃዮቹ አሁን ላይ ከበፊቱ የተሻለ ሰላም መኖሩን በማንሳት፥ ይህንን ሰላም አስተማማኝ በማድረጉ ረገድ መንግሥት እንዲሰራ፣ ክረምት እየገባ በመሆኑም ወደ እርሻ ሥራ መመለስ እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው መንግሥት በቻለው መጠን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል የገቡ ሲሆን፥ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር እንዲቀርብ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል።
ጉጂ እና ጌዲኦ ለዘመናት አብሮ የኖሩ ህዝቦች መሆናቸውን ከመወቃቀስ ለሰላም ሁሉም በጋራ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
እፀገነት አክሊሉ