አስታራቂ ምክሮች – ለሀገር ጽናት

አስታራቂዎች ብጹዓን ናቸው ይላል ታላቁ መጽሐፍ። ማስታረቅም ሆነ መታረቅ ለብጹዕነት የሚያበቃ የክብር አክሊል ከሆነ ማስታረቅና መታረቅ ለምን አቃተን? ወደሚል ጥያቄ እመጣለሁ። የትኛውም ችግር አስታራቂ ሃሳብ ካገኘ ወደ ፍቅር የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም። ችግሮቻችንን ከዚህ አንጻር ስንቃኛቸው አስታራቂ ነው ያጣነው ወይስ አስታራቂ ሃሳብ ነው የሌለን? ወደሚል ይመሩናል። አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሁለቱንም ያጣን ነን። ሁለቱንም ማጣት ደግሞ ጉዳቱ ምን ያክል እንደሆነ መረዳት አይከብድም።

ብሔራዊ ምክክር የአስታራቂነትን ሚና በመውሰድ ሃሳብ ተኮር በሆነ ሕዝባዊ መድረክ መጥቷል። ይሄ ዕድል ላጣነውና እያጣነው ላለው ፍቅርና አንድነት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰድ ብቻ ሳይሆን ዳግም የምንተቃቀፍበት የእርቅና የይቅርታ መድረክም ጭምር ነው። ስለሆነም ብሔራዊ ምክክር ኮሚሽንን እንደ አስታራቂ በመውሰድ የመታረቂያ ሃሳቦችን ደግሞ ከእያንዳንዳችን በማዋጣት ከምንምነት ሁሉም ወዳለው ማንነት መሸጋገር ይቻላል።

የተለያዩ የዓለም ሀገራት ፖለቲካዊና ማህበራዊ ችግሮቻቸውን በእንዲህ ዓይነት መንገድ ነው የፈቱት። ለአብነት ደቡብ አፍሪካንና ሩዋንዳን ብንወስድ ለእንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ጥሩ አርአያ የሚሆኑ አፍሪካዊ ሀገራት ናቸው። በዚህ ሕዝባዊ ተሳትፎ በኩል ነው አሁን ላላቸው ሀገራዊ ቁመና የበቁት። በርግጥ በዕድሉ ያልተጠቀሙ አንዳንድ ሀገራትም አሉ። መድረክ አዘጋጅቶ ከመወያየት ባለፈ ይሄ ነው የሚባል ቁምነገር ያልሰሩ።

የእኛ ሀገራዊ ምክክር ግን ከዚህ የተለየ ነው። በልምድና በተሞክሮ፣ በሕዝባዊ ውይይት ሀገር ከለወጡ የአፍሪካና የአውሮፓ ሀገራት ተሞክሮ ተወስዶ የተጀመረ ነው። ልክ እንደዚህ ሁሉ ከዚህ በፊት ሳንጠቀምባቸው ባለፉን የሀገራዊ ምክክር እድሎች ተምረን ለለውጥና ለተሐድሶ እንቅስቃሴ የጀመረ ነው። ስለሆነም አዋጪነቱ ከፍ ያለ ነው። በሄደባቸው ዓመታትን በወሰደ የዝግጅትና የቅድመ ሁኔታ እንቅስቃሴ ዓላማውን እንደሚመታ የሚናገሩ ብዙዎች ናቸው። አሁናዊ ቁመናውን ብንፈትሽ እንኳን የምክክሩ የመጨረሻ ምዕራፍ በሆነውና ወደተግባር በሚወስደው የክዋኔ አቅጣጫ ላይ እንደሚገኝ ማወቅ ተችሏል።

በአስራ አንድ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለምክክሩ የተሳታፊ ልየታና የአጀንዳ መነሻ ሃሳቦችን የማሰባሰብ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ አረጋግጠዋል።

ኃላፊነት እንዳለበት ባላደራ ኮሚሽን ሁሉንም ነገር በጥንቃቄና በኃላፊነት ይዞ እየተጓዘ እንደሚገኝ በተለያየ ጊዜ ከሰማናቸው የኮሚሽኑ መግለጫዎች ለማወቅ ችለናል።

በሀገሪቱ ከሚገኙ አስራ ሶስት ክልሎች በአስራ አንዱ ላይ የተሳታፊ ልየታና የመወያያ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ሂደት ጨርሶ ወደቀጣይ ምዕራፍ ተሸጋግሯል ያሉት ኮሚሽነሩ በኦሮሚያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሱማሌ ክልል የተባባሪዎችን ስልጠና ጨርሶ ወደሌሎች ክልሎች በመንቀሳቀስ ላይ ነው ብለዋል። የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ አባገዳዎችን፣ አዳ ሲንቄዎችን፣ ከእድር የተወጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ያሳተፈው የተባባሪዎች ስልጠና በዝግጅትና በቅድመ ሁኔታ የተሳካለት እንደነበር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በአማራና በትግራይ ክልል ተመሳሳይ ሥራ ሊሰራ ዝግጅት ያለቀ ሲሆን በተለይ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከሲቪክ ማህበራትና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ጥሩ ሥራ እንደሚሠራ አያይዘው ተናግረዋል። ከዋናው ሀገራዊ ምክክር በፊት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ክልላዊ ሕዝባዊ ምክክር እንደሚደረግ የተጠቆመ ሲሆን ከዞን፣ ወረዳና ቀበሌ የተመረጡ ተሳታፊዎች በክልል ደረጃ ቅድመ ምክክር እንደሚያደርጉ በኮሚሽነሩ በኩል ተገልጿል። ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በውጭ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች በዚህ ምክክር ላይ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ተጠቁሟል።

በያዝነው 2016 አጋማሽ ላይ ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ሕዝባዊ የእርቅና የተግባቦት መንገድ እንደ አጀማመሩ ጥሩ ውጤቶችን ለሀገርና ሕዝብ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል። በትላንት በዛሬ የፖለቲካ ዥዋዥዌ ውስጥ ወዲያ ወዲህ ለምትል፣ ባልሻረ እና ሊሽር ባላለ ቁስል እዬዬ ለምትል ሀገር ይሄን ዓይነቱ ነጻና ገለልተኛ መድረክ መፍትሔ ስለመሆኑ ብዙዎች መስክረዋል። የነበሩና ያሉ ወደፊትም የሚኖሩ አንድነትንና አብሮነትን የሚያወይቡ ችግሮች በጦርነት ሳይሆን በምክክር እንደሚፈቱ ለትውልዱ አጽንኦት ከመስጠት ባለፈ የተለማመድናቸውን እልፍ የኃይል ልምምዶች ያስቀራል ተብሎ ይታሰባል።

ንቃት ተኮር ፖለቲካን ሳንለማመድ ሕዝብን ለማንቃት የሄድንበት ርቀት ወደኋላ አስቀርቶናል። ከጦርነት በፊት ውይይትና እርቅ አልሆን ብሎን ከብዙ ዋጋ መክፈል በኋላ እየተጨባበጥን ቅደም ተከተሉን ባልጠበቀ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ፊተኝነትን ተነጥቀን ኋለኞች ሆነናል። ባስታራቂነቱና በይቅር ባይነቱ ታሪክ የጻፈ የሰላምና የፍቅር አለቃ ሕዝብ በአጉል ትርክት ሰላምና አንድነት አጥቶ ላልኖረበት ዘመን እዳ ሲከፍል ሰንብቷል። በወንድማማች መሀከል ጠብን በሚዘሩ ጥቂቶች ብዙሃኑ ተፈራርቶ የጎሪጥ እየተያየ ኢትዮጵያዊነትን ፈርቶ ሸሽቶ ቆሟል።

ከሌማቱ እያነሳ፣ ከገንቦው እየቀዳ ከብላና ጠጣ በቀር ጉርብትና የሌለው ሕዝብ ዛሬ እንደ አይጥና ድመት ካብ ለካብ እየተያየ የፍቅር ወደቡን በስጋት ቀይሯል። ለጥቂት ትርፍ ታሪክ አዛንፈው፣ በሀሰት ስብከት፣ ትውልዱን ደም ለማቀባባት ራሳቸውን ፊተኛ ያደረጉ እኩያን ጥንተ ፍቅራችንን ነጥቀውናል። ከኢትዮጵያዊነት ሌላ ምልክት የሌለን በኩረ ነፍሶች ብሔር የሚል ጋፍ ስም ለጥፈውብን ባለምልክት አድርገውናል። ኢትዮጵያ የሚለውን አፍ የፈታንበትን የልጅነት እውቀታችንን በዘረኝነት ለውጠው ተወናብደው አወናብደውናል።

መዳኛችን ምንድነው? መዳኛችን ስክነት ነው። ሰክነንና ረግተን በኢትዮጵያዊነታችን መሀል ምን እየተካሄደ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል። ከዚህ መረዳት በኋላ ስናደርገው የነበረውና አሁንም እያደረግነው ያለው ነገር ልክ እንዳይደለ መረዳት ላይ እንደርሳለን። ከዚህ ንቃት በኋላ ወደነበርንበት የከፍታ ማማ በሚወስደን የመፍትሔ ሃሳብ ላይ እናተኩራለን። መፍትሔው ደግሞ ስለአንድነትና አብሮነት የሚከፈል የጋራ መስዋዕት ይሆናል። ይሄውም ምክክርና ውይይት እርቅና ተግባቦት ሆኖ ይገለጣል። መጀመሪያ ስንነሳ በስክነት ነበር። ቀጥሎ ምን እንደነበርንና አሁንስ ምን እንደሆንን ድሮና ዘንድሮን ወደ መረዳት መጣን። ቀጥለን እያደረግነው ስላለው ነገር ማሰብ ጀመርን። ቀጥለን የመፍትሔ ሃሳብ ላይ አተኮርን። በስተመጨረሻም ኢትዮጵያዊነትን በሚመልስ እርቅና ምክክር ላይ አረፍን።

በስክነት ተነስተን በእርቅ ቋጨነው። አያችሁ ከየት ተነስተን የት እንደደረስን? ከዚህ እውነታ በመነሳት እንደ ሀገር ምን እንደጎደለን ማወቅ እንችላለን። ስክነት የለንም። በኃይል ካልሆነ ሰክነንና ረግተን መፍትሔ የሰጠንበት ጉዳይ እምብዛም ነው። ከየትም፣ እንዴትም ይነሱ መከራዎቻችን የእኛን ትዕግስት ማጣት ተጠቅመው ነው የልብ ልብ ያገኙት። የመከራዎቻችን አቀጣጣዮች በመሆን፣ እኛው በእኛው ላይ ጨክነን ብዙ ዋጋዎችን ከፍለናል። መከራ እንዲበቃን ስክነት የታከለበት አእምሮና ልብ ያስፈልገናል።

ስክነት የምንም ነገር መነሻ ነው። ክፉን የሚያራራ፣ ኃይለኛውን የሚያረጋጋ። በኃይልና በእልህ ተሞልተን ርምጃ ከመውሰዳችን በፊት በስክነት ሁሉንም መቃኘት ዋጋ ከመክፈል የሚታደግ ብልህነት ነው። እንደሀገር ይሄ ብልሃት ያስፈልገናል። በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ እንስቅቃሴዎች ውስጥ ስክነት ያለበት ብልሃት እጅግ አትራፊ ነው። በሀገራዊ ምክክር መድረክ ፊት ስንቀርብ ተሟግቶ ለማሸነፍ፣ ተከራክሮ ለመርታት ሳይሆን ተወያይቶ ለመግባባት እና ወደ እርቅ ለመሄድ እንደሆነ መረዳቱ አላማችንን ለመጨበጥ ወሳኝ ነው።

መቼና እንዴት በማን እንደተፈጠሩ በማናውቃቸው ትርክት ውስጥ ነን። ታቅደውና ታስቦባቸው በተፈበረኩ እብለቶች እና አሉባልታዎችም ውስጥ ነን። እኚህ ሁሉ ስክነት ይሻሉ። ቢያንስ ከየት መጡ? ማን አመጣቸው? ለምን መጡ? የሚለውን መሠረታዊ የእርቅ ጥያቄ ለመመለስ ይረዱናል። እኚህ ጥያቄዎች እንደ ሀገር ወደተግባቦት ለመሄድ ወሳኝ ናቸው። ወሳኝነታቸው የሚረጋገጠው ደግሞ ሰክነን ስንናገር፣ ሰክነን ስናደምጥ እና ሰክነን ስንግባባ ነው።

አስታራቂ ምክሮች የሀገር ምሰሶዎች፣ የትውልድ ካስማዎች ናቸው። በጎ አንደበቶች የፍቅርና የይቅርታ መሀሉን ናቸው። በወሬ እንደፈረስን ሁሉ መጽኚያችንም አስታራቂ ሃሳብ ነው። በትርክት እንደተለያየን ሁሉ መተቃቀፊያችንም ስክነት ነው። ያልበላንን ከማከክ ወጥተን አልድን ላለን ቁስላችን መፍትሔ ማምጣቱ ላይ ማተኮር ነው ዘላቂ ሰላምን የሚሰጠን። ከይዋጣልን ወጥተን እንዴት በውይይትና በድርድር አሸናፊ መሆን እንደሚቻል ማወቁ ነው በትላንት እንዳንዳክር በዛሬ እንዳናፍር የተሐድሶ አቅጣጫን የሚሰጠን።

ብሔራዊ ምክክር እንደ ስሙ ሀገራዊ ተግባቦትን የሚፈጥር ከሕዝቦች ለሕዝቦች ጽንሰ ሃሳብ ነው። ከሕዝብ የሚነሱ ማናቸውም ቅሬታዎች እንዲህ ባለው መድረክ ፊት መፍትሔ የሚሰጣቸው ናቸው። ከላይ እንዳልኩት የትኛውም ውይይት ፍሬ የሚያፈራው አስቀድሞ ለእርቅ በተሰናዳ አእምሮ በኩል ነው። ለውይይት ስንቀመጥ ለማሸነፍ ሳይሆን ለመሸነፍ፣ ለመርታት ሳይሆን ለመረታት ነው። ምክንያቱም የምንፈልገው የሰላምና የአብሮነት ትንሳኤ ያለው በመሸነፍ ውስጥ ስለሆነ።

በማሸነፍ ስለመጣን የመሸነፍን ዋጋ አናውቀውም። ትላልቅ ድሎች ያሉት በመሸነፍ ውስጥ እንደሆነ የገባቸው ጥቂቶች ናቸው። እኛም ስለፍቅር ስንል፣ ተዋዶና ተከባብሮ ስለኖረ ሕዝብ ስንል ስለአብሮነት መሸነፍን ካልመረጥን በማሸነፍ ፖለቲካ እና የኃይል ልምምድ አርነት መውጣት አይቻለንም። ትላንትን ረስቶ፣ ዛሬን ተስማምቶ ነገን ተስፋ አድርጎ ለመኖር ስለአብሮነታችን ብዙ የቤት ሥራዎች አሉብን።

በፖለቲካ እና በአጉል ትርክት ቁስለኛ ከሆንን ዘለግ ያለ ዓመታት ተቆጥረዋል። ቁስሎቻችን ከመዳን ይልቅ ጥዝጣዜን እየፈጠሩ እንደ ሀገር ሀበሳን፣ እንደ ትውልድ ደግሞ ጥላቻን አልብሰውናል። ቁስሎቻችንን ከማዳን ይልቅ እንዳይድኑ እሽሩሩ እያልን እንደመጻጉ ድውዮች ሆነን ይሄው አጎንብሰናል። እስከ መቼ ቀና ማለት ተስኖን እንደጎበጥን እንደምንኖር አላውቅም። ባልገባንና ባላወቅነው ሁናቴ እያዳለጡ የጣሉን የራስ ወዳድነት ማቆች ከላያችን ላይ ተቀደው እንዲወድቁ መሸነፍ ያለበት፣ ፍቅርን ፊተኛ ያደረገ የምክክር እና የእርቅ ፍኖት እንደሚያስፈልገን ስጠቁም በእርግጠኝነት ነው።

ሀገራችን እንደ ሀገር አረንጓዴ ብጫና ቀይ ቀለም ተሸልማ፣ በህብረ ብሔራዊነት ቆንጅታ የነፃነት እና የሉዓላዊነት ፋና ወጊ የሆነችው በምክረ ሃሳብ ነው። ሕዝባችን በአብሮነት እና በመደማመጥ የጀገናው አንድም አክብሮ ሁለትም ተከብሮ ነው። እነዛ ፊተኝነትን ያጎናጸፉን የአብሮነት ቀለሞቻችን ዳግም አብበው እንዲያደምቁን የሃሳብ መዋጮ ያስፈልገናል። አንተም ተው አንተም ተው የሚሉ የእርቅ ሃሳብ። በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ የሚሰብኩ ብሩካን አንደበቶች ያሹናል።

ሃሳብ እናዋጣ። ሀገራችንን በሃሳብ ማግረን በፍቅር ካላጸናናት ከብሔር ቡዳኔ አንወጣም። ገርተውና አቃንተው የሚያስተቃቅፉ አስታራቂ ሃሳቦች ያስፈልጉናል። የምንናገረውን የሚያደምጥ ብዙ ትውልድ አለ። የሰማውን የሚናገር እንደዚሁ ሌላ ትውልድ አለ። ሀገር ቅብብሎሽ ናት። ከዛሬ ወደነገ ፍቅርን እንጂ ጥላቻን ይዘን እንዳንሄድ በፍቅር የሻረ ትውልድ መገንባት ኢትዮጵያን ከምንወድ ከሁላችን የሚጠበቅ ተግባር ነው።

በእንዲህ ካልሆነ ቁስሎቻችንን አናሽራቸውም። በእንዲህ ልሆነ ጥዝጣዜዎቻችንን አናክማቸውም። ብሔራዊ ምክክር ኢትዮጵያዊነትን ወደነበረበት ለመመለስና የሕዝቦችን ወንድማማችነት ለማረጋገጥ ላለፉት ዓመታት ሚናውን በመወጣት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ቆሟል። ከእኛም የሚዋጣ የሃሳብ መዋጮ አለና በጋራ ሃሳብ ከጎበጥንበት ለመቅናት እንረባረብ።

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን  ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You