የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ናቸው። ገና በአፍላው የእድሜ መባቻ ላይ ያሉ። ለዚህ ጽሑፍ ግብዓት ይሆነኝ ዘንድ የትምህርት ቤቱን ወጣት ተማሪዎች ለማነጋገር በሄድኩበት ወቅት ነበር የተገናኘነው። ስማቸው እንዳይጠቀስ ያስጠነቀቁን ወጣቶች በፍፁም ነፃነት እንዲህ ብለውናል።
ልጅነታቸው ያሳሳል። የሚያወሩት ነገር በሙሉ ለእድሜያቸው የማይመጥን መሆኑ ደግሞ ነገሩን ከበድ ያደርገዋል። ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ መጠቀምን ምንም ጉዳት እንደማይኖረው ነው የሚያስቡት። በአፍላ የወጣትነት ጊዜ ላይ ግንኙነት መጀመራቸውን እንደ ጥፋት አይመለከቱትም። ሁለቱም ወጣት ሴቶች የወንድ ጓደኛ እንደላቸውና በወር ከሶስት እስከ ስድስት ለሚደርስ ጊዜ ፆታዊ ግንኙነት እንደሚያደረጉ ነው የሚናገሩት።
ኤች አይ ቪና ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች እንዳይዟቸው ብሎም እርግዝናን ለመከላከል ኮንዶም ይጠቀሙ እንደሆነ ብዬ ብጠይቃቸውም ምንም ዓይነት ኮንዶም የመጠቀም ፍላጎት እንደሌላቸውና ለእርግዝና መከላከያነት ግን በቋሚነት ፖስት ፒሊን እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል። የኤች አይ ቪ ጉዳይ ብዙም እንደማያሳስባቸውና ዋናው ጭንቀታቸው እርግዝና መሆኑን ሁሉም በአንድ ቃል የሚናገሩት ነው።
ስለ ፖስት ፒል በስፋት ስለሚወራ ሁሉም በሚባል ደረጃ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ያውቁታል የሚሉት ወጣቶቹ በእርግዝና ምክንያት በማህበራዊ ሕይወት ላይ ከሚመጡ ችግሮች ስለሚያደናቸው እንደሚወዱት ይናገራሉ።
ይህን ቅጥ ያጣ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ አጠቃቀም አፍላ ወጣት ሴቶች ላይ የሚያደርሰው የጎንዮሽ ጉዳት አይኖር ይሆን ስንል በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስትና ዲፓርትመንት ሄድ Department Head የሆኑትን ዶክተር ዳዊት መስፍንን አነጋግረናል።
ዶክተር ዳዊት እንደሚሉት አንዲት ሴት ግንኙነት ከጀመረች በኋላ ላልተፈለገ እርግዝና እንዳትገለጥ የሚያደርጉ በርካታ ዓይነት የወሊድ መቆጣጠሪያ ዓይነቶች አሉ። በክንድ የሚቀበር፤ በማህፀን ውስጥ የሚቀመጥ፤ በአፍ የሚወሰድ ክኒንና ተፈጥሯዊ የመከላከያ መንገዶች ተጠቃሽ ናቸው።
ፒስት ፒልም የድንገተኛ የወሊድ መከላከያ ነው። ይህ ድንገተኛ መቆጣጠሪያ ቋሚ ወይም መደበኛ የወሊድ መቆጣጠሪያ ከሚባሉት ውስጥ አይመደብም። ያልታሰበ ግንኙነት ካለ ወይንም ደግሞ አንዲት ሴት ቋሚ የሆነ የወሊድ መቆጣጠሪያ የምትጠቀም ሆና ሳለ ድንገት የምትረሳ ከሆነ፤ ወይም ደግሞ ኮንዶም የምትጠቀም ሆኖ ኮንዶሙ የመቀደድ የመሳሰሉት ነገር ካለ ፖሰት ፒል እንድትጠቀም እንመክራለን ይላሉ።
ከተጠቀሱት ነገሮች ውጭ አንዲት ሴት ደጋግማ ፖስት ፒል እንድትጠቀም አይመከርም የሚሉት ዶክተር ዳዊት ይህም የሆነበት ምክንያት ፖስት ፒል እስከ ሰማኒያ በመቶ ስኬታማ መቆጣጠሪያ ነው ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን አስራ አምስት ከመቶ በሚሆኑ ሴቶች ላይ በብዙ ነገሮች ምክንያት ፖስት ፒል ላይሳካና እርግዝና ሊከሰት የሚችልበት ሁኔታዎች በመኖራቸው ፖስት ፒልን አዘውትራ እንድትጠቀም እንዳይፈቀድ አድርጎታል።
ሌላው ፖስት ፒል የሚሰራው የእንቁላል መለቀቅን በማዘግየት ነው። ያ ማለት አንዲት ሴት በአንድ ወር ውስጥ አንድ እንቁላል ነው የምትለቀው። ያም ኦቭሌሽን ይባላል። ያንን እንቁላል እንዳይለቅቅ ወይም እንዲዘገይ በማድረግ መስራት ነው እንግዲህ የፖስት ፒል ተግባር። ነገር ግን እንቁላሉ ከተለቀቀ በኋላ ፖስት ፒልን አንዲት ሴት ለመውሰድ ብትሞክር እርግዝና የመከሰት እድሉ ከፍተኛ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
ፖስት ፒል ተደጋግሞ በሚወሰድበት ጊዜ ፔሬድን (የወር አበባን) ማዘግየት ወይም አንዲት ሴት የምትጠብቀውን ፔሬድ አዘግይቶ ወይም ከቀኑ አስቀድሞ ማምጣት፤ ፔሬድ በሚመጣበት ጊዜ ከፍተኛ ህመም እንዲሰማት ማድረግ የፖስት ፒል የጎንዮሽ ጉዳት ነው ተብሎ ይታሰባል።
ሌላው ጉዳት ከላይ እንዳነሳነው ፖስት ፒል ሥራውን የሚሰራው እንቁላል መለቀቅን በማዘግየት ሲሆን ሌላው ደግሞ መራቢያ አካላት ላይ ያሉ ፈሳሾች በማወፈር እርግዝና እንዳይከሰት ወይም የወንድ ዘር እንዳይገባ የማድረግ ሥራን ይሠራል። ፖስት ፒል ውስጡ ፕሮጅስትሮን የተባለ ንጥረ ነገር አለው፤ ይህ ነጥረ ነገር አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሴቶች ላይ እንቁላል ቱቦ ላይ እንዲቆይ ያደርገዋል። እንቁላል የሚቀበለው ቱቦ ማለትም እንቁላልን ተቀብሎ ወደ ማህፀን የሚያስተላልፍ ሥራ ነው የሚሰራው። ይህ የቱቦን ሥራ ወይንም እንቁላልንና የወንድ ዘርን ተቀብሎ ወደ ማህፀን የማስተላለፍ ሥራ ማዘግየት፤ ወደ ማህፀን የሚያመጣበትን አንድ ሳምንት በማዘግየት ከማህፀን ውጭ እርግዝና ሊከሰት እንዲችል ሊያደርግ ይችላል ብለዋል።
በአጠቃላይ “ድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሎች በተደጋጋሚ ሲወሰዱ የሆርሞን መዛባትን በማስከተል የወር አበባ ማስተጓጎል፣ ማህጸን እርግዝና እንዳይዝ በማድረግ ጉዳት የሚያስከትል ተጽዕኖ አላቸው” ‹ፖስት ፒል› ድንገተኛ እንጂ ቋሚ የእርግዝና መከላከያ አይደለም። ተደጋግሞ የሚወሰድ ከሆነም የሚያስከትለው የጎንዮሽ ጉዳት አለ። የብልት መድማት፣ የማህጸን ጽንስን መሸከም አለመቻል ከሚያስከትላቸው ዘላቂ የጤና ጉዳቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
ከፖስት ፒል ጋር ተያይዞ ያሉ ጉዳቶች ብቻ ሳይሆን የተሳሳቱ አመለካከቶችም አሉ የሚሉት ዶክተር ዳዊት ፖስት ፒል መካንነት ያመጣል የሚባለው ነገር እጅግ በጣም የተሳሳተ ነው ብለዋል። ፖስት ፒል ማህፀን ላይ ዘላቂ የሆነ ሥራ ስለሌለው መካንነትን ሊያመጣ አይችልም። በርግጥ ፖስት ፒልን በተደጋጋሚ የሚወስዱ ሴቶች ፔሬድ መዘባት ስለሚገጥማቸው ወቅታዊ እርግዝና የማይፈጠርበት አጋጣሚ ሊኖር ቢችልም ለዘላቂ ጉዳት ግን አይዳርግም ብለዋል።
“ሌሎቹ የወሊድ መከላከያ መንገዶች የተዘነጉ ይመስላል” ያሉን ዶክተሩ። “በተለይ ወጣቶች ከቅድመ ጥንቃቄ ይልቅ የድህረ-ርምጃዎች ላይ አተኩረዋል። የሚፈሩት እርግዝናን ብቻ ነው። የሚጠነቀቁት እንዳያረግዙ ብቻ ነው። ይህ መሆኑ የድንገተኛ እርግዝና መከላከያ እንክብሎችን ሽያጭ ብቻ ሳይሆን ኤች አይ ቪን ጨምሮ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎችን ሥርጭትም ጨምሯል” ይላሉ።
እንደ አጠቃላይ ወጣቶች ስለጉዳዩ በቂ እውቀት ስለሌላቸው እያንዳንዱ ነገርን አቅልሎ የመመልከት ሁኔታ ይታይባቸዋል የሚሉት ዶክተሩ፤ ወጣቶቹ በቂ እውቀት እንዲኖራቸው በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ጠንከር ያለ የሥነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት መስጠት አስፈላጊ ነው ይላሉ። ወጣቶቸ ያላቸው የእውቀት ውስንነት ስላለ ነው ኤች አይ ቪና ሌሎች የአባላዘር ህመሞችን ሳይፈሩ እርግዝናን እንዲፈሩ ያደረጋቸው ስለዚህ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ያስፈልጋል ብለዋል።
“በመድኃኒት ቤቶች ላይ እንደተፈለገ ነው ይህ መድኃኒት የሚገኘው። እዚህ ጉዳይ ላይ መንግሥትም አፅንኦት ሰጥቶት መድኃኒት ቤቶችም ገደብ እንዲኖራቸው፤ ወይም በማዘዣ ብቻ የሚገዛ ሊሆን ቢችል ከመድኃኒቱ ጋር የሚመጣው የጎንዮሽ ጉዳት ሊቀንስ ይችላል ብዬ አስባለሁ” በማለት አሳስበዋል።
ሌላው ፖስት ፒል ብቻ በመጠቀም ከእርግዝና በላይ አስፈሪ የሆኑትን ህመሞች ማለትም ሂፕታይተስን፤ ኤች አይ ቪን፤ የአባላዘር በሽታዎችን እንድንረሳ እየተደረገ ነው። ፖስት ፒል ስጠቀሙ በግንኙነት ምክንያት የሚመጡ ህመሞች ላይ ትኩረት ማድረግ አልተቻለም።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ በስፋት ከተዋወቁት የወሊድ መቆጣጠሪያ መንገዶች መካከል «ፖስት ፒል» ወይም ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የብዙዎችን ወጣቶች ቀልብ ስቧል። ሆኖም ስለሚያስከትለው ጉዳት ግን ብዙ የሚባል ነገር የለም።
ሆኖም ያልተጠበቀ ወሲባዊ ግንኙነትን፣ ሌላ የእርግዝና መከላከያዎች አስተማማኝነት በሚያጠራጥርበት ጊዜ ወይንም መደፈርን ተከትሎ ከሚወሰዱ የተለያዩ የእርግዝና መከላከያ መንገዶች መካከል የአስቸኳይ ጊዜ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች የሚባሉት በረሳቸው ቋሚ መከላከያ ሊሆኑ የማይችሉ ናቸው።
እነዚህ እንክብሎች ግንኙነት በተደረገ በ72 ሰዓታት ውስጥ መወሰድ ሲገባቸው የሚወሰዱበት መጠን እንደ ኬሚካል ይዞታቸው ይለያያል። መከላከያዎቹን ለመውሰድ መዘግየት እርግዝና ሊያጋጥም የሚችልበትን ሁኔታ ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል።
ዶክተር ዳዊት እንደሚሉት ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የሚባሉትን ከአንድ ጊዜ በላይ መጠቀም አይመከርም። እርግዝናን የሚሸሹት ወጣት ሴቶች የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ የሚባሉት ተጠቃሚዎች ለጎንዮሽ ጉዳቱ ተጋላጭ ናቸው።
“የፖስት ፒል አጠቃቀም ‘መረን የለቀቀ ነው’ የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በጥናት ላይ የተደገፈ መረጃ ማቅረብ ያስፈልጋል” ብለውናል። “ማንኛውም መድኃኒት ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት በተገቢው ሐኪም ሊታዘዝ፣ በታዘዘው መሠረት ሊወሰድ ይገባል። መድኃኒት መደብር ውስጥም ሆነ በቤት ውስጥ ሲቀመጥ በአምራች ድርጅቱ በተፈቀደው የአየር ንብረት እና እርጥበት ሊሆን ይገባል። እነዚህ ነገሮች ካልተሟሉ የመድኃኒቱ ፈዋሽነት ሊቀንስ፣ ታካሚውን የተወሳሰበ የጤና ችግር ውስጥ ሊከት የሚችልበት አጋጣሚ ከፍ ያለ ነው” የሚሉት ሐኪሙ ድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ከሆርሞን ጋር ግንኙነት ስላላቸው በዓመት በተደጋጋሚ ሊወሰዱ እንደማይገባ መክረዋል። የእንክብሎቹ በተደጋጋሚ መወሰድ ከማሕጸን ውጭ ለሚፈጠር እርግዝና ሊያጋልጥ እንደሚችል ያነሱት ዶክተሩ “የድንገተኛ የእርግዝና መከላከያ ስሙ እንደሚያመለክተው ከብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ በድንገት ለሚፈጠር ክስተት እንዲያገለግሉ እንጂ እንደ ቋሚ መከላከያ እንዲቆጠሩ አይመከርም” ሲሉ ንግግራቸውን ቋጭተዋል።
ዶክተር ዳዊት እንደሚሉት በሌላ በኩል በመጀመሪያዎቹ የወጣትነት ዕድሜዎች ላይ ግንኙነት መጀመር በአብዛኛው ለማህፀን ጫፍ ካንሰር ያጋልጣል። ይህን የማህፀን ጫፍ ካንሰርን የሚያመጣው ቫይረስ ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ይባላል። ይህ ቫይረስ ደግሞ አንዲት ሴት በለጋ ዕድሜዋ ማለት የማህፀን ጫፍ ለጋ በሆነበት ባልዳበረበት ጊዜ ግንኙነት የምትጀምር በመሆኑ ለቫይረሱ ሊጋለጥ ይችላል።
ሌላው በለጋ ዕድሜ ወይም በኩርድና ጊዜ የሴት ልጅ የመራቢያ አካል ብዙ ዓይነት ለውጦች ያመጣል ይህ ለውጥ ደግሞ የተለያዩ ኬሚካሎች መፈጠራቸው ማህፀን ጫፍ ላይ ለውጦች ያመጣል። ይህ ለውጥ ለዚህ ቫይረስ የመጠቃት ዕድልን ይጨምራል። ጥንቃቄ የጎደለው ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ተጋላጭነቱ ይጨምራል።
ይህ ቫይረስ ብዙ ሴቶች በአንድ ዓመት ውስጥ ሰውነታቸው የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ እስከሆነ ድረስ ሊገሉት ይችላሉ። ሰውነታቸው በሽታን የመቋቋም አቅማቸው አነስተኛ በሆኑ ሰዎች ላይ ይህ ቫይረስ ሥራውን በመቀጠል የማህፀን ጫፍን ካንሰር ሊያደርግ ይችላል።
ይህ ካንሰር እስከ አስር ዓመት ጊዜ ሊሰጥ ስለሚችል ሴቶች ግንኙነት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ምርመራ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ይህ ማለት ቫይረሱ የፈጠራቸውን ካንሰሮች ከአምስት እስከ አስር ደቂቃ በሚደርስ ሕክምና ማከም ይቻላል። ሕክምናውም መቶ በመቶ ውጤታማ ነው። ስለዚህ ሴቶች ግንኙነት ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በየሶስት ዓመቱ ምርመራ ማድረግ ይገባቸዋል።
ማወቅ ለመዳንም፤ ለቅድመ መከላከልም ጠቃሚ ነውና ወጣቶቻችን ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መሥራት ይገባናል በሚል መልእክት ዶክተር ዳዊት የነበርን ቆይታ ቋጭተዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም