የዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ወደ 1964ዓ.ም ይወስደናል። በወቅቱ ተከስተው ካለፉ፤ አለፍ ሲሉም ግርምትን የሚያጭሩብን ጉዳዮችን እናስታውሳለን። በጆሞ ኬንያታ የተሰየመው የአዲስ አበባው ጎዳና፤ የጉማሬው ንክሻና በቁማር ሰው ያጋደለውን ኮት ጨምሮ ሌሎች ጉዳዮችንም በማከል ቀርበናል።
ፊደል ሠራዊት እርዳታ ለማግኘት በዓል ያዘጋጃል
በኢትዮጵያ የፊደል ሠራዊትን ጠቅላላ አገልግሎት በበለጠ ከፍ ለማድረግ ባለው ዕቅድ መሠረት፤ አንድ ከፍተኛ በዓል ተዘጋጅቶ አንድ ሚሊዮን ብር ለማግኘት የሚያስችል ዕቅድ እንዳለው ተገለጸ።
ከታኀሣሥ 7 ቀን እስከ ጥር 7 ቀን 1964ዓ.ም የሚከበረው የኢትዮጵያ የፊደል ሠራዊት አራት ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ በ1 ሺህ ተማሪዎች አማካይነት የገንዘቡ እርዳታ ፕሮግራም የሚካሔድ መሆኑን ዶክተር ኤፍሬም ይስሐቅ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። የገንዘቡም ስብሰባ የሚከናወነው፤30 ሺህ የደረት ጌጦች በመሸጥ ነው።
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 3 ቀን 1964ዓ.ም)
በአዲስ አበባ ከተማ በጆሞ ኬንያታ ስም መንገድ ይሰየማል
በመስቀል ዓደባባይና በድራይቭ ኢን ቲያትር መካከል ያለው ጎዳና፤ “የክቡር ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ መንገድ” ተብሎ ዛሬ 4 ሰዓት ላይ የሚሰየም መሆኑን ትናንት ከአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የደረሰን ዜና ገለጠ።
የመንገዱንም ስያሜ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ፈቃድ በሥፍራው ተገኝተው በይፋ የሚያስተዋውቁት፤ ክቡር ዶክተር ኃይለ ጊዮርጊስ ወርቅነህ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ናቸው።
በዚህም ሥነ ሥርዓት ላይ የኬንያ ኤምባሲ ከፍተኛ ባለሥልጣኖችና የተጋበዙ እንግዶች፤ እንዲሁም የከተማው ሕዝብ ይገኛሉ።
ክቡር ከንቲባው መንገዱ በክቡር ጆሞ ኬንያታ የኬንያ ፕሬዝዳንት ስም እንዲጠራ ከግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መፈቀዱን በሚያስተዋውቁበት ወቅት፤ አጭር ንግግር ያደርጋሉ። የጦር ሠራዊት የሙዚቀኞች ጓድም በዚሁ ሥፍራ በመገኘት በሥነ ሥርዓቱ ወቅት የሁለቱን ሀገሮች የሕዝብ መዝሙር ያሰማል።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 24 ቀን 1964ዓ.ም)
በቁማር የተያዘ ኮት ሰው በጩቤ አጋደለ
በቁማር ጨዋታ ብዙ ገንዘብ ተበልቶ ኮቱን በዕዳ አስይዞ፤ በመጨረሻው በዕዳ የተያዘውን ኮቱን ለማስመለስ በተነሣው ጠብ፤ ተክለ አረጋይ ወሰኔ የተባለው፤ እሸቱ ማተቤን በጩቤ ወግቶ ገድሏል በመባል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀረበ።
ሟቹን ገደለ የተባለው ሰው በአዲስ አበባ ደጃዝማች ነሲቡ ሠፈር ከአንድ ሻይ ቤት ጓዳ ውስጥ ከሌሎች ግብረአበሮቻቸው ጋር ቁማር ሲጫወቱ በመጀመሪያ ሟች ብዙ ገንዘብ በቁማር ወስዶበት፤ በመጨረሻም ተክለ አረጋይ በጨዋታው በማየሉ በተፈጠረው አለመግባባት መሆኑን፤ አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ/ ወንጀል ችሎት የቀረበው የዓቃቤ ሕግ ክስ ይዘረዝራል።
ሟቹ አደጋው ሊደርስበት የበቃው መጀመሪያ ኮቱን በቁማር አስይዞ ራቁቱን ወደ ቤቱ ለመግባት ባደረበት ብስጭት ምክንያት፤ ከአራት ገላጋዮች አምልጦ ገዳዩን በመያዙ፤ገዳዩም አልሞት ባይ ተጋዳይ በመሆን በጩቤ የወጋው መሆኑን ምስክሮች አስረድተዋል። ተከሳሹም አምኗል።
የቁማር ቤት ተጋዳዮች አዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ፤ ገዳዩ በቀጠሮ ወህኒ ቤት ሆኖ፤ የአልሞት ባይ ተጋዳይ ክርክሩን ከፍቶ በጠበቃው አማካይነት በነጻ መለቀቅ አለብኝ በማለት ሙግቱን ቀጥሏል።
(አዲስ ዘመን ህዳር 13 ቀን 1964ዓ.ም)
ጉማሬ በንክሻ ሰው ገደለ
ጅማ፤(ኢ.ዜ.አ)- ተነቦ ቀበሌ ነዋሪ የነበር አንድ የ22 ዓመት ወጣት ባለፈው ማክሰኞ በጉማሬ ተነክሶ ሞተ።
ከድር አባጊቤ ይሔው ወጣት በጉማሬ ተነክሶ የሞተው በሊሙ ኮሳ ወረዳ ውስጥ ተነቦ በተባለው ቀበሌ በእርሻ ሥራ ላይ እንዳለ መሆኑን የወረዳው ዋና ጸሐፊ አቶ ለማ አዱኛ ገልጠዋል።
ከድር ከጊቤ ወንዝ ውስጥ በወጣው ግዙፍ ጉማሬ የቀኝ ታፋውን በተነከሰበት ወቅት ባሰማው ጩኸት የአካባቢው ሕዝብ ወዲያውኑ ለእርዳታ ደርሶ ነበር። ሆኖም ጉማሬው በቶሎ ተመልሶ ወደ ዉሀው ውስጥ ሲገባ በደረሰበት አደጋ ወዲያውኑ ሕይወቱ አልፏል።
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 10 ቀን 1964ዓ.ም)
ለፈገግታ ያህል
በአንድ አገር አንድ ፌዘኛ ሰው ከሚስቱ ጋር ይኖር ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ሚስቱ አርግዛ ልትወለድ ስታምጥ ሰውየው ሰለቸውና፤ ወደ ውጪ ወጥቶ አንድ መጠጥ ቤት ገብቶ ሲጠጣ ሦስት ሰዓት ሆነ፤ ከዚያም ወደቤቱ ሲገባ ጎረቤቶቹ እንኳን ደስ አለህ ሚስትህ ሦስት ልጆች ወልዳለች አሉት። ኸረ ጥሩ ነው እንኳን በስድስት ሰዓት አልመጣሁ፤ ስድስት ወልዳ ትጠብቀኝ ነበር እኮ አለ ይባላል።
(አዲስ ዘመን ጥር 13 ቀን 1964ዓ.ም)
አንድ ጥያቄ አለኝ
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*እኔ ባረጀሁበት ጊዜ የሚፈጠረው ሴት ሁሉም ቆነጃጅት ነው። ይኸ ነገር እንዴት ነው?
– ኃ-ዳ
-የርሶም ልጅነት ጊዜ ብዙ ቆነጃጅት ነበሩ። ያኔ እኩያ ለእኩያ እየተናነቃችሁ ልብ አትሉትም ነበርና ነው።
*ንጉሥ ዳዊት ያኖራቸው ሚስቶች በጠቅላላው 140 ሲሆኑ፤ ልጁ ሰለሞን የተወለደው ከየትኛዋ ሴት ነው? ስሟስ ማን ይባላል?
ተፈራ አሊጋዝ(ከጎንደር)
-ከኦርዮ ከነጠቃት ቤርሳቤህ ከምትባለው ሚስቱ ነው።
*አንዳንድ ሴቶች ቡና ያፈሉና አንድ ሁለት ሲኒ ከምድር ላይ ያፈሳሉ። ምን ማለታቸው ነው?
ታደለ ህሌቦ(ከመቂ)
-እንዲያው የሚሆን እየመሰላቸው የያዙት አጉል አምልኮ ነው። ምንም ጉዳይ የለውም። ይልቅስ ቡናቸውን ባያባክኑ ደኅና ነው።
*አበበና አልማዝ የአንድ እናት ልጆች ናቸው። አበበ ሚስት አግብቶ ለማን ወለደ። ለማ ደግሞ በለጠን ወለደ፡፤ አልማዝ ባል አግብታ ሽፈራውን፤ ሽፈራው ደግሞ አዲስን ወለደ፤ የበለጠና የአዲስ ዝምድና ምን ይባላል?
ግርማ ደምሴ
-ያንድ አያት ልጆች ይባላሉ።
(አዲስ ዘመን ህዳር 13 ቀን 1964ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 23 ቀን 2016 ዓ.ም