. 4 ነጥብ 25 ቢሊየን ብር ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ ታወቀ
. 84 ነጥብ 4 ሚሊየን ብር ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ ያለበት ገንዘብ ፈሰስ አለመደረጉ ተረጋገጠ
. 960 ነጥብ 8 ሺ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት
ተገኝቷል
አዲስ አበባ፡- በፌዴራል ዋና ኦዲተር የፌዴራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች የ2010 ዓ.ም የፋይናንስ ህጋዊነት ኦዲትና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ ላይ በተካሄደ ኦዲት በ129 መስሪያቤቶች እና በ10 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች 4 ቢሊየን 252 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በወቅቱ አለመወራረዱን ዋናው ኦዲተር ይፋ አድርጓል፡፡
የ2010 የመንግሥት መስሪያ ቤቶችና ድርጅቶች የኦዲት ሪፖርትን ዋና ኦዲተሩ ገመቹ ዱቢሶ ትናንት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ 176 መስሪያቤቶችን እና 46 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶችን ገቢና ወጪ አጠቃላይ ኦዲት የተደረገ ሲሆን፤ በ9 መስሪያ ቤቶች እና በ6 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ከመቼ ጀምሮ በተሰብሳቢነት እንደተመዘገቡ እንዲሁም ከማን እንደሚሰበሰቡ በቂ ማስረጃ ሊቀርብባቸው ያልቻሉ 1 ቢሊየን 298 ሚሊየን ብር ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የአገር መከላከያ ሚኒስቴር በ1 ቢሊየን 203 ሚሊየን፣ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በ33 ሚሊየን፣ የቀድሞ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን በ23 ሚሊየን ብር ዋነኞቹ ሲሆኑ፤ ዋና ኦዲተሩ ውዝፍ
ተሰብሳቢ ሂሳቦቹን ህግ በሚፈቅደው መሰረት ተከታትለው ገንዘቡን ከማን እንደሚሰበስቡ የማይታወቁት ደግሞ ተጣርተው ትክክለኛነታቸው በማስረጃ ተረጋግጠው እንዲወራረዱ ማሳሰቡን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡
በዋና ኦዲተሩ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ያልተጠቀሙበትን ገንዘብ ለገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ በተካሄደ ኦዲት ፈሰስ የማያደርጉ መኖራቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ባለበጀት መስሪያ ቤቶች ያልተጠቀሙበትን በባንክ የሚገኝ ገንዘብ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማዕከላዊ ግምጃ ቤት ፈሰስ ማድረግ የሚኖርባቸው ቢሆንም ፈሰስ የማያደርጉ መኖራቸው ታውቋል፡፡
ዋና ኦዲተሩ እንዳመለከቱት በተካሄደ ኦዲት ከቀድሞ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንና ከ4 ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ብር 84 ሚሊየን 426ሺ ፈሰስ አለመደረጉ ማወቅ ተችሏል፡፡ በመሆኑም ዋናው ኦዲተር ተቋማት እንዲጠቀሙበት በህግ ያልተፈቀደላቸውን ገቢ ሂሳብ ለሚመለከተው አካል ፈሰስ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
በተካሄደው የኦዲት ሥራ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ፣ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ በአጠቃላይ የ960 ነጥብ 8 ሺ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትም የተገኘ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኦዲተሩ፤ በሁለት የገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች የ102ሺ ብር የገንዘብ ጉድለት ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪ የተሟላ የወጪ ማስረጃ መኖሩን ለማረጋገጥ በተካሄደ ኦዲት በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ ነገር ግን የተሟላ ማስረጃ ያልተገኘለት አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ማስረጃ ሳይቀርብ በ63 መስሪያ ቤቶች በወጪ ተመዝግቦ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ገመቹ ገለፃ፤ ገቢ ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች በገቢ ግብር ፣ቀረጥና ታክስ እንዲሁም ገቢ መሰብሰብ በአዋጅ፣ በደንብ እና በመመሪያ የተፈቀደላቸው ተቋማት በተገቢው መልኩ የመንግስትን ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በቀድሞ ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን መስሪያ ቤት እና በሥሩ ባሉ 15 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ብር 302 ሚሊየን 835ሺ ብር ከ59 መስሪያቤቶች እና ከ2 ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤቶች ደግሞ 54 ሚሊየን 615ሺ በድምሩ 375ሚሊየን 450ሺ ብር አለመሰብሰቡ ተረጋግጧል፡፡
መሰብሰብ ሲገባው ያልተሰበሰበ የጉዳት ካሳ መኖሩንም ያመለከቱት ዋና ኦዲተሩ በ15 መስሪያ ቤቶች ከህንፃ ተቋራጮች እና ዕቃ አቅራቢዎች ጋር በገቡት ውል መሰረት አገልግሎቱን ባለማግኘታቸው ብር 53 ሚሊየን የጉዳት ካሳ ወይም ቅጣት መሰብሰብ ሲኖርባቸው ገንዘቡን አለማግኘታቸው ታውቋል፡፡ ከ3 መስሪያ ቤቶች 3 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር የጉዳት ካሳ መሰብሰብ ቢኖርባቸውም አለመሰብሰቡንም ነው የገለፁት፡፡
የጉዳት ካሳውን ካልሰበሰቡት ውስጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 19 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ፣ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ 12 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ፣ አሶሳ ዩኒቨርሲቲ 10 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ 6ነጥብ 4ሚሊየን ብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ በመሆኑም መስሪያ ቤቶቹ በመንግሥት መመሪያና በገቡት ውል መሰረት እስከአሁን ያልሰበሰቡትን የጉዳት ካሳና ሌሎች ገቢዎች እንዲሰበሰቡና ለወደፊቱም መመሪያው በሚጠይቀው መሰረት እንዲፈፅሙ ማሳሰባቸውን ዋና ኦዲተሩ ገልፀዋል፡፡
የዋና ኦዲተሩን ሪፖርት ያዳመጠው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም የኦዲት ግኝቱን ከማድመጥ ባሻገር የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ተቋማቱን ተጠያቂ አድርጎ ሥራውን መስራት እንዳለበት የጠቆሙ ሲሆን፤ በቀጣይ ሳምንት ጠቅላይ ዓቃቢ ህግ ተቋማቱን እንዲጠይቅ የሚያሳስብ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 23/2011
ምህረት ሞገስ