በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ ጥንታዊ ቤቶች እንዳይፈርሱና ለታሪክ እንዲቀመጡ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የከተማው ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ተናገሩ፡፡
ሀላፊው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት በከተማዋ በርካታ የመሰረተ ልማት ስራዎች በመሰራት ላይ ከመሆናቸው የተነሳ አሁን ላይ የተለያዩ ጥንታዊ ቤቶችን ማፍረስ እየተባባሰ እንዳለ ጠቁመው ቢሮው ይህንን ነገር ለማስቀረት በትኩረት እየሰራ ነው ፡፡
ብዙዎቹ በከተማዋ ያሉ ቅርሶቻችን በግለሰብ ፣በመንግስት ተቋማት ወይም በሀይማኖት ተቋመት እጅ ነው ያሉት፤ ይህ ደግሞ ግለሰቦችም ሲቸገሩ ይሸጧቸው ነበር፤ በጣም በርካታ ጥንታዊ ቤቶች በግለሰቦች ተሽጠው ሲፈርሱ ቆይተዋል፤ ይህ ደግሞ በጣም አሳዛኝ ተግባር ነው ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ይናገራሉ፡፡
አሁንም ባለማወቅ ሆነ ሆን ተብሎ በሚደረጉ ተግባራት ይህ ፈተና በከተማችን ውስጥ በስፋት ይስተዋላል ይህን ፈተና ቢሮው ቀድሞ በመከላከል በከተማዋ ከ400 በላይ ቅርሶችን መመዝገብ መቻሉን እና ቅርሶቹን በመጠበቅ ፣በመንከባከብና በማስተዋወቅ ላይ እንዳሉም ሀላፊው አስረድተዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ቢሮው ቅርሶች እንዳይፈርሱ ብዙ ጥበቃዎችን የሚያደርግ ሲሆን ግለሰቦች በእውቀት ማነስ ምክንያት የቅርስ ቤቶችን ለማፍረስ ሲከራከሩ እንደሚውሉ ተናግረው የፍትህ አካላት በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በየዕለቱ ፍርድ ቤት እንደሚውሉም አስታውቀዋል፡፡
እንደ ሀላፊው ገለፃ ቢሮው በሀገሪቱ ከተጀመረው ለውጥ ጋር በተያያዘ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው በዋናነትም ቅርሶችን መለየትና መጠበቅ እንዲሁም እነዚህን ቅርሶች ማስተዋወቅ ላይ በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ አንፃር ቢሮው በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ ነው ፡፡ለአብነትም በ 2019 ዓ.ም (Europian Council for Tourism and Culture) በተባለ ተቋም አዲስ አበባ የአለም የቱሪዝምና የባህል ከተማ ሆና እድትመረጥ አድርገናል፡፡ ይህ ደግሞ ከተማችን የቱሪስት መዳረሻ ከማድረግ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ሃለፊው ገልፅዋል፡፡
እንደ ሀላፊው ገለፃ ከተማችን አዲስ አበባ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አማካይነት ከዘጠኝ ቢሊዮን በላይ መንገደኞች ትራንዚት የሚያደርጉባት ከተማ ናት፤ ነገር ግን እነዚህ መንገደኞች ከተማችን ውስጥ ገብተው ለመመልከት ብዙ ጊዜ የሚስባቸው ነገር እንደሌለ ነው በጥናት የተረጋገጠው ስለዚህ በከተማችን ውስጥ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የሚሰሩ በርካታ የልማት ስራዎች እና ታላላቅ ፕሮጀክቶች በቢሮው ድጋፍም እየተሰሩ ሲሆን ፕሮጀክቶቹ ትልቅ የቱሪዝም ማስገኛ ናቸው፡፡
እነዚህ ፕሮጀክቶች በሚያልቁበት ወቅት ከተማችን በከፍተኛ ሁኔታ የቱሪስት መስዕብ ትሆናለች እንዲሁም በአየር መንገዳችን ትራንዚት የሚያደርጉ መንገደኞች ተዝናንተው የተለያዩ እቃዎችን ሸምተው መሄድ የሚያስችላቸውም ሁኔታን የሚያመቻችም ነው፡፡መስሪያ ቤቱም በዚህ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል የቅርስን ጠቀሜታ አውቆና ተረድቶ ልክ አሁን እንደሚያደርገው ለቅርሶች ጥብቅና በመቆም ለልጅ ልጆቻቸው መተላላፍ እንዲችል መስራትም ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በሀይማኖት ከበደ