ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ዛሬ ለተወካዮች ምክር ቤት የ2010 በጀት ዓመት የፌደራል መስሪያ ቤቶችን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የኢትጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት መጤ ዝርያዎች አከባቢን እንዳይበክሉ በህግ የተሰጠውን ሀላፊነት አልተወጣም።
የኢትጵያ ብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩት ከውጭ የሚገቡ መጤ ዝርያዎች አከባቢውን እንዳይበክሉ በህግ ሀላፊነት የተሰጠው ተቋም ቢሆንም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ጥናት እያደረጉበት ነው በሚል ግንዛቤ የተጣለበትን ሃላፊነት እየተወጣ አይደለም ብለዋል ዋና ኦዲተሩ፡
አረሙ በ2003 ዓ.ም በጣና ገባር በሆነው መገጭ ወንዝ ላይ በሶስት ሄክታር ላይ ይታይ እንደነበር ያነሱት ሃላፊው በወቅቱ መቆጣጠር ባለመቻሉ በ2004ዓ.ም አምስት ቀበሌዎች በማዳረስ አራት ሺህ ሄክታር ፣ በ2005 ዓ.ም ደግሞ 15 ቀበሌዎችን በማዳረስ 20 ሺህ ሄክታር ያዳረሰ ሲሆን በእነዚሁ ቀበሌዎች 50 ሺህ ሄክታር መድረሱን ዋና ኤዲተሩ አብራርተዋል፡፡
እንደ ዋና ኦዲተሩ ገለፃ አሁኑ ሰዓት በእንቦጭ አረም የተሸፈነው የውሃ አካሉ መጠን በፌድራል ደረጃ ጥናት ያልተከናወነ ቢሆንም ይህን መጥፎ አረም የመከላከል ስራ በአስቸኳይ ካልተከናወነ ታላቁን የህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎችም ሀይቆችና ወንዞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
የእንቦጭ አረም በጣና ሀይቅ፣ በአባ ሰሙኤል ግድብ ፣ በቆቃ ግድብ ፣ በዝዋይ ሀይቅ በአባያና ጫሞ ሀይቆች እንዲሁም በባሮ፣ በአዋሽና በአባይ ወንዞች ላይ ቢታይም የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን ለመንግስትና ለህብረተሰቡ አለማሳወቃቸው እንዳሳሰበው ዋና ኦዲተሩ በሪፖርታቸው አመላክተዋል፡፡
ዳግማዊት ግርማ