በግብርናና ተያያዥ ሙያዎች የተመረቁ ተማሪዎችን በመስኖ ልማት እንዲሰማሩ ለማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ 50 ሺህ ሄክታር መሬት በዘመናዊ መንገድ እንዲለማ እየተደረገ መሆኑን የውሃና መስኖና ኢነርጂ ልማት ሚኒስትሩ ገለጹ።
ሚኒስትሩ ዶከተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በአፋር ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰመራ ከተማ የተማሩ ወጣቶች የመስኖ ልማት ፕሮግራም ስልጠና የመክፈቻ ፕሮግራም እንደገለጹት ትግባራው በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የስራ አጥነት ለመቅረፍና ድህነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለዋል።
የተማሩ ወጣቶችን በማደራጀት መሬት፣ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ በማቅረብ የመስኖ ልማትን እንዲስፋፋ በማድረግ ግብርናውን ያዘምናል ብለዋል ሚኒስትሩ ። ትግበራው ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ያስቀራለ፣ የውጪ ምርቶችን በአይነትና በብዛት ለማሳደግ ያግዛል እንዲሁም በአገራችን እየተገነቡ ላሉ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማቅረብ እንደሚያግዝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
በአገር ውስጥ ሊለማ የሚችል 5 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት መኖሩን የጠቆሙት ሚኒስትሩ ከዚህ ውስጥ እስካሁን የለማው ከ20 በመቶ ያልዘለለ እንደሆነም ተናግረዋል። የሚሰለጥኑት ወጣቶች ትኩረት ሰጥተው በመስራት ይህንን ታሪክ መቀየር አለባቸው ብለዋል።
ትግበራውን ለማሳካት በተለያዩ ግድቦች ተይዞ የሚገኘውን ውሃ በመጠቀም በአቅራቢያ ለሚገኙ መሬቶች በማዳራስ፣ የከርሰ ምድር ውሃን በማልማት፣ ተፋሰሶችን ተከትሎ ባሉ መሬቶችን ወንዞችን በመጠለፍ ተጨማሪ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋትን ያካትታል ብለዋል።ለስራው ሰልጣኞች ትኩረት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
በትግበራው በተለያየ አየገሪቱ ክፍሎች 12 ፕሮጀክቶች መለየታቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ በአፋር ክልል የትንዳሆ የመስኖ ግድብ ስድስት ሺህ ሄክታር ይለማል ብለዋል። ለዚህም በክልሉ 300 ወጣቶች ተመልምለው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና መጀመራቸው ተገልጿል።
ከኦሮሚያ ክልል 863፣ ከሶማሌ ክልል 750፣ ከጋንቤላ ክልል 420 ወጣቶች ተመዝግበዋል ያሉት ሚኒስትሩ ለስልጠና ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል። በትግበራው በግብርናና ተመሳሳይ ዘርፎች የተማሩ ወጣቶች እንደሚሳተፉም ጠቁመዋል።
መንግስት ዘመናዊ እርሻ እንዲስፋፋ አስፈላጊውን ግብዓቶች ለማሟላት ፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል ያሉት ዶክተሩ ወጣቶችም ራሳቸውንና ማህበረሰባቸውን ጠቅመው በአገር በአገር ዕድገት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲያበረክቱ አደራ ብለዋል።
ዘላለም ግዛው ሰመራ