
በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያን ለማስጀመር አዋጅ ተዘጋጅቶ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባ ዓመት አልፎታል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የካፒታል ገበያ እንቅስቃሴን ለማስጀመር የፀደቀውን አዋጅ ወደ ተግባር የመቀየርና ባለሥልጣኑን የማደራጀት ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል። በአሁኑ ወቅትም የሕግ ማዕቀፍ እና መመሪያ ተዘጋጅቶ አስራ አምስት አሻሻጮች ፍቃድ የሚያገኙበት አሠራር ተዘርግቷል።
የካፒታል ገበያ ለልማት ያልዋሉ ገንዘቦችን በማሰባሰብ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና እንዲውሉ የማድረግ፤ ይህንንም ተከትሎ ዜጎችም በአቅማቸው በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ተሳታፊ በመሆን ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚያስችል መሆኑም ይነገራል። ለመሆኑ የስቶክ ማርኬት ወደትግበራ መግባት ለአጠቃላይ የሀገር ኢኮኖሚ እድገት ብሎም ለዜጎች ተጠቃሚነት የሚኖረው ፋይዳ ምንድን ነው?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ተኪኤ ዓለሙ(ዶ/ር) የስቶክ ማርኬት መቋቋም ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አለው ይላሉ። ባለሙያው እንደሚያብራሩት ስቶክ ማርኬት ማለት ተቋማዊ በሆነና በተደራጀ መንገድ የአንድ ድርጅት ድርሻ በአክስዮን ወይንም ቦንድ መልክ የያዙ የገንዘብ ሰነዶች ግብይት የሚፈጸምበት ቦታ ማለት ነው። ሰነዶቹን የሚያቀርበው ድርጅት መንግሥታዊ ወይንም የግለሰብ ሊሆን ይችላል። የሚሸጡት ሰነዶችም የተለያዩ ማለትም የአጭርና የረጅም ጊዜ፤ እንዲሁም በወለድና በብድር መልክ ለግብይት የሚቀርቡ ሊሆኑ ይችላሉ።
በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት የአክስዮን ግብይት ልምዱ ቢኖርም በአንድ ወገን ተመኑ ሻጮች ያወጡት ብቻ የሚተገበር ሲሆን በሌላ በኩል አንዳንድ ግዜ ገዥው በፈለገ ግዜ አትርፎ መሸጥ የማይችልባቸው አካሄዶችም ስለነበሩ ትክክለኛ የአክስዮን ገበያ ነበር ለማለት አይቻልም። በመሆኑም መንግሥት ሕጋዊ አደረጃጀት ያለው ተቋም መፍጠሩ ትክክለኛውን አክስዮን በትክክለኛው ዋጋ በተፈለገ ግዜ ለመግዛት፤ ለመሸጥ ብሎም ማስተላለፍ የሚያስችል ታማኝ ምሕዳር እንዲፈጠር ያደርጋል ብለዋል።
ይህም ሰዎች ትንሽም ቢሆን ያላቸውን ገንዘብ በመጠቀም አክስዮን ለመግዛት የሚያስችላቸው ሲሆን በተመሳሳይ መሸጥ በፈለጉም ግዜ ያለምንም ውጣ ውረድ የሚገባቸውን ዋጋ አግኝተው እንዲሸጡ የሚያስችላቸው ይሆናል። በዚህ ሂደትም የገንዘብ ዝውውር እንዲጨምር የሚያደርግ ሲሆን ይህም እንደ ሀገር ለኢኮኖሚ እድገት የራሱ አወንታዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ሲሉም አብራርተዋል።
ተኪኤ(ዶ/ር) ሂደቱን አስመልክተው እንዳብራሩትም በዓለም ያለው ተሞክሮ እንደሚያሳየው ስቶክ ማርኬት በግለሰቦችም በመንግሥትም የሚደራጅ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን ያለው በመንግሥት ስር የተቋቋመ ነው። ስቶክ ማርኬት ሲቋቋም ገዢውና ሻጩ በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ በተለይም የገዢው ደህንነት እንዲጠበቅ ያስፈልጋል። ለገበያ የሚቀርበው አክስዮንም የተረጋገጠ ታማኝ ከሆኑ ኩባንያዎች መሆን ይጠበቅበታል። በመሆኑም ይህንን ምሕዳር ለመፍጠር አሁን ባለው ሁኔታ ተገቢ የሆኑ ሕጎች የማውጣትና የመቆጣጠር ኃላፊነት መንግሥት መያዙ ተገቢ ነው ብለዋል።
በተመሳሳይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያና አማካሪ የሆኑት ሞላ ዓለማየሁ(ዶ/ር) በበኩላቸው በሚቀጥሉት ዓመታት የግሉ ዘርፍ በሀገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል።
በመንግሥት ወይንም በግለሰቦችና በጥቂቶች ጥምረት ብቻ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ተይዞ የትም ሊደርስ አይችልም ያሉት ሞላ(ዶ/ር)፤ የስቶክ ማርኬት መቋቋም ዜጎች ባላቸው አቅም ከኢኮኖሚው ተሳታፊም ተጠቃሚም እንዲሆኑ ያስችላል ይላሉ።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ ያደጉ፤ እያደጉ የመጡና ማደግ የሚፈልጉ በስቶክ ማርኬት ውስጥ ለመንቀሳቀስ አቅሙም አደረጃጀቱም ያላቸው በርካታ ኩባንያዎች አሉ። እነዚህ ኩባንያዎች ለማደግ ደግሞ ከፍተኛ ካፒታል ያስፈልጋቸዋል። በሀገሪቱ ያሉት እንደ ባንኮች ያሉና ሌሎች የፋይናንስ አበዳሪ ተቋማት ደግሞ ያላቸው ሀብት ውስን ነው። የስቶክ ማርኬት መፈጠር እነዚህ ተቋማት ከሕዝቡ በትንንሽ መጠን የሚሰበሰብ ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ይሆናል። እነዚህ ክፍተቶች በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ስቶክ ማርኬትን ለመተግበር የሚያስችል ምቹ የኢኮኖሚ ምሕዳር መኖሩንም የሚያመላክት ሁኔታ ነው ሲሉም አብራርተዋል።
ሞላ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን መቋቋሙም ለአክስዮን ገዢዎች ብዙ ጥቅም አለው። አንደኛው ሰዎች እነሱ ላሰቡት የንግድ እንቅስቃሴ የማይበቃ ገንዘብ ካላቸው የትም አልደርስም በሚል እንዳያባክኑት በር ይከፍታል። በተጨማሪ በአክስዮን ሽያጭ የሚገኝ ወለድ ከሌሎች ፋይናንስ ተቋማት የተሻለም ነው። ይህ በተዘዋዋሪ የኑሮ ውድነትንም የሚቀርፍ ብሎም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር የሚጠቅምና ዜጎች ከሀገር አድገት ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችልም ነው። ስቶክ ማርኬት ላይ የገባ ኩባንያ ፈቃድ ሲያገኝ ችግሮቹንና መልካም አጋጣሚዎችን በግልጽ ስለሚያሳይና ድርጅቶቹ ያሉበት አቋም ስለሚታወቅ ከመጭበርበር ይታደጋል።
ባጠቃላይም የስቶክ ማርኬት መተግበር የገበያ መስፋፋትን በመፍጠር የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ዘመናዊ የሆነና የተቀላጠፈ አሠራር እንዲፈጠር ይረዳል ያሉት ምሑራኑ፤ ይህም ሆኖ ከሕግ መውጣት ጀምሮ አተረገባበሩን፤ ወደሥራ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችንና የገበያ ሂደቱን በጠናከረ መንገድ መቆጣጠር እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2016 ዓ.ም