ከሥፍራው የደረስነው ረፋድ ላይ ነበር። ከበር ላይ እንግዶችን የሚቀበሉ የድርጅቱ ሠራተኞች ተቀበሉን። ወደ ውስጥ ዘለቅን። አንዳንዶች ስማቸው እየታየና በድርጅቱ የተሰጣቸውን መታወቂያ እያሳዩ ወደ አዳራሽ ውስጥ ገቡ። እነዚህ እንግዶች ሳይሆኑ የድርጅቱ ቋሚ ተጠቃሚ መሆናቸው በድርጅቱ ሠራተኞች እየተረጋገጠ ወደ ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ።
እኛ በድርጅቱ የሚሠሩ ሥራዎችን እንድንጎበኝ ተፈቅዶልን ጉብኝታችንን ከአዳራሽ ጀመርን። በአዳራሹ ውስጥ አረጋውያን፣ አቅመ ደካሞች፣ ህፃናት የያዙ እናቶች፣ ጎልማሶች፣ ወጣቶች ሁሉም አይነት የህብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ።
የሰዎቹ እዛ መኖር ምክንያቱን ላልተረዳ ሰው፤ ስብሰባ ተጠርተው ሊመስል ይችላል። የቆሸሸ ልብስ የለበሰ አለመኖሩም ችግረኞች ናቸው ብሎ ለማሰብ ያስቸግራል። በአንድ አዳራሽ ውስጥ የተሰባሰቡት ሰዎች ቆሽሾ መታየት የድህነት መገለጫ መሆን የለበትም የሚለውን የድርጅቱን መመሪያ አክብረው እንጂ፤ የተሰበሰቡት ድርጅቱ ቋጥሮ የሚሰጣቸውን የዕለት ጉርሳቸውን የሚጠባበቁ ሰዎች ነበሩ ።
በተለያየ ምክንያት ለችግር ተጋልጠው ሌማታቸው ባዶ ሆኖ እጃቸውን ቢዘረጉም ንጽህናቸውን ግን መጠበቅ እንዳለባቸው በማስገንዘብ ድርጅቱ ንጽህናቸውንም እንዲጠብቁ ሳሙና በመስጠት ያበረታታቸዋል። ልብስ ለሌላቸውም ከበጎ አድራጊዎች የተገኘ ልብስ እንደሚሰጣቸው በጉብኝታችን ወቅት ተነግሮናል።
የምግብ እደላ መርሃግብሩ ከስድስት ሰአት በኋላ ነበር። በአስጎብኝያችን እንደተነገረን እነርሱ ግን ከረፋድ ጀምሮ በአዳራሹ ተገናኝተው የግል ጨዋታቸውን እየተጫወቱ መጠበቅ ልማዳቸው አድርገውታል። እኛም ቀድመን ተገኝተን ስለነበር እውነታውን አረጋግጠናል። አንዳንዶቹ ቀድመው የሚገኙት መድኃኒት ለመውሰድ፣ ልብስ የቸገራቸው ድጋፍ ለመጠየቅ፣ ሌላም ጥያቄ ያላቸው ለድርጅቱ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ነው። ሠራተኞች በበኩላቸው በማስተናገድ ፋታ አልነበራቸውም።
በማብሰያ ቤት ክፍል ውስጥ የነበሩ ሴቶችም ምሣ ለማድረስ እየተረባረቡ ነበር። ወጥና እንጀራው ተዘጋጅቶ፤ ከማብሰያው ጎን ምግብ የሚታሰርበት ሳህን ተሠናድቶ ነበር። ሳህኖቹ ምግቡን የሚቀበሉ ሰዎች ቢሆንም፤ ምግብ የሚቋጠርላቸው የምሣ ዕቃው በድርጅቱ ሠራተኞች ተሰብስቦ እና ታጥቦ የሚቀርብ ነው።
የእንጀራ መጋገሪያ ክፍሉም በአንድ ጊዜ ብዙ እንጀራ ለመጋገር የሚያስችል ምጣድ የተዘጋጀበት ነው። ድርጅቱ የሚሠራውን ሥራ ለማየትም ሆነ ለመደገፍ ፍላጎት ያለው እንጀራ ይጋግራል። አንድ እንጀራ ጋግሮ 50 ብር ይለግሳል። ዓላማው ድጋፍ በመሆኑ ወንዶችም እንዲሳተፉ ይደረጋል። ሰዎች እንዲህ በቀላሉ ሠብዓዊ በጎ ተግባር በመፈጸም የዜግነት ግዴታቸውን ይወጣሉ። እኛም ተሳታፊ በመሆን ሌሎችን ተጋርተናል።
ድርጅቱ ዋና ዓላማና ግቡ የእለት ጉርስ ለሌላቸው ወገኖች ምሣና እራት በሳምንት አንድ ቀን ደግሞ ቁርስ በማብላት በጎ ተልእኮ መወጣት ቢሆንም፤ ጎን ለጎን በአልባሳት ስፌት፣ በጫማ ሥራ፣ በዳቦና እና በዳቦ ቆሎ የአጫጭር ጊዜ ሥልጠና በመስጠት የሙያ ክህሎት ይሰጣል። ይህን ዕድል እንዲያገኙ እያደረገ ያለውም በተለያየ ምክንያት ችግር ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ነው። በድርጅቱ ውስጥ በተለያየ የሥራ ዘርፍ ተቀጥረው የሚሠሩትም አብዛኞቹ እንዲሁ ሥራ ያልነበራቸው በችግር ውስጥ የነበሩ ናቸው።
ድርጅቱ እንዲህ ያሉ ዜጎችን እየረዳ ያለው ከአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጋር በመተባበር ነው። መረዳት ያለባቸው ሰዎች ሳይረዱ እንዳይቀሩ ከሚኖሩበት ቀበሌ ማረጋገጫ መያዝ ይኖርባቸዋል። እኛ በአካል ተገኝተን ያየናቸውን እንጂ በጤና እና በእድሜ ምክንያት ቤት ውስጥ ውለው አስታዋሽ የሌላቸውንም ድርጅቱ ቤት ለቤት እየረዳቸው እንደሆነም ከድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ከሠራተኞችም ሰምተናል። እጅግ አቅም ላጡ ጥቂት ሰዎችም ቤት ተከራይቶላቸዋል። በጦርነት ምክንያት ተሰደው ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ ሶሪያውያንም ወርሃዊ ቀለብ ይሰጣቸዋል።
እንዲህ ኃይማኖት እና ዘር ሳይለይ ለበጎ ተግባር የቆመና የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን በመደገፍ ላይ የሚገኘው ድርጅት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዶ/ር፤ በአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሳይቀር ሥራው መታየቱን በፎቶ በማዕከሉ ውስጥ ይገኛል። በተለያየ ጊዜ ለማዕከሉ የተበረከተ የምስክር ወረቀትና ሽልማትም እንዲሁ አይተናል። ይህ ማዕከል በቡልኸይር የበጎ አድራጎት የምገባ ማዕከል ነው። በቡልኸይር የበጎ ሥራ በር ማለት ነው። ይህን ማዕከል አቋቁመው የበጎ ሥራ እየሠሩ ያሉት ወይዘሮ ሐናን መሐመድ ናቸው።
ወይዘሮ ሐናን አንቱታን የሚያሰጣቸው በጎ ሥራ እየሠሩ በመሆናቸው እንጂ በእድሜ ለአንቱታ አልበቁም። እኛም ሥራቸውን አክበረን አንቱ በማለት ስለበጎ ተግባራቸው፣ ስለራሳቸውም እንዲያጫውቱን ቆይታ አድርገናል። ወይዘሮ ሐናን ለበጎ ተግባር የተነሳሱበትን አጋጣሚ እንዲህ ያስታውሳሉ፤ በአንድ አጋጣሚ ፤ የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ የለበሱ ሁለት ሴት ታዳጊዎች መገኘት ከሌለባቸው አካባቢ ሲወጡ በድንገት ይመለከቷቸዋል። አንዷ ፀጉሯን የተሸፋፈነች ሙስሊም ስትሆን፣ ሌላኛዋ ደግሞ በአንገቷ መስቀል ያደረገች ክር ያሰረች ክርስቲያን ናት። ልጆቹ የነበሩት ጎረምሶች በበዙበት ሥፍራ ነበር።
እርሳቸውም እናት ናቸውና ታዳጊዎቹ ለጥቃት በሚጋለጡበት ቦታ መገኘታቸው በጣም አሳስቧቸው ነበር። ተናደውባቸዋልም። የነበሩበት ቤት ምግብ ቤት ቢሆንም በእነርሱ እድሜ የሚገኙበት ስፍራ ባለመሆኑ ማለፍ አልፈለጉም። ሲወጡ ጠብቀው ለምን እዛ ቦታ እንደተገኙ ጠየቋቸው። ታዳጊዎቹም እውነታውን ሊነግሯቸው አልፈለጉም ነበር። እርሳቸው ግን እውነቱን ካልነገሯቸው ተከትለዋቸው ቤተሰባቸው ጋር እንደሚሄዱና ያዩትንም እንደሚነግሯቸው ጠንከር ብለው ጠየቋቸው።
ከታዳጊዎቹ ያገኙት እውነታ ግን እርሳቸው እንዳሰቡት አልነበረም። ከቤታቸው ሲወጡ ውሃ ብቻ ጠጥተው እንደወጡ ምንም እንዳልቀመሱ ነገሯቸው። ምግብ ቤት የገቡት የሚበላ ፈልገው እንደሆነ ሲነግሯቸው ወይዘሮ ሐናን እንባቸውን ሊቆጣጠሩ አልቻሉም። ስሜታቸው ተነካ። ‹‹አላህ እድሜ ከሰጠኸኝ ሰዎች በእኩልነት በፍትህ ያለምንም ጫና የሚመገቡበት ማዕከል እከፍታለሁ። ›› ብዬ ለራሴ ቃል ገባሁ ይላሉ። ይህ ታሪክ የዛሬ አስር አመት ቢሆንም ለእኛም ታሪኩን ሲያጫውቱን ስሜቱ አሁን ላይም እንዳለቀቃቸው እያስታወሱ ሲያለቅሱ ነበር።
‹‹ሰዎችን የምንረዳቸው በተሳሳተ መንገድ ነው ። ሁሌም ፈራጆች ነን። እነዛን ልጆች ባልጠይቃቸው ኖሮ ችግራቸውን አልረዳም ነበር›› የሚሉት ወይዘሮ ሐናን፤ የታዳጊዎቹን የቤተሰብ ሁኔታ ባዩ ጊዜ ልባቸው በጣም እንደተነካ ነበር የገለጹልን። ‹‹እኛ ስለምንለብሰው ልብስና ስለምንይዘው ቦርሳ ስንጨነቅ፤ እነርሱ ለቀን ጉርስ ይጨነቃሉ። እኩል ፍጥረት፣ የአንድ ሀገር ዜጎች ሆነን አንዱ የሚርበው፣ ሌላው በተሻለ ሁኔታ የሚኖር መሆኑ እጅግ ያሳዝናል›› አሉ። ያሉባቸውን ችግሮች ከተገነዘቡ በኋላ ወይዘሮ ሐናን ወዳጆቻቸውን በማስተባበር ታዳጊዎቹ ለትምህርት ቤት የሚያስፈልጓቸውን ወጪ በማሟላት፣ ቤተሰቡም የእለት ጉርስ የሚያገኝበትን ምቹ ሁኔታ ፈጠሩላቸው።
የተለያየ ዝግጅት እያዘጋጁ ከጓደኛና ቤተሰብ ጋር በደስታ ማሳለፍ የተለመደ ነው። እርሳቸው ግን እንዲህ ያለው መሰባሰብ በበጎ ተግባር ላይም ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል የሚል እምነት ነበራቸው። ታዳጊዎቹን መነሻ አድርገው ጓደኞቻቸውን፣ ወዳጆቻቸውንና ቤተሰባቸውን በማስተባበር 70 ተማሪዎች እንዲታገዙ አድርገዋል። ወይዘሮ ሐናን በተለይም የተጎዱ ሴቶችን ማለፍ አይሆንላቸውም። ስለተጎዱ ሴቶች ሲያነሱም እምባ ይቀድማቸዋል። ይህ በጎ ሥራቸው እየሰፋ የምገባ ማዕከል እስከማቋቋም ደረጃ ደረሰ።
ወይዘሮ ሐናን አቅማቸው በቻለው ሰብዓዊ ተግባር ለመፈጸምና የዜግነታቸውን ድርሻ ለመወጣት እንጂ፤ ሕጋዊ የሆነ ተቋም አቋቁመው ለመንቀሳቀስ ሃሳቡ አልነበራቸውም። የሚረዷቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ፤ አንዳንድ ሰዎችም ማዕከል እንዲያቋቁሙ ምክር ሲሰጧቸው፣ ሕጋዊ ማድረጉን መረጡ። ከጓደኞቻቸውና ወዳጆቻቸው ጋር በየወሩ ተገናኝተው የሚያሳልፉት ጊዜም ይህን ያህል ቁምነገር ያለው ሆኖ አልታያቸውም። ቁምነገር ላይ የሚውል ሥራ መሥራት እንደሚፈልጉ ነገሯቸው።
እነርሱም በሃሳባቸው ተስማምተው የድጋፍ ሥራውን በጋራ አጠናከሩት። በሂደትም ባቡልኸይር የበጎ አድራጎት ድርጅት የምገባ ማዕከል ሕጋዊ ሆኖ መሥመር የያዘው። ከተመሠረተም አምስተኛ ዓመቱን ይዟል። አሠራሩም ሕጋዊ እንዲሆን ማዕከሉ ከሚገኝበት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጋር እየተናበቡ መሥራት ጀመሩ። ከወረዳ ከሚመጣላቸው መረጃ በተጨማሪ ድርጅቱም የራሱን የማጣራት ሥራ ይሠራል። በዚህ መሠረት መረዳት ያለባቸው ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
ማዕከሉ አገልግሎቱን መስጠት የጀመረው በኪራይ ቤት ውስጥ ሆኖ ነው። በወቅቱም ይረዳቸው የነበሩ ሰዎች 126 ብቻ ነበሩ። የበጎ ሥራቸውን የተገነዘበው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሥሪያ ቦታ ፈቅዶላቸው በቦታው ላይ ግንባታ አከናውነው አሁን ላይ በተሻለ ሁኔታ አገልግሎቱን እየሰጡ እንደሆነ ነው ወይዘሮ ሐናን የነገሩን።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉሙሩክ ባለሥልጣን ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የአልባሳት እገዛ አድርገውላቸው እንደነበርና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የማዕከሉን ሥራ እንደሚያውቁ አጫወቱን። በአሁኑ ጊዜ በማዕከሉ የሚጠቀመው 3 ሺህ 880 አባወራ ነው። ምግቡ የሚቋጠርላቸው እንደቤተሰባቸው ብዛት ነው። አገልግሎቱን እየሰጡ የሚገኙት በቤተሰብ ደረጃ እስከ 15 ሰው በመታደግ ነው። በምገባ ማዕከሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አርቲስቶችን ጨምሮ ከሀገር መሪዎች ጋር ሳይቀር ትልቅ ሥራ የሰሩ የሀገር ባለውለታዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች ተሳቅቀው ችግራቸውን ደብቀው የቆዩ ናቸው። መታየትም አይፈልጉም።
የበጎ ሥራውን ለማየት የሚፈልግ ወይም ‹‹ልዘይራችሁ›› የሚል ካለ፤ ምን ይዘህ የሚል ጥያቄ ይቀርብለታል። ተረጂዎቹ የምግብ ብቻ ሳይሆን፤ የህክምናና ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎችን የሚፈልጉ በመሆናቸው የሌሎች ድጋፍ ወሳኝ ነው። በጤና አገልግሎት የጤና መድህን ተገዝቶላቸው የሚጠቀሙ አሉ።
የኑሮ ውድነቱ ከሚሠሩት በጎ ሥራ ጋር እንዴት እየተወጡት እንደሆነም ወይዘሮ ሐናንን ጠይቀናቸው፤ ‹‹እኔ አንድ ደካማ ሰው ነኝ። ግን አላህ እየረዳኝ ነው።›› በማለት በአጭሩ መለሱልኝ። በየእለቱ ምግብ የሚቋጠርላቸው ብቻ ሳይሆኑ፤ 150 የሚሆኑት ቋሚ ሠራተኞቻቸው ሁኔታም ያሳስባቸዋል። እጅ ቢያጥራቸው እርሳቸውን ተስፋ አድርገው ጠዋት ለሥራ ወደ ማዕከሉ የሚመጡና የዕለት ምግባቸውን የሚቀበሉ ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲያስቡ ይጨነቃሉ።
ለሠራተኞች ደመወዝ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ያወጣሉ። ይህ ሁሉ የበጎ ሥራ በቋሚ በጀት ሳይሆን፤ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ለጋሾች እየታገዙ ነው። ለጋሾች በአይነትም በገንዘብ እንደአቅማቸውና እንደፍላጎታቸው እገዛ ያደርጋሉ። ከውጭ በአሜሪካን ሀገር ውስጥ የሚያስተባብሩ ለጋሾችን ማግኘት ችለዋል።
ሰዎች የሚያስተባብራቸው ካገኙ ለበጎ ፈቃድ ልባቸው ክፍት እንደሆነ በሥራቸው አጋጣሚ ትምህርትም እንዳገኙበት ነግረውናል። እርሳቸውም ሳይታክቱ የማስተባበሩን ሥራ ይሠራሉ። በማህበር የተደራጁ የእስልምናና የክርስትና እምነት ተከታይ የሆኑ ወጣቶች፣ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከጎናቸው እንደሆኑም ገልጸውልናል።
በማዕከሉ ድጋፍ እየተደረገላቸው ያሉትም ሆኑ ተቀጥረው የሚሠሩት እንዲሁም በተለያየ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉትና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡት ኢትዮጵያውያን ናቸው። ወይዘሮ ሐናን፤ ‹‹ለእኔ አንድ ኢትዮጵያዊም ሆነ ኬንያዊ ወይንም የሌላ ዜጋ አንድ ነው። በዘር፣ በኃይማኖት ልዩነት መፍጠር በፈጣሪም የማይደገፍ ከሰውም የሚጠበቅ አይደለም። በማዕከሉ ማን ቸገረው እንጂ ሃይማኖቱ እና ብሔሩ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ አይነሳም።›› ይላሉ። ማዕከሉ በተወሰነ ሰው ኃላፊነት ብቻ የሚከናወን እንዳልሆነ ለሀገር የተከፈተ መሆኑም ግንዛቤ እንዲያዝ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተካተቱበት አባላት ያለው ኮሚቴ ተዋቅሮ ሥራው እንደሚሠራ የነገሩን ወይዘሮ ሐናን፤ ፍትሐዊነት እንዲኖርና እርሳቸውም ችግር ቢያጋጥማቸው ሥራው ቀጣይ እንዲሆን ከማሰብ እንደሆነም ገልጸውልናል።
ወይዘሮ ሐናን ሰዎችን ያለልዩነት በሠብዓዊነት መርዳት፣ማገዝ ከቤተሰብም የወረሱት ሳይሆን አይቀርም። ስለቤተሰባቸው እንዳጫወቱን በመስጠት መልካምነትን የሚሠራ ቤተሰብ ነው ያላቸው። የእርሳቸውም መልካምነት ከቤተሰብ የመጣ ይሆን ብለን ጠይቀናቸው ‹‹ወላሂ እኔ አላውቅም›› በማለት የተጎዳን ማገዝ መርዳት የመንፈስ እርካታ እንደሚሰጣቸው ነው የገለጹልን።
ለጋስ በመሆን እናታቻውን ፣ ሴትና ወንድ አያታቸውን ያነሳሉ። ሠብዓዊነት ምን ማለት እንደሆነ ሳይገባቸው እናታቸው ወይዘሮ አበራሽ ዓሊ የበዛ ደግነት ሲያደርጉ እንደአባካኝ ያይዋቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። የሴት አያታቸው ደግነት ደግሞ ይገርማቸዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ከውጭም ከሀገር ውስጥም በተለያየ መንገድ ስጦታ ስለሚበረከትላቸው በቤተሰቡ እድለኛ ተድርገው ይታያሉ። የተሰጣቸውን ስጦታ ግን እርሳቸው ሳይጠቀሙበት የሚሰጡት ለሌሎች ነበር። ይህን ያየው ቤተሰብ ግን በመቆጨት እራሳቸው እንዲጠቀሙበት ይደብቅባቸዋል።
አያታቸው ግን የለበሱትን ልብስ አውልቀው ከመለገስ ወደ ኋላ አላሉም። አንድ ቀን አንዲት ወደቤታቸው የመጣች ሴት ልብሷ ተቀዳዶ በማየታቸው የለበሱትን አውልቀው አለበሷት። መስጠት የለመደ እጅን መከልከል ወይም የመስጠት ሱስን ማስጣል እንደማይቻል አያታቸውን በምሳሌ ያነሳሉ።
ወንድ አያታቸውም በአካባቢያቸው ለመቃብርና ለተለያየ አገልግሎት የሚውል የግል መሬታቸውን በመስጠት ይታወቃሉ። በታሪክም ይታወሳሉ። ከአዲስ አበባ ከተማ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሸኖ የሚኖሩት አያታቸው በአካባቢው የእህል ወፍጮ፣ ወፍጮቤት ውስጥ ለእህል ማበጠሪያ የሚውል ዘመናዊ ማበጠሪያ እንዲሁም ሬዲዮ፣ መኪና ያስገቡ፣ ፎቅቤት የሰሩ፣ የመጀመሪያው ሰው ናቸው። በወቅቱም የአካባቢው ማህበረሰብ በአድናቆት ያያቸው እንደነበርና በተለይም ሬዲዮን በሰሙ ጊዜ ‹‹ሐጂ ዓሊ ብሎ ሼጣን አመጣ›› ብሏቸውም ነበር። መኪናውንም ወደ አካባቢው ይዘው በገቡ ጊዜ የአካባቢው ነዋሪ በፈረስ ሆኖ በዘፈን አጅቧቸዋል።
አያታቸው ሀጂ አሊ ግብይት በደረሰኝ እንዲፈጸም በማድረግ፣ የሸኖ ቅቤንም ለውጭ ገበያ በማቅረብ በተለይም የተነጠረ ቅቤ የመን ለገበያ የላኩና የአረቡ ማህበረሰብ የሸኖን ቅቤ እንዲያውቅ በማድረግ ረገድ ከአካባቢው ቀዳሚ ሰው ናቸው። እነዚህ ሁሉ በአካባቢው ላይ እውቅናን አትርፎላቸዋል።
ከዚህ ቤተሰብ የተገኙት ወይዘሮ ሐናን የተወለዱት ሸኖ ነው። ያደጉት ግን አዲስ አበባ ከተማ መሳለሚያ አካባቢ ከሚኖሩ ሴት አያታቸው ጋር ነው። አብረዋቸው እንዲሆኑ የተደረገው አያታቸው ጋር ሴት ልጅ ባለመኖሩ ምክንያት ነበር። ግን ሸኖ ወላጆቻቸው ጋርም ይመላለሱ ስለነበር በማሳደግ በኩል የወላጆቻቸውም ድርሻ እንዳለበት ይናገራሉ።
ወይዘሮ ሐናንን ስለትምህርታቸውም ጠይቀናቸው። 12ኛ ክፍል እንዳጠናቀቁ በግላቸው ባህሬን ሀገር ሄደው ‹‹እስላሚክ ፍትህ›› ተምረው ከባህሬን ዲስከቨሪ እስላም ፍትህ በዲፕሎማ ተመርቀዋል። አንድ ሰው ፍታዊ ሊሆን የሚያስችለውን ትምህርት ተከታትለዋል።
በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኝ እናት ሜዲካል ኮሌጅ ‹‹ቻይልድ ሳይኮሎጂ›› የሚባለውን የትምህርት አይነት ተምረዋል። በውጭም በሀገር ውስጥም የተማሯቸውን የትምህርት አይነቶች በጥሩ ውጤት ማጠናቀቃቸውንና ተሸላሚ እንደነበሩም አጫውተውናል። ወይዘሮ ሐናን ቻይልድ ሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ የመረጡበት ምክንያት ነበራቸው፤ ለሥራ አጋጣሚ ዱባይ ከተማ በነበሩበት ወቅት በከተማዋ ከተለያየ ዓለም የመጡ የሚማሩበት ትልቅ ትምህርት ቤት ነበር።
በዚህ ትምህርት ቤት ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊት ልጇን ታስተምራለች። ተማሪዎችን ከበር ላይ የሚቀበሉ የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች የሌላ ሀገር ዜጎችን አቅፈው ሲቀበሏቸው፤ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎቹን ግን በእጃቸው ብቻ ይጨብጧቸው ነበር። ልዩነት መፍጠራቸው ለወይዘሮ ሐናን ጥሩ ስሜት አልሰጣቸውም። ቁጭትም ፈጥሮባቸዋል። ቁጭቱ የተፈጠረው ኢትዮጵያዊቷ እዛ ትምህርት ቤት ውስጥ ልጆችዋን ማስተማር የቻለችው አቅሟ ቢፈቅድ ነው እና ክብሩም እኩል መሆን አለበት ከሚል ነበር።
ከተጎዱ ሰዎች ጎን መቆም ባህሪያቸው እንደሆነ የሚናገሩት ወይዘሮ ሐናን፤ በዛ ሀገር ያዩትን ልዩነት ለማስቀረት፣ በሌላ በኩልም ዱባይ ከተማ ውስጥ ትምህርት ቤት ከፍተው ኢትዮጵያውያንም መሥራት እንደሚችሉ በማሳየት ቁጭታቸውን ለመወጣት አቅደው ቻይልድ ሳይኮሎጂ ተማሩ።
ወይዘሮ ሐናን በዱባይ ከተማ አሜሪካኖች፣ እንግሊዞች፣ ህንዶች የተለያዩ ዜጎች ትምህርት ቤት ከፍተው ስለሚያስተምሩ እርሳቸውም አንዷ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የነበራቸውን እቅድ አላሳኩም። አንዱ ምክንያት ትዳር መመሰረታቸው ነው። አምስት ልጆች በተከታታይ ወለዱ። ሌሎችም ምክንያቶች ተደማምረው አልተሳካላቸውም።
ያደኩት በሥራ ነው የሚሉት ወይዘሮ ሐናን፤ ከቤተሰብ ጋር በንግድ ሥራ ውስጥ በመቆየታቸው አሁንም በንግድ ሥራ ላይ ይገኛሉ። ወይዘሮ ሐናን የግል ኑሮአቸውንም አሁን የሚገኙበትን የበጎ አድራጎት ሥራ ጎን ለጎን በማስኬድ ደፋ ቀና እያሉ ነው። የበጎ አድራጎቱ ሥራ ዘለቄታ እንዲኖረው ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤተል በሚባለው አካባቢ አምስት ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለግንባታ ፈቅዶላቸዋል። ወይዘሮ ሐናን በዚህ ቦታ ላይ ስለሚገነባው ህንጻ እንደነገሩን፤ የሚገነባው ህንፃ በማዕከሉ የሚሠጠው አገልግሎት ቋሚ ገቢ እንዲኖረው ለንግድና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች እንዲኖረው ይደረጋል። በጎ ፈቃደኞችና ለጋሾች ከሚያደርጉት እገዛ በተጨማሪ ገቢ ሲኖረው አሁን ላይ የደጋፊዎች እጅ ሲያጥር የሚኖረውን ጫና ይቀንሳል። በመጨረሻም ወይዘሮ ሐናን ለህንጻው ግንባታም የበጎ ፈቃደኞችን እገዛ እንደሚጠብቁ እንዲሁም ሁሉም ሰው ለወገኑ በበጎ እንዲቆም ጠይቀዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 21 ቀን 2016 ዓ.ም