• 494 ኤጀንሲዎች ህጋዊ ፍቃድ ወስደዋል
አዲስአበባ፡– 494 ኤጀንሲዎች ህጋዊ ፍቃድ ወስደው ለቤት ሰራተኝነት ወደ ተለያዩ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በቅርቡ መላክ እንደሚጀመር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የኤጀንሲ ፈቃድ መስጫ ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እሸቱ ይጥና ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ኤጀንሲዎቹ የመንግሥት ለመንግሥት ስምምነት በተደረገባቸው ሳውዲ፣ ኳታር እና ጆርዳን ሀገሮች ለመላክ ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ሲሆኑ፣ፈቃድ ከተሰጣቸው መካከልም ወደ 100 የሚሆኑት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውል የማስፈጸም ሂደት ላይ ይገኛሉ፤ በቅርብ ጊዜም መላክ እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
አቶ እሸቱ እንዳብራሩት ኤጀንሲዎቹ በተለያየ መንገድ በማስታወቂያ ጥሪ በማድረግ መስፈርቱንቨ
ያሟሉትን ይመዘግባሉ።ለጉዞ የሚያስፈልጉ አሻራ፣የጤና ምርመራ እና ሌሎችንም ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት ለሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በማስፀደቅ ለጉዞ ያዘጋጃሉ፤ ሚኒስቴር መስሪያቤቱም ኤጀንሲዎቹ አሟልተው ያቀረቡለትን ለማረጋገጥ ጊዜ አይወስድበትም ባለው ዋናው ተግባር የኤጀንሲዎች መሆኑን አስታውቀዋል።
እስካሁን ሠራተኞችን የመላኩ ሥራ ያልተጀመረበትንም አቶ እሸቱ እንደገለጹት ምክንያቶቹ የተለያዩ ቢሆኑም ወደ እንቅስቃሴ ከተገባም በኋላ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅታዊ ሥራ አለመኖርና አለመናበብ ከምክንያቶቹ መካከል ይጠቀሳል።ሁሉም በእኩል የተቀላጠፈ አገልግሎት ካልሰጡ አንዱ በማጓተቱ ብቻ ሊዘገይ ይችላል ብለዋል።
መዘግየቱ ለህገወጥ የሰዎች ዝውውር መንገድ እየከፈተ ስለመሆኑ አቶ እሸቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ መንስኤ ሊሆን ቢችልም
ግን በህገወጥ መጓዝ ከሚያስከትለው ጉዳት አንጻር መታገስ ያስፈልጋል ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ህገወጥነትን ለመከላከል ከዘጠኝ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንና በዳይሬክቶሬቱ ሥር ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን የሚከላከል ቡድን መኖሩን አመልክተዋል። ቡድኑም ህገወጥ ዝውውር በስፋት ባለባቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች እንደ እድር ባሉ የማህበረሰብ አገልግሎቶችና በትምህርት ቤቶች ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እንዲሰጥ በማድረግ እንዲሁም በሽልማትና በተለያዩ ማበረታቻዎች ህገወጥነትን ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ እሸቱ ገለጻ በሚኒስቴሩ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በእንቅስቃሴ ላይ የሚገኙት ኤጀንሲዎች 14 ያህል መስፈርቶችን አሟልተው ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን፣ ከመስፈርቶቹ መካከልም የተቋም አደረጃጀታቸው በሰው ኃይል የተሟላና ለተገልጋዮች ምቹ መሆኑ፣ ሰራተኛ በሚልኩባቸው ሀገሮች ወኪል ስለመሰየማቸው፣ በተቀባይ ሀገር ያለው ወኪል የሥነምግባር ሁኔታ፣ሰራተኛ በሚልኩባቸው ሀገሮች በነጻነት መግባትና መውጣት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ያቀረቡ፣ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያላቸው መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የሥራ ሥምሪቶችን በተመለከተም ከሶስቱ ሀገራት በተጨማሪ ከተባበሩት አረብ ኤምሬት ጋር የመንግሥት ለመንግሥት የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈረሙ ኤጀንሲዎች ወደዚህ ሀገር ለመላክ እንዲችሉም ሚኒስቴሩ ማስታወቂያ አውጥቷል። ከባህሬን፣ከኦማን፣ከኩዌት ሀገራት ጋርም የስምምነት ሰነድ ተልኮ መልስ እየተጠበቀ ነው። በሂደት እንደ እንግሊዝ፣ አሜሪካና በሌሎችም ከፍተኛ ባለሙያ የሚፈልጉ ሀገሮች ጋር ስምምነት በመፈጸም የሰለጠነ የሰው ኃይል የሥራ ስምሪት ለማመቻቸት እቅድ መኖሩን ከዳይሬክተሩ ማብራሪያ መረዳት ተችሏል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
ለምለም መንግሥቱ