ሀዋሳ፡– በሲዳማ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ለሁለት ሳምንታት የሚከበረው የፍቼ ጫምበላላ በዓል ያለእንከን በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አስታወቁ፡፡
የሲዳማ ዞን ባህል ቱሪዝምና የስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ ትናንት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዛሬና ነገ በሀዋሳ ከተማ፣ ለቀጣይ ሁለት ሳምንታት ደግሞ በዞኑ ውስጥ በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች የሚከበረው የፍቼ ጫምበላላ በዓል በሰላም ያለእንከን እንዲጠናቀቅ እስከታች ባለው መዋቅር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ በዓሉ መላ ኢትዮጵያውያንን ባሳተፈና በሚወክል መልኩ የሚከበር ሲሆን፣ የተለያዩ የውጭ ሀገር አምባሳደሮችም ይሳተፋሉ፡፡
ለበዓሉ ስኬታማነት ሁሉም የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ከህብረተሰቡ ጋር ምክክር መደረጉን፣ ግንዛቤ የመፍጠርና የተግባቦት ስራዎች መከናወናቸውን የጠቆሙት አቶ ጃጎ ባለፉት ጊዜያት በሀዋሳ ከተማ የተደረጉ ትዕይንተ ህዝቦች ላይ የከተማዋና የዞኑ ወጣቶች ያበረከቱትን በጎ ተሞክሮዎችን በመቀመር አሁን በሚከበረው የፍቼ ጫምበለላ በዓል ላይ በተመሳሳይ አስተፅኦ ለማበርከት በተለይም ወጣቶች ቃል መግባታቸውን አመልክተዋል፡፡
የፍቼ ጫምበላላ በዓል ቄጤላ የተባለውና ልጃገረዶች የሚጫወቱት ሆሬ ብቻ ሳይሆን በርካታ እሴቶች እንዳሉት አቶ ጃጎ ጠቅሰው፣ ከእሴቶቹ መካከልም እርቅ፣ ሰላምና የአካባቢ ጥበቃ ዋነኞቹ እንደሆኑና እነዚህ እሴቶችም ጎልተው እንዲታዩ ይሰራል ብለዋል፡ ፡ ከእሴቶቹ መካከል ቄጤላ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም(ዩኔስኮ) ከተመዘገበ ወዲህ በዓሉ ትኩረት ማግኘቱን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
መላኩ ኤሮሴ