የዛሬው የዘመን እንግዳችን ፕሮፌሰር አደም ከማል ናቸው:: የኢትዮ ዓረብ ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ እና ጸሐፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አደም፤ ከ27 ዓመታት በላይ በውጪ አገር ኖረዋል:: በእነዚህ ዓመታት ከኖሩባቸው ሀገራት መካከል አንደኛዋ ግብፅ ናት:: ረዳት ፕሮፌሰር አደም፣ ግብፅ እና ሌሎችም አገራት ኢትዮጵያን የሚያዩበት ሁኔታ እጅግ ያስከፋቸው ስለነበር፤ የተንሸዋረረ እይታቸውን ለመቀየር ዋነኛ አማራጭ ነው ብለው ባመኑበት በዓባይ ወንዝ ዙሪያ ብዙ ምርምር አካሂደዋል::
ስለዓባይ ብዙ ጥናቶችን ከማካሔድ ባሻገር በዓረብኛ ቋንቋ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለኢትዮጵያ እና ስለዓባይ የሚዘግቡትን ተከታትለው ምላሽ በመስጠት የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል:: ዓባይ ኢትዮጵያን የማሳደጊያ ትልቅ መንገድ ነው ብለው እንደሚያምኑ ደጋግመው የሚገልፁት ፕሮፌሰር አደም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ዓባይን እንዳትጠቀም፤ ሀገራችን ከድህነት ወጥታ ጠንካራ እንዳትሆን በብዙ መልኩ በስተጀርባ በርካታ ተንኮል እየተሠራባት ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ::›› ይላሉ:: ከእኚሁ የኢትዮ ዓረብ ከፍተኛ የታሪክ ተመራማሪ እና ጸሐፊ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ከማል ጋር የሰሞኑን የግብፅን ሁኔታ በተመለከተ እና ከግድቡ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል:: መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- በህዳሴ ግድብ ድርድር ወቅት በግብፆች በተደጋጋሚ ከሚነሱ የመከራከሪያ ጥያቄዎች ውስጥ ታሪካዊ የውሃ መብት የሚለው ነው:: ለመሆኑ ግብፆች ታሪካዊ መብት የሚሉት ምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- እነርሱ ታሪካዊ መብት እና ስምምነት አለን የሚሉት ከቅኝ ገዢዎቻቸው ጋር በመሆን ሱዳን የተወሰነ ኮታ ቀሪውን ደግሞ ግብፅ እንድትጠቀምበት እ.አ.አ በ1929 እና በ1959 ዓ.ም የተፈራረሙትን ነው:: ያ መነሻ በምንም መልኩ ከኢትዮጵያ ጋር ግንኙነት የለውም:: ምክንያቱም እኛ 85 በመቶ የውሃው መነሻ የሆንን ሀገር ነን:: ይሁንና ሃሳባችንም ሆነ ፈቃደኝነታችን አልተጠየቀም:: በእነርሱ ዓይን ኢትዮጵያ ድሃ እና የረሃብተኞች ሀገር ናት:: የኢትዮጵያ ስዕል አድርገው የሚጠቀሙትም የ1966 እና የ1977ቱን የረሃብ ስዕል ነው:: በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ የውሃ መብት መጠየቅ ቀርቶ ስለውሃ የማታውቅ ናት ብለው ያምናሉ:: በፊትም እንዲህ እያሉ ይሳለቁብን ነበር:: በወንዛችን እየተጠቀሙ ባለውለታችን ናቸው ብሎ ከማሰብ ይልቅ መሳለቂያቸው አድርገውናል::
አዲስ ዘመን፡- ግብፅ ዓባይን በተመለከተ የምትሠራው ሴራ ምን ያህል ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- በግብፅ ወደ አራት ሺህ አካባቢ መገናኛ ብዙኃኖች አሉ:: 90 በመቶ የሚሆኑት በአብዛኛው የሚዘግቡት የዓባይን ውሃ በተመለከተ ነው:: የግብፅ እመቤቶች ልጆቻቸውን ጡት ሲያጠቡ ‹‹የማጠጣህ ወተት የዓባይ ወንዝ ውሃን ነው፤ ያለእርሱ ሕይወት የለህም::›› እያሉ ነው:: የግብፅ የውትድርና ኤታማዦር ሹም የነበሩ ሰው ከ18 ዓመት ጀምሮ ያለ ወጣት በሙሉ ሲሠለጥን ቃለ መሐላ የሚፈፅመው ለግብፅ ሕዝብ ከማለት ይልቅ ለዓባይ እሞታለሁ ብለው ቃል እንዲገቡ ያደርጉ ነበር::
ግብፆች ምንም እንኳ የተማሩ ቢሆንም፤ ሁልጊዜም አመለካከታቸው ዓባይ ከፈጣሪ ለግብፅ የተሰጠ ስጦታ ነው ተብሎ መታመን አለበት ይላሉ:: በትምህርት ቤታቸው ለልጆቻቸው ከሕፃናት መዋያ ጀምረው የሚነግሯቸው እና የሚመግቧቸው መረጃ ይህንኑ ነው:: በተጨማሪ ለግብፆች የምንገብረው ውሃ ብቻ አይደለም፤ በሚሊዮን ቶን የሚቆጠር አፈርም ለግብፆች እናሻግራለን:: ሌላው ግብፆችን የሚያሳስበው የውሃ እጥረት አይደለም:: ከቀይ ባሕርም ሆነ ከሜዲትራኒያን ባሕር አጥልለው ውሃ መጠቀም ይችላሉ:: ቆፍረውም ሊያገኙ ይችላሉ:: ነገር ግን ሁልጊዜ የግብፆች ስጋት እና ጭንቀት ሌላ ነው::
እንደሚታወቀው ግብፆች በኢኮኖሚም ሆነ በዕውቀትም ጥንካሬ ከዓረቡ ዓለም የበላይ ናቸው:: የገልፍ ሀገራት ነዳጅ በማምረት የሚያገኙት የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ነው:: ዓረቦችም ግብፆችን በሰፊው ይደግፏቸዋል:: ለምሳሌ በፈረንጆቹ በ2023 ሳዑዲ ለግብፆች ያበረከተችው 32 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ነው::
ገልፎች ለግብፆች ታዛዥ የሆኑት ለምንድን ነው? ብለን ብንጠይቅ አንደኛ የገልፍ ሀገራት ነዳጅ አምራቾች ናቸው:: የምግብ ዋስትና እና የውሃ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ይፈታተናቸዋል:: የሕዝብ ቁጥራቸው በጨመረ ቁጥር የውሃ እና የምግብ ፍላጎታቸውም እየጨመረ ይመጣል:: ሳዑዲዎች ግብፅ ውስጥ በሰባት ሺህ ኩባንያዎች ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ ኢንቨስት ያደርጋሉ:: ምክንያቱም ሳዑዲ ከግብፅ ብዙ ጥቅም ታገኛለች:: ሳዑዲዎች 20/30 የሚባል ፕሮጀክት አላቸው:: በ2020 ሳዑዲን መካ መዲናን የሚጎበኙ ሰዎች ቁጥር 20 ሚሊዮን መድረስ አለበት:: በ2030 ደግሞ 30 ሚሊዮን የሃይማኖት ጎብኚዎች ይመጣሉ ብለው እየሠሩ ነው::
በዛሬ ጊዜ ዓመት ጠብቆ ለሐጅ የሚሔደው ሰው፤ አሁን ሐጅ በዓመት አንድ ጊዜ ቢሆንም ዑምራ ግን በየወሩ ክፍት ሆኗል:: ባወጡት ዕቅድ መሠረት ሰዎች ወደ ሳዑዲ እየሔዱ በመሆኑ ወደ 18 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝተዋል:: ለዛ ጎብኚ ውሃን ጨምሮ ምግብ እንዲሁም አትክልት እና ፍራፍሬ የሚመጣው የኢትዮጵያን ውሃ በመጠቀም ከምታመርተው ከግብፅ ነው::
ለጎብኚው የሚቀርበው ብርቱካን፣ ፓፓያ፣ ሙሉ ፍራፍሬ እና አትክልት የሚጋዘው ከግብፅ ነው:: ስለዚህ የግብፅ ስጋት ይህ ግድብ ተግባራዊ ከሆነ በኢትዮጵያ ልማት ከመጣ ቱሪስቶች በሙሉ ኮብልለው ወደ ኢትዮጵያ ይሔዳሉ፤ ፍራፍሬ እና አትክልት አምራቿም ኢትዮጵያ ትሆናለች ብለው ይፈራሉ:: ለረዥም ጊዜ ያስተላልፉ የነበረው መልዕክት ኢትዮጵያ ሰላም የሌላት የችግር ሀገር ናት የሚለውን ለማዳበር የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም:: የግብፆች ስጋት በገልፍ ውስጥ ያለውን አምርቶ የመሸጥን ሁኔታ ኢትዮጵያውያን ይካፈሉናል እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ያስቀሩብናል ከሚል ነው::
ትግላቸው በግድቡ ላይ ብቻ አይደለም:: የእኛ ችግር የሚቦካ እና የሚጋገረው በዓረብኛ መሆኑ ነው:: ግብፆች በዓለም አቀፍ ሚዲያ ውስጥ በሰፊው እጃቸው አለ:: ስለዚህ ከ12 ዓመት በፊት እኛ የግድቡን መሠረት ስንጥል፤ ከውጪ ርዳታ እንዳናገኝ ገደብ ጥለውብን ነበር:: ግብፆች ከግድቡም ባሻገር ኢትዮጵያ ሰላም እንዳይኖራት እና እንዳታድግ በብዙ መልኩ ይሠራሉ::
ድርድር እያሉ ግድቡን ለማደናቀፍ የሚሞክሩት ጉዳዩን የሥልጣን ማራዘሚያ በማድረጋቸው ነው:: የኢኮኖሚያቸውን መዳሸቅ የሚደብቁበት እና የዓረብ ነውጥ መልሶ እንዳይመጣ የሚከላከሉበት አንደኛው መንገድ ይኸው የዓባይ ወንዝ ጉዳይ ነው:: ሕዝቡን ግድቡ ከተገደበ ለረሃብ ትጋለጣለህ፤ ምንም አታገኝም እያሉ ሕዝባቸውን ያስፈራራሉ:: ፕሬዚዳንት አልሲሲ አሁንም ግብፅን ለመምራት 98 በመቶ ያገኙት የዓባይ ወንዝን በተመለከተ በሚሠሩት ፕሮፖጋንዳ ነው:: ትግሉ ወደፊትም ሊቀጥል ይችላል:: ድርድሩ ለምን ከሸፈ? በሚዲያ ግብፆች ለምን ጦርነት ከፈቱ? ከተባለ ጨዋታው የፖለቲካ ነው:: ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ ትፈራርሳለች ትዳከማለች ብለው ቢያስቡም እንደጠበቁት አልሆነችም::
አዲስ ዘመን፡- በ1929ኝም ሆነ በ1959ኙ እነርሱ ፈረምነው በሚሉት ስምምነት ላይ የኢትዮጵያ ሚና ምን ነበር? ድርድሮች በየጊዜው ለምን ይከሽፋሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- ኢትዮጵያ በእነዚህ ስምምነቶች ላይ አልተሳተፈችም:: ጥሪም ጥያቄም አልቀረበላትም:: እነርሱ ስምምነት ያደረጉት ከቅኝ ገዥያቸው ከእንግሊዝ ጋር ነበር:: የውሃውን 18 በመቶ ሱዳን ስትወስድ እኛ አልተጠየቅንም:: ስለዚህ በዛ ውል ባልተሳተፍንበት ሁኔታ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ልትጠቀም ስትል ሃሳቡ በፍፁም መነሳት የለበትም::
አሁን ድርድሩ በተደጋጋሚ እየከሸፈ ያለው ለምንድን ነው? ለሚለው የግብፆች ጥያቄ እና የሱዳን ጥያቄ አስቸጋሪ ነው:: የእነርሱ አጀንዳ አንድ ቢሆን ኖሮ፤ በእኛም በኩል ሁለቱንም ለመከላከል ያመቸን ነበር:: በመጀመሪያ ደረጃ ግብፆች አፍሪካዊነታቸውን ክደው እስከ መጨረሻ ድረስ ዓረብ መሆናቸውን አንፀባርቀዋል:: በመጀመሪያ ዙር የዓረብ ሊግ አባል ከመሆናቸው ባሻገር የሊጉ ዋናው ጽሕፈት ቤት ግብፅ ውስጥ ነው:: መሪዎቹም ከጥንት ጀምሮ ግብፆች ናቸው:: ስለዚህ ይህንን መድረክ በመጠቀም የውሃውን ጉዳይ የዓረብ ዓለም ጉዳይ ለማስመሰል ጥረት አድርገዋል:: ተፅዕኖ ለመፍጠር ሞክረዋል::
ቀጥሎ ደግሞ የግብፅን እንቅስቃሴ ከጥንት ጀምሮ ስናየው፤ ከአፍሪካ ኅብረት ይልቅ ወደ አሜሪካን ሔደው ተስፋ ለማግኘት እቅደው ነበር:: የመጀመሪያውም ሁለተኛውም ተመሳሳይ ነው:: በተለይ መጨረሻ ላይ የነበረው ዕቅዳቸውን ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንዳስሰው እንደሚታወቀው ገልፍ ውስጥ ኳታር ላይ ኤሜሬት፣ ሳዑዲ፣ ባሕሬን እና ግብፅ አንድ አቋም ነበራቸው:: መጨረሻ ላይ የጋራ ስምምነት እንዲፈጠር ዶሃ ላይ ስምምነት ተደረገ:: ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጉዞ የግብፅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሽኩሪ እና የሱዳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ መሬም የልዑካን ቡድን ይዘው ወደ አሜሪካ ተጓዙ:: ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ሲሔዱ ትራምፕ ከመውረዱ በፊት ግድቡ ይመታ የሚል አቋም አሳይቶ ነበር:: ለፀጥታው ምክር ቤት ሲያቀርቡ ለጊዜው ለእኛ ለኢትዮጵያውያን በጣም አስጨናቂው ነበር::
አቅራቢዋ የቱኒዝ ተወካይ ነበረች:: ምክንያቱም ቱኒዝ የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባል ነበረች:: እዛ ላይ ተማምነው የሔዱት እና ተስፋ የተሠጣቸው ግብፆች በኢትዮጵያ ግድብ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ነበር:: ይህን ተከትሎ ሁለት ጊዜ ወታደራዊ ሥልጠና ሱዳን ላይ ተካሂዶ ነበር:: ነገር ግን አጀንዳው እንደቀረበ ሁሉም በአንድ አቋም በጊዜው የወሰዱት የአሜሪካንም ሆነ የፈረንሳይ እንዲሁም የጀርመን ተወካዮች ይህ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ ስለሆነ ወደ አፍሪካ ኅብረት ይመለስ የሚል ውሳኔ ሰጡ:: ያ ውሳኔ ለግብፆች በጣም አሳፋሪ እና አስደንጋጭ ነበር::
ያ አጋጣሚ ሙከራቸው በሙሉ የከሸፈበት ዕለት ነበር:: ነገሩ ግን ያ አጀንዳ ተቀባይነት አግኝቶ ውይይት ቢካሔድበት ለሌሎች አገሮችም መጥፎ በር ይከፍት ነበር:: ምክንያቱም አሜሪካ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስኗት ግድቦች አሏት:: ኢራቅ እና ቱርክን የሚያዋስን ግድብ አለ:: ቻይናም እንዲሁ የሚያዋስናት ግድብ አላት፤ ስለዚህ ሁሉም ይህንን በር መክፈት አልፈለጉም:: በዓለማችን ከ200 በላይ ትልልቅ ግድቦች አሉ:: የግድብ ጉዳይ በፀጥታው ምክር ቤት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም:: የሚታየው እና የሚዳሰሰው በቅኝ ገዥዎች ምክንያት ችግር የተፈጠረባቸው የድንበር ጉዳዮች ብቻ ነው:: የእኛ ግድብ ጉዳይ ቀርቦ ቢወሰን ኖሮ፤ ለእነርሱም የራስ ምታት በር ይከፈትባቸው ነበር:: ስለዚህ ጉዳዩን ወደ አፍሪካ ኅብረት መለሱት:: ከዛ በኋላ የግብፆች ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወደ አውሮፓ፤ የሱዳኗም ወደ ራሺያ ሔዱ:: ነገር ግን ምንም ውጤት ሳያገኙ ሁለቱም ሀገራት ወደ አፍሪካ ኅብረት ተመለሱ::
አሁን የግብፆች አጀንዳ የታሪክ ስምምነት መነሻ ይሁን የሚል ነው:: ነገር ግን የእነርሱ ታሪካዊ ስምምነት እኛን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም:: ሁለተኛው በአፍሪካ ኅብረት ድርድር ውስጥ አፍሪካውያን ብቻ ሳይሆኑ የአውሮፓ እና የአሜሪካ ተወካዮች መኖር አለባቸው ይላሉ:: ለቅኝ ገዥዎች ያልተበገረች አገር ከአውሮፓ ታዛቢ ለምን ይመጣላታል? የአፍሪካ ኅብረት ሊዳኘን ይችላል እያልን ነው::
ሦስተኛው ይህ ጉዳይ በአፍሪካ ይታይ ሲባል የግብፆች ጥያቄ ‹‹እኛም በግድቡ ዙሪያ እንደታዛቢ ከግድቡ ሥራ ጋር አብረን መኖር አለብን፤ መክፈቱም መጠቀሙንም ቦታውንም መቆጣጠር ያለብን እኛ ነን::›› እያሉ ነው:: ለቅኝ ገዢዎች ያልተበገረች ሀገር እንዴት በራሷ ወጪ በሠራችው ግድብ ላይ የግብፅ ታዛዥ ትሆናለች? እንዴት ግብፆች ይህን ጨምሩ፤ ይህን ቀንሱ ማለት ይችላሉ? ይህንን የኢትዮጵያ 126ቱም ሚሊዮን ሕዝብ የሚቀበለው አይመስለኝም:: ምክንያቱም ለቅኝ ገዢዎች ያልተስማማን እንዴት ለግብፆች እንታዘዛለን? ይህም ተቀባይነት የለውም:: ሌላው አንደኛ ዙርም፣ ሁለተኛ ዙርም፣ ሦስተኛ ዙርም ሆነ አራተኛ ዙር ባልተጠበቀ መልኩ ተሞልቷል:: ይህ የፈጣሪ ርዳታም ታክሎበት የሆነ ነው:: አሁን ወደ አምስተኛ ዙር ስንደርስ ስጋት ይኖርባቸዋል:: ይህንን አምነን መቀበል አለብን:: ስለዚህ ከምንጊዜውም በላይ የዲፕሎማሲ እና የመከላከያ ጥንካሬያችን ላይ በአግባቡ መዘጋጀት አለብን::
ከዚህ ቀጥሎም ግብፆች አሁንም ሌላም ጥያቄ ይኖራቸዋል:: የውሃ ሙሊቱን በተመለከተ ከአሁን በኋላ ሁለት ዓመት መቆየት አለበት:: ቀስ በቀስ መሆን አለበት:: ግብፅን ለችግር የሚጋብዝ ከሆነ መሙላት የለባችሁም የሚል ውሳኔ እያስተላለፉ ነው:: ነገር ግን እነርሱ ምንም ድጋፍ ባላደረጉበት እንደውም እርዳታ እና ብድር እንዳናገኝ ከልክለው በራሳችን አቅም በገነባነው ግድብ እንዴት እነርሱ ይህንን ይቆጣጠራሉ? እኛ ይህንን አንቀበልም፤ ምክንያቱም እኛ ረሃብ እና ድህነትን ለመዋጋት መፍጠን አለብን:: የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ለመሆን እና ኢንዱስትሪውንም ለማስፋፋት እየፈጠንን መሥራት አለብን::
እነርሱ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት እንዳይኖር የማያደርጉት ጥረት አይኖርም:: በአማርኛ፣ በትግሪኛ፣ በኦሮሚኛ እና በዓረብኛ መገናኛ ብዙኃን በመክፈት ኢትዮጵያ ሰላም እንዳልሆነች፤ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳትሔዱ ተጠንቀቁ እያሉ ዜና እያሠራጩ ነው:: ስለዚህ እኛም በበኩላችን አንድነታችንን በማጠናከር የግብፅ ሴራ ማሰናከል ይኖርብናል:: አሁንም ለድርድር ሲመጡ አጀንዳቸው ሰፊ ነው:: በቅንነት የሚንቀሳቀሱ አይደሉም::
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባው ግድቡን ለማፍረስ አስቀድመው ተዘጋጅተው ነበር:: ከፈረንሳይ በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር የተገዛ ልዩ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላን ከግብፅ ሦስት ሺህ ኪሎ ሜትር ርቆ ሔዶ መምታት የሚችል ነበር:: ለአየር ኃይል አዛዡ በደረቁ እንዲመታ ትዕዛዝ ተሰጥቶት ሱዳን ውስጥ ሲለማመዱ ነበር:: ነገር ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ የመጀመሪያው ሙሊት ተካሔደ፤ ሁለተኛው ሙሊት ሲቀጥል እዛ ላይም የማይሆንላቸው ሆነ:: አሁን ባለው ሁኔታ ግድቡ ከመሬት በላይ ከፍ ያለ ሲሆን፤ ከሱዳንም ሆነ ከግብፅ ከፍታ ላይ በመሆኑ አሁን ቢመታ ወደ ጎን 150 ኪሎ ሜትር ውሃ ይረጫል:: ወደ ላይም ስለሚረጭ ከሱዳን 20 ሚሊዮን ሰው ጠራርጎ ከሰባት ሰዓት በኋላ ግብፅ አስዋን ግድብ ይደርሳል:: ስለዚህ አሁን ላይ ይህ ግድብ ራሱን መከላከል ይችላል:: ምክንያቱም እነርሱንም ያጠፋቸዋል::
ከዚህ ሁሉ በኋላ አሁንም አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነው እየተከራከሩ ነው:: ሱዳኖች ግድቡ እንደገና መመርመር አለበት፤ የቴክኒክ ችግር አለበት እያሉ ነው:: ነገር ግን ግብፅ እና ሱዳንም አይስማሙም:: አሁን ላይ ሱዳንን የሚወክል ቋሚ ተከራካሪ አለ ለማለት ያስቸግራል:: በግብፆች በኩል ፖለቲካቸው እያስጨነቃቸው በመሆኑ ያንን ለማረጋጋት ሲሉ ይህኛው ድርድር እንዲከሽፍ አድርገዋል:: በእኛ በኩል ግን ተረጋግተን ሰላም በማሰፍን ግድቡን መጠቀም አለብን:: ይህንን ለትውልዱ ማሳወቅ ይጠበቅብናል::
ኢትዮጵያውያን ለዚህ ግድብ ብዙ ደክመናል፤ ግብፆች ደግሞ ያሰቡት ሴራ ከሽፎባቸዋል:: ነገር ግን አሁንም እንደማይተኙልን ማወቅ አለብን:: አሁንም ጥረት እያደረጉ የኢትዮጵያን ሕዝብ በብሔር እና በጎሳ እንዲሁም በሃይማኖት በመከፋፈል ለማጋጨት ይሞክራሉ::
ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም ላይ ኢትዮጵያ የግድቡን መሠረት ስትጥል፤ የግብፅ መሪ ፕሬዚዳንት ሙርሲ የሃይማኖት ድርጅት መሪዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችን እና የሀገራቸውን መከላከያ ሚኒስትር ጨምሮ ሁሉንም ባለሥልጣናት ጠርተው በቀጥታ በቴሌቪዥን ሥርጭት በማስተላለፍ ስብሰባ አድርገዋል:: በዛ ጊዜ የተላለፈው ሃሳብ አንደኛው ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ተኩስ እንድትከፍት እና ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ እንድትገባ የሚል ነበር:: ሁለተኛው የጅቡቲ መንግሥት የዓረብ ሊግ አባል ስለሆነ ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን የወደብ አገልግሎት እንዲያቆም የሚል ነበር:: ሦስተኛው ሼህ መሐመድ አላሙዲንን በማስገደድ በኢትዮጵያ ኢንቨስተርነቱን እንዲያቆም ማድረግ ነው:: የኢትዮጵያ ሙስሊሞች በሥርዓቱ ላይ እንዲያኮርፉ የሚል አጀንዳ ተነድፎ ነበር:: ሌላው የኦጋዴን ነፃ አውጪዎችን በመደገፍ ኢትዮጵያን እንዲበጠብጡም ታስቦ ነበር:: ነገር ግን አንዳንድ ሰዎች ኢትዮጵያን መንካት ተገቢ አይደለም ብለው ነበር:: ሙርሲ እንዳሰቡት አልሆነላቸውም:: እንደውም ሁለት ወር ሳይሆናቸው እስር ቤት ገብተው በዛው ተሰናበቱ::
ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በሙስሊሙ ሕዝብ ያላትን ከበሬታ በመጠቀም አብረን ለመኖር ጥረት እናደርጋለን:: ነገር ግን የውሃ ጉዳይ ላይ እኛ በከፊል ብንጠቀም እነርሱ ብዙ የሚጎዱት ነገር የለም:: ነገር ግን ግብፆች ይህንን በቅንነት የማይመለከቱት መሆኑን አውቀን ግድባችንን ለማጠናቀቅ እስከ መጨረሻው ጥረት ማድረግ ግዴታችን ነው::
አዲስ ዘመን፡- የቅኝ ግዛት ውሎቹ ኢትዮጵያን ያገለሉና ጭራሹኑም ለኢትዮጵያ ዕውቅና የማይሰጡ ናቸው:: ተወያዮቹ ይህን መጥቀስ እና መነሻ ማድረግ ለምን አስፈለጋቸው?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- ቅኝ ገዥዎች መሣሪያ ነጋዴዎች ናቸው:: ዋናውን ሥራ የሚሠሩት እነርሱ ናቸው:: አፍሪካውያን ይህንን ማወቅ አለባቸው:: በቅርቡ ባገኘሁት እና አልጀዚራም ባስተላለፈው የጥናት ሰነድ የገልፍ ሀገራት እና የአፍሪካ ሀገሮች የጋራ ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል ይላል:: በጥናቱ ሰላም እና መረጋጋት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ መስፈን እንዳለበት እና ለእዚህም ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በ40 ሚሊዮን ሕዝብ የምትበልጠዋ ኢትዮጵያን መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑ ተጠቅሷል::
ኢትዮጵያ ውስጥ ችግር ከተከሰተ ለአፍሪካ ቀንድ እና ለሌሎችም ጎረቤት አገሮች ከባድ መሆኑን ግብፆችም ከግምት ውስጥ የሚያስገቡት ጉዳይ ነው:: ቅኝ ገዢዎች ግን ከዚህ በተቃራኒው ናቸው:: ዋናው ጉዳይ የገልፍ ሀገሮች አሁን ባለው የፖለቲካ ዓለም መቀያየር ምክንያት አሜሪካንንም ሆነ አውሮፓን የሚፈሩበት እና ስለእነርሱ የሚጨነቁበት ሁኔታ ተቀዛቅዟል:: ይህ ባለበት ሁኔታ እኛን የሚያሳስበን ነገር የለም:: ነገር ግን እነርሱ የሚቆሰቁሱት ግብፅ እና ኢትዮጵያ ጦርነት ውስጥ ሲገቡ እነርሱ ፍላጎታቸው የጦር መሣሪያዎችን ለመሸጥ ነው:: ዋናው ጉዳይ የዓለም ሁኔታ እየተቀያየረ ስለሆነ የኢትዮጵያ የውጪ ዲፕሎማሲ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ያለን ግንኙነት በሚዳብርበት ሁኔታ ላይ በደንብ መሥራት ይገባል::
በሌላ በኩል መከላከያ መዳከም የለበትም:: ግብፆች 92 ሺህ መለዮ ለባሽ አለን ይላሉ:: ኢትዮጵያ ደግሞ 150 ሺህ መለዮ ለባሽ አላት:: ከፍተኛ የወታደርም ሆነ የመሣሪያ ኃይል አለን ሲሉ፤ በመሣሪያ እናሸንፋለን ብለው አይደለም:: ምክንያቱም እኛ ድሮም ለቅኝ ገዥዎች አልተገዛንም:: አሁንም በቅኝ ገዥዎች ተፅዕኖ አንበረከክም:: አሁን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ላይ መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ትንንሽ በክልል በጎሳ ውስጥ ለውስጥ የምናደርገው ያልተገባ እንቅስቃሴ መቆም አለበት:: ወደ ሰላም በመምጣት ሀገሪቷን አጠንክረን መጓዝ አለብን::
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ባልፈረመችውና በቅኝ ግዛት ውስጥ ያልነበረች ሀገር እንደመሆኗ በእነዚህ ውሎች የመገዛት ግዴታ አለባት?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- በምንም መልኩ መገዛት የለባትም:: ምክንያቱም እኛ በዛ ወቅት ምንም አልመከርንም፤ ይህ ጉዳይ ጭራሽ አይመለከተንም:: በዚህ ስምምነት ላይ ተመሥርተን አንደራደርም:: ለመደራደርም ታሪክ አያስገድደንም:: ይህን ሃሳብ የሚቀበል ካለ፤ ከግብፅ ጎን የሆነ ነው:: በዚህ ላይ የዓለም ሕግም አያስገድደንም:: እኛ እነርሱ የሚሉትን ስምምነት ብንቀበል ለሚወዱን አፍሪካውያንም ውርደት ነው:: ሌላው አፍሪካዊም እሠራለሁ ሲል፤ ቀዳዳ ይፈጠርበታል:: ስለዚህ እኛ አፍሪካውያንም ሆኑ ሙስሊም ሀገራት ከጎናችን ናቸው:: ይህንን መጠቀም አለብን:: ይህንን እኛ በመንግሥትም ሆነ በሕዝብ ደረጃ አንስማማበትም፤ ጭራሽ አንቀበለውም:: ነገር ግን አሁን ደግሞ አዲስ ነገር ይዘው ብቅ ለማለት እየሞከሩ ነው:: ‹‹ቤኒሻንጉልም የሱዳን ነው::›› እያሉ ነው:: ማስረጃ አለን ብለው እያቀረቡ ነው::
አዲስ ዘመን፡- በፈረንጆቹ 2015 ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የተፈራረሙት የመርሕ ስምምነት ምንድን ነው? ይህን ስምምነት ለመተግበር ግብፆች አሻፈረኝ ያሉት ለምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡– በዛ ጊዜ የፈረሙት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ነበሩ:: በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ነበሩ:: በሱዳን በኩልም ፕሬዚዳንት አልበሽር ነበሩ:: የግብፁ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ሲፈርሙ የተሰጣቸው መመሪያ አንደኛ የግብፅ ተቃዋሚዎች እንደሚያቀርቡት ሀገራቸው በምትመራበት ሕግ አንቀፅ 151 ላይ ይህንን ስምምነት ሲፈርሙ ከፓርላማው ድጋፍ ሊኖራቸው ይገባ ነበር:: ይህንን ስላላደረጉ ውድቅ ሆኗል ይላሉ::
ሁለተኛው አልሲሲ በሰዓቱ አዲስ ናቸው:: ልምዱም ያልነበራቸው በመሆኑ ያንን የፈረሙት በዘፈቀደ ነው ብለው ያብጠለጥሏቸዋል:: ሦስተኛው እርሳቸው የፈረሙት ግብፆች በዓለም አቀፍ ተቋማት የሌሉበት ቦታ የለም:: ስለዚህ ኢትዮጵያ አምስት ቢሊዮን ዶላር የማውጣት አቅም የላትም:: አንድ ቢሊዮንም ማግኘት አትችልም ብለው አማካሪዎቻቸው አሳምነዋቸው ስለነበር ፈርመው ነበር:: 304 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንዳናገኝ ገደብ አስጥለውብናል:: ፕሮጀክቱን የሚያስፈፅሙ የጣሊያን እና የፈረንሳይ ድርጅቶች እንዳይሠሩ ጥረት አድርገዋል::
ግድቡ ሥራ ላይ ከዋለ በቀን ሰባት ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጥ ይፈጠራል:: ይህ ከሆነ ቀይ ባሕር ሀገራትን ለአደጋ ይጋብዛል ብለው ፕሮፖጋንዳ ሲሠሩ ነበር:: ያንን ለዓረብ ሊግ አባላት አቅርበዋል:: ይህንን ያሉት አሉ የሚባሉ የግብፅ የውሃ መሐንዲሶች ናቸው:: ስለዚህ መሠራት የለበትም ብለው ርዳታ እና ድጋፍ ቢያስቀሩም ግድቡ በእኛው አቅም 40 በመቶ ሲደርስ መጨነቅ ጀመሩ:: በየቀኑ በሳተላይት ሲከታተሉ ቆይተው በየአቅጣጫው መረባረብ ጀመሩ::
መከላከያቸውን፣ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲያቸውን እና መገናኛ ብዙኃን ላይ እና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ሳይቀር በዘመቻ በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ሞከሩ:: ሆኖም ኢትዮጵያ ያ ሁሉ ተፅዕኖ ተቋቁማ አራተኛውን የውሃ ሙሌት መሙላት ቻለች:: ያ የ2015 ዓ.ም ስምምነት ግድቡን መገንባት እንደሚያስፈልገን እና እንደምንችል ይህም በግብፅ ላይ ጉልሕ ተፅዕኖ እንደማያመጣ የሚያመላክት ነው:: ያንን አንዴ ፈርመዋል::
አዲስ ዘመን፡- አሁንም ግብፆች አላርፍ ያሉት እና ታሪክ እያሉ ከ2015 ዓ.ም በፊት የነበሩትን የቅኝ ግዛት ውሎች እየጠቀሱ የሚከራከሩት ለምንድን ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- በሕዝብ ብዛት እና በመሬት አቀማመጥ እንበልጣቸዋለን:: በአፍሪካ ደረጃ እና በሙስሊሙ ዓለም ከፍተኛ ቦታ አለን:: ለእነርሱ ይህ ያሰጋቸዋል:: ምናልባት አሁን ጥረት የሚያደርጉት የአፍሪካ ኅብረትን ቦታ መቀየር ነው:: ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት እና የቤት ሥራችንን መሥራት አለብን:: ሰላም ከሰጡን ለሠላም በራችን ክፍት ነው:: በጦርነት ከመጡ ግን መከላከያችን ብቁ ነው:: ነገር ግን መዘንጋት የሌለብን ስጋት አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ እናመሰግናለን::
ረዳት ፕሮፌሰር አደም፡- እኔም አመሰግናለሁ::
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 20 ቀን 2016 ዓ.ም