አዳማ:- በፌዴራል ከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የሴቶች ኢንተርፕሪነርሺፕ ልማት ፕሮጀክት በተለያየ ንግድ ሥራ ላይ ለሚገኙ 35 ሴት ኢንተርፕሪነሮች እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ያለዋስትና ብድር ተጠቃሚ ማድረጉን የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አስታወቁ።የአጭር ጊዜ የክህሎት ስልጠና በመስጠት የንግድ ሥራቸውን እንዲያሳድጉ እገዛ ማድረጉም ተጠቁሟል።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ሰለሞን ለአዲስዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የብድር አገልግሎቱ የተበዳሪዎችን የሥራ እንቅስቃሴና የንግድ ዓይነት፣ባህሪና ሌሎች መስፈርቶችንም ባካተተ በቴክኖሎጂ በታገዘ ጥናት በማካሄድ መስፈርቱን ላሟሉ የሚሰጥ ሲሆን፣ እስካሁንም ሙከራው በተጀመረበት አዳማ ከተማ መስፈርቱን ላሟሉ 35 ሴት ኢንተርፕሪነሮች ብድር ተሰጥቷል።ወደ ሦስት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ብር የሚሆን ለብድር አገልግሎት ውሏል። በዓመት አንድ ቢሊዮን ብር የማበደር አቅምም ተፈጥሯል።
ተጠቃሚዎች ብድራቸውን በመመለስና ሥራቸውን በማስፋፋት ውጤታማ መሆናቸው በመረጋገጡ በቅርቡም አሰላ ከተማ ላይ ለመጀመር ቅድመ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን የገለጹት አቶ ዮሐንስ የብድር አገልግሎቱ ለሙከራ አዳማ ላይ ቢጀመርም የክህሎት መሳደጊያ ስልጠናው ግን በ10 ከተሞች ለ17ሺ585 ኢንተርፕሪነሮች ስልጠና መሰጠቱን አስረድተዋል።ስልጠናው አብዛኞቹን ከልምድ አሰራር ያላቀቃቸው መሆኑን ከኢንተርፕሪነሮቹ ውጤታማነት ማረጋገጥመቻሉንም ጠቁመዋል። ከተሞቹን ወደ 18 ከፍ በማድረግ የስልጠናውን ተደራሽነት ለማሳደግ ታቅዷል። የክህሎት ስልጠናው ከአምስት የግልና ከ21 የመንግሥት ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ጋር በትብብር እየተሰጠ ይገኛል።
ለብድር አገልግሎቱ ከዓለምባንክ 50 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጃፓን መንግሥት 50 ሚሊዮን ዶላር፣ ከጣሊያን መንግሥት ደግሞ 15 ሚሊዮን ዶላር በብድር መገኘቱን የገለጹት አቶ ዮሐንስ ብድሩ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኩል እንደሚሰራጭና ተበዳሪዎቹ ጋር ተደራሽ የሚሆነውም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ እና የዓለምባንክ መስፈርትን በሚያሟሉ 12 አነስተኛ አበዳሪ ተቋማት አማካኝነት እንደሆነ አስረድተዋል።ለብድር አገልግሎት ውሎ ተመላሽ የሆነ ገንዘብም መልሶ ለብድር እንዲውል በመንግሥት መፈቀዱን አመልክተዋል።
የተለያዩ ባንኮችም ያለዋስትና የብድር አገልግሎት እንዲተገብሩ በፕሮጀክቱ በኩል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት አቶ ዮሐንስ ሥራዎች ከተጠናከሩ ሀገራዊ ፋይዳ ያለው የንግድ ሥራ የሚያከናውኑ ኢንተርፕሪነሮች ማፍራት እንደሚቻል አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
ለምለም መንግሥቱ