እማማ ሸጌ ሰፈሩ ውስጥ የታወቁ አረቄ ነጋዴ ናቸው። ከእጃቸው ላይ ማንቆርቆሪያ ከፊታቸው ላይ ፈገግታ ጠፍቶ አያውቅም። ቀይ ናቸው፣ በቀይ መልካቸው ላይ ተመዞ የወጣው አፍንጫቸው ማንም ሳያየው ዓይን ውስጥ ይገባል። እንደ ቀለበት መንገድ አንገታቸው ላይ የተጥመለመለው ንቅሳት በነጭ ብራና ላይ የተነደፈ ስዕል ይመስላል።
ከወገባቸው ጠፍቶ የማያውቀው መቀነት በሀገር ባንዲራ ተሸልሞ ሲታይ ሀገር ወዳድነታቸውን ያሳብቃል። እማማ ሸጌ በሁለት ነገር አይታሙም አንደኛው በቁጥር ነው። የትኛውም ጠጪ ምንም ያክል ቢጠጣ ከእማማ ሸጌ ስሌት አያመልጥም። በጓዳ ጎድጓዳው እየተዋከቡ ጭንቅላታቸው ግን የእያንዳንዱን ጠጪ መለኪያ ይቆጥራል። ሁለተኛው ደግሞ ፍራንክ ነው..እማማ ሸጌን ከማታለል ከጆባይደን ቢሮ መረጃ መስረቅ ይቀላል። የአንድን ጠጪ ሂሳብ ለማስላት ምንም አይነት የቴክኖሎጂ ውጤት አይጠቀሙም ለጥቂት ደቂቃ ዝም በማለት በጭንቅላታቸው ካወጡ ካወረዱ በኋላ የማይጠጋጋ ሂሳብ ይነግሩሀል። ይሄ ልዩ ብቃታቸው ነው።
የሚገርመው ደግሞ ምንም አይነት የትምህርት ደረጃ የሌላቸው መሆናቸው ነው። በሦስት መንግሥት ላይ ተረማምደው መጥተው እንኳን ለሀገሬ ሕዝብ ባለውለታ ለሆነው መሰረተ ትምህርት ባይተዋር ናቸው። የጭንቅላታቸው አይኪው መዛኝ ቢያገኝ ኖሮ በሂሳብ ስሌት አቻ የሌላቸው እድሜ ጠገቧ አዛውንት ይሆኑ ነበር።
አስረሳኸኝ የእማማ ሸጌ የረጅም ጊዜ የአረቄ ደንበኛ ነው። አስረሳኸኝን ከሌሎቹ ጠጪዎች ለየት የሚያደርገው አረቄን እንደውሃ መጠጣቱና ራዕይ ያለው ሰካራም መሆኑ ነው። አረቄ ሲጠጣ ዓለም ላይ ጣፋጩን መጠጥ የሚጠጣ ነው የሚመስለው። አያቃጥለው፣ አይጎረብጠው በቃ አንስቶ ዥው..ምጥጥ፣ ሽምጥጥ። ከእማማ ሸጌ ቤት ሌላ ህይወት ያለ አይመስለውም። እማማ ሸጌ እግዜሩ ናቸው..ምንም ፈልጎ የማያጣባቸው።
ከእሳቸው ውጪ እስትንፋስ የሌለው ይመስል ውሎ አዳሩ እዛው ነው። ሰፈር ሲለቁ ሰፈር እየለቀቀ፣ ሀገር ሲለቁ ሀገር እየለቀቀ በሄዱበት በመሄድ ዛሬም ድረስ ምርጥ ደንበኛነቱን አስመስክሯል። ከወገቡ ጎበጥ ያለ ነው። እድሜ ግሳንግሱን ጭኖበት ወደ መሬት ያለ..። በግንባሩ ሜዳ ላይ ዘመን ያሰመራቸው ቀጫጭን መስመሮች ይታያሉ። በዘመን የተኳሉ..በጊዜ የተቀለሙ አለላ መልኮች።
የአስረሳህኝ ሌላው ስሙ ባለራዕዩ ነው። በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ከመጠሪያ ስሙ በላይ በዚህ ስሙ ይታወቃል። አስረሳኸኝና ራዕይ ተነጣጥለው የማይታዩ የአንድ እጅ መዳፍና አይበሉባ ናቸው። ገና እግሩ ደፍ ሳይረግጥ ቀድመውት የመጡት የአረቄ ቤት ወዳጆቹ ባለራዕዩ ሲሉ በጭብጨባ ይቀበሉታል። ያልኖረው ወደፊት እኖረዋለው ብሎ የሚያስበው ህልም አለው። እውነት ለመናገር እየኖረው ያለውን ህይወቱን አይወደውም።
አረቄ ቤት ከመዋልና ሰክሮ የትም ወድቆ ከማደር ባለፈ ለዚች ዓለም ያበረከተው አስተዋጽኦ የለም። በዚህ ይበሳጫል..ነገ ላይ ሌላ ሰው ሆኖ ራሱን ማየት ይፈልጋል። ከዚህ የበዛ እምነቱ በመነሳት ጓደኞቹ ባለራዕዩ አሉት..ባለራዕዩ ሆኖ ቀረ። ህልሙ የሚጀምረው ግን እማማ ሸጌ ቤት ሲደርስና አንድ ሁለት መለኪያ አረቄ ሲደረግም ነው። ከዛ በኋላ ሌላ ነው..ባለቢጫ አይኖቹ ጓደኞቹ በወሬው እስኪሰለቹ ድረስ ስለ ህልሙ ይዘባርቃል።
እማማ ሸጌ ከነማንቆርቆሪያቸውና ከነፈገግታቸው ከእቃ ቤቱና ከሳሎኑ አዋሳኝ ላይ ቆመው መለኪያው የጎደለበትን ይቃኛሉ። በዚህ መሀል ጎጃም አዘነ የለበሰ አንድ አዙሮ አደር ‹ሎተሪ..ነገ የሚወጣ..አስር ሚሊዮን ብር› እያለ ወደ ውስጥ ገባ።
አስረሳኸኝ የሎተሪ አዟሪውን እጅ አፈፍ አድርጎ…‹አ..አን..ንድ ስጠኝኝኝ› አለው…ስካር ባነቀው ንግግር። እጁን ሱሪው ኪስ ከቶ ፍራንክ ሊያወጣ እየተፍጨረጨረ። ባለሎተሪው ከትከሻው የተንሸራተተ ጎጃም አዘነውን ሽቅብ እያጣፋ እንደተባለው አንድ በጥሶ ሰጠው።አስረሳኸኝ ሎተሪውን አፍጦ እየተመለከተ ‹እድለ ቢስ ነኝ ግን ደግሞ ባለራዕይ..ያልተኖረ፣ ያልተነካ ድንግል ራዕይ።
ከቀናት በኋላ አስረሳኸኝ እማማ ሸጌ ቤት አምሽቶ ሰክሮ ቤቱ ሲገባ ጠዋት የከፈተው ሬዲዮ እያወራ ያገኘዋል። ጫማውን ሊያወልቅ ሲንደፋደፍ ሬዲዮው የምሽቱን የሎተሪ አሸናፊ ቁጥር ሲናገር አንድ ሆነ። እጁን ወደ ኪሱ ከቶ ሎተሪውን አወጣ..። የሰዓቱ ዜና አንባቢ የመጀመሪያውን ቁጥር ተናገረ አስረሳኸኝ እጅ ላይ ካለው የሎተሪ ቁጥር ጋር ተመሳሳይ ነበር። አስረሳኸኝ አላመነም..ስካሩ ለቀቀው።
ዜና አንባቢው ቀጥሎ ያለውን ተናገረ…አሁንም ተመሳሰለ። ሰካራሙ ሰው እየሆነ ያለውን ነገር ማመን አልቻለም። በዜና አንባቢው አፍ ያልተጠሩ የመጨረሸ አራት ቁጥሮች ይቀራሉ። አስረሳኸኝ ስሜቱን መቆጣጠር አልቻለም።
በመሀል ሬዲዮኑ ቀጠለ..የአስረሳኸኝን የሎተሪ ቁጥር እያየ የሚናገር ይመስል ቁጥሩ ከቁጥሩ ጋር አንድ ሆነ። አስረሳኸኝ ሳያስበው ከዚህ በኋላ የሆነውን አያስታውሰውም..። የመጨረሻ ሁለት ቁጥሮች ይቀሩታል። ከነዚህ ሁለት ቁጥሮች በኋላ የአስረሳኸኝ ታሪክ ይቀየራል። ዜና አንባቢው ገና አልጠራቸውም..ልቡ ድም..ድም አለ።
ከሁለቱ አንዷ በዜና አንባቢው አፍ ተጠራች። በደስታ ውስጥ ሆኖ አንዷን ሰማት..እሱ እጅ ላይ ካለችው ጋር ተመሳሳይ ነበረች።አስረሳኸኝ ደስታ አሸነፈው..የመጨረሻዋን ቁጥር ሳይሰማት በደስታ መሬት ላይ ተዘረረ።
ሌሊት ሲነጋጋ አስረሳኸኝ ራሱን ከሳተበት ነቃ። ምን ተከስቶ እንደነበር ለማስታወስ አልተቸገረም። እስኪነጋ በደንብ አሰበ። እማማ ሸጌ አረቄ ቤት ላይደርስ፣ መርካቶ ጠጅ ቤት ላይገባ፣ ሰባተኛ ጉሮኖ ውስጥ ላይገኝ መዋያውን ዱባይና ሙባይ ከቆነጃጅት ጋር ሊያደርግ እንዲህ አሰበ።
ሌሊቱ ራቀበት..ንጋት ተሰወረበት። ነግቶ እየመሸ እንጂ መሽቶ እየነጋ አልመስልህ አለው። ሰዓቱ ወደ ኋላ እንጂ ወደ ፊት የሚቆጠር አልመስልህ አለው።12 ሰዓት ላይ ብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር ሄደ…የሥራ ሰዓት እስኪደርስ እየተንቆራጠጠ መጠበቅ ግድ ነበረበት።
‹ምን ልርዳህ? አሁን አሁን መነጽሩን ወደ ቅንድቡ የሚገፋ ሰው ጠየቀው።
‹አስረሳኸኝ እባላለሁ…እ…› አስረሳኸኝ ያልተጠየቀውን መለሰ።
‹እኮ ምን ልርዳህ? መነጽሩን እየገፋ በድጋሚ ጠየቀ።
‹በሎተሪ አሸናፊ ሆኜ፣ አንደኛ እጣ ደርሶኝ፣ ገንዘቤን ልቀበል መምጣቴ ነው። በታላቅ ጉራና መኩራራት መለሰ።
‹ሎተሪውን ልታሳየኝ ትችላለህ?
አስረሳኸኝ በቅድሙ መኩራራት በእጁ ጨምድዶ የያዛትን የሎተሪ ትኬት ዘረጋለት። ዓለም ፊቱ ላይ ትታየዋለች..ተዘርግታ ልትቀበለው።
መነጽሩን ወደ አፍንጫው ካልገፋ ህይወት ያለው የማይመስለው ሰውዬ የሎተሪውን ቁጥር በደንብ ካየ በኋላ አጠገቡ ያለውን ኮምፒውተር መጎርጎር ጀመረ።
አስረሳኸኝ..ከጥቂት ደቂቃ በኋላ ስላለው አስደናቂ ህይወቱ በማሰብ ላይ ነበር።
‹አቶ አስረሳኸኝ…› ከኮምፒውተሩ ላይ ቀና ብሎ ጠራው።
አስረሳኸኝ ከሃሳቡ ባኖ እየወጣ..‹አዎ ነኝ..አስር ሚሊዮን ብር..አቤት..አቤት› እየዘላበደ ወደ ሰውዬው ተንደረደረ።
‹አዝናለሁ! ሎተሪው አልደረሰህም…
አስረሳኸኝ ነፍስ ላይ ረጅም ዝምታ ሰፈረ…
‹የመጨረሻዋ አንድ ቁጥር የተለየች ናት› መነጽሩን ወደ አፍንጫው እየገፋ ተናገረ።
በአስረሳኸኝ ገጽ ላይ ጀምበር ተሰወረች። ከተስፋው ምሥራቅ ላይ ጀምበር ጠለቀች። የፈገግታው፣ የጽናቱ፣ የሁሉ ነገሩ ፀሐይ ዳመነች። ከእምነቱ ጋር ተኳረፈ…
ወደ ኋላው መሬቱ ላይ ሲዘረር..ዳግም ላለመነሳት የማለ ይመስል ነበር።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም