ከወደብ ፍላጎታችን ጀርባ ያሉ አስገዳጅ ሁኔታዎች

በዓለም ላይ 44 የሚሆኑ ሀገራት የባሕር በር ወይም ወደብ እንደሌላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የባሕር ወደብ ከሌላቸው የዓለም ሀገራት ትንሽ የቆዳ ስፋትና አነስተኛ የሕዝብ ብዛት እንዳላት የሚነገርላት በአውሮፓ አህጉር የምትገኘው ቫቲካን የተባለች ሀገር ነች። በተቃራኒው የባህር በር ከሌላቸው የዓለም ሀገራት ከፍተኛ የቆዳ ሥፋት ያላት በመካከለኛው ኤሺያ የምትገኘው ካዛኪስታን ነች። ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ተሸክማ ወደብ የሌላት የዓለማችን ብቸኛ ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ሆና በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍራለች።

ወደብ አልባነት ብዙ ሕዝብ ባላቸው ሀገራት እና ጥቂት ሕዝብ ባላቸው ሀገራት ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ በእጅጉ ይለያያል። ዛሬ ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የሕዝቧን ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም የገቢ ወጪ ንግዷን አቅም ማሳደግ ግድ ብሏታል። ይሁንና ወደብ ስለሌላት ብቻ ባሰበችው ልክ እንዳትራመድ ሆናለች።

በአፍሪካ 16 የሚሆኑ ሀገራት የባህር በር ወይም ወደብ የላቸውም። ከእነዚህም ቻድ፣ ቦትስዋና ፣ ኒጀር ፣ ማላዊ፣ ማሊ ሩዋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ለውቅያኖስ የአፍና አፍንጫ ያህል ርቀት ኖሯት ወደብ አልባ የሆነችው ኢትዮጵያ ነች። ከአስራ ስድስቱ የአፍሪካ ወደብ አልባ ሀገራት ውስጥ አብዛኛዎቹ የወደብ ባለቤት መሆን ያልቻሉት ከውቅያኖስ ርቀው ስለሚገኙ ነው።

ኢትዮጵያ ቀይባሕርን ራስጌዋ ሕንድ ውቅያኖስን ግርጌዋ አድርጋ የባህር በር ያጣችበት ምክንያት ሁሌም በዜጎቿ ዘንድ ጥያቄ የሚፈጥር፣ የሚያስቆጭ እና ለተመልካችም ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው። የውቅያኖሱን ዳርቻ ተከትሎ ረዥም ኪሎሜትር የሚዘልቀው የጎረቤቶቿ ወሰን ዝግ ‹‹land locked›› ሀገር አድርጓታል።

ኢትዮጵያ ከ95 በመቶ በላይ የገቢ ወጪ ንግዷን የምታካሂደው በባሕር ትራንስፖርት በተለይም በጂቡቲ ወደብ አማካኝነት ነው። ለምትጠቀምበት የወደብ አገልግሎትም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ትከፍላለች። በዚህም ቢበቃ ጥሩ ነበር፤ ኮንቴነሮች ወደብ ላይ ከተራገፉ በኋላ በፍጥነት ሳይነሱ በመቅረታቸው ምክንያት በየቀኑ በሚቆጥርባቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ትጠየቃለች።

የጂቡቲ ወደብ ባለበት ጫና ምክንያት ደንበኞችን በፍጥነት የማስተናገድ አቅሙ አናሳ በመሆኑ ከወደቡ እቃ ለመጫን ከኢትዮጵያ ወደ ሥፍራው የሚሄዱ ሾፌሮች ለአላስፈላጊ የጊዜ ብክነትና ወጪ መዳረጋቸውም ሌላው የኢኮኖሚ ጉዳት ነው። ይህ ሁሉ ዋጋ ተከፍሎ ምርቶቹ ወደ ሀገር ውስጥ ከገቡ በኋላ ወደብ ላይ በመቆየታቸው ብቻ የአገልግሎት ጊዜያቸው አብቅቶ ከጥቅም ውጭ የሚሆኑትም በርካታ ናቸው። እንግዲህ እነዚህ ችግሮች ተደማምረው በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ምን አይነት ተጽዕኖ እያሳደሩ እንደሆነ መገመት አይከብድም።

ኢትዮጵያ ከሰላሳ ዓመት በፊት የራሷ ወደብ የነበራት ሀገር ስለመሆኗ ዓለም የሚመሰክረው እውነታ ነው። የንግድና የጦር መርከቦቿም መልህቃቸውን ይጥሉ የነበረው በራሷ ወደብ ላይ ነበር። የወደብ ባለቤት በነበረች ጊዜ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት እየተሰማሩ የወጪ ገቢ ንግዷን የሚያቀላጥፉላት የንግድ መርከቦች የትናንት ትውስታችን ናቸው። እነዚህ መርከቦች ዛሬም ሸበሌ፣ ጊቤ፣ አሶሳ፣ ጋምቤላ፣ ሀዋሳ፣ ሰመራ ወዘተ የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸው ለቀይ ባሕርና ለህንድ ውቅያኖስ ባይተዋር ሆነው መልህቃቸውን የሚጥሉበት የእኔ የሚሉት ወደብ ሳይኖራቸው ዓለምን እያካለሉ ይኖራሉ።

ዓለም ሁሌም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ በማህበራዊ እና በሌሎችም ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ውስጥ ስለምታልፍ የነበረውን መልኳን ይዛ አትቀጥልም። ትናንት የነበረው ዛሬ የለም፤ ዛሬ የነበረውም ነገ አይኖርም፤ ኢትዮጵያም ትናንት የነበራትን የባህር በር ያጣቸው ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች በአንዱ ነው። ዛሬ ያጣችውን የባህር በርም እየተሻሻለ በሚሄደው የዓለም የትብብርና የዲፕሎማሲ መንፈስ ነገ ልታገኘው ትችላለች።

ኢትዮጵያ ዛሬ የሕዝብ ቁጥሯ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል፤ ዓለምአቀፍ ግንኙነቷ አድጓል፣ የወጪ ገቢ ንግዷም ተስፋፍቷል። የትብብርና የሰጥቶ መቀበል ፖሊሲን በማራመድ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቷን የሚያረጋግጥላትን ስትራቴጂ ከወቅቱ ጋር እያጣጣመችና እያዘመነች የምትሄድ ሀገርም ሆናለች።

በዚህ የትብብር መንፈስ ለጎረቤቶቿ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞቿን በረከት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ከማቋደስ አልፋ የኤሌክትሪክ ሃይል እያመረተች እንዲጠቀሙም አድርጋለች። በንግድ፣ በትራንስፖርት፣ በሰላምና እና በሌሎች ጉዳዮች በትብብር ትሠራለች።

በአራቱም ማዕዘኖች የጎረቤት ሀገር ስደተኞች ቢመጡባት ፊቷን ሳታዞር እጇን ዘርግታ በመቀበል አስፈላጊውን ዓለምአቀፍ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግም ትታወቃለች። ለዚህ ደግሞ ከሱማሊያ ፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከሱዳን ፣ ከኤርትራ ሌላው ቀርቶ ከየመን እና ከሶሪያ መጥተው በኢትዮጵያ ከተጠለሉ ስደተኞች በላይ እማኝ ሊሆን የሚችል የለም።

ስደተኞችን መቀበል ዓለምአቀፍ ሕግ ቢሆንም አንዳንድ ሀገራት ግን የሚደርስባቸውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው ጫና በመፍራት ድንበራቸውን ዘግተው እንደሚቀመጡ አይተናል። ኢትዮጵያ ግን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆናም ቢሆን በሯን የዘጋችበት ሁኔታ የለም። ይህ የሚያሳየን የቀጣናው ችግር የእኔም ችግር ነው በሚል ትብብርና መረዳዳትን ስለምታስቀድም ነው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የልዩ ልዩ ሀገር ስደተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ተመዝግበው ተጠልለዋል። እ.አ.አ ሀምሌ 2023 የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መረጃ ብቻ ብንመለከት እንኳን ብዛታቸው 165ሺህ የሚገመቱ ኤርትራውያን ስደተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ። የሌሎች ጎረቤት ሀገራትም በተመሳሳይ እንደየ ደረጃቸው ብዛት ያላቸው ስደተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛሉ። ይህ የሚያመለክተው ቀጣናው ላይ ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ስደተኞችም ኢትዮጵያን ልክ እንደ ሀገራቸው ቆጥረው እንዲጠለሉ በሆደ ሰፊነት በሯን ክፍት ማድረጓን ነው።

ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ ለጎረቤቶቿ፤ ጎረቤቶቿም ለኢትዮጵያ አንዳቸው ለአንዳቸው የሚያደርጉት ድጋፍና የሚረዳዱባቸው ጉዳዮች እንዳላቸው ነው። በመሆኑም የኢትዮጵያ በር በችግር ጊዜ ለጎረቤቶቿ ክፍት ከሆነ በሰላማዊና በትብብር መንፈስ እነርሱም የባህር በር የምናገኝበትን ቀናና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የመፈለግ የሞራል ግዴታ ይኖርባቸዋል የሚል እምነት አለኝ።

ኢትዮጵያ አሁን በዲፕሎማሲያዊና ሕግን በተከተለ መንገድ እያሳየች ያለችው የባሕር በር ፍላጎት አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል። ሁሉም ጎረቤት ሀገሮች በትብብር መንፈስ ቢሠሩ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ከመቅረፍ አልፈው ለሕዝቦቻቸው የሚተርፍ በረከትን ማውረድ ይችላሉ። ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ለማሳካት ከየትኛውም ጎረቤት ሀገር ጋር በትብብር በመሥራት የሕዝቦቿን አኗኗር ማሻሻልና እድገቷን ማረጋገጥ የምንጊዜም ሕልሟ እንደሆነ ደጋግማ መናገሯም ለዚህ ነው።

ይህ የትብብርና ተደጋግፎ የመጓዝ አስተሳሰብ ቢጠናከር የቀጣናውን ሀገራት እድገት ማፋጠኑ የማይቀር ነው። ለምሳሌ በአንድ ሀገር ተትረፍርፎ ያለና ጥቅም ሳይሰጥ የተቀመጠ ሀብት የሌሎች ሀገራትን አድገት ለማስወንጨፍ ጉልበት ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር በይዞታቸው ስር ሆነው እምብዛም አገልግሎት የማይሰጡ የባህር በር አማራጮች ላይ ኢትዮጵያ ወደብ የመገንባት እድል ብታገኝ በኢኮኖሚያዊ እድገቷ ላይ ከፍ ያለ ትርጉም ያመጣል። ኢትዮጵያ ከምታመርተው መጠነ ሰፊ የኤሌልክትሪክ ሃይል ወይም ከሌሎች ሀብቶቿ ደግሞ ጎረቤቶቿን ተቋዳሽ የሚያደርጉ ስምምነቶች ቢደረጉ የቀጣናው እድገት ይፋጠናል።

ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን የሚያስገድዷት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ መምጣታቸው አይቀርም። ለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ጂኦፖለቲክሱ ምን ይመስላል? ወደፊት በቀጣናው ምን አይነት ፍላጎቶች ጎልተው ሊወጡ ይችላሉ? የሚለውን አስቀድሞ በማሰብ መፍትሄ ማፈላለግ የመሪዎችን አርቆ አሳቢነት የሚጠይቅ ነው። አጠገባቸው ግጦሽ እያለ በረሃብ እንዲሞቱ በበጎቹ ላይ የሚፈርድ እረኛ ቢኖር እንኳ በጎቹ ከምንሞት ብለው ወደ መስኩ ለመሰማራት ትግል ማድረጋቸው የማይቀር መሆንኑ ማሰቡም አይከፋም።

ኢትዮጵያ ለምን የባሕር በር ፍላጎት አሳየች በሚል ሸሚዝ መሰብሰብ ፣ ትከሻ እንለካካ ማለት ግን ትርጉም አይኖረውም፤ የሠለጠነ አካሄድም አይደለም። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ዓለም እየተከተለ ያለውን የሥልጣኔ ፣ የትብብር እና የዲፕሎማሲ መንገድ ካለመረዳት የመጣ ስለሚሆን ቆም ብሎ በማሰብ አረማመድን ማስተካል ያስፈልጋል።

ዋናው ጉዳያችን ወደብና ዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጦች ጥብቅ ትስስር ያላቸው ስለመሆኑ እና ዓለም አቀፋዊና ቀጣናዊ እድገትን ለማረጋገጥ ወደብ አይነተኛ ሚና ከሚጫወቱ መሠረተ ልማቶች ግንባር ቀደም መሆኑን መረዳቱ ላይ ነው።

ወደብ ለአንድ ሀገር ብቻ ይጠቅማል ተብሎ የሚገነባ ሳይሆን በአቅራቢያው ያሉ ሀገራትን እልፍ ሲልም የዓለም ሀገራትን የንግድ ልውውጥ እንዲያደላድል ታስቦ የሚገነባ ነው። ፍላጎትና አቅርቦትን በማጣጣም በዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ሀገራት የባህር ላይ ትራንስፖርትን ተጠቅመው በተለይም የንግድ ግንኙታቸውን የሚያቀላጥፉበት ማዕከል እንደመሆኑ የብዙዎችን እንጂ የአንድን ሀገር ተጠቃሚነት ብቻ የሚያረጋገጥ ሊሆንም አይችልም።

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት አብዛኛዎቹ ሀገራት ወጪና ገቢ ንግዳቸውን የሚያጓጉዙት በባህር ትራንስፖርት ነው። ለዚህም ምክንያቱ የባህር ትራንስፖርት ለምሳሌ ከአውሮፕላን ትራንስፖርት ጋር ሲነጻጸር ዋጋው ስለሚቀንስና በአንድ ጊዜ ከፍተኛ ቶን ጭነትን ማጓጓዝ ስለሚያስችልም ነው።

የወደብ መሠረተ ልማት ያላቸው እና በወደብ ኮሪደር አቅራቢያ የሚገኙ ሀገራት ከፍተኛ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀስባቸው ናቸው። ለቴክኖሎጂዎችም ቀድመው ተደራሽ ስለሚሆኑ እድገታቸው ፈጣን ነው። ዛሬ በዓለም ላይ በሥልጣኔ ፣ በኢንዱስትሪ ወይም በሥነ ህንጻ ውበታቸው ከሌሎች ልቀው ከሚገኙት ግንባር ቀደም ከተሞች ውስጥ አብዛኛዎቹ በባሕር ዳርቻ የተከተሙና የባህር በር ያላቸው ናቸው።

ኢትዮጵያ ዛሬ ‹‹ሳይተርፋት አበደረች- ሳትቀበል ሞተች›› እንዲሉ በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት የባሕር በሯን ሰጥታ ለከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ተዳርጋለች። በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የእኔ ናቸው ብላ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በማፍስስ አስፋፍታ ስትጠቀምባቸው የነበሩ ወደቦቿን አጥታለች።

ኢትዮጵያ በወደብ የመጠቀም ታሪክ ያላት ሀገር ብቻ ሳትሆን ከቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኝ እንደመሆኗ የወደብ ባለቤት የመሆን ተፈጥሯዊ መብት ያላትም ነች። ከአውሮፓና ከኤዢያ በብዙ ማይልስ ርቀው የሚገኙ አንዳንድ ሀገራት ቀይባሕር ላይ የጦር መርከቦቻቸውን የሚያዙበት ወደብ ሲኖራቸው ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ግብይት ለማድረግ የሚረዳት ወደብ አይኑራት ማለት ፍትሐዊ ሊሆን አይችልም፤ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነትም አይኖረውም።

ዛሬ በውቅያኖሶች ክፈፍ ላይ የተቀመጡ ጥቂት ሀገራት ትንሽ ቁጥር ይዘው ከጀርባቸው ላለው ለብዙኋኑ ሕዝብ ጀርባችንን ሰጥተን እንቀመጥ ቢሉ ዓለምአቀፍ ሕግም ፤ የተፈጥሮ ሕግም የሚፈቅድላቸው አይሆንም። ከሕዝብ ቁጥር መጨመርና ከፍላጎት ማደግ ጋር ተያይዞ እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ ቀጣይነት ይኖራል ተብሎም አይታሰብም።

ስለዚህ ወደብ ለ120 ሚሊዮን ሕዝቦች ቅንጦት ሳይሆን ሕይወት በመሆኑ የኢትዮጵያን የወደብ ፍላጎት በዲፕሎማሲ ፣ በትብብር መንፈስና በሠለጠነ መንገድ ማስተናገድ የነገውን ተደጋገፎ መጓዝ የተቃና ያደርገዋል እንጂ ማንንም ተጎጂ አያደርግም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ወደብ እንጂ ወጀብ እንዳልፈለገች ጎረቤቶቻችን በቅጡ ተረድተው የቀረቡትን የሰጥቶ መቀበል አማራጮች በመጠቀም በጋራ መልማትን መርሀቸው አድርገው ሁሉንም አትራፊ የሚያደርጉ ተራማጅ አስተሳሰቦችን ለመቀበል መዘጋጀት ይኖርባቸዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You