• በዝናብ የሚፈጠሩ አደጋዎችን ለመከላከል በቂ ዝግጅት ተደርጓል፤
አዲስ አበባ፡– የከተማዋ መንገዶች የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና የትራፊክ እንቅስቃሴውን የተሳለጠ ለማድረግ ባለፉት አስር ወራት ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የተለያዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች መሰራታቸውን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። በዝናብና ጎርፍ ምክንያት ሊፈጠሩ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል በቂ ዝግጅት መደረጉንም ገልጿል።
የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት የመዲናዋ መንገዶች ከተጨማሪ ብልሽት እንዲድኑና በወቅቱ ተጠግነው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በበጀት ዓመቱ 800 ሚሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ ይገኛል። የከተማዋ የህዝብ ቁጥር በየጊዜው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የትራፊክ እንቅስቃሴውም እየጨመረ በመሆኑ ባለስልጣኑ ለመንገዶች ጥገናትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ በተያዘው የበጀት ዓመትም በተለያዩ የመንገድ ጥገና ዘርፎች ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። በዚህም ጊዜ 450 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራ ለመስራት ታቅዶ ወደ ስራ የተገባ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን የተለያዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ ለመስራት ከተፈለገው የመንገድ ጥገና ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 102 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአስፋልት፣ 50 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣ 22 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ጥገና መከናወኑን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንደዚሁም 327 በሚሆኑ የተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ከ90 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን ቀላል፣ 300 አካባቢዎች ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን መካከለኛና በ46 ቦታዎች ስድስት ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ ከፍተኛ የውሃ ማፋሰሻ የመንገድ ጥገናዎች ተከናውነዋል። በመሆኑም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በድምሩ ከ400 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍኑ የመዲናዋ መንገዶች ጥገና ተደርጎላቸዋል።
በክረምት ወራት በዝናብና በጎርፍ ምክንያት የሚፈጠረውን ተፅዕኖ ለመቀነስና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ገልፀዋል። በዚህ ረገድ ባለስልጣኑ በማፋሰሻ ዘርፍ ያከናወናቸው የመንገድ ጥገና ሥራዎች በክረምት ወቅት ሊከሰት የሚችሉትን የጎርፍና ተያያዥ አደጋዎች ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው መሆኑን አመላክተዋል።
ህብረተሰቡ በአካባቢው ለጎርፍ አደጋ የሚያጋልጡ አደጋዎች መኖራቸውን በሚመለከትበት ወቅት ፈጥኖ ለባለስልጣኑ ማሳወቅ የሚችልበትና ችግሩ ከመከሰቱ በፊት አስቀድሞ መከላከል የሚቻልበት የአሰራር ሥርዓትም ተዘርግቷል። 8267 ነጻ የስልክ መስመር መዘጋጀቱን አስታውቀዋል። ከመንገድ ጥገና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በሚመለከት ባለስልጣኑ 24 ሰዓት የሚሰራበት ሁኔታ መኖሩንም አስገንዝበዋል።
በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ግንቦት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ለመንገዶች ጥገና የበጀት እጥረት ለጥራት መጓደል ችግር ሆኗል›› በሚል የተዘገበው የተሳሳተ መሆኑንና ባለስልጣኑ ምንም ዓይነት የመንገድ ጥገና የበጀት እጥረት የሌለበት መሆኑን የኮሙዩኒኬሽን ዳሬክተሩ አስታውቀው በወቅቱ ይህን መረጃ የሰጠው ኃላፊ የአንድ ሎት ስራ አስኪያጅ በመሆኑ ባለስልጣኑን ወክሎ መናገር የማይችል በመሆኑ በዚህ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
ይበል ካሳ