አዲስ አበባ፡– የኢፌዴሪ መንግሥት የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ መስራች ዶክተር ካትሪን ሐምሊን በኢትዮጵያ ባለፉት 60 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ሽልማት አበረከተ፤ በስማቸው የቆመው ሐውልትም ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ትናንት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ የካትሪን ሐምሊን ሐውልትን በመረቁበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ዶክተር ካትሪን ከእኔ ዘር ውጪ አላይምየሚል አመለካከት በበዛበት በአሁኑ ወቅት ከዘር፣ ከቀለም፣ ከጾታ በላይ ሰውነትንና ሰውን ማዳን ያሳዩ እናት ናቸው። ህዝቡ ከእርሳቸው ተግባር መማር ይገባዋል፤ ‹እኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ባለሥልጣናትም እንደዚህ ዘመን የማይሽረው ለትውልድ የሚጠቅም አሻራ ለማስቀመጥ መስራት ይጠበቅብናል› ሲሉም ተናግረዋል።
ዶክተር ካትሪን ‹‹እ.አ.አ ከ1959 ዓ.ም ጀምሮ ላለፉት ስልሳ ዓመታት ከስልሳ ሺ በላይ እናቶችንና ሴቶችን መታደግ ችለዋል። ይህ ደግሞ ‹ስልሳ ሺ ተገሎ በሚጨፈርበት ሀገር ስልሳ ሺ ያዳኑ የድሀ እናት› የሚያስብላቸው መልካም ስራቸው ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢፌዴሪ መንግሥት ያዘጋጀላቸውን የወርቅ ሀብል ሽልማት ለዶክተር ካትሪን አበርክተውላቸዋል።
የሐምሊን ፊስቱላ ኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም በዶክተር ካትሪን ሀምሊንና በባለቤታቸው ዶክተር ሬጅናልድ ሐምሊን የተመሰረተና ነፃ ህክምና የሚሰጥ ሲሆን፣ በባህርዳር፤ በመቀሌ፤ በይርጋለም፤ በሐረርና በመቱ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ አራት ሺ ህሙማን ህክምናውን እያገኙ ቢሆንም 39 ሺ የሚደርሱ እናቶችና ሴቶች በፌስቱላ የጤና ችግር ውስጥ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትር ያካሄደው ግምታዊ ጥናት ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ