‹‹ አመራሮችን ጨምሮ 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል››
– የወረዳው መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን
አዲስ አበባ፡– ‹‹በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በዘላቂነት ለመፍታት ሕዝብን ከሕዝብ እያሥታረቅን ባለንበት ወቅት አንዳንድ ለውጡን ያልተቀበሉና ሠላም የማይፈልጉ አመራሮች ፈተና ሆነውብናል›› ሲሉ በመተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ከሚገኙ 29 ቀበሌዎች የተመረጡ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡
በዞኑ ባሉ የተለያዩ ወረዳና ቀበሌዎች ተፈጥሮ የነበረው ግጭት አሁን ወደ ሰላም እየተመለሰ ይገኛል፤ ለዚህም በየአካባቢው የተመረጡ አባቶች ከማህበረሰቡ ጋር የሚያደርጉት ውይይት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የሀገር ሽማግሌዎቹ ይናገራሉ፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚኖሩት የአገር ሽማግሌ አቶ በሪሁን አንዳርጌ እንደገለጹት፤ የክልል እና የፌዴራል የሰላም ሚኒስቴር አካላትም ማህበረሰቡን በማወያየት በኩል የጀመሩት ተግባር በጎ ነው፡፡ ውይይቱ እስከ ቀበሌ ድረስ በመዝለቅ ሕብረተሰቡን በማወያየት የበለጠ ሰላም እንዲሰፍን የላቀ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
አያይዘውም መንግሥት የጀመረው አጥፊዎችን በተዋረድ ለሕግ እንዲቀርቡ የማድረግ ሥራ በማህበረሰቡ ዘንድ የሚያስደስትና የሕግ የበላይነት እንዲከበር የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የወረዳ አመራሮች የሚደረገውን የሰላም ጥረት ጥላሸት በመቀባትና ባለመደገፍ የሚያሳዩት ያልተገባ ባህሪ መታረም እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ማንቡክ ወረዳ ዙሪያ በለስ ቁጥር ሁለት ቀበሌ ነዋሪው አቶ መላክ ታደለ እንደተናገሩት ችግሩን ለመቅረፍ በአንዳንድ የዳንጉር ወረዳ አመራሮች በኩል የሚስተዋለው ቁርጠኝነት አናሳ ነው፡፡ ይህ የሚጀምረው ደግሞ ችግሩ ሲፈጠር ጀምሮ የሰው ሕይወትና ንብረት ሳይጠፋ እዚያው አጥፊውን ተጠያቂ ማድረግ ይቻል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የአገር ሽማግሌዎች አንጃ ኩያ ፣ቆታ፣ አይሲካ፣ ሕይወትና ንብረት ሳይጠፋ እዚያው አጥፊውን ተጠያቂ ማድረግ ይቻል እንደነበር ተናግረዋል።
የአገር ሽማግሌዎች አንጃ ኩያ፣ ቆታ፣ አይሲካ፣ ደንገዝ፣ ጉብላክ፣ ድልሳምቤ፣ ዳበኮከል፣ ጆንቲያ፣ ግሂጺ፣ አዛርቲኪቲሊ፣ አሊፑዋፑዋ፣ 01፣02፣ ቁጥር ሁለት፣ ማንቡክና ኪትሊ፣ ግልባንጂ፣ ድልንቹኪ፣ ጊዝር በተሰኙ በዳንጉር ወረዳ ሥር በሚገኙ ቀበሌዎችና ሰፈሮች ተዘዋውረው በጉሙዝ ማህበረሰብና በሌሎች መካከል ቂምና በቀል እንዳይኖርና ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ማስታረቃቸውን አቶ መላክ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ጥቅሙ የተነካበት አንዳንድ የወረዳ አመራር የሽማግሌዎችን ጥረት እየደገፋቸው አለመሆኑን ገልጸዋል።
በዳንጉር ወረዳ ቦሪንጋ ሥላሴ ነዋሪ አቶ ማንደፍሮ ቆለጭ እንደሚሉት፤ በሕዝቡ መካከል ምንም ችግር የለም። ችግሩ ያለው መደመርን ባልሆነ መንገድ በተረዱና ጥቅማቸው በተነካባቸው ጥቂት አመራሮች ነው ብለዋል። ስለዚህ መንግሥት አሁን ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ማቅረብ በመጀመሩ በቀጣይ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በማንቡክ ወረዳ 2 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሙሐመድ ሐሰን በበኩላቸው የተፈጠሩት ችግሮችና በጃዊ የንጹሐን የጉሙዝ ህጻናት ጭምር ደም መፍሰስ አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት አሁን የጀመረውን የሕግ የበላይነትን ማስከበር አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ተናግረዋል።
እንደ አቶ ሙሐመድ ገለፃ ከታች እስከ ላይ ድረስ መጠየቅ የሚገባቸው ብዙ አካላት አሉ። መንግሥት አሁን በጀመረው መንገድ ማህበረሰቡን እያሳተፈ ለጥቂት ጊዜ እንኳን ቢቀጥል አካባቢው ሙሉ በሙሉ ወደ ሰላም እንደሚመለስ ሙሉ እምነት እንዳላቸው አስቀምጠዋል። የተፈናቀሉትም ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ወደ እርሻቸው መሰማራት እንዲችሉ ጎን ለጎን ተጠናክሮ መሰራት አለበት።
‹‹እኛ የአገር ሽማግሌዎችም ወጣቶችን፣ ሴቶችን እና አጠቃላይ ማህበረሰቡን እየመከርን፣ እያስታረቅን አንድ ሁነን አብረን እንደ በፊቱ በሰላም መኖር እንድንችል ማድረግ ካልቻልን ከታሪክ ተወቃሽነት አንድንም። ግጭቱን የሕዝብ ያስመሰሉት ያለተንኮል እንጀራ የሌላቸው ጥቂት መሰሪዎች ናቸው፤›› ብለዋል።
የማንቡክ ቀበሌ 02 ነዋሪው አቶ ተላይነህ ገበየሁ በበኩላቸው በሕብረተሰቡ መካከል ሆን ብለው ችግሮች የሚነዙትን ከመንግሥት ጋር በጋራ መከላከል ይኖርብናል። የተጀመረው ሰላም የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዲችል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ጥረት ማድረግ እንደሚገባው ተናግረዋል።
የዳንጉር ወረዳ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽንና ባህል ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ዋና የሥራ ሂደት ቡድን መሪ አቶ ሰይድ ኡመር እንደገለጹት፤ የፌዴራልና የክልል ባለሥልጣናት ተገኝተው በሕዝቡ መካከል ችግሮች እንዲፈጠሩ የሚያደርጉ አንዳንድ አመራሮች መኖራቸውን ገልጸው በዚህም እስከ አሁን በዳንጉር ወረዳ አመራሮችን ጨምሮ 33 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ጠቁመዋል።
በመተከል ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ችግር ወደነበረበት ሰላም ሙሉ በሙሉ ለመመለስ የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው እየሰሩ ነው ያሉት አቶ ሰይድ የአገር ሽማግሌዎች ከዚህ በፊትም አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ ግጭቶችን ሲፈቱ ቆይተዋል። አሁንም የሰላም ኮሚቴ ጭምር ተዋቅሮ እርቀ ሰላም እንዲፈጠር በተለይም ደግሞ የተፈጠረውን ችግር ብሔር ተኮር ለማስመሰል የሚደረጉ የተንኮል ሴራዎች በመስተዋላቸው እነዚህን ቀርፎ ወደ ማህበረሰቡ በአንድነት መኖር እንዲቻል እየተሰራ ነው።
በየቀበሌው የአገር ሽማግሌዎች ተመርጠው እንደ ወረዳ 29ኙም ቀበሌዎች የተሳተፉበት እና አጎራባች ከፓዊ ወረዳ ወደ 6 ቀበሌዎች ከ400 በላይ የአገር ሽማግሌዎች፣ የወጣቶችና የሴቶች ተወካዮች እና የሐይማኖት አባቶች የተሳተፉበት የሰላም ውይይት ተደርጓል። በዚህም ሰፊ መተማመንና መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።
በክልሉ ጸጥታ ምክር ቤት ኮማንድ ፖስት አማካኝነት አዋጅ ታውጇል። ከዚህ በኋላ ከሕዝቡ በሚደርስ ጥቆማ በወንጀሉ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ አካላትን በቅንጅት ወደ ሕግ የማቅረብ ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረግ ተችሏል ብለዋል። በዘረፋና በነፍስ ግድያ የተጠረጠሩ አካላትም የሚገኙ ሲሆን በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል 13 በግድያና ዝርፊያ፣ 10 ተጠርጣሪዎች ደግሞ በምርመራ መለየታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 22/2011
ሙሐመድ ሁሴን