ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት በቱሪዝም ዘርፍ በርካታ ለውጦች እያስመዘገበች ስለመሆኗ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተለይ በመዳረሻ ልማት እየተመዘገበ ያለው ውጤት የሀገሪቱን ቱሪዝም አንድ እርምጃ ወደፊት የሚያራምድ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎችም ያረጋግጣሉ።
መንግሥት ቱሪዝምን ትኩረት ሰጥቶ ከሚሠራባቸው አምስት የምጣኔ ሀብት ዘርፎች መካከል አንዱ አድርጎታል። ሕጎችን በማሻሻል፣ የቴክኖሎጂና የገበያ ትውውቅ ሥራውን በዲጂታል አማራጭ በመደገፍ የታሰበው ውጤት እንዲመጣ እየተሠራ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጥ ይሰማል።
የቱሪዝም ዘርፍ በመንግሥት ብቻ የሚዘወር አይደለም። የግሉ ዘርፍ ለቱሪዝም እድገት ቁልፍ ከሚባሉ ባለድርሻዎች ውስጥ አንዱ ነው። መንግሥትም ይህንን በማመን በቱሪዝም ኢንቨስትመንት፣ በገበያና ማስታወቂያ እንዲሁም በልዩ ልዩ ንዑስ ዘርፎች ውስጥ የግሉ ዘርፍ የራሱን ሚና እንዲጫወት ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል።
ቱር ኦፕሬተሮች፣ አስጎብኚ ድርጅቶችና ግለሰቦች፣ ሆቴሎች፣ የቱሪዝም ምርት አቅራቢዎችና ሌሎችም ተቋማት የቱሪዝም የጀርባ አጥንት ተደርገው ከሚወሰዱት ውስጥ በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ይሰለፋሉ። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥም እነዚህ አካላት በቱሪዝም እድገት ላይ ጉልህ ሊባል የሚችል ድርሻን ወስደው ውጤት ማምጣት ችለዋል። ሆቴሎች የሆስፒታሊቲ፣ ኮንፍረንስና ማበረታቻዎችን በማላቅ፤ ቱር ኦፕሬተሮች ጉዞዎችን በማሰናዳት፣ አስጎብኚዎች የኢትዮጵያን ባሕላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ልዩ ልዩ መስሕቦችን በማስጎብኘት፣ ሁሉም የድርሻቸውን ጠጠር በመጣል ለዘርፉ እድገት ማሳየት አስተዋፅዖ አላቸው።
የቱሪዝም የግሉ ዘርፍ አንቀሳቃሾች በቀዳሚነት ከሚሳተፉበት ሙያዊ ተግባር ባሻገር ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ እና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር በማድረግ ድርሻ አላቸው። የዘርፉ ልዩ ልዩ ማኅበራት በጋራ በመሆን ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይዎች፣ ኮንፍረንሶችና መሰል መድረኮች ላይ ከቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን ይሳተፋሉ። በጥቅሉ በሀገራችን 10 በመቶ የሚሆነውን የሥራ እድል የመፍጠር አቅም ባለው የቱሪዝም ዘርፍ ላይ የግሉ ዘርፍ ቁልፍ ድርሻ እንዳለው ይታመናል።
ወጣት ፀጋአብ ጌታቸው ይባላል። የሰኒ ላንድ ኢትዮጵያ አስጎብኚ ድርጅት ባለቤት ነው። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የውጪና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የመስሕብ ሀብቶችን በአዲስ መንገድና እንቅስቃሴ እንዲጎበኙ ያመቻቻል። በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የታሪክ፣ ቅርስ፣ ባሕል፣ ተፈጥሮና መሰል መስሕቦች እንዲጎበኙ እንደሚያመቻች ይገልጻል። በዚህ እንቅስቃሴውም ኢትዮጵያ የውጪ ምንዛሪ እንድታገኝ እና በጎ ገፅታ እንድትገነባ በግሉ ዘርፍ ውስጥ ተዋናይ በመሆን እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የወጣት ፀጋአብ ድርጅት ሰኒ ላንድ ከሌሎች አስጎብኚ ድርጅቶች ለየት ይላል፤ የሳይክል ጉዞ (ባይክ ቱሪዝም) በማስተዋወቅና በዚያም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ስፍራዎች ቱሪስቶች እንዲጎበኙ በማድረጉ የተለየ መሆን የቻለው። ይህ ዘርፍ ብዙም በኢትዮጵያ ያልተለመደና በጎብኚዎች ግን ተወዳጅ እንቅስቃሴ መሆኑን ወጣት ፀጋአብ፣ በዚህም ድርጅቱ ጎብኚዎች አዳዲስ ልምዶችንና የጉብኝት ባሕሎችን እንዲለምዱ ከማድረግም ባሻገር ከተለመደው የኢትዮጵያ የጉብኝት ባሕል በመውጣት ዘርፉን የሚያሳድግ ልምድ እንዲዳብር እየሠራ መሆኑን ይናገራል።
በብስክሌት ጉዞ የሚደረግ ጉብኝት ለቱሪስቱ ጤና ጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ ከተፈጥሮ ጋር የሚስማማ መሆኑን ወጣት ፀጋአብ ይጠቁማል። እሱ እንዳለው፤ በብስክሌት ጉብኝት የሚያደርጉ ቱሪስቶች ከኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ጋር በቅርበት እንዲገናኙ፣ ንፁሕ አየር እንዲያገኙ፣ ከሌሎች ጎብኚዎች ጋር እንዲገናኙና አዝናኝ ጭውውት እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል:: ድርጅቱ ከተለመደው የመኪናና የአየር የጉብኝት ባሕል በተጨማሪ በባለ ሁለት እግር ብስክሌት ኢትዮጵያን መጎብኘት እንደሚቻል ለሀገር ውስጥም ሆነ ለኢንተርናሽናል ቱሪስቱ ለማስተዋወቅ እየሠራ ነው:: በዚህም መንግሥት ዘርፉ ያለውን አማራጭ ለማስፋት የሚያደርገውን እቅድ ያግዛል።
በዓለም ላይ የብስክሌት ቱሪዝም እየታወቀና ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱን የሚናገረው ወጣት ፀጋአብ ኢትዮጵያ ይህንን ባሕል ለማስፋትና ተጠቃሚ ለመሆን እምቅ ሀብት እንዳላት ይገልጻል። አራት ሺህ 500 ጫማ ከፍታ ካለው መልክዓ ምድር እስከ ደናክል ዲፕረሽን (የአፋር ዝቅተኛው መሬትና የዓለም ሞቃታማው መሬት) ከባሕል ጠለል በታች እስከ 130 ሜትር ድረስ ያለው ተፈጥሮ ባለቤት እንደሆነች ጠቅሶ፣ ይህን አካባቢ በብስክሌት የመጎብኘት ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ጨምሮ የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን በማሳተፍ አዲስ የቱሪዝም ባህል፣ የገቢ ምንጭና መዳረሻ ለመፍጠር ድርጅቱ እየሠራ መሆኑን ይናገራል። በዚህ ዘርፍም የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ለማገዝ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ በዓለም ላይ መልካም ገፅታ እንዲኖራትና የቱሪስት ፍሰቱም እንዲጨምር ፍላጎት እንዳለውና ይህንን ስኬታማ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ፀጋአብ፣ ዓላማው ከግብ እንዲደርስ መንግሥት በልዩ ልዩ መልኩ እገዛ እያደረገለት መሆኑን ጠቅሷል።
እሱ እንዳለው፤ የግሉ ዘርፍና መንግሥት እጅና ጓንት ሆነው የሚሠሩ ከሆነ ኢትዮጵያን በቅርብ ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ ተመራጭ ከሆኑ የቱሪስት መዳረሻዎች ከቀዳሚዎቹ ተርታ ማሰለፍ ይቻላል:: ድርጅቱ ከብስክሌት ቱሪዝም ባሻገር አዳዲስና ተመራጭ መንገዶችን ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነም ተናግሯል።
ወጣት ሕይወት መድህን አውተንቲክ የተባለ ጉዞንና የጉብኝት ዝግጅቶችን በቴክኖሎጂ የሚያመቻች ድርጅት ከጓደኞቿ ጋር በመሆን መሥርታለች። ድርጅቱ መንግሥት የኢትዮጵያን ቱሪዝም በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝና ጎብኚዎች በቀላሉ ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩ የሚረዳ መሆኑን ትናገራለች።
እሷ እንደተናገረችው፤ አውተንቲክ ጎብኚዎችን ከአስጎብኚ ድርጅቶች እና ከጉዞ አዘጋጆች ጋር በቀላሉ በዌብሳይትና በቴሌግራም (ቦት) ፕላትፎርም እንዲገናኙ ያመቻቻል:: ይህም የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች በቀላሉ የሚፈልጉትን የጉብኝት ስፍራ፣ የሚያርፉበትን ሆቴል፣ የቱሪዝም ምርት ቀላል የክፍያ አማራጮች ሳይጉላሉ በአንድ ስፍራ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። ቱሪስቱ በውስብስብ አሠራሮች፣ የክፍያ ሂደቶችና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዳይሰላች ያደርጋል።
አውተንቲክ ከርቀት ሆነው የጉብኝት ሂደታቸውን ማመቻቸት ለሚፈልጉ የውጪ ሀገርና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች ቀላል አማራጭ ይዞ መምጣቱን የምትናገረው ወጣት ሕይወት፣ በተጨማሪ ለጉዞ አዘጋጆችም እፎይታን መፍጠሩን ትናገራለች። አንድ ቱር ኦፕሬተር፣ አስጎብኚ ድርጅት በዋናነት ባዘጋጀው ጉዞና የጉብኝት ፕሮግራም ብቻ ትኩረቱን እንዲያደርግ ፕላትፎርሙ እድል እንደሚሰጥ ገልጻለች።
በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ቴክኖሎጂን ለማላመድ መንግሥት ብቻ ሳይሆን የግሉም ዘርፍ ተሳታፊ መሆን እንዳለበት የምታምነው ወጣት ሕይወት መድሕን፣ እነርሱም ይህንን ሚና ተክተው የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሆነ አመልክታለች። በአሁኑ ወቅት በሚፈለገው ልክ ቱሪዝምና ቴክኖሎጂ በቅንጅት እየተሠራበት ባይሆንም መንግሥት የወሰደው ቁርጠኝነትና እየሄደበት ያለው ርቀት ግን አበረታች ነው የምትለው ወጣት ሕይወት፣ ይህንን ጥረት የግሉ ዘርፍ ማገዝ እንዳለበት አስገንዝባለች:: የእነርሱም ድርጅት በዚህ ላይ በሙሉ ፍቃደኝነትና ፍላጎት እየሠራ መሆኑን ትገልፃለች። የኢትዮጵያ ቱሪዝም እና የመስሕብ ሀብቶች በቴክኖሎጂ ከተደገፉ የቱሪስት ፍሰቱ ከመጨመር ባሻገር ተመራጭ መዳረሻ ለመሆን ብዙ ጊዜ እንደማይፈጅም ገልፃለች።
ወጣት ምዕራፍ ታምራት በዋን ላይ ቱርና መኪና ኪራይ ድርጅት ውስጥ በማርኬቲንግና ፋይናንስ ባለሙያነት እየሠራች ትገኛለች። ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ በግሉ ዘርፍ የራሱን ድርሻ ወስዶ በአስጎብኚነትና መኪና የጉዞ መኪና ኪራይ አቅርቦት ተሰማርቶ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ትገልፃለች።
ወጣት ምዕራፍ እንዳለችው፤ ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የታሪክ፣ የባሕል፣ የተፈጥሮ እና ልዩ ልዩ የቱሪስት መስሕብ ስፍራዎችን ያስጎበኛል፤ ከዚህ በተጨማሪ በአስቸጋሪ መልክዓ ምድር ላይ ለጉዞ ምቹ የሆኑ መኪኖችን በማከራየትም የቱሪዝም ዘርፉን እያገዘ ነው። ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ አካባቢዎች ለመመልከትና ለመዝናናት በሚሹበት ወቅት በሁሉም ቋንቋ መግባባትና ማስጎብኘት የሚችሉ ባለሙያዎችን (ቱር ጋይድ) በማቅረብም ጉዞዎችን ያመቻቻል።
ድርጅቱ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ውስጥ አስፈላጊ የሚላቸውና መንግሥት በራሱ የማይደርስባቸውን አገልግሎቶች በመስጠት በአጋዥነት እንደሚሠራ ወጣት ምዕራፍ ትናገራለች። እሷ እንደምትለው፤ ከዚህ ውስጥ ቱሪስቶች ሆቴሎች በሌሉባቸው መዳረሻዎች የሚያስፈልጓቸውን የማደሪያ ድንኳኖች፣ ቁሳቁስ ከማቅረብ ባሻገር ምግብና መጠጥ በማይገኝባቸው የጉብኝት ስፍራዎች የግል ሼፎች (ምግብ አብሳይ ባለሙያዎችን) ከጎብኚዎች ጋር አብረው እንዲጓዙ በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል። ይህም ቱሪስቱ በቀላሉ እንዳይሰላችና የአገልግሎት (ሆስፒታሊቲ) ክፍተት እንዳይፈጠር ማድረግ ያስችላል።
ጉዞ አመቻቾች (ቱር ኦፕተርስ) ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ምቹ ሁኔታንም ይፈጥራል፤ አንድ ቱሪስት ቀድሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊት (አንድ ወርና ከዚያም በላይ) ቅድመ ዝግጅት ይደረጋል፤ ለእዚህም የቱሪስቱ ፍላጎት ጥናት ይሠራል። ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት፣ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምርና ኢትዮጵያ ተመራጭ እንድትሆን ለማስቻል ታቅዶ የሚሠራበት አካሄድ ነው።
ወጣት ምዕራፍ ድርጅቱ ዋን ላቭ ቱርና የመኪና ኪራይ መንግሥት የኢትዮጵያን ቱሪዝም በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማነቃቃት የነደፈውን ስትራቴጂ ለማሳካት በአጋርነት እንደሚሠራ ትናገራለች። በተለይ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ሀገራቸውን የመጎብኘት ባሕላቸው ደካማ እንደሆነ በመግለፅ ይህንን ልምድ ለመስበር እየሠራ መሆኑን ትገልፃለች።
እንደ መውጫ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት በኩል ዘርፉን ለማልማት እየተሠራ ነው:: መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትኩረት ከሰጣቸው የምጣኔ ሀብት ዘርፎች መካከል የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ ነው:: ባለፉት ዓመታት በቱሪዝሙ ዘርፍ በቱሪዝም መሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ሀሳብ አመንጪነት በርካታ ፕሮጀክቶች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል፤ ሌሎች ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ ይገኛሉ:: ይህን ተከትሎም ለውጦች እየተመዘገቡ ናቸው::
የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ከገጠመው መቀዛቀዝ ለማውጣትና ዘርፉ እንዲነቃቃ እና የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት ለማድረግ የአስር ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እየተተገበረ ይገኛል:: እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ በቁልፍ አጋርነትና ባለድርሻነት ከተለዩት መካከል ደግሞ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን ቀዳሚዎቹ ናቸው። ለእቅዱ ተግባራዊነትና ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እድገት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ያነጋገርናቸው እነዚህ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን አረጋግጠዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 2016 ዓ.ም