ጥርስ ከማኘክና ከመካነ ድምጽነት ዋና ሚናው ባሻገር የውበት መገለጫም ነው፡፡ የጥርስ ደህንነት መጓደል መንታ ጉዳት ያስከትላል የሚባለውም ጥርስ ጤናም ውበትም ስለሆነ ነው። እንደዛሬው የጥርስ ክትትልና ሕክምና ማዕከሎች ከመስፋፋታቸው በፊት ሰዎች የተለያዩ ባህላዊ የጥርስ አጠባበቅ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል። እንደ ንቅሳት፣ ከሰል፣ መፋቂያ፣ ጨውና የመሳሰሉት ከጥርስ መጠበቂያ ዘዴዎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ጥርስ የውበት መገለጫ ስለመሆኑ በርካታ የሀገራችን ድምጻውያንና ባለቅኔዎች ከጥንት ጀምሮ ሲቀኙለት ኖረዋል፡፡ ለአብነትም- ‹‹ጥርሴማ ወዳጅሽ ያላንቺ አልስቅ አለ››፣ ‹‹ እርሷ ቆንጆ ጥርሷ የሚያምር- ያዘኝ ፍቅር››፣ ‹‹ያቺ ቆንጆ ጥርሰ በረዶናት-ውብ ዓይናማ ናት››፣ ‹‹ፍንጭቷ- ነው ምልክቷ›› የሚሉትን ስንኞችና ሐረጎች ማስታወስ ይቻላል፡፡ ዛሬ ደግሞ የጥርስ ጤንነት በዓለማችን ጥልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሆኗል፡፡ የተለያዩ የጥርስ ሕክምና መስጫ መሳሪያዎችም በየጊዜው እየዘመኑ መጥተው ለዚሁ ተግባር እየዋሉ ይገኛሉ፡፡
የሰው ልጅ የእድገት ደረጃውን ሲጨርስ 32 የሚሆኑ የተለያየ ተፈጥሯዊ ባህሪ ያላቸው ጥርሶች እንደሚኖሩት ሳይንስ ይናገራል፡፡ እነዚህም ጥርሶች በተለያዩ ቅርጾችና መጠን ተግባራቸውን ለማከናወን አብረው የሚሠሩና የተለያዩ ንብርብሮች ያሏቸው ናቸው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዲያ በከፍተኛ ሁኔታ የጥርስ ሕመም ችግር እየተስፋፋ እንደሚገኝ ይነገራል፡፡ የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ መሠረት በዓለም ላይ ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ የጥርስ ጤና ችግር አለበት፡፡ ከዚህ ቁጥር ውስጥ ከአራት ሰው ሶስቱ የሚገኙት በታዳጊ ሀገር መሆኑ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡
እንዲሁ ሲታዩ ጥርሶች ቀላልና ያልተወሳሰቡ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን በቅርበት ሲመረመሩ የተለያዩ ንብርብሮች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ጥርስ ‹‹ኢናሜል፤ ዲንቲን፤ ፐልፕ እና ሲሜንቲን›› የተሰኙ ድርብርቦሽ አሉት፡፡ የጥርስ ጤንነት እና ደህንነት መጠበቅ ከማኘክ እና ከመናገር በዘለለ ለሰው ልጆች ትልቅ ውበትን የሚያጎናጽፍ በመሆኑ ደህንነቱ የተጠበቀ ጥርስ በራስ መተማመንን ይጨምራል፡፡ ለዚህም ነው በርካታ ሰዎች ጥርሶቻቸውን የሚያሳጥቡት፣ የሚያስሞሉትና የጥርስ ብሬስ የሚያደርጉት። የዛሬው የአዲስ ዘመን የማህደረ ጤና አምድም በብሬስ የጥርስ ደህንነትና አጠባበቅ ላይ ያተኩራል።
ዶክተር ዳንኤል ሹካሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ሕክምና ትምህርት ቤት የጥርስ ሕክምና ማዕከል ኃላፊና የትምህርት ክፍሉ ተጠሪ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፣ ጥርስ የሚገኘው የመንጋጋ አጥንት ውስጥ ሲሆን ከመንጋጋ ወደ ጭንቅላት ከሚሄድ ነርቭ ጋር ይገናኛል፡፡ አንድ ጥርስ ለብቻው ነርቭ፣ የደም ስር እና ከላይ ከሚገኘው ጠንካራ ክፍል የተዋቀረ ነው፡፡
ጥርስ የተሠራው ከካልሺየምና ካልሺየም ካለባቸው ንጥረ ነገሮች ነው፡፡ አፍ ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኙ ባክቴሪያዎች ምግብ ከተበላ በኋላ አፍና ጥርስ የማይፀዳ ከሆነ በፈርመንቴሽን ወደ አሲድነት ይቀይረዋል፡፡ ይህም የጥርስን ጠንካራ ክፍል ይበላዋል፤ ለጥርስ መቦርቦርም መንስዔ ይሆናል፡፡
የጥርስ ሐኪሙ ዶክተር ኢዮኤል ገብሬ በበኩላቸው እንደሚናገሩት ጥርስ ከተቦረቦረ በኋላ ውስጠኛው ክፍል ላይ ነርቭ ስላለ በቅዝቃዜ ወቅት ሲታኘክበት ሕመም ይፈጥራል፡፡ ዳቦ፤ መኮረኒ እና ፓስታ የመሳሰሉ ካርቦሃይድሬት ያለባቸው ምግቦችን ከተመገቡ በኋላ ጥርስ የማይፀዳ ከሆነ የምግብ ትራፊዎቹ በባክቴሪያዎቹ ወደ አሲድነት ተቀይረው ጥርስን ይጎዳሉ፡፡ ይህ ችግር ትኩረት ከማጣት የተነሳ በሕፃናቶች ላይ በብዛት ይታያል። በተጨማሪም በተለምዶ ‹‹ሴቶች ጣፋጭ ነገር ስለሚያዘወትሩ እና አረጋውያን ጥርሳቸው ለረጅም ጊዜ ከማገልገሉ የተነሳ ደህንነቱ ላይጠበቅ ይችላል››።
በበርካቶች ዘንድ የጥርስ ደህንነትና ጤንነት እንዳይጠበቅ የሚያደርገው ምክንያት ጥርስ በተገቢው መንገድ አለማጽዳትና በየስድስት ወሩ በቋሚነት ባለሙያ ጋር እየሄዱ አለመታየት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ግን እንደ ሲጋራ እና አልኮል ሱስ ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ለጥርስ ደህንነት ችግር ብቻ ሳይሆን ለአፍ ውስጥ ካንሰር ጭምር ተጋላጭ ናቸው፡፡ የአፍ ውስጥ ካንሰር በራሱ የጥርስ አቃፊዎችን የሚጎዳ ሕመም በመሆኑ የጥርስ ሕመምን ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ እንደ ቡናና ሻይ ያሉ ትኩስ ነገሮች በራሳቸው ጥርስን የማበለዝ ባህሪ ያላቸው ሲሆን ውስጣቸው በሚጨመርባቸው ስኳር አማካኝነት ደግሞ ጥርስ እንዲቦረቦር ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ በተገቢው መንገድ ጥርስን ካለማጽዳት በተጨማሪ የጥርስ ጤንነትን የሚጎዱ የውስጥ ደዌ ሕመሞች አሉ። ለአብነትም የጨጓራ ሕመም፤ የደም ግፊት ሕመም እና የስኳር ሕመምን መጥቀስ ይቻላል። በተለይ የጨጓራ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ጨጓራቸው ውስጥ የሚፈጠረው አሲድ ወደ አፍ በመምጣት የጥርስ ክፍሎችን እና ድድን ሊያጠቃ ይችላል፡፡ ስኳር ያለባቸው ታማሚዎችም ሌሎች የሰውነት ክፍሎቻቸውን በየጊዜው እየሄዱ እንደሚመረመሩት ሁሉ ጥርሶቻቸውን ስለማይታዩ የጥርስ አቃፊዎቻው ተጎድተው ጥርሶቻቸው እስከመውለቅ ይደርሳሉ። የደም ግፊት መድኃኒት የሚወስዱ ሰዎች ደግሞ መድኃኒቱ በራሱ የድድ እብጠት ስለሚያመጣ የጥርስ ደህንነትን ይጎዳል፡፡
የጥርስ አፈጣጠር የሚጀምረው ልጆች ከመወለዳቸው በፊትና ከተወለዱ በሳምንታት እድሜ ውስጥ በአጥንት ውስጥ እንደሆነ ይታመናል። ልጆች ከተወለዱ ከስድስት ወር ጀምሮ ደግሞ መብቀል ይጀምራል፡፡ እስከ ሁለት ዓመት ተኩል 20 ጥርሶች አብቅለው ይጨርሳሉ፡፡ ስድስት ዓመት ሲሞላቸው ሁሉም ጥርሶች በየተራ ይወልቃሉ፡፡
በአሁኑ ጊዜም በርካታ ሰዎች ውበታቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ወጪ አውጥተው እራሳቸውን ለማስዋብ ይሞክራሉ፡፡ ከዚህ ውስጥም የውበት መለኪያ ተደርጎ የሚወሰደው የጥርሳቸውን አቀማመጥ ለማስተካከል በርካታ ወጪ አውጥተው የሚያሰሩት የጥርስ ብሬስ ነው፡፡ ይህን የሚያሰሩት ደግሞ በአበቃቀል ምክንያት የተበላሸውን ጥርስ ለማስተካከል ነው፡፡
ለአበቃቀል ችግር እንደምክንያትነት የሚቀርበው የወተት ጥርሶች በጊዜው ሳይወልቁ ሲቀሩ እና ቀድመው ተቦርቡረው እንፌክሽን ፈጥረው ከወለቁ ቋሚ ጥርሱ እሱን ተከትሎ የሚበቅል በመሆኑ ከተገቢው አቀማመጥ ተንሻፈው ሊበቅሉ ይችላሉ፡፡ ሌላኛው ደግሞ ሰዎች የጥርስ አቀማመጣቸውንና መጠናቸውን ከወላጆቻቸው የሚወርሷቸው በመሆኑ ከዛ ጋር ተያይዞም የአበቃቀል ችግር ሊከሰት ይችላል፡፡ ለአበቃቀል ችግር እንደመፍትሔ የሚወሰደውም የጥርስ ብሬስን ማሰር ነው፡፡
ዶክተር ኢዮኤል እንደሚሉት ሰዎች የጥርስ ብሬስን ለአበቃቀል ችግሮች ብቻ ሳይሆን ከሕመም ጋር ለተያያዘ ሁኔታም ሊጠቀሙት ይችላሉ፡፡ የጥርስ ማስተካከያ ብሬሶች ከውበት ባሻገር ለጥርስ ጤና ጥቅምም ይደረጋሉ፡፡ ጥርሶች ተደራርበው የተቀመጡ ከሆነ ለማጽዳት አስቸጋሪ ስለሚሆን የጥርስ ብሬስ ሊታሰር ይችላል፡፡ የአበቃቀል ችግር ሲኖርና የአነካከስ ችግር ካለም የጥርስ ብሬስ እንዲያደርጉ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡
በዚህ ዘመን በርካታ የተለያዩ የብሬስ ዓይነቶች እየተዋወቁ ቢሆንም በዋናነት ግን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ እነርሱም ቋሚ እና ወጪ ገቢ የሚባሉ የጥርስ ብሬስ (የጥርስ ማስተካከያ) ዓይነቶች ናቸው፡፡ ቋሚ የጥርስ ማስተካከያዎች ጥርስ ላይ ተጣብቀው ጥርሶችን እንዲያስተካክሉ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ቋሚ የጥርስ ብሬስ ዓይነቶች የተለያዩ ቢሆኑም በስፋት የተለመዱት ከስይንለስ ስቲል የተሰሩ እና ከሴራሚክ የተሰሩት ናቸው። እነዚህን የጥርስ ብሬስ ዓይነቶች ታካሚዎች እንዲጠቀሙ የሚደረገው እንደ ታካሚዎቹ የጥርስ አቀማመጥ እና እንዳሉበት የጤና ሁኔታ የሚወሰን ነው፡፡
ዶክተር ዳንኤል እንደሚናገሩት ብሬስ ሲሰራ ከሐኪሞች በኩል ሊደረግ የሚገባው ጥንቃቄ በቅድሚያ ብሬሱን ከማሰራቸው በፊት ችግሩን በተገቢው መንገድ በመለየት የትኛውን የብሬስ ዓይነት ማድረግ እንደሚገባቸው፤ ለምን ያህል ጊዜ መቆየት እንዳለበት፤ የታካሚውን የጥርስ አቀማመጥ በማሳየት ስለሁኔታው ማስረዳት፤ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች በሙሉ መኖራቸውን ማረጋገጥና እና እቅድ በማውጣት የክትትል ጊዜውን መለየት አስፈላጊ ነው፡፡
በጥርስ ብሬስ ታካሚዎቹ በኩል ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች መካከል በቅድሚያ ከሐኪሞቻቸው ጋር በመመካከር የሚሰራው ሥራ ምን እንደሆነ ሊያውቁ ይገባል፡፡ የጥርስ ማስተካከያ ብሬሱ ለረጅም ጊዜ ሊቆይ የሚችል በመሆኑ በተገቢው መንገድ ክትትል ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማረጋገጥና በቀጠሮ ቀናት እየተገኙ ተገቢውን ክትትል ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ራቅ ወዳለ ቦታ የሚሄዱና ለክትትል የሚመች የሥራ ሁኔታ ከሌላቸው ሕክምናውን ማድረግ መጀመር የለባቸውም፡፡
ብሬስ ሲደረግ ጥርስ ላይ የሚቀመጠው የምግብ ትራፊ ስለሚበራከት በተደጋጋሚ ማጽዳትና ጥርሶችን ለማጽዳት እንደማይመች በመረዳት ለብሬስ ተብለው የሚሰሩ የጥርስ ማጽጃ ብሩሾችን በመጠቀም በብሬሶቹ መካከል ማጽዳት ይኖርባቸዋል፡፡ ብሬሱ ሲደረግ የጥርሶች እንቅስቃሴ ስለሚኖር የጥርስ አቃፊ ደህንነት ለመጠበቅ የተለያዩ የአፍ መጉመጥመጫዎች መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ከፍተኛ የሕመም ስሜት ካላቸውም ከሐኪሞች ጋር በመነጋገር በቶሎ ችግሩን ሊፈቱት ይገባል፡፡
ይህ ዓይነቶቹ ጥንቃቄዎች በሐኪሙና በታካሚው በኩል ካልተደረጉ የጥርስ አቃፊዎቻቸው መድማት ይጀምራሉ፡፡ በዚህ ወቅት ተገቢውን የሕክምና ርዳታ ሳያገኙ ከቀሩ ጥርሶቻቸው መነቃነቅ እና ሙሉ ለሙሉ እስከመውለቅ ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተገቢው መንገድ ክትትል ካላደረጉና በባለሙያ የጥርስ ብሬሱ ካልታሰረ በፊት ከነበረው በባሰ መልኩ የጥርሱ አቀማመጥ ሊበላሽ ይችላል። ከዚህም አለፍ ሲል ለአፍ ውስጥ ጤና ችግሮች ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ታካሚዎች በተገቢው መንገድ ጥርሶቻቸውን ካላጸዱ ለአፍ ውስጥ እጢ ችግር፤ የድድ ሕመም፤ ለጥርስ መነቃነቅ እና መውለቅ ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡
የጥርስ አቀማመጥ ችግር ክትትሉ ገና በልጅነት የሚጀመር ቢሆንም ብሬስን ወይም የጥርስ ማስተካከያን ማድረግ የሚገባቸው ግን የልጅነት ጥርስ (የወተት ጥርስ) ሙሉ በሙሉ ወልቆ ሲያልቅና ቋሚ ጥርሶች ሲበቅሉ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም እድሜያቸው የገፋ ሰዎች የጥርስ ብሬስን እንዲያደርጉ አይመከርም፡፡ ከተደረገም ተጨማሪ ጥንቃቄና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሌላው የጥርስ ብሬስን እንዳያደርጉ የሚመከሩት ያልተቆጣጠሩት የስኳር ሕመም ያለባቸውና የደም ግፊት መድኃኒትን የሚወስዱ፤ የልብ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ናቸው፡፡
እንደ ዶክተር ዳንኤል ማብራሪያ ስኳር ሕመም ያለባቸውና የስኳር መጠናቸውን መቆጣጠር ያልቻሉ ሰዎች የጥርስ አቃፊያቸው ላይ ችግር ስለሚኖር ብሬስ አድርገው ንጽህናውን የማይጠብቁ ከሆነ ችግሩን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡ የልብ ሕመም ያለባቸው ሰዎች ካሉና ጥርሶቻቸው ተደራርበው ከተቀመጡ የብሬስ ሕክምናውን ለመጀመር በሐኪሙ ትእዛዝ ጥርስ መውለቅ ሊኖር ስለሚችል ያለባቸውን የጤና ችግር በቅድሚያ ለሐኪሙ በመናገር ተገቢው ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ሰዎች ጥርሶቻቸውን ከመታከማቸው በፊት ተገቢውን የጤና ተቋም መምረጥና ስለሐኪሙ የሙያ ደረጃ ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በጥርስ ሕክምና ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ሐኪሞች ጋርም መሄድ ያስፈልጋል፡፡ ተጨማሪ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ከሐኪሞቻቸው ጋር በመመካከር ተገቢውን የጤና ክትትል ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 13 ቀን 2016 ዓ.ም