አዲስ አበባ፡- የዓድዋን ድል ለመዘከር ለሚገነባው የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ የሚውሉ የገንዘብ፤ የቁሳቁስና የእውቀት ድጋፎችን ለማሰባሰብ ከድጋፍ አድራጊ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የምስረታ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ቢተው በላይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ለዩኒቨርሲቲው ምስረታ በርካታ ድርጅቶችና ግለሰቦች ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት አሳይተዋል። የትግራይ ክልል መንግሥት ለግንባታው ለመስጠት ቃል ከገባው 250 ሚሊዮን ብር ውስጥ የተወሰነ ገንዘብ ሰጥቷል፡፡ ለዲዛይኑም ድጋፍ እያደረገ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡
“ለዩኒቨርሲቲው ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ክልሎችም እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የገቡትን
ቃል እንደሚፈፅሙ ነግረውናል፡፡ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ከገቡ አካላት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 10 ሚሊዮን ብር ሰጥቷል፡፡ ሌሎች ክልሎችም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል” ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ “በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንንና የሌሎች አገራት ምሁራንን አነጋግረናል። የተለያዩ ኮርሶችን ለማስተማርና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ እንደሆኑ ገልጸውልናል” ብለዋል፡፡
በ2010 ዓ.ም በአዲስ አበባና በዓድዋ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች መካሄዳቸውን አስታውሰው፤ በወቅቱ ከበርካታ አካላት ጋር ግንኙነት መፈጠሩንና የካሪኩለም ቀረፃ ስራዎችንና የማስተማር አገልግሎቶችን በፈቃደኝነት ለማከናወን ፍላጎት ካላቸው ምሁራን ጋር ስለመነጋገራቸውም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፣ ኮሚቴው ለግንባታው የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ለመቀበል የሚያስችል የገንዘብ ማስገቢያ የባንክ አካውንት እንዲከፈትለት ከመጋቢት 2010 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ጊዜያት ይህል ጥያቄውን ለጽሕፈት ቤቱ ቢያቀርብም እስካሁን ድረስ ምላሽ ባለማግኘቱ ኮሚቴው አሁንም ምላሽ እየጠበቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚገኘውን ድጋፍ ለመቀበል እንዲሁም ሕዝቡ ከድጋፉ ስለሚገኘው ገንዘብ ማወቅና ገንዘቡም ሕጋዊ አሰራርን ተከትሎ ኦዲት መደረግ ስላለበት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚከፈት ዝግ የባንክ አካውንት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
ለግንባታው 10 ቢሊዮን ብር ያስፈልገዋል የተባለው የዓድዋ ፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ የግንባታው የመሰረት ድንጋይ በሚያዚያ ወር 2009 ዓ.ም በቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና በኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ አማካኝነት መቀመጡ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
አንተነህ ቸሬ