የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ሰኞ..ሲያስጠላ። በዚች ቀን ደስተኛ የሆነ ማነው? ተማሪው፣ የመንግሥት ሠራተኛው ሁሉም የሚጠላው የቀን ሀሌታ። ለሉሊት ግን እንደዛ አልነበረም፣ እለተ ሰኞ ከቀኖች ሁሉ ልዩ ቀን ነበር።
ሉሊት ያለወትሮዋ ጠዋት ተነስታ መስተዋቱ ፊት ቆመች። ያለፉት ሁለት ቀናቶች ቅዳሜና እሁድ የሁለት ዓመታት ያክል ርቀውባት ነበር የከረሙት። ከሃሳቧ ያልጠፋውን ሄኖስን እንደምታፈቅረው ማስረጃ ሆነዋታል። ሰዎች ሁሉ የሚወዷቸው ሁለቱ የሰንበት ቀናቶች ከምትወደው ሰው ስላራቋት ጠላቻቸው። ፍቅር በተፈጥሮ ላይ አስጨከናት…
ዛሬ ፍቅሯን ለመግለጽ የመጨረሻ ቀኗ ነው። ፊቱ ስትቆም እንደምትወደው ትነግረዋለች ከእንቅልፏ የነቃችው እንዲህ እያሰበች ነበር። ‹ዛሬ የመጨረሻ ነው..አዋራዋለሁ፣ በቃ የሆነ ነገር ፈጥሬ እንዲያወራ አደርገዋለሁ› ስትል መስተዋቱ ፊት እንደቆመች ለራሷ አወራች። ወደዚያ ወደዚህ እያለች መልኳን በመስተዋቱ ውስጥ አጤነችው። አጠር ብሎ ከርደድ ያለው ጸጉሯ የሴቶች የውበት ሳሎን ውስጥ ገብቶ ለስለስ ብሏል። ትልልቅ አይኖቿ በጥቁር ኩል ልመው ሲታዩ ከማማር ባለፈ ያስደነግጣሉ። ከንፈሯ ያምራል..በወፍራም ሥጋ ደልቦ በቀላሉ ዓይን ውስጥ ይገባል። ከረጅም ቁመት ጋር የተሰጣት የደስ ደስ በሁሉም ወንዶች ዘንድ ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል። መስተዋቱ ፊት..በስስ ፒጃማዋ ካልተኳኳለ የማያምር የሌሊት ጉድፍ ያጎደፈውን ውበቷን ስታሰማምር ብዙ ቆየች። አምሮባት ሄኖስ እንዲያያት ፈልጋለች። እሱ ፊት ከዓለም ምርጧን ሴት ሆና መቆም የምንጊዜም ምኞቷ ነው..።
ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ላትመለስባት መስተዋቱ ውስጥ የምትታያትን የራሷን ምስል እያየች ‹እንዲህ አምሮብኝ እማ ካላንበረከኩት ሉሊት አይደለሁም ስትል ዝታ ልብሷን በመለባበስ ቦርሳዋን አንጠልጥላ ከቤት ወጣች። ከሃሳቧ ያልጠፋውን የታክሲ ሾፌር ሄኖስን እያሰበች ብዙ ተጓዘች። ለፍቅር ስስ ልብ ያላት ሴት ናት። ማንም በጥሩ ጎኑ ከመጣባት ያሸንፋታል። ግን ደግሞ ከወደደችው ከአንዱም ጋር ኖራ አታውቅም። የፍቅር እድለ ቢስ ናት። ከሁሉም ተሰማ አትረሳውም። ተሰማ የሁለት ዓመት ፍቅረኛዋ ነበር ሊጋቡ ቀን ተቆርጦ፣ ወዳጅ ዘመድ ተጠርቶ ለሙሽራነት አንድ ቀን ሲቀረው በመኪና አደጋ ሕይወቱ አለፈ። ክብሮምም በእሷ ሕይወት ውስጥ በርቶ የጠፋው አንድ ጊዜ ነው። አብረው ውለው፣ አብረው አድረው ጠዋት ከተኛበት ሳይነሳ በዛው አሸልቦ ቀረ። የማነህም እስካሁን የት እንዳለ አታውቅም..እመጣለሁ ጠብቂኝ እንዳላት ብቻ ነው ትዝ የሚላት።
ከሁሉም በኋላ የሰዎች ትልቁ በሽታ የሚወዱትን ማጣታቸው ነው ትላለች። ሕይወቷ ጉራማይሌ ነው..አንድ ቀን ሳቅ አንድ ቀን መከራ። በፈገግታዋ ማግስት የደስታዋን ጀምበር ጠልቃ ታገኛታለች። ‹እኔ ስቄ እንዳለቅስ ሆኜ የተፈጠርኩ ሰው ነኝ።› ታሪኬም ሲጻፍ በአጭር ሀዘንና በአጭር ደስታ ተወስኖ ነው ትላለች።
የአሁን ታሪኳም በዚህ እንዳይቋጭ ሰግታለች። ሄኖስ የመጨረሻዋ ሆኖ ወደ ሕይወቷ ቢገባ ደስታዋ ልክ አይኖረውም። ይሳካላት ይሆን? አታውቀውም።
ሄኖስን አታውቀውም። ታክሲ ተራ ነው ያየችው..ከብዙ ጊዜ በኋላ ሹፌር እንደሆነ አወቀች። እሱ እየሾፈረ እሷ ጎኑ ተቀምጣ ብዙ ጊዜ ሄዳ ታውቃለች ግን አውርተው አያውቁም። ረዳቱን አትወደውም። በአሁኑ ሰዓት ምድር ላይ ከምትጠላቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ የሄኖስ ረዳት ነው። የሆነ ሰው ሾፌሩን ካናገረ ቀድሞ መልስ የሚሰጠው ይሄው ረዳት ነው። ለምን በሾፌሩ ፈንታ መልስ እንደሚመልስ አይገባትም። ሰው ሄኖስ ብሎ እየተጣራ አቤት የሚለው እሱ ነው ወያላው። ብዙ ጊዜ ሄኖስን ለማናገር ሞክራ በዚህ ረዳት አማካኝነት ምኞቷ ሳይሳካ ቀርቷል። ቡጭቅጭቅ ብታደርገው ደስታዋ ነበር..ረዳቱን።
ታክሲ ተራ ደረሰች..አሁን ሄኖስን ልታየው ነው። ልቧ በደስታ ይሆን በፍራቻ ይደልቃል። አፍታ ሳትቆይ ሄኖስን አየችው..። ታላቅ ነገር እንደሆነለት ሰው በነፍስ በሥጋዋ ታደሰች። ሌላ ቦታ የምታይ መስላ እስኪበቃት አየችው። ጠይም ፊቱ እንደረጋ ውቅያኖስ ጠላላ ነው። ጸጥ ረጭ ያለው ገጹ የአማዞንን ያህል ያስፈራል። ዝምታ እንዲህ ያስፈራል? ዝምታ እንዲህ እንደሚያስፈራ አታውቅም ነበር። በቄንጥ ተራምዳ አጠገቡ ደረሰች..ዛሬ የሆነ ነገር መፍጠር አለባት። እለተ ሰኞ ካለአንዳች አስደሳች አጋጣሚ ዝም ብሎ እንዲያልፍ አልፈለገችም። የሆነ ሃሳብ መጣላት። ያላየች በመምሰል በዛውም ሽቶዋን እንዲያሸትላት ገፋ አድርጋው ታልፋለች። በዚያች ቅጽበት ሃሳቧን ለማስፈጸም ትክክለኛ አማራጭ ስለመሰላት እንዳሰበችው ለማድረግ ወዳለበት ተንፏቀቀች። ግን እንዳሰበችው አልነበረም የሆነው..ገፍቼው አልፋለሁ ብላ ሳታስበው ደረቱ ላይ ወደቀች። ያን ተንኮል፣ ያን ቀን፣ ያን አጋጣሚ መቼም አትረሳውም። እግዜር እንደዛ ቀን የተባበራት አይመስላትም። ሰይጣንም እንደዛ ቀን ፊቱን ያዞረባት አይመስላትም። ለትከሻው ሄዳ ደረቱ ላይ ወደቀች። ራሷን በፈርጣማ ክንዱ ውስጥ አገኘችው። ክንዱ አቀፋት..ደረቱ ላይ አረፈች። በሕይወቷ ጥሩ ነገር አስባ እንደዛ ቀን የተሳካላት የለም። ገፍቼው አልፋለሁ ብላ የዘየደችው ተንኮል ስሯ ባለ እንቅፋት ዳብሮ ደረቱ ላይ ጣላት። ያላሰበችው ስለነበር ደንግጣ ነበር…እሱም ምንም አላለም። ቶሎ ብላ ከደረቱ ላይ ሸሽታ ታክሲ ውስጥ ገባች። አጋጣሚውን ወደ ኋላ ተመልሳ ስታስበው ድንቅና የተለየ ነበር። ከዚህ በኋላ እንዲህ ዓይነት የተሳካ ምኞትና ድርጊት ምድር ላይ ድጋሚ እንደማይከሰት እምነት አሳደረች።
ለምን ምንም አላለኝም? በውስጧ ተብሰለሰለች። ግን እኮ አንቺም ምንም አላልሽውም.. እንደዛ ካየር ላይ እንደበረኛ ቀልቦሽ እንኳን አመሰግናለሁ አላልሽውም። እሱን ለመቅረብ ከዚህ የተሻለ ምን አጋጣሚ ታገኛለሽ? ከውስጥ መንፈሷ ሹክ አላት። በዚህ ሃሳብ ውስጥ ሳለች..ከጎኗ አንድ ሰው ነካት ወያላው ነበር።
‹ተረፍሽ? ሄኖስ ባይኖር እኮ ጥርስሽን ለቅመሽ ነበር?
‹እሱ ባይኖር እኔም አልወድቅም ነበር..› መለሰችለት።
‹ማለት? እሱ ስላለ ነው የተደናቀፍኩት እያልሽ ነው? ተገርሞ ጠየቃት።
ዝም አለችው..አንድ መዐት ዝምታ።
‹ለምን እሱ አይጠይቀኝም? ያደናቀፈኝ እሱ፣ የወደኩት እሱ ላይ…እንዴት ሆንሽ እንዴት አይባልም? ተበሳጨት።
‹እሱ እኮ…›ወያላው መጨረስ አቃተው።
‹እሱ እኮ ምን?
‹ሄኖስ እኮ መናገር አይችልም..ዱዳ ነው። ዝግ ያለ አሳዛኝ ድምጽ ከወያላው አንደበት ፈለቀ።
በተቀመጠችበት በድን ሆነች። እጣ ፈንታዋ ዛሬም አልተዋትም እየተከተላት ነው። ለደስታ አስባት ትላንት ላይ ሆና ነገ ባለቻት ዛሬ መከራዋን አየች።
ሳታስበው የሆነ እጅ ጉንጭዋ ላይ አረፈ….የሆነ እጅ ጉንጭዋን ዳበሰው።
ወደ ጎን ዞረች ሄኖስን አየችው…መከራዋን ረሳችው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 12 ቀን 2016 ዓ.ም