ባህርዳር፤ በቅርብ ዓመታት በአማራ ክልል ተከስተው በነበሩ ግጭቶች ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው የግል ተቋማት ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ 25 በመቶ የጉዳታቸውን ዋጋ በመክፈል ወደሥራ ለማስገባት መታቀዱን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል እንደገለጹት፤ በአማራ ክልል በሚገኙ የግል ተቋማት ላይ በተለያዩ ጊዜያት ለደረሰው ጉዳት ክልሉ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ቢኖረውም ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።
ከሚቀጥለው በጀት ዓመት፤ ማለትም ከሐምሌ ወር ጀምሮ ግን ጉዳት ለደረሰባቸው ተቋማት የጉዳታቸውን 25 በመቶ ድጋፍ ለማድረግ ተግባራዊ ሥራ ይጀመራል። ክልሉ ይህን ድጋፍ ሲያደርግ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ቀሪውን ድጋፍ እንዲያደርጉ መነሳሳትን ይፈጥራል።
እንደ አቶ መላኩ ገለጻ፤ በክልሉ በሚገኙ ተቋማት ላይ ብቻ በደረሰ ጉዳት አንድ ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሟል። በዚህ ምክንያት የተለያዩ ሆቴሎች እና አምራች ድርጅቶች፤ እንዲሁም አገልግሎት ሰጪዎች ስራቸውን አቁመው ቆይተዋል። የክልሉ መንግሥት ድጋፉን የሚያደርገው ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማት በፍጥነት ወደሥራ ገብተው ኢኮኖሚውን እንዲደግፉ በማሰብ ነው። እስከአሁንም ለድጋፉ የሚሆን ሃሳብ በክልሉ ጉባዔዎች ቀርቦ ስምምነት ቢደረስበትም ተግባራዊ ማድረግ ያልተቻለው በአገር አቀፍ ደረጃ ባጋጠመው የፋይናንስ እጥረት ምክንያት ነው።
በመሆኑም በተያዘው ዓመት መጨረሻ ጀምሮ በሚኖረው አዲሱ በጀት ወቅት የተጎዱ ተቋማትን የማቋቋም ሥራው እንደክልል ይቀጥላል።
አቶ መላኩ እንደገለጹት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ማለትም ከለውጡ ማግስት እና አስቀድሞ በርካታ የግል ተቋማት ላይ ጉዳት ደርሷል። ጉዳቱ አንድም በአካባቢያቸው በተከሰቱ ግጭቶች በሌላ በኩል ደግሞ በተሳሳተ መረጃ በተፈጠሩ ግርግሮች ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። በመሆኑም የአማራ ክልላዊ መንግሥት ስር የሚገኙ የግል ተቋማት በፍጥነት ወደሥራ እንዲገቡ የያዘውን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ድጋፍ ለማድረግ ወስኗል።
በተጨማሪ ጉዳት ለደረሰባቸው ድርጅቶች ለሥራ የሚሆናቸውን የተለያዩ መሳሪያዎች እና ንብረቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ውይይት መደረጉን የተናገሩት አቶ መላኩ፣ ይህም ተቋማቱን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
ጌትነት ተስፋማርያም