አዲስ አበባ፤- በየመን በተፈጠረው ግጭት በኤደን አካባቢ ተጠልልው የሚገኙ ሁለት ሺህ 44 ዜጎችን ማስመለስ መጀመሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ትናንት ረፋዱ ላይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በየመን በተፈጠረው ግጭት በኤደን አካባቢ ተጠልልው የሚገኙ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በመግለጫቸው ላይ ትናንት ከሰዓት በኋላ 134 ኢትዮጵያን ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ አንስተዋል። ሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለሰን በየቀኑ ሁለት በረራዎች እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ዜጎችን ወደ አገራቸው የመመለሱን ስራ ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት፤ በጅቡቲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ጋር በመተባበር ይከናወናል ብለዋል።
በሌላ በኩል ቃል አቀባዩ፤ ግንቦት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በሚኒስቴሩ ደረገጽ ላይ ለተጠቀመው የተሳሳተ የአፍሪካ ካርታ ይቅርታ ጠይቋል። የተጠቀመው ካርታ ሱማሌን የኢትዮጵያ አካል ያደረገ ሲሆን፤ የሌሎችንም አገራት ልዓላዊ ግዛት ያዛባ ነው። ለዚህም ሚኒስቴሩ ማዘኑን አንስተው ችግሩ ማንና ለምን እንዴት እንደተፈጠረ እያጣራ ነው። ተጣርቶ ሲያልቅም ችግሩን በፈጠረው አካል ላይ ርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝርዝር የግንኙነት ጥናት በምን ደረጃ እንደሚገኝ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ የሁለቱ አገራት የሰላም ግንኙነት ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ክትትል እየተደረገ ነው። ዝርዝር ስራዎች የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ ነው። ስራዎቹ እንደተጠናቀቁ ለህዝብ ይፋ ይሆናሉ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ