በሚቀጥለው ዓመት ይደረጋል ተብሎ ለሚታሰበው ምርጫ ህዝቡ ፓርቲዎቹን በአግባቡ እንዲያውቃቸው እና ሃይላቸውን አስተባብረው ጠንካራ አማራጭ ይዘው ለመቅረብ እንዲያስችላቸው በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራቱ አማራጭ መሆኑን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
የጋምቤላ ህዝቦች ነጻነት ንቅናቄ አስተባባሪ አቶ ታደለ ብሩ፤ አንድነት ሃይል እንደመሆኑ በተበታተነ መልኩ ከመስራት ይልቅ በጋራ ጉዳዮች ላይ አብሮ መስራቱ ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው ከሌሎች ስምንት ፓርቲዎች ጋር ግንባር መፍጠሩን እና በቀጣይም ሌሎች መዋሃድ የሚፈልጉ ፓርቲዎችን በማካተት ጠንካራ አማራጭ ይዞ ለመቅረብ ሃሳብ እንዳለው ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ፤ በኢትዮጵያ ፓርቲዎች ቁጥር መበራከት የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። የፓርቲዎች አደረጃጀት በራሱ ችግር እንዳለበት ገልጸው፤ ትክክለኛ የፖለቲካ ምህዳር
ለመፍጠር የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ሊቀንስና ህዝቡም ስለ ፓርቲዎቹ ጠንቅቀው ሊያውቁ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
የገዳ ስርዓት አራማጅ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ ሮበሬ ታደሰ በበኩላቸው ለህዝቡ ጠንካራ አማራጭ ለመሆን ሁለት ፓርቲ በቂ ነው ብለዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል14 የሚሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እነዚህን ፓርቲዎች ወደ አንድ ለማምጣት የተለያዩ ስራዎች እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ኮንግረስ ሊቀመንበር አቶ ገረሱ ገሳ፤ ፓርቲዎች ከመዋሃዳቸው በፊት ግንባር በመፍጠር እርስ በእርስ በደንብ እንዲተዋወቁና ውህደቱን ዘላቂና አስተማማኝ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳሉትም፤ ፓርቲዎች በራሳቸው አደረጃጀትና በራሳቸው ውሳኔ የሚዋሃዱት በቦርዱ ህግና ደንብ መሰረት ነው። ቦርዱ በአሁን ጊዜ የተለያዩ ህጎችን እያሻሻለ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ ከማሻሻያዎቹ መካከል የፓርቲዎች ምዝገባ ይገኝበታል።
ህጉ እስኪሻሻል ድረስ ቦርዱ ውህደት በመፍጠር እንደ አዲስ የሚመዘገቡ ፓርቲዎችን እያስተናገደ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ለቦርዱ የቀረበለት የውህደት ጥያቄ ከሁለት እንደማይበልጥ አስታውቀዋል።
መንግስት ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ እንዲፈጠር ተመሳሳይ አጀንዳ ያላቸው ተዋህደው አብረው እንዲሰሩና የፓርቲዎች ቁጥር እንዲቀንስ ፍላጎት እንዳለው ማሳወቁ ይታወሳል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011