አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ከ1971 ዓ.ም ጀምሮ ሲያስተዳድረው የነበረው የወላይታ ሶዶ ኦቶና ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት በመዘጋት አፋፍ ላይ መሆኑ ተገለፀ።
አቶ ወሰን ዓለሙ የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዘዳንት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ማህበሩ የወላይታ ሶዶ ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን ለ2012 የትምህርት ዘመን ሊያስቀጥል የሚችል በጀት የሌለው በመሆኑ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦበታል ብለዋል። ከጀማሪ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ይህ የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማህበሩ ባጋጠመው የበጀት እጥረት የተነሳ እስከ አራተኛ ክፍል ብቻ ሲያስተምር መቆየቱን አስታውሰዋል።
ማህበሩ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ከዓመት ዓመት የተማሪ ቅበላም ሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራቱ እየቀነሰ መጥቷል። ከዚህም ባሻገር ማህበሩ በአሁኑ ወቅት ያሉትን ተማሪዎች አስፈላጊውን ሁሉ ወጪ ሸፍኖ ይዞ መቀጠል ባለመቻሉ ትምህርት ቤቱ ሙሉ ለሙሉ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦበት ይገኛል።
በመሆኑም፤ ይህ አንጋፋና ብዙ ዓይነ ስውራን ምሁራንን ያፈራ የነበረው የወላይታ ሶዶ ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ብዙ እገዛ የሚሹ ማየት የተሳናቸውን ህፃናት ከእቅፉ ሊያወጣቸው እየተገደደ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ኢስሙ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ማህበርን ጨምሮ በአገሪቱ የሚገኙ ሁለት የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ሙሉ ወጪ በመሸፈን ሲረዳ የነበረው ሲቢኤም የተባለ የጀርመን ተራድኦ ድርጅት መሆኑን ገልፀው፤ ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ ቁጥር 621/2001 ዓ.ም መውጣቱን ተከትሎ ርዳታውን እንዳቋረጠ ይናገራሉ። በመሆኑም ማህበሩ ከፍተኛ የሆነ የበጀት እጥረት ሲያጋጥመው በኦሮሚያ ክልል የሚገኘውን የባኮ ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትን ቀደም ሲል ለመንግስት አስረክቦ የኦሮሚያ ክልል ትምህርት ቢሮ እያስተዳደረው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከዚህም በላይ፤ በአሁን ወቅት ለመላው ኢትዮጵያውያን ዓይነ ስውራን ተማሪዎች ብቸኛ የሆነውና በደቡብ ክልል የሚገኘው የወላይታ ሶዶ ዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤትም የመቀጠል ዕድሉ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል። ትምህርት ቤቱ ከ110 በላይ የሆኑ ተማሪዎችን በየዓመቱ እየተቀበለ ሲያስተምር የቆየ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ማህበሩ ባጋጠመው የበጀት እጥረት ከዓመት ዓመት የቅበላ አቅሙ እያሽቆለቆለ ሄዶ በያዝነው ዓመት በቁጥር ከ50 በታች የሆኑ ተማሪዎችን ሲያስተምር መቆየቱን አስረድተዋል።
ማህበሩ እነዚህን ተማሪዎች በቀጣይ ዓመት ይዞ የመቀጠል አቅም የሌለው በመሆኑ የክልሉን ትምህርት ቢሮ ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉና ትምህርት ቤቱ በስራው እንዲቀጥል ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳላገኙ ስራ አስኪያጁ ጨምረው ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣም፤ “ለመዘጋት አፋፍ ላይ ደረሰ የተባለውን የወላይታ ሶዶ ኦቶና የዓይነ ስውራን ትምህርት ቤት የገጠመው ችግር ምንድነው?” ሲል ለወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ ጥያቄ አንስቷል። ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት አቶ መሰለ ወልደ ሰንበት የወላይታ ዞን ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ናቸው።
እንደሳቸው ገለፃ፤ ጽሕፈት ቤቱ ከበጀት ውጭ ያሉትን ሙያዊ የሆኑ ክትትልና ድጋፎችን ለሁሉም ትምህርት ቤቶች እየሰጠ እንደሚገኝና የኦቶና ዓይነ ስውራን ትምህርት ቤትም አሁን በሚባለው ደረጃ የበጀት እጥረት አጋጥሞት ሊዘጋ መድረሱን አናውቅም ብለዋል።
ማህበሩም የበጀት እጥረት ገጥሞኛል ብሎ ወደ ጽሕፈት ቤቱ ያመጣው ጥያቄ የለም። እኛ የምናውቀው ትምህርት ቤቱን ማህበሩ እያስተዳደረው እንደሚገኝ ነው። ምንም እንኳን ጽሕፈት ቤቱ የበጀት ጉዳይ ባይመለከተውም ማህበሩ የበጀት ችግር እንደገጠመው ለትምህርት ጽሕፈት ቤቱ ጥያቄ ቢያቀርብ፤ ጽሕፈት ቤቱ ራሱ ለከተማ አስተዳደሩም ሆነ ለክልሉ ትምህርት ቢሮ ጉዳዩን ያቀርብለት እንደነበር ተናግረዋል። አዲስ ዘመን ጋዜጣም፤ ይህን ምላሽ በመያዝ የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮን ለማግኘት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
የወላይታ ሶዶ ዓይነስውራን ኦቶና አዳሪ ትምህርት ቤት ከቀለም ትምህርት በተጓዳኝ የተለያዩ የክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ህፃናቱን የሚንከባከብና አጠቃላይ ወጪያቸውን ሸፍኖ የምግብ፤ የአልባሳትና የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ያለ አንጋፋ የዓይነ ስውራን አዳሪ ትምህርት ቤት ነው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
ፍሬህይወት አወቀ