አዲስ አበባ፤– መንግስት የሰራተኞቹን የቤት ችግር መፍታቱ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት ምሁራን አስታወቁ።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ምሁሩና ተመራማሪው ዶክተር ዘሪሁን አየነው፤ መንግስት የሰራተኞቹን የቤት ችግር በመቅረፍ በርካታ ጠቀሜታ ማትረፍ ይችላል። ወደ ገበያ የሚረጨውን ገንዘብ በመቀነስም ግሽበቱን ይቀንሳል።
የአገሪቱም ሀብትም ይጨምራል። የስራ አካባቢው የተረጋጋ እንዲሆን በማድረግ፤ የሰራተኛውን የስራ ተነሳሽነት በመፍጠር የመንግስትን አገልግሎት ውጤታማ ያደርጋል። የመንግስት አገልግሎት ሲቀላጠፍ የአገሪቱ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚዊ እና ፖለቲካዊ ስራዎች ውጤታማ ይሆናሉ። ይህም የአገሪቱን ዕድገት ያቀላጥፋል ብለዋል።
ምሁሩ እንደተናገሩት፤ ሰራተኞች በረጅም ጊዜ በሚከፍል ብድር ቤት ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ውጤታማ ሰራተኞችን መያዝና መሳብም ይቻላል። ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመንግስት ሰራተኞች በከተሞች ይገኛሉ። እነዚህ ቤት ካገኙ የአዕምሮ መረጋጋት ይፈጥራሉ። ከበታችነት ስሜትም ይወጣሉ። ሰራተኞች ውስጣቸው ሲረጋጋ በስራ ላይ ውጤታማ ይሆናሉ።
በከተሞች ከምግብ ሸቀጥ በሁለትና ሶስት እጥፍ በላይ እያደገ ያለውን የቤት ኪራይ ጭማሪ በማረጋጋት ህብረተሰቡን ጭምር ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ያመላክታሉ።
የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ መንግስት ደመወዝ ጨምሮ የአገሪቱን ግሽበት በመጨመር ችግር ከማምጣት ይልቅ የመኖሪያ ቤት አገልግሎት ቢያቀርብ አሁን በአገሪቱ ላለው የመንግስት ሰራተኞች ችግር መፍትሄ መሆኑን ይናገራሉ።
ዶክተር ወንዳፈራሁ፤ አሁን ላይ ለመንግስት ሰራተኛው የኑሮ ውድነት ከአቅሙ በላይ ሆኗል። መንግስት ይህን ማስተካከል ካልቻለ መቋቋም አይችልም። መንግስት ለሰራተኞቹ የደመወዝ ጭማሪ ከማድረግ ይልቅ ቤት ቢያቀርብ ለመንግስት የሚቀለውና የሰራተኞቹን ችግር የሚቀርፍ ነው።
በዚህም፤ የአገሪቱን የቁጠባ ባህል ያበረታታል፤ ሀብትም ይጨምራል። በቤት አቅርቦቱ ሂደት የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ኢኮኖሚው መነቃቃት ይፈጥራል። የቤት ኪራይን እንዲቀንስ በማድረግ የዜጎች ችግር ይቀረፋል። ኢኮኖሚን በማረጋጋትና ግሽበትን በመቀነስ ትልቅ ሚና እንደሚጫወትም አመላክተዋል።
መንግስት ለሰራተኞቹ የደመወዝ ማስተካካያ ከማሰብ ባለፈ የሰራተኛውን መሰረታዊ ችግር በማጥናት ችግሩን የሚቀርፉና በአገር ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ሚና የሚጫወቱ አማራጮችን ተግባራዊ ማድረግ ይገባዋል። ይህ አካሄድ የሰራተኞችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
አጎናፍር ገዛኸኝ