ኢትዮጵያን ይዞ በኢትዮጵያ ያልታገደ፤ አፍሪካን ብሎ በአፍሪካ ያልተወሰነ፤ አድማሰ ሰፊው አዲስ ዘመን ዓለም አቀፍ ሁነትና ክስተቶችንም በእኩል እየሮጠ ሁሉንም በጊዜና ሰዓቱ ከማኅደሩ ላይ አስፍሮታል። የዛሬው አዲስ ዘመን ድሯችንም ከእነዚሁ ትሩፋቶች መካከል በዋነኛነት ስለአንድ ጉዳይ ያስታውሰናል። ሁለቱ ቀንደኛ ባላንጦች ዩናይትድ ስቴትስና ሶቪየት ኅብረት “ጨረቃ ላይ እንገናኝ” ተባብለው ተቀጣጥረው ነበር። ሀሳቡን ያመነጩት ፕሬዚዳንት ኬኔዲ ግን ለቀጠሮው እንዳይደርሱ ገና በሦስተኛ ወሩ ተገደሉ። ኬኔዲን ማን ገደላቸው? ስለ ኬኔዲ በአዲስ አበባ…ይህን ጉዳይ በተመለከተ የወጡ ተከታታይ ዘገባዎችን እናስታውስ።
ጨረቃ ላይ እንገናኝ
በባዕድ አገር የተገናኙ የአንድ ሀገር ሰዎች እንደ ወንድማማች ይቀራረባሉ ይባላል። በበረሃ የተገናኙ መንገደኞች በቀላሉ ይዋደዳሉ። ከሠፈራችን አካባቢያችን በሄድን መጠን ከሚያጋጥመን ሰው ጋር ለመቀራረብ ያለን ፍላጎት እየጠነከረ ይሄዳል ይባላል።
ይህ ዝንባሌ በፖለቲካ ግንኙነት መካከልም ሊኖር ይችላል። በተለይ ዩናይትድ ስቴትስና የሶቪየት ኅብረት አቀራረብ ይህንኑ አይነት ዝንባሌ የተከተለ ይመስላል። በመሬት ላይ በብዙ ጉዳዮች ላይ ፈጽሞ የማይስማሙት በአውሮፓ፤ በመካከላቸው ግንብ ያጠሩት፤ በኩባ የተፋጠጡት፤ በሩቅ ምሥራቅ የተጋፈጡት ሁለቱ ኃያላን፤ ዩናይትድ ስቴትስና ሶቪየት ኅብረት ወደ ጨረቃ በአንድነት ለመጓዝ አስበዋል። ሐሳቡ ያስቅ ይሆናል። ግን ቀልድ አይደለም። በቁም ነገር የተያዘ ነው።
ሐሳቡን ያመነጩት ፕሬዚዳንት ኬኔዲ ለአሥራ ስምንተኛው ጠቅላላ ጉባኤ ባደረጉት ንግግር ነበር።
…..
የሶቪየት ኅብረት ሐሳቡን እንደተስማማበት ይታመናል። ባይሆን ኖሮ ግሮሚኮ የፕሬዚዳንቱን ንግግር በጭብጨባ አይቀበሉትም ነበር።
…….
ከጉዞው በኋላ ደግሞ ሌላ አንድ ጥያቄ አለ። በጨረቃ ላይ የሚተከለው የማን ሰንደቅ ዓላማ ይሆናል? የሶቪየት መዶሻና ማጭድ? የዩናይትድ ስቴትስ መሥመርና ኮከብ? የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት? ወይንስ በዩናይትድ ስቴትስ መሥመር ላይ ማጭድና ነጠብጣብ በማቀነባበር?
……
ወደ ጨረቃ ለመጓዝ የሚደረገው ወጭ ለብዙ ተፈላጊ ነገር ይውል ነበር። ሆኖም ሁለቱ ባላንጣዎች ለመቀራረብና ለመወዳጀት በጨረቃ በኩል ዙረው መመለስ ካስፈለጋቸው ወጭውን እንደኪሣራ አንቆጥረውም።
(አዲስ ዘመን መስከረም 17 ቀን 1966 ዓ.ም)
እጅግ አሳዛኝ የሆነው የፕሬዚዳንት ኬኔዲ ሞት
ትናንት ኅዳር 12 ቀን 1967 ዓ.ም ሌሊት በደረሰን ወሬ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ክቡር ሚስተር ኬኒዲ ዳላስ ከሚባለው ከተማ በአውቶሞቢል ተቀምጠው ሲያልፉ 3 ጥይት ተተኩሶባቸው እንደሞቱ ተነግሯል።
ይህ እጅግ አሳዛኝ የሆነው ወሬ ጋዜጣችን በእትም ላይ ሳለ ስለደረሰን፤ ዝርዝር ሁኔታውን በነገው ጋዜጣችን እንገልጻለን።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 13 ቀን 1966 ዓ.ም)
የኬኔዲ ሞት መላውን ዓለም አሳዝኖታል
የቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ዛሬ ይፈጸማል
35ኛው የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ክቡር ሚስተር ጆን ፊት ዘጀራልድ ኬኔዲ ከቴክሳስ አገረ ገዥ ከሚስተር ጆን ኮናሊ ጋር ዳላስ ውስጥ በግልጽ አውቶሞቢል ሆነው ሲጓዙ በጥይት ተመትተው በጠና በመቁሰላቸው ምክንያት ባለፈው ዓርብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ፕሬዚዳንት ኬኔዲ በፓርክ ላንዳ ሆስፒታል ውስጥ ያረፉት አንገታቸውን በጥይት ተመተው ከቆዩ ከ25 ደቂቃ በኋላ ነው።
የ37 ዓመት ዕድሜ ያላቸው እኚህ የመጀመሪያው የዩናይትድ ስቴትስ የካቶሊክ ፕሬዚዳንት፤ ከአንድ ያልታወቀ ሰው በተተኮሰ ጥይት የቆሰሉት በዳላስ የንግድ አዳራሽ ውስጥ ንግግር ለማድረግ ሲሔዱ እንደሆነ ታውቋል።
ከፕሬዚዳንቱ ጋር አብረው የነበሩት የቴክሳሱ አገረ ገዥ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ሆኖም ሕይወታቸው እንደተነገረው በአሥጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተገልጧል።
የፕሬዚዳንቱ ባለቤት ሚስስ ጃኩሊን ኬኔዲ ከባድ የኅዘን መልክ ይታይባቸው ነበር። እሳቸውም ያጣጥሩ ከነበሩት ባላቸው ጋር ወደ ሆስፒታሉ ሲገቡ ልብሳቸው በፕሬዚዳንቱ ደም ተበክሎ እንደነበር ታውቋል።
የፕሬዚዳንቱ ገዳይ ከነበረበት ሕንጻ ውስጥ ፖሊሶች አጉልቶ የሚያሳይ መነፅር ያለበት አንድ ባ-303 ሚሊ ሜትር ጠመንጃ ሦስት ቀለሀ ከአንድ መስኮት አጠገብ አግኝተዋል።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 15 ቀን 1966ዓ.ም)
ስለ ኬኔዲ ዕረፍት በአዲስ አበባ
የተደረገ ጸሎተ ፍትሐት
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋ ወሰን በተገኙበት ኅዳር 15 ቀን ትናንት ስለ ክቡር ሚስተር ጆን ኦፍ ኬኔዲ ዕረፍት በመንበር ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት ተደርጓል።
….
ይህ ሁኔታ በቅርብ የሚያውቋቸውንና በዝና የሚያውቋቸውን ሁሉ ልብ በጥልቅ የኀዘን ፍላፃ እንዲወጋ ያደረገው፤ ለሰው ዕድል ፈንታ የሆነውን የሞት ፅዋ በመቀበላቸው ሳይሆን፤ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ ድረስ በደከሙበት በተቀደሰው ዓላማቸው ምክንያት ነው።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 1966ዓ.ም)
ጥያቄ አለኝ
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
* እነዚህ መብት አለን እያሉ በፆታ ሳይሆን በሱሪ ተወጥረው ሞለል ሞለል የሚሉት የሴት አጋንድሮች የጀግኖችን ሱሪ ከማበላሸታቸው በላይ፤ ትንባሆ የሚምጉት መብት አለን ብለው ነው?
ሙላቱ መንገሻ(ከክብር ዘበኛ)
– መብት አለን ብለው ሳይሆን አማረብን ብለው ነው።
* ጓደኛዬ ስኳር የሚሠራው ከእንጨት ነው ቢለኝ አይደለም አልኩትና ተወራረድን። በኋላ ሸንኮራ እራሱ እንጨት ስለሆነ ተረተሃል አሉኝ። ዳኛችንም ፊታውራሪ ኃይሉ በፈቃዱ እውነቱን ነው መረታት አለብህ ብለውኝ የተወራረድንበትን 30 ብር ለጓደኛዬ ሰጡት። ልረታ ይገባኛል? ይግባኜን ስማኝ።
– መረታት አይገባህም። ምክንያቱም ሸንኮራ አገዳ የሣር ወገን ነው እንጂ የእንጨት ወገን አይደለምና ነው።
….
ሸንኮራውን እንጨት ነው ያሉህ እንዲያው ነውና ፊታውራሪ የሰው ገንዘብ ይመልሱ።
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 1966 ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 9 ቀን 2016 ዓ.ም