አዲስ አበባ፡– የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ብቻ ሲያቀርበው የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በግል ባንኮችም በኩል ለማቅረብ የወሰነው ውሳኔ የወጪና ገቢ ንግድን ለማመቻቸት እንደሚያግዝ ተጠቆመ ።
በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር አረጋ ሹመቴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ውሳኔው የውጭ ምንዛሬን በቀላሉ ለማግኘት በማስቻልና የንግዱን ሂደት በማፋጠን የወጪና ገቢ
ንግዱ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው ያደርጋል ። በወጪና ገቢ ንግዱ ላይ ከተጋረጡት ዋነኛ መሰናክሎች መካከል አንዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት በመሆኑ ርምጃው ችግሩን በመጠኑም ቢሆን እንዲቃለል ያደርገዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፤ ውሳኔው ሙስናን ከመቀነስ አኳያም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ። “ከአንድ ቋት ብቻ ይገኝ የነበረ የውጭ ምንዛሬ ከሌሎች ምንጮችም መገኘት ሲችል የውጭ ምንዛሬውን ለማግኘት ሲባል የሚፈፀሙ እንደ ጉቦ መስጠት ያሉ ሕጋዊ
ያልሆኑ የጎንዮሽ አሰራሮች ይቀንሳሉ” ብለዋል፡፡ የግል ባንኮች ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ክምችት እንዲያገኙ እንደሚረዳቸውም ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከአንድ ቦታ ብቻ ይገኝ የነበረ የውጭ ምንዛሬ በብዙ ባንኮች በኩል ሲከፋፈል ባንኮቹ ሀብቱን በስርዓት የማያስተዳድሩት ከሆነ ብክነት ሊፈጠር ስለሚችል የባንኮቹ የቁጥጥርና የአስተዳደር ስርዓት ጠንካራ መሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡
ይሁን እንጂ፤ ውሳኔው የውጭ ምንዛሬን በቀላሉ ለማግኘት በማስቻል የወጪና ገቢ ንግዱ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው ማድረጉ በረጅም ጊዜ የሚገኝ ውጤት በመሆኑና ለባንኮች የሚቀርበው የውጭ ምንዛሬ አዲስ የተፈጠረ ሀብት ባለመሆኑ የውጭ ምንዛሬን ችግር በዘላቂነት ሊፈቱ በሚችሉ ሌሎች ርምጃዎች ላይ አተኩሮ መስራት እንደሚገባም ዶክተር አረጋ ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 21/2011
አንተነህ ቸሬ