በክልሉ ለመኸር ወቅት የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ለአዝመራው ስብሰባ ትኩረት ተሰጥቷል

ግብርና የምጣኔ ሀብት መሠረቷ ለሆነው ኢትዮጵያ አሁን ያለንበት ወቅት አዝመራ የሚሰበሰብበት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የሚጀመርበት ነው። የግብርናው ምርትና ምርታማነት በእጅጉ ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ርብርብ ውስጥ ይህ ወቅት ትልቅ ስፍራ ይሰጠዋል፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተደረገ ባለው ጥረት እንደ ሀገር ለ2015/16 የምርት ዘመን ሰፊ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ሥራ መገባቱ ይታወቃል። ለእዚህም ምንም እንኳ በአንዳንድ ክልሎች በማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ቅሬታዎች ሲነሱ የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ለምርት ዘመኑ 21 ቢሊዮን ብር ለማዳበሪያ ግዥ ድጎማ ማድረጉ ይታወሳል።

በምርት ዘመኑ የመኸር ወቅት ብቻ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር የተሸፈነ ሲሆን፣ ይህን ሰብል መሰብሰብ ከተጀመረ ቆይቷል። አሁን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የመኸር ሰብል አሰባሰብ በሀገሪቱ በ2015/16 የምርት ዘመን ወደ 17 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ነው በዘር የተሸፈነው። በዚህም የእቅዳችን 101 በመቶ መፈጸም ችለናል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀው የምርት አሰባሰቡን አስመልክተው በተለይ ለአዲስ ዘመን ሰሞኑን እንዳሉት፤ በተለይ በቆላማ እና ወይና ደጋ አካባቢዎች የደረሱ ሰብሎችን ቶሎ የመሰብሰቡ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በዚህም አሰባሰቡም እስከ ታኅሣሥ አንድ ድረስ ክልሎች በባሕላዊ የአዝመራ አሰባሰብ ወደ ዘጠኝ ነጥብ ስድስት ሄክታር፣ በኮምባይነር ደግሞ ከ844 ሺ 922 ሄክታር በላይ በድምሩ 10 ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ያለ ሰብል ተሰብስቧል።

ምርት አሰባሰቡም በባሕላዊ መንገድ ከሆነ ተሰብስቦ ተክምሮ ይቆይና ነው የሚወቃው። በኮምባይነር ከሆነ ደግሞ ወዲያው እየተሰበሰበ ይወቃል። ከዚህ አስር ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ የአራት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬቱ ሰብል ተውቅቷል። ከዚህም 114 ሚሊዮን 239 ሺ 964 ኩንታል ምርት ተገኝቷል።

አዝመራ የመሰብሰቡ ሥራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት አቶ ከበደ፣ በባሕላዊ መንገድ ከተሰበሰበው አብዛኛው ገና አልተወቃም፤ ተክምሮ ነው ያለው ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ አንዳንድ ያልደረሱ ሰብሎች አሉ፤ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊኖር ይችላል፤ ይህንንም ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት በሰጠን የአየር ፀባይ ትንበያ መረጃ መሠረት ፀሐያማና ነፋሻማ በሆነ ጊዜ አርሶ አደሩ፣ አመራሩ፣ አጠቃላይ ኅብረተሰቡ፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኛው በቅንጅት ቶሎ የመሰብሰብና ጎተራ የማስገባት ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በኩል እንዲሠሩ ምክረ ሀሳብ ተሰጥቷል፤ በዚያ መሠረትም እየተሠራ ነው።

ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ ግሪሳና የመሳሰሉትን ተባዮች በመከላከል በኩልም ጉዳት ከመድረሱ በፊት ምክረ ሀሳቦችን ለአርሶ አደሩና ለግብርና ባለሙያው እንዲደርሱ መደረጉን አቶ ከበደ ገልጸዋል። አየሩ ፀሐያማ፣ ደረቃማና ነፋሻማ ሲሆን አርሶ አደሩ ሰብሉን እንዲሰብሰብ ማድረግ ላይ በሚገባ መሠራቱንም ጠቅሰው፣ እሰከ አሁን በዝናብ ሳቢያ ሳይሰበሰብ የቀረ፣ ጉዳት የደረሰበት ሰብል አለ ተብሎ ሪፖርት የተደረገ ነገር እንደሌለም ተናግረዋል።

የአዝመራ መሰብሰቡ ሥራ በክልሎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል። በአማራ ክልልም አዝመራ የመሰብሰቡ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታውቋል። በክልሉ በ2015/16 የምርት ዘመን በመኸር እርሻ አምስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምሳሉ ጎባው ጠቅሰው፣ ከዚህ ውስጥም 160 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ይገልጻሉ፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ወቅቱ ምርት የሚሰበሰብበት እንደመሆኑ በክልሉ እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥም በሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር ላይ የሚገኝ ሰብል ተሰብስቧል፤ ይህም እንደሚሰበሰብ ከሚጠበቀው ምርት 68 በመቶ ያህል ይሆናል። የምርት አሰባሰብ ሂደቱም በሁለት አይነት መንገድ እየተከናወነ ሲሆን፣ አንደኛው ተለምዷዊ የሆነው ወይም ባሕላዊ መንገድ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዘመናዊው ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምርቱ የሚሰበሰብበት መንገድ ነው፡፡

ተለምዷዊ በሆነው በባሕላዊ መንገድ ሲባል አርሶ አደሩ እርስ በእርስ በመተጋገዝና በመተባበር ምርቱን በጉልበቱ የሚሰበስብበት መንገድ መሆኑን ኃላፊው ጠቅሰው፣ በዘመናዊ መንገድም እንዲሁ ምርት መሰብሰቢያ ማሽን ኮምባይነር በመጠቀም ምርቱ እየተሰበሰበ መሆኑን ገልጸዋል። ለዚህም ክልሉ 29 የኮምባይነር ማሽኖችን አሠማርቶ ከፍተኛ ሥራ እየሠራ መሆኑን ነው ያስረዱት።

እነዚህ ዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ ማሽኖች በተለይም በምሥራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃምና በሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ላይ ሰፊ ሥራ እየሠሩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አምሳሉ፤ በክልሉ በሰባት ሺ ሁለት መቶ ሄክታር ያህል መሬት ላይ የሚገኝ ምርት በኮምባይነር መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ክልሉ በምርት ዘመኑ ያመረተውን ምርት ለመሰብሰብ ባቀደው ልክ ሰብስቦ አላጠናቀቀም፤ ሌላው ደግሞ በምርቱ የዕድገት መጠን ልክ በቀጣይ ይሰበሰባል። በቀጣይ እስከ ጥር መጨረሻና የካቲት መጀመሪያ ድረስ የሚሰበሰብ ምርት ይኖራል። ጥራጥሬን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎች በዚሁ ወቅት ነው የሚሰበሰቡት።

አሁን አርሶ አደሩ ያለውን አቅም በሙሉ አስተባብሮ በምርት ስብሰባ ላይ እየሠራ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህም ዋናው ምክንያት የእርሻ ሥራውን ካቋረጠ በእጅጉ እንደሚጎዳ ማወቁ ነው ብለዋል። ስለሆነም የክልሉ ግብርና ቢሮ አርሶ አደሩ አቅሙን አሟጦ አቅም በፈቀደለት ልክ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። አርሶ አደሩ አሁን በክልሉ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ውስጥም ሆኖ የግብርና ሥራውን መሥራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል፡፡

አቶ አምሳሉ እንዳብራሩት፤ አርሶ አደሩን በማቀናጀትና በማስተባበር እንዲሁም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ረገድ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ክልሉ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፤ ለዚህም ቢሮው በርካታ ስልቶችን በመጠቀም ድጋፍ እያደረገ ነው። በየአካባቢው ያሉት የግብርና ባለሙያዎች በክልሉ ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች በአካል አርሶ አደሩ ዘንድ በመድረስ አርሶ አደሩን እየደገፉ ናቸው።

በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የተለያዩ የግብርና መረጃዎች ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ እየተደረገም ነው። ግብርና ዓመቱን ሙሉ የሚሠራ ሥራ እንደመሆኑ ከግብርና ዘመን አቆጣጠር ጋር በማገናኘት በሰብል ስብሰባ፣ በመስኖ ሥራ፣ ችግኞችን በመንከባከብና በመከታተል እንዳይጎዱ፣ እንዳይነቀሉና እንዲጸድቁ የማድረግ መሰል ሥራዎችን አስመልክቶ ተገቢውን መረጃ ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ተደራሽ እየተደረገ ነው።

የግብርና ሥራውን ሊደግፉና ሊያሻሽሉ የሚችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከመጠቀም አንጻርም እንዲሁ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድጋፎች ይደረጉ እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ ድጋፍ ግን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ዘንድሮ በክልሉ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት መቀነሱን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ከኦሮሚያ ክልል የሚመጡ ኮምባይነሮችን በመጠቀም ከሌሎች አሻጋሪ ከሆኑ ዞኖች ጋር በቅንጅት ይሠራ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን እንዲህ አይነቱ የመደጋገፍና የመረዳዳት ሁኔታ መቀነሱን ገልጸዋል።

በክልሉ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብና የግሪሳ ወፍም ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አምሳሉ፤ የመከላከል ሥራውም ተጠናክሮ መሠራቱን ገልጸዋል፡፡ በዚህም ቢሮው ማድረግ የሚገባውን በሙሉ ማድረጉን ተናግረዋል።

‹‹እንደ ግብርና ቢሮ የግብርና ሥራ መቆም የለበትም በማለት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት እየተሠራ ነው። የትኛውም ነገር ይፈጠር ግብርና ማለት የቀይ መስቀል ሥራ ነው። ቀይ መስቀል ሊሞት ያለና አደጋ የደረሰበት ሰው እንደሚያድን ሁሉ ግብርናም ምግብ አምራች እንደመሆኑ ሥራው አይቆምም፤ መቀጠል አለበት›› በሚል እምነት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አምሳሉ እንደተናገሩት፤ ከሜካናይዜሽን አኳያ አርሶ አደሩ የሚፈልገው ምን እንደሆነ በመለየት፤ የተለያዩ ማሽኖች የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሠረት በማድረግ እንዲቀርቡ ይደረጋል። ከኦሮሚያ፣ ከደቡብም፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝም የሚመጣ ከሆነና አስቻይ ሁኔታዎች ካሉ እንዲመጣ ይደረጋል።

ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብና በግሪሳ ወፍ ምክንያት የደረሰውን የጉዳት መጠን አስመልክቶም ከወረርሽኙ በኋላ ራሱን የቻለ የባለሙያ ቡድን ተዋቅሮ መረጃ እየተሰበሰበ መሆኑን አቶ አምሳሉ ጠቁመዋል። የግሪሳ ወፍም ሆነ የአንበጣ ወረርሽኝ ስላደረሰው የጉዳት መጠን አሁን መናገር እንደማይቻል አስታውቀዋል።

እንደዚህ አይነት ክስተቶችን ለመቀነስ የግብርና ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት የአደጋ ጊዜ ኮሙኒኬሽን እቅድ አለው ያሉት አቶ አምሳሉ፤ ለምሳሌ አንበጣ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ ተምች ቢከሰት ተብሎ የሚዘጋጅ ራሱን የቻለ እቅድ እንዳለም አስታውቀዋል። በዚህም ላይ የሕዝብ ግንኙነቱ ተከታታይነት ያለው እና ኅብረተሰቡ እንዳይወዛገብ ማድረግ የሚችል መረጃ ይሰጣል ብለዋል፡፡

ከሰብል ብክነት ጋር በተያያዘም አርሶ አደሩ በጭቃ ተሰቃይቶ ብርድ፣ ዝናብ ቁርና ፀሐይ ተፈራርቆበት ካመረተው ምርት አብላጫው ይባክናል ያሉት አቶ አምሳሉ፤ አርሶ አደሩ በብዙ ልፋትና ድካም ካመረተው ምርት ከ33 በመቶ በላዩ እንደሚባክን ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ገልጸዋል። በተለይም የብርእ ሰብል ቅንጣት ይቆረጣል፤ ከመሬት ንቃቃት ይገባል፤ በከብቶች ሲወቃም እንዲሁ በብዛት ይባክናል ብለዋል።

እሳቸው እንዳሉት፤ በውቂያ ወቅትም በበሮች ሽንትና እበት ይበላሻል እንዲሁም ከቦታ ቦታ ሲጓጓዝም እንዲሁ ይባክናል። ስለዚህ ይህንን ብክነት ለመቀነስ ሁሉም ሰው መረባረብ ይኖርበታል። ሰብሉን በጥንቃቄ፣ ከብክነት በፀዳ መልኩ መሰብሰብና ለገበያ ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡

በብዙ ድካምና ልፋት የተገኘን ምርትና ሀብት በአግባቡና በትክክል መጠቀም ካልተቻለ አርሶ አደሩም ሆነ ከተሜው ተጠቃሚ አይሆንም ያሉት አቶ አምሳሉ፤ ማኅበረሰቡ ብዙ ወጪ የሚጠይቁ እንደ ድግስ ያሉትን መቀነስ እንደሚገባም ተናግረዋል። ስለዚህ ስለምርት ብክነት መከላከል ኢኮኖሚያዊ ጠቀሚታ አርሶ አደሩ እንዲገነዘብ ሚዲያው ማስረዳትና ማስገንዘብ እንዳለበትም አስታውቀዋል።

አማራ ክልል በጣም ትልልቅ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች እንዳሉ ጠቅሰው፣ አርሶ አደሩ እነዚህን የከርሰምድርና የገጸ ምድር ውሃዎች በመጠቀም ሊያጣ የሚችለውን ምርት መተካት ከዚያ በላይም ማምረት እንዳለበት አስታውቀዋል። ይህን አስፈላጊ፣ ወሳኝና የማይቆም የግብርና ሥራን በትብብርና በቅንጅት መሥራት ተገቢና የግድ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሰኞ ታኅሣሥ 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You