በስድስት ወራት በኤሌክትሮኒክስ የገንዘብ ዝውውር ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ተዘዋውሯል

አዲስ አበባ፡- ባለፉት ስድስት ወራት በዲጂታል ፋይናንሲንግ ሥርዓት ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ሊዘዋወር ችሏል ሲል የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ::

በኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሮኒክስ መንግሥት ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አቢዮት ሲናሞ (ዶ/ር) ለኢፕድ እንደገለጹት፤ በስድስት ወራት በዲጅታል ባንኪንግ ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ዝውውር ተደርጓል::

የዲጂታል ፋይናንሲንግ ሥርዓት ከተጀመረ አምስት ዓመታትን ማስቆጠሩን በመጥቀስ፤ በአሁኑ ወቅት የነዳጅ ክፍያን ጨምሮ የመንግሥት ድርጅቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እየተጠቀሙ መምጣታቸው የገንዘብ ዝውውር መጠኑ እንዲያድግ አድርጓል ሲሉ አስረድተዋል::

የኢንተርኔት ባንኪንግን ጨምሮ የዋሌት የክፍያ ሥርዓት እያደገና እየተስፋፋ መምጣቱን የገለጹት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ አጠቃላይ የክፍያ ሥርዓቱን የተቀናጀ ለማድረግ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል እየተሠራ ይገኛል ብለዋል::

በዚህም ከመመሪያዎች አንጻር በብሄራዊ ባንክ የተዘጋጀው የዲጂታል ፋይናንሲንግ እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተዘጋጀው ለተጠቃሚዎች ከለላ የሚሰጡ አዋጆች በዲጅታል ፋይናንሲንግ ለሚደረገው እንቅስቃሴ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል::

ዶክተር ኢንጂነር አብዮት እንደተናገሩት ፤ ተገልጋዩ ከመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት በኤሌክትሮኒክስ አማራጭ ካመለከተ በኋላ ክፍያ ለመፈጸም በአካል እንዲቀርብ ይደረጋል:: በመሆኑም አሠራሩን በማስፋፋት የተሳለጠ ለማድረግ እና እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እየተሠራ ነው::

የዲጅታል ፋይናንሲንጉ የተፈለገውን ለውጥ እንዲያመጣ መሠረተ ልማቶችን ማሟላት ወሳኝ ነገር ነው :: በዚህ ረገድም የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት እንዲያስችል ከመንግሥት በኩል ግብረኃይል ተቋቁሞ እየተሠራበት ይገኛል ሲሉ አስረድተዋል::

የዲጂታል ፋይናሲንግ መጠቀሙ ከባንክ ውጭ የሚዘዋወር ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመጣ አድርጓል:: በዚህም የገንዘብ ዝውውርን መንግሥት እንዲቆጣጠር እና ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት እድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ ተገልጋዩ ጊዜውን እንዲቆጥብ የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል::

መሪ ሥራ አስፈጻሚው እንደተናገሩት ፤ ከተግዳሮት አንጻር የኢንተርኔት ተደራሽነት ችግር ፤ ያሉት የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች ውስንነት እና ማህበረሰቡ በዲጅታል ፋይናንሲንግ ላይ የግንዛቤ እጥረት ያለው መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው::

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ላይ የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እየሠራበት ይገኛል ያሉት ዶክተር አብዮት፤ በዚህም የኔትወርክ ተደራሽነት ላይ እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እየተሠራበት ይገኛል ብለዋል::

የመጡ ውጤቶች አበረታች ቢሆኑም በሀገሪቱ ከፍተኛው የማህበረሰብ ክፍል በገጠር አካባቢዎች የሚገኝ እንደመሆኑ፤ የኔትወርክ እና የሲስተም ማስፋፋት ሥራ በእነዚህ አካባቢዎች ትኩረት ተደርጎ ይሠራል ሲሉ ገልጸዋል::

አመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 7 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You