/የኢትዮጵያ አየር ኃይል 88ኛ የምስረታ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተቋሙ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ ሙሉ ቃል /
ጥያቄ፤- የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከተመሠረተ 88 ዓመታትን አስቆጥሯል። ያለፉት 88 ዓመታት ጉዞው ምን ይመስላል ?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ የገባው ከ88 ዓመት በፊት ነው። አንዳንዶቹ ሀገሮች አውሮፕላን ምን እንደሚመስል በማያውቁበት ጊዜ እኛ ግን አውሮፕላኑን ታጥቀናል። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ አውሮፕላን ያረፈው ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም ነው። ከዚያ በኋላ የተለያዩ ክስተቶች ነበሩ።
አውሮፕላኑ እንደመጣ ፖስታ እና ባለሥልጣን የማመላለስ ሥራ ከመሥራት በተጨማሪ በውጊያም ተሳትፎ ነበር። በራስ ጉግሳ ወሌ እና በንጉሱ መካከል በነበረው ጭቅጭቅ፤ ወረቀት የመበተን እና ቦንብ የመጣል ሥራዎች አከናውኗል።
ከዛ በኋላ በጣሊያን ወረራ ምክንያት የገባው የአየር ኃይል ትጥቅ በመሉ በመሬት ላይ እንዳለ ወደመ። ከወረራ በኋላም አየር ኃይሉን እንደገና የማንሠራራት ሥራ በስውዲን እና በአሜሪካ መንግሥታት ድጋፍ ተሠርቷል።
በንጉሱ ዘመን የነበረው አየር ኃይል፤ በተለይ ወደ ምዕራባውያን ትጥቅ ያደላ እና ከምዕራባውያኖች ጋር የሚያገናኙ ትጥቆችን የታጠቀ ነበር ። በዚያ ወቅትም በጣም ትልቅ ገድሎች ተፈፅመዋል። የመጀመሪው በኦጋዴን የሶማሌ ወረራንም ያከሸፈው ይኸው ተቋም ነው።
የደርግ መንግሥት ወደ ሥልጣን ሲመጣ የርእዮተ ዓለም ለውጥ መጣ። ምዕራባውያን የሶማሊያን ጎራ መደገፍ መጀመራቸው እና እኛ የጠየቅናቸው ትጥቆች ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፤ የደርግ መንግሥት ወደ ምሥራቅ ፤ወደ ሶቬየት ሕብረት ዞሮ በርካታ ትጥቆች እንደ ሚግ ሃያ አንድ፣ ሚግ ሃያ ሶስት፣ ራዳሮች መታጠቅ ቻለ ። ይህን በ1969ዓ.ም እና በ1970 የነበረው የሶማሊያ ወረራን መቀልበስ ያስቻለ ነው ።
በወቅቱ ድሬዳዋ ላይ የአየር ማረፊያ ክልል (ኤር ቤዝ) ብለን የመሠረትነው ቦታ ድረስ የሶማሊያ ታንኮች አፍንጫ ደርሰው ነበር። እርሱን ከአየር ወደ ምድር በመተኮስ ውጊያን መቀልበስ የቻለው ይኸው ተቋም ነው። እንደሚታወቀው በደርግ ዘመን ከኤርትራ እና ከወያኔ ጋር የእርስ በእርስ ጦርነት ላይ ነበርን።በጦርነቱ ደርግ ሲወድቅ ተቋም ሙሉ ለሙሉ ፈረሰ።
ግንቦት 1983 ዓ.ም በራሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ተበተኑ።ወደ ኬንያ፣ ወደ ዑጋንዳ፣ ወደ ጅቡቲ፣ ወደ ሶማሊያ፣ ወደ ሱዳን እና ወደ የመን ተበተኑ። ሰውም ትጥቆቻችንም በዛው መጠን ተበተኑ። ከዛ ከአንድ ዓመት በኋላ በተቻለ መጠን መልሶ የማሰባሰብ ሥራ ተሠራ።ሥልጠናዎችንም ለማካሔድ ሙከራ እየተጀመረ እያለ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት መጣ።
የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ሀገሪቷን ከእንቅልፍ የማባነን እና የነበሩ መሪዎችም ‹‹ይሄ ነገር ያስፈልጋል እንዴ›› /የአየር ኃይሉ/ ብለው እንዲያስቡ እድል የፈጠረ ነበር። አሁን የምናያቸው የተወሰኑ ትጥቆች እንደአዲስ የገቡበት ያ ጊዜ ነበር። ተቋሙም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ያደረጉት እነዚሁ ትጥቆች ናቸው። ሌላው ቀርቶ ተቋሙ ከዛ በፊት አልሸባብ በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ ባወጀ ጊዜ ከፍተኛ ጀብድ የፈፀመ ተቋም ነው።
በተለይም ከ2000 ዓ.ም ወዲህ የተቋሙ ግንባታ ወደ ቁልቁለት የሄደበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ከዛ በኋላ ደግሞ የለውጡ መንግሥት በሰጠው ትኩረት አየር ኃይል በሰው ኃይል፤ በትጥቅ፤ በመሰረተ ልማት ራሱን እየገነባ ነው። በአጭሩ አውሮፕላን ኢትዮጵያ ውስጥ ከገባ ጀምሮ ብዙ ታሪኮች አሉ ። ከመንግሥት መንግሥት ከነውጣውረዱ ተሸጋግሮ እዚህ ደርሷል ማለት ይቻላል።
ጥያቄ ፦ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከለውጡ በፊትና በኋላ የነበረው ቁመና እንዴት ይገለጻል ፤ ምን ዓይነት ተጨባጭ ሥራዎችን ተገበረ ምንስ ውጤት ተገኘ?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- ከለውጡ በፊት ስለ ተቋሙ የነበረውን አስተሳሰብ ማየት በጣም ተገቢ ነው ። እኔ እስከማውቀው በደርግ ዘመን በተለይም 1982 ዓ፣ም የኢትዮጵያ አየር ኃይል በከፍተኛ ደረጃ የተነቃቃበትና ጫፍ የደረሰበት ዘመን ነው።ይህም ሲባል አየር ኃይሉ በበረራም በትጥቅም በዘመኑ ትልቅ ደረጃ ደርሶ ነበር።
ውድቀቱም ከዚሁ ነው የሚነሳው። አየር ኃይሉ በቀላሉ አሰልጥኖ የማያገኛቸው እንደ ምድር ኃይል በተወሰኑ ወራት አሠልጥኖ የማያደርሳቸው ባለሙያዎች ተበተኑበት። በቀላሉ የማያገኘውንም ትጥቅ አጣ።ተቋም ተበተነ ማለት መልሶ ለማደራጀት በጣም ብዙ ሀብትና ጊዜ ይጠይቃል።
ተቋሙን መልሶ ለማደራጀት የተሞከረው ሥራ በአግባቡ አልነበረም። ይህ ለምን ሆነ ሲባል ደግሞ ከፖሊሲና ስትራቴጂ ነው የሚነሳው። በወቅቱ የነበረው አገዛዝ አየር ኃይል ያስፈልጋል፤አያስፈልግም በሚል ጥርጣሬ ውስጥ ነበር የነበረው። ችግሩም የሚነሳው ከዚህ ነው። ወደመጨረሻ አካባቢ አየር ኃይል አያስፈልግም ወደሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ።
በዚህም ምክንያት የማሠልጠኛ ትምህርት ቤቱ ሙሉ በሙሉ ተዘጋ፤ ማቴሪያሎቹ፤ መጽሐፍቱ ተጭነው ወደ ኢንጂነሪግ ኮሌጅ ሄዱ። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ተቋሙ እየወደቀ መጣ ።በመካከል ደግሞ ቢጀመር ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚል ሃሳብ ደግሞ መጣ። በጠቅላላው ግን በተቋሙ ዙሪያ የነበረ ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚምታታ ነበር
ሌላው አየር ኃይል ላይ ሙያዊ አመራር ያስፈልጋል። ለምሳሌ ባህር ኃይል ሄደሽ ባህር ኃይል እንዴት ይመራል? እንዴት ይደራጃል? እንዴት ይዋጋል ? ለሚሉት ጥያቄዎች የራሱ አውደ የውጊያ ጽንሰ ሃሳብ አለው። አየር ኃይልም ባለሙያ እንዴት ይሰለጥናል? እንዴት ይደራጃል? ትጥቅ እንዴት ይዘጋጃል? በአየር እንዴት ትዋጋለህ ?የሚለው የራሱ አውድና ሳይንስ አለው። ይህ ነገር ነው የተሳተው። አውዱን ያወቀና የሚመጥን ሳይንሳዊ አቀራረብ ባለመኖሩ ነው አየር ኃይል ለውድቀት የተዳረገው።
ይህ ምን ማለት ነው? አውሮፕላን ገበያ ላይ ስላማረ አይገዛም ፤ የጥገና ሲስተሙ ምን ይመስላል? ቀጣይነት ያለው ቴክኖሎጂ ምን ይመስላል? መለዋወጫዎቹ ምን መልክ አላቸው? ለዚህ አውሮፕላን የሚያስፈልገው መሰረተ ልማት ምንድን ነው ?የሚሉት ነገሮች በጣም በጥልቀት መጠናትና መታወቅ አለባቸው፤ ገንዘብ ወይም ቦታ አለኝ ተብሎ ብቻ አይመጣም። እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች በአግባቡ አለመታየታቸው አየር ኃይልን አዳክመውታል ።
እኔ እንደ አየር ኃይል አዛዥ ተሹሜ ቢሮ ስገባ ያየሁት ነገር ያለፉትን ጊዜያት እንደ ጨለማ ዘመን እንዳስብ አድርጎኛል። ይህንን የምለው ያለፉትን አመራሮች ለመውቀስ ራሴን ከፍ ለማድረግ አይደለም፤ ተጨባጭ መረጃ አለ። ለምንድን ነው እንደዛ የምለው ከመጀመሪያው የማሠልጠኛ አውሮፕላን ብነሳልህ ፤አውሮፕላኖቹ ከገቡ 40 ዓመት ሞልቷቸዋል፤ እድሜያቸውን ጨርሰው ቆመዋል።
የሚከፋው ነገር ደግሞ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ተመልምለው መጥተው ስልጠናቸውን ለማካሄድ የሚጠባበቁ ተማሪዎች ነበሩ።እነዚህ ተማሪዎች 7 ዓመት ሳይበሩ ለመጠበቅ ተገደዋል። እነዚህ ዜጎች ወይ ሄደው ትምህርታቸውን አልተማሩ ወይ እዚህ በራሪ ሆነው ሀገሪቱን አልጠበቁ ። ይህ እንግዲህ በዜጎች ላይ መጫወት ማለት ነው። አውሮፕላኑ ቆሟል የሚሠለጥን ሕዝብ ደግሞ ተሰልፏል።
ሁለተኛ የመሠረታዊ ጀት ማሠልጠኛው እድሜውን ጨርሷል ሙሉ በሙሉ ቆሟል። እዛጋም ለመሠልጠን ወጣቱ ተሰብስቧል። ወይ ወደ ውጭ ልከን አላሰለጠንን ወይ እዚህ ውስጥ አቅም ኖሮን አላሰለጠንነው፤ ከፍተኛ ችግር የነበረበት ነው። ወደተዋጊ ብንመጣ አሁን ዛሬ የምናያቸው ተዋጊዎች በሙሉ መሬት ላይ ናቸው፤መብረር አይችሉም። ከዓመት ዓመት በረራ ሳይበር የሚያልፍ በራሪ አለ። ምንደነው የሚሠራው ወይ ቢሮ ሥራ አልሠራ ፤ዝም ብሎ ቁጭ ብሏል። ይህ ሀብት / ሪሶርስ ባለመኖሩ ነው።
ወደ ትራንስፖርት ስንመጣ ትራንስፖርት ሄቪ ትራንስፖርት የምንለው በራሪ የለም። አይሮፕላኖቹም የሉም፤ ካሉም ቆመዋል። ሂሊኮፍተር በኢትዮጵያ ታሪክ ሰብለ የምትባለዋ አንዷ ናት። በሶሻል ሚዲያ እንድትታወቅ አድርገናል። ሰብለ ተብሎ ስም የወጠላት ምክንያት ቀለም የምንቀባበት ጊዜ አጥተን ነው። ከቦታ ቦታ ስንወረውር ያው የኛ ሀገር ሶሻል ሚዲያ ሰብለ ብሎ ስም አወጠላት። እሷ ናት የነበረችው አሷም አሁን ለከባድ ጥገና ገብታለች። ይሄን ሁሉ ደምረህ ስታየው ከትጥቅ አንፃር አስቸጋሪ ነበር።
ሁለተኛው ከሰው ኃይል አንፃር ነው። የሰው ኃይል እንደተባለው በከፍተኛ ደረጃ የሠራዊትና የፖለቲካ ጋብቻ የተፈፀመበት ነው። ሠራዊት ስለፖለቲካ ነው የሚያወራው፤ ስለ ኢህአዴግ ነው የሚያወራው። ስለሆነ ተቃዋሚ ድርጅት ነው የሚያወራው፤ እንጂ ስለ በራሪው ስለሙያው አይደለም የሚያወራው፤ ቴክኒሺያን ስለሙያው አይደለም የሚያወራው። ስለብሔር ነው የሚያወራው። እና የሰው ኃይል በአስተሳሰብ መከፋፈል ሌላ ፈተና ነው። ይሄን ወደ አንድ ማምጣት ከዚህ ማውጣት ሌላ ፈተና ነው።
ሦስተኛ የውጊያ መሠረተ ልማት ነው። ዛሬ ያያችኋቸው የአውሮፕላን ማቆሚያ ሀንጋሮች መንገዶች ኤሌክትሪክ አካባቢውን ያያችሁት በሙሉ ምናልባትም ከሁለት ዓመት በፊት ብትመጡ ይሄን ሳይሆን ሌላ ገፅ ነበር የምታዩት። ይሄን ማንም በዚህ ያለፉትም በተለያየ ጊዜ መጥተው የሚጎበኙትም ወዳጆቻችንም የሚመሰክሩት ነው።
አውሮፕላን ገዝተህ የምትጠግንበት ቦታ ከሌለህ፤የምታቆምበት ከሌለህ፣ መለዋወጫዎችን የምትጠግንበት ሾፕ ከሌለህ፤ሰውን የምታሰለጥንበት ቦታ ከሌለህ ምንድነው ትርጉሙ። የውጊያ መሠረተ ልማት የምንለው በጣም ከፍተኛ ችግርና ውድመት የነበረበት ነው። ይሄ ሁኔታ ከለውጡ ጋር አብሮ ተለውጧል። ለውጡ ደግሞ በዚህ ረገድ የፖሊሲና ስትራቴጂ ለውጥ አምጥቷል።
አየር ኃይል ያስፈልገናል ብቻ ሳይሆን ከአሁን በኋላ ሊያጋጥመን የሚችለው ጦርነት የአየር ኃይል ወይ
የሚሳኤል ነው። ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም። አሁን በተጨባጭ እያየን ያለነው በሀገሮች መካከል የሚደረግ ውጊያ ወይ ሚሳኤል ነው ወይ አውሮፕላን ነው ወይ ዩኤቪ ነው ወይ ሳይበር ነው።
ትዝ የሚለኝ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ፤ መጀመሪያ የሰበሰቡን ጊዜ ከአሁን በኋላ እንደ ድሮው ምሽግ ቆፍረን ታንክና መድፍ አንጋግተን የምንዋጋበት ዘመን አብቅቷል። አምስተኛ ትውልድ የውጊያ ዘመን ላይ ነን ብለው እስከ ስድስተኛ ትውልድ አብራርተውልናል።
በመንግሥት በኩል ዘመናዊ አየር ኃይል መገንባት አለብን የሚል ትልቅ የፖሊሲ ሽፍት ተደርጓል። የአስተሳሰብ ለውጥ የመጣው እዚህ ጋ ነው። ይህ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቷ ባላት አቅም በጀት የመመደብ፤ በቅርብ የአመራር ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ሥራ ተሠርቷል። ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጀምሮ እስከ ክቡር ጦር ኃይሎች ኢታማጆር ሹም ከፍተኛ ክትትል ነው እየተደረገ ያለው።
እሱ ብቻ ሳይሆን እንደ አየር ኃይል “ቲም” መለወጥ አለብን፤ ይሄን ተቋም መቀየር አለብን የሚል ቁርጠኝነት ይዘን ነው የተነሳነው። ወደ ሥራ ስንገባ ራእዮቻችን ተልእኮዎቻችን እሴቶቻችን በሚገባ ቀርፀን ነው ወደ ሥራ የገባነው። እሱ ብቻ ሳይሆን ፣ በእያንዳንዱ አመራር፤ በእያንዳንዱ ሠራዊት ጭንቅላት ውስጥ አራት መሠረታዊ እሳቤዎችን ማስቀመጥ።
አንደኛና የመጀመሪያው የሰው ሀብት ነው። ተቋም አደገ የሚባለው የሰው እእምሮ ሲያድግ ነው። የሕንፃ ማማር ወይም የሆነ ነገር ምናምን አይደለም። የሰው ኃይል ስንል ምንድነው የምንሠራው አንደኛ ነባሩን አሁን ወደሚፈለገው አስተሳሰብ መቀየር። ምን ማለት ነው ከፖለቲካ ፤ከሃይማኖት ፤ ከብሔርተኝነት እንዲፀዳና አንድ ለሀገር የቆመ ብሄራዊ ሠራዊት፤ ለሕገ መንግሥት የቆመ ሠራዊት እንዲሆን የማድረግ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ መሥራት።
ለአንድ ሕገመንግሥት የቆመ ሠራዊት እንዲሆን የማድረግ ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ ሠርተናል ።ሠራዊት ሀገር እንጂ ብሔር የለውም። አንድ ጊዜ ሠራዊት ሠልጥኖ ባንዲራ ስር ተንበርክኮ ለሀገር ቃለ መሀላ ከፈፀመ ኢትዮጵያዊነት እንጂ ብሔር አይመለከተውም። እሱ እዚያው እንዳለ የነባሩን ባለሙያ ክህሎት በፍጥነት የማሻሻል ሥራ ሠርተናል።
ለምሳሌ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ደረጃ 5,7,9 የሚባሉ ሥልጠናዎች አሉ፤ ቴክኒሽያኑ ከደረጃ ወደ ደረጃ እየተሸጋገረ በሙያ ልምዱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግበት የሚደረግበት ሂደት ነው።ይሄ አካሄድ ከለውጡ በፊት ቆሞ ነበር። ደረጃ 5 አይሰለጥንም ነበር ደረጃ 7 አይሰለጥንም ነበር ደረጃ 9 አይሰለጥንም ነበር።
አንድ ሰው ዝም ብሎ ጊዜውን ጠብቆ የሆነ ማዕረግ ያገኛል እንጂ በሥልጠና ሂደት የሚገኝ ነገር የለም።ይህን ለማሻሻል በሥነ ሥርዓት ሥርዓተ ትምህርት (curriculum)ተቀርፆ፣ ዶክመንት ተዘጋጅቶ፣ ፈተና ተዘጋጅቶ በተግባር የተደገፈ ሥልጠና እንዲኖር አድርገናል። ነባሩ ላይ ይህንን ሁለቱን ነው የሠራነው። ሙያዊ ደረጃውን የማሻሻልና አስተሳሰቡን የመቀየር ሥራ ነው የሠራነው።
ሁለተኛ በሰው ኃይል ላይ የሠራነው፤ ነገ ያማረ አየር ኃይል ለማየት ከዚህ ንፁህ አዕምሮ ካላቸው ወጣቶች ነው መጀመር ያለብን በሚል የምልመላ ሥርዓታችንን አስተካከልን። የሥልጠና ሥርዓት ትምህርት (curriculum) አስተካከልን፤ የሥልጠና ትጥቆችን አስተካከልን፣ የሥልጠና ቦታ አስተካከልን። ስለዚህ በጣም በአካዳሚ ብቃታቸው፣ በጤንነታቸው፣ በዲስፕሊናቸው ነጥረው የወጡ ቴክኒሽያን በራሪዎችን አሠልጥነን ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀሉ አደረግን። ከገቡ በኋላ ደግሞ ጥራት ያለው ሥልጠና እንዲሰጥ አደረግን ።በዚህ ረገድ በጣም የተሳካ ሥራ ሠርተናል ብለን እናስባለን።
በዛሬው ዕለትም የምናስመርቃቸው በራሪዎች፣ ቴክኒሺያኖች የወደፊት የአየር ኃይል መሪ የሚሆኑ ኦፊሰሮች ናቸው።ስለዚህ አንዱ መሠረታዊ ጉዳያችን (Pilar) የሰው ሀብት ግንባታ ነው። በነገራችን ላይ የሰው ኃይል ግንባታ በጣም በጥረት ከማሠልጠናችን የተነሳ ብዙ ተቋማት እየጠየቁን ነው። አየር መንገድ እየጠየቀን ነው። 70 ሰው ከእኛ ተውሰው እየሠሩ ነው።ከዚህ በተጨማሪ የውጭ ሀገር ሰዎችም እየጠየቁን ነው።
በርካታ ሀገራት /ስም መግለጽ አስፈለጊ ባይሆንም / እየወሰዱ በከፍተኛ ደረጃ የሙያ ችሎታ ያላቸውን እየተጠቀሙ ነው። ይህንን በጣም አጠናክረን እንቀጥላለን። ዜጎቻችን ብቃት ያለው ሥልጠና ወስደው በተለያየ የዓለም ሀገራት ላይ ዞረው እንዲሠሩ ልምድ እንዲያገኙ ነው የምንፈልገው። ስለዚህ ከሰው ኃይል አንፃር የሠራነው በጣም ከፍተኛ ውጤት አስገኝቶልናል ብለን ነው የምንወስደው።
ሌላው የትጥቅ ጉዳይ ነው፤ ከለውጡ በፊት የነበረው ትጥቅ በጣም ደካማ ነበር ። ስለዚህ ምን ይሻላል የሚል ጥያቄ አነሳን።እንግዛ ብንል ኪሳችን የታወቀ ነው።አንድ በዘመኑ ያለ ተዋጊ አውሮፕላን ለመግዛት ምናልባትም ከ100 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ዶላር በላይ ይፈጃል። ሌላውን ሳይጨምር፤ ተተኳሽ ምን ምን ሳይጨምር አክሰሴር (accessory)ሳይጨምር ገንዘቡ ብዙ ነው።
እሱንም ገንዘብ ኖሮን እንግዛ ብንል ደግሞ ጊዜ የለም ማንም እንደ ሸቀጥ አይሸጥም። ከሱቅ ገዝተህ ገንዘብ እንካ የምትለው አይደለም። በጣም አነሰ ከተባለ ተዋጊ አውሮፕላን ለመግዛት 5 ዓመት ነው የምትቀጠረው። ስለዚህ 5 ዓመት ጠብቆ የትኛው ጠላት ወይም ሀገር ነው እኛ እስክንደራጅ የሚጠብቀው፤ በጣም አደገኛ ነው። ስለዚህ ያደረግነው ሁለት ነገር ነው።
አንደኛ በውስጥ አቅምና በፍጥነት መስራት የምንችለው ምንድነው የሚለውን ለየን ።በፍጥነት የተቋሙን ዝግጁነት ለማረጋገጥ ከማሠልጠኛ አውሮፕላኖች አንፃር፣ ከውጊያ፣ ከትራንስፖርት አንፃር ምንድነው ማድረግ የምንችለው የሚለውን ለየን ከመጀመሪያ ማሰልጠኛ አውሮፕላን አንጻር በኋላ መንግሥት ወስኖ በጣም ምርጥ የዘመኑን ደረጃ ያሟሉ አውሮፕላኖች ታጠቅን።
ሁለተኛ የL 39 የመጀመሪያ ደረጃ ጄት ማሰልጠኛ መግዛት አንችልም፤ እንግዛ ብንልም ግዜው የለንም። ስለዚህ ከአምራች ድርጅት ጋር ስምምነት በመፍጠር በአጠቃላይ የማሳደግና ዕድሜቸውን የማራዘም ሥራ እንዲሠራ አደረግን። ከአናሎግ (analog ) ወደ ዲጂታል ቀየርን በአጭር ጊዜ ውስጥ እነርሱንም ከፋብሪካ ተሠርተው እንዲወጡ አደረግን ።አሁን በራሪዎቻችን እየሠለጠኑበት ነው። ዛሬ የሚመረቁት በራሪዎች የሠለጠኑትም በእርሱ ነው።
ሦስተኛ ኤሌኮፕተር ነው።ኤሌኮፕተር እንዳልኳችሁ የትራንስፖርት የለንም፤ የVIP ኤሌኮፕተርም አልነበረም። በዛን ጊዜ ሁሉም የሚሰሩ አልነበሩም።ስለዚህ እሱንም በፍጥነት ከአምራች ድርጅት ጋር በመስማማትና በመፈራረም ቶሎ ተሰርተው እንዲወጡ አደረግን ።አሁን የሚታዩት እነዚህ ኤሌኮፕተሮች በሙሉ ምናልባት ከሁለት ወር በፊት ከፋብሪካ የወጡ ናቸው። ሌሎቹም አሁን ቀጥሎ የሚወጡ አሉ።
በቁጥር ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣም በብዛት አለ። በተለያየ ጊዜ ተገዝተው የቆሙ። የማናጅመንቱ ወይም የአስተዳደር ሥርዓቱ ነው የተበላሸው። የጥገና ሥርዓቱ ነው የተበላሸው። በትጥቅ በኩልም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ መንግሥትና ሀገሪቱ ባላቸው አቅም መግዛት። የማይሆን ከሆነ ደግሞ ቶሎ ብሎ ያለንን ወደ ኃይል መመለስ ነው፤ በዚህ መልኩ ወደ ኃይል የመለስናቸው ስፍር ቁጥር የላቸውም።
ምናልባት በዳታ ልታዩት ትችላላችሁ። ኤል 39 አለ፤ ሂሊኮፕተር አለ፤ የትራንስፖርት አውሮፕላን አለ። ዙ 27 አለ፤ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠግነን ኦቨር ኦል አድርገን ወደኃይል መልሰን አሁን ግዳጅ እየተወጣንበት ነው ያለው። በነገራችን ላይ በዚህ አጋጣሚ ምንድን ነው ያደረግነው፤ እነርሱ መጥተው እንዲጠግኑልን ብቻ አይደለም እኛ የምናስበው። እኛም አብረን ተሳትፈን የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የእውቀት ሽግግር፣ ገንዘብ የማዳን ሥራ ለመሥራት ነው።
እያንዳንዷን ውል ስንፈጽም የቱ ላይ ነው ወጪ ማዳን የምንችለው የሚለው ልቅም አድርገን አውጥተን አይተናል፤ እነርሱ ሊያግዙን በሚችሉበት ቦታ ብቻ ላይ እንዲያግዙን ሌላው እኛ መስራት የምንችለውን እኛ እንድንሰራ ነው አካሄዳችን። በዚህ አካሄዳችን ወደ 45 ቴክኒሽያኖች በፋብሪካ ሰርቲፋይድ ሆነዋል። ኦቨር ኦል ማድረግ ይችላሉ ተብሎ ሰርተፊኬት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ቀላል አይደለም። ከየትኛውም ገንዘብ ይበልጣል።
ማንኛውም አውሮፕላን ከዚህ በኋላ ኦቨር ኦል ማድረግ የሚችል፣ ሊጠገን የሚችል፣ አፕግሬድ ማድረግ የሚችል፣ የሰው ኃይል አለን ማለት ነው። ትልቁ ነገር ደግሞ ለእኔ እሱ ነው። ስለዚህ ትጥቆቻችንን በዚህ መልኩ ነው ያሻሻልነው።አሁን የውጊያ ፕላትፎርማችን ጨምሯል። የትራንስፖርት ፕላትፎርማችን ኤር ሞቢሊቲ ጨምሯል። የማሠልጠኛ አቅማችን ጨምሯል።
ሌላው መንግሥት ወስኖ የገዛቸው አዳዲስ ወደ ተቋሙ የተቀላቀሉ ለምሳሌ ሰው አልባ ተጨማሪ ተዋጊ አውሮፕላኖች ፣. ተጨማሪ የትራንስፖርት አውሮፕላኖች ወደተቋሙ የተቀላቀሉ ትጥቆችም አሉ። እነዚህ ሲደመሩ በአሁኑ ሰዓት የአየር ኃይል ግዳጅ የመወጣት የግዳጅ ዝግጁነት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል ማለት ይቻላል።
ሦስተኛ መሠረተ ልማት ነው። ቅድም እንዳልኳችሁ መሠረተ ልማት ማለት ወሳኝ ነው። አውሮፕላን ቢንጋጋ፣ ራዳር ቢንጋጋ፣ ሚሳዔል ቢንጋጋ ለዚያ አውድ የሚመጥን መሠረተ ልማት ከሌለ ዋጋ የለውም። እንዳልኳችሁ ለአውሮፕላን ሃንጋር፣ መንደርደሪያ /ራናዌይ/ ያስፈልጋሉ። ማታ የሚበረርበት የራንዌይ መብራት፣ የጥገና ቦታ፣ ኔትዎርክ ያስፈልጋሉ። የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ያስፈልጋል።
ይህን ሁሉ ታሳቢ አድርገን በከፍተኛ ደረጃና በፍጥነት እየሠራን ነው። አንዳንድ ቦታዎችንም ጎብኝታችሁ በአይናችሁ ተመልክታችሁ ሊሆን ይችላል። ይህን በማድረጋችን በሚገርም ሁኔታ ድሮ ከኛ ጋር መስራት የማያስቡ ሀገሮች ከእናንተ ጋር መጥተን ብንሠለጥን፣ የእናንተ የሥልጠና ቦታችሁ በጣም ያምራል እያሉን ናቸው።
ቃል በቃል ዓለም አቀፍ /ዎርልድ ስታንዳርድ / የሥልጠና ማእከል ነው ያላችሁ ብለው የመሰከሩ ሀገሮች አሉ። ስለዚህ ከእናንተ ጋር ብንሰልጠን፣ ብታሰለጥኑልን፣ የጥገና ቦታችሁ በጣም ጥሩ ስለሆነ ብትጠግኑልን፣ አብረን የልምድ ልውውጥ ብናደርግ ብለው በርካታ ሀገሮች እየጠየቁን ናቸው። አንዱ የአየር ትርኢት የምናካሂደውም የእነሱ ውጤት ነው። እነዚህን መሠረተ ልማቶች ባንገነባ ኖሮ ማንም በጫካ ውስጥ አውሮፕላኑን የሚያስቀምጥ የለም። የመሰረተ ልማቱ ግንባታ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ እንድናገኝ ጠቅሞናል።
አራተኛ አየር ሀይል እንደ አየር ሀይል ፤ለሀገሪቱ ማንኛውም ተቋም ምሳሌ ነው መሆን ያለበት። በውበቱም፣ በጥራቱም፣ በጽዳቱም ለኢትዮጵያ የሚመጥን አየር ሀይል መሆን ያለበት። በውበቱም በጥራቱም ፤ሰራዊቱ የሚሰራበት፣ የሚኖርበት፣ የሚጠግንበት አካባቢ የሚማርክ መሆን ይኖርበታል። ምሳሌ መሆን አለበት ብለን ነው የተነሳነው።
በምንም ታምር በተበለሻሸ እና አቧራ በሆነ ሰፍራ መኖር የለብንም ብለን በከፍተኛ ደረጃ ከሠራዊታችን ጋር ተግባብተን ተነስተናል። ይህንንም እንደምታዩት የሚያሳፍር ደረጃ ላይ አይደለንም። ጨርሰናል አንልም፤ በርካታ ነገሮች ይቀሩናል፤ ፊት ለፊቱን ነው የከፋፈትነው፤ የሚቀሩን ብዙ ነገሮች አሉ፤ ይህንን ለመጎብኘት ከበርካታ ወገኖች ጥያቄዎች እየቀረቡልን ናቸው።
ጥያቄ ፡- ጦርነትን በሩቁ የሚያስቀር እንዲሁም የኢትዮጵያ የአየር ክልል አስተማማኝ ዘብ ከመሆን አንጻር የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምን ቁመና ላይ ይገኛል?
ሌተናል ጀነራል ይልማ፡- ጠንካራ ኃይል፤ ጠንካራ አየር ኃይል፣ ጠንካራ መከላከያ፣ ጠንካራ ምድር ኃይል የምትገነባው በሰላም ለመቆየት ነው። እኛ የምንገነባው በሰላም ለመቆየት ነው። ይህን እንዴት ነው የምታረጋግጠው ለሚለው፦
አንደኛ አቅምህን አይቶ ነው ሰው መጥቶ የሚደራደርህ። ስለዚህ የሰለጠነ የሰው ኃይል ካለ፣ ቴክኖሎጂን መሸከም የሚችል፣ ታርጌቶችን/ኢላማዎችን/ በደንብ ያለምንም መሳት መምታት የሚችል በራሪ ካለ፣ ያን አውሮፕላን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠግን፣ የሚቀይር፣ የሚያሻሽል የሰው ኃይል ካለ፣ በአጠቃላይ ጠንካራ ዲስፕሊን ያለው የሰው ኃይል ከገነባህ፣ ከሰው ኃይል ጋር ደግሞ ለዘመኑ የሚመጥን ትጥቅ ካለ፣ ለዚህ ትጥቅ ደግሞ የሚመጥን መሠረተ ልማት ካለ ማንም ብድግ ብሎ አያስብህም።
አሁን ባለንበት ሁኔታ ተዋጊ አውሮፕላኖቻችን ጥሩ ናቸው፤ ትራንስፖርት አውሮፕላኖቻችን ጥሩ ናቸው፤ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ታጥቀናል፣ጥሩ ነው፤ የሳይበር ሰኪዩሪቲ አቅማችን ጥሩ ነው። እነዚህን እየገነባን ነው ያለነው። ይህም እዚሁ ጋ የሚቆም ነው ማለት አይደለም። ለምን ነገሮች ይቀያየራሉ።
ሌላው ደግሞ የረጅም ዓመት እዳ እየከፈልን ነው፤እዳ ነው እያወራረድን ያለነው። አሁንም ዛሬ መሆን የሚገባን ቦታ ላይ አይደለም ያለነው። አሁን ባለው ደረጃ አቅማችን እጅግ በጣም ጥሩ ነው ማለት ይቻላል።
አሁን በሠራዊታችን፣ በመንግሥት በእኛ በተሰራው ሥራ ጥሩ መሻሻሎች አሉ። ለማንኛውም ለሚታሰብ ነገር መልስ መስጠት ይቻላል። የአየር ክልል ጥበቃችን 24/7 ነው። 24/7 ዓይናችንን፣ የአየር ክልላችንን እየጠበቅን ነው። ስለዚህ ይህ ሲታሰብ በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ይቻላል።
ጥያቄ ፡- የአየር ትርዒት ልምምዶች እየተደረጉ እንደሆነ ተመልክተናል። የአየር ትርዒት ልምምዶቹ የተባባሩት አረብ ኤምሬቶች አውሮፕላኖችንም ያካተተ እንደነበር ነው ያየነው። አሁን የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከተባባሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር በጋራ እያደረገ ያለው የአየር ትርዒት ልምምድ ምን እንድምታ አለው?
ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ ፡- ይህ መነሻው የሁለቱ ሀገሮችና የሁለቱ ሀገር መሪዎች ያላቸው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ውጤት ነው። አሁን በዲፕሎማሲ ደረጃ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያለው ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ወደ ወንድማማች ሀገር ደረጃ እየደረሰ ነው ያለው። በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት አድርገናል።
ከዲፕማሲ፣ ከፖለቲካ፣ ከኢኮኖሚ ስምምነት ባሻገር ወታደራዊ ስምምነትም ፈፅመናል። ከዚያ ተሻግሮ አየር ኃይል ለአየር ኃይል በጣም በርካታ ግንኙነቶች አሉን። በተለያዩ ስልጠናና ልምምዶች ላይም እኛን ይጋብዙናል። እኛም ሄደን እንሳተፋለን።
በዚሁ ቀጣይነት ያለው ሁኔታ ይህንን 88ኛ የአየር ኃይል ቀን በዓል ለማክበር ስናስብ ለምንድን ነው በጣም የሚቀርቡንን ወዳጅ ሀገሮች የማንጋብዘው ብለን ጥያቄ አቀረብንላቸው። እነሱም አላቅማሙም። አላቅማሙም ስንል የነበረውን አቅም ያውቁ ነበር መጀመሪያ፤ በተለይ ደግሞ ያለው መሠረተ ልማት፤ አውሮፕላኖችን ማስተናገድ መቻል አንድ አቅም ነው። እነሱም እሱን ስላዩ፣ ስላወቁ ሁለተኛ የኢትዮጵያ የአየር ሁኔታ በጣም አመቺ በመሆኑ ጥያቄያችንን ተቀበሉ።
መቀበል ብቻ ሳይሆን አሁን በኤር ሾው /በአየር ትርኢቱ/ ላይ የሚሳተፉ አቅሞችን በሙሉ ከሀገራቸው ይዘው መጡ። አሁን አብረን ልምምድ እያደረግን ነው። ትርኢቱንም በጋራ እናደርጋለን።
ይሄ አንድምታው በመሰረቱ የሁለቱ ሀገሮች የግንኙነት ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ያደገ መሆኑን ያሳያል። ብዙ ጊዜ ሀገሮች ያላቸውን ወታደራዊ አቅም አንዱ ላንዱ አያሳይም። ያው እርስ በእርስ ስለሚጠራጠር። በእነርሱ ደረጃ ግን እኛ ወንድማማች የሆነ ግንኙነት ስላለን ያለንን ካፓብሊቲ / ችሎታ/ አብሮ የመጠቀምና አብሮ ልምምድ፣ የልምድ ልውውጥ፣ ኤር ሾው /የአየር ትርኢት/ ማድረግ ላይ እንሠራለን፤ በነገራችን ላይ ሥልጠናዎችም እየተቀያየርን ነው። የኛም ሄዶ የሚሠለጥንበት፣ የእነርሱም እዚህ የሚሠለጥኑበት ሁኔታ አለ።
ስለዚህ ይሄ የዲፕሎማሲው ውጤት ሆኖ አሁን ወደ ወታደራዊ፣ ተቋማት ወደ መከላከያ ወደ አየር ኃይልም ወርዶ በዚህ ደረጃ እየሠራን ነው። በዚህ በኩል እነርሱም በጣም ደስተኞች ናቸው፤ እኛም በጣም ደስተኞች ነን።
ጥያቄ ፡- በርካታ የአፍሪካ ሀገራትም በዚሁ በዓል ላይ ለመሳተፍ እንደሚመጡ ሰምተናል፤ ለዚህ የአየር ኃይሉ አጋርነት ወይም ደግሞ ትብብር ከአፍሪካዊ ወንድም ሀገሮች ጋራ በምን አይነት ደረጃ ላይ ይገኛል ማለት እንችላለን?
ሌተናል ጀነራል ይልማ ፡- አንዱ የመጀመሪያው ነገር ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሀገር ናት። እኛ በቅኝ ገዢዎች አልተገዛንም። አለመገዛት ብቻ ሳይሆን ፣ለእነርሱም ነፃነት ለአፍሪካ ነፃነትም ታግለናል፤በታሪክ እንደምናውቀው።
ስለዚህ አሁንም ቢሆን የአፍሪካ አየር ኃይል ማንም መጥቶ የሚፈነጭበት ለምን ይሆናል? ለምን በጋራ ሰብሰብ ብለን እንዴት ብንሄድ ነው ጠንካራ የአፍሪካ አየር ኃይል የምንገነባው? በየሀገሮች ዘንድ በጋራ የምንለማመደው? በጋራ የአየር ክልላችንን የምንጠብቀው? በጋራ ጥገናዎችን የምናደርገው? በጋራ ሥልጠና የምናካሂደው? እንዴት ቢሆን ይሻላል? የሚል ሃሳብ አንስተን ወደ 26 የአፍሪካ ሀገሮችን ጋብዘናል። ከእነዚህ ጋርም በሥልጠና በጥገና በልምድ ልውውጥ ጥሩ የሆነ ግንኙነት እናደርጋለን።
ይህንን እንዴት እንቀጥል? የእያንዳንዱ ሀገር አየር ኃይል በመደመር የአፍሪካ አየር ኃይልን /የአፍሪካ ኤርፎርስ /ራሱን ችሎ እንዲቋቋም እንዴት እናድርግ? በነገራችን ላይ አየር ኃይሉ አሁንም ከቅኝ ግዛት ራሱን ችሎ አልወጣም። በተለይ በአቬሽን ቴክኖሎጂ ከቅኝ ግዛት አልወጣንም። ለምን አሁንም ስንቸገር ግዥ ነው የምንሄደው። ሲፈልጉን ይሸጡልናል፤ ሳይፈልጉን ደግሞ ይከለክሉናል። እንዴት አድርገን ነው ነጻ መውጣት ያለብን? በአጠቃላይ የቴክኖሎጂ ነጻነት እንዴት እናገኛለን? የሚል ውይይት ከእነርሱ ጋር ማድረግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ጋብዘናቸዋል።
በተመሳሳይ በኤር ሾው/ አየር ትርኢቱ/ ላይም ይሳተፋሉ። ውይይቶች፣ ፎረሞችና የልምድ ልውውጦች ይኖሩናል። በጋራ የምንሰራባቸው አጀንዳዎች እንወጣለን ብለን እናስባለን። ስለዚህ ትልቅ አጋጣሚ ነው ብለን ነው የምናሰበው።
ጥያቄ ፡- ኢትዮጵያ ካለችበት የጂኦፖለቲካ አቀማመጥ አንጻር የትኩረት ነጥብ ነች። ከቀጣናው አስፈላጊነትና ስትራቴጂክነት አንጻር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምን አይነት ተወዳዳሪነትና ብቃት አለው? የኢትዮጵያን ጥቅምስ ከማስከበር አንጻር ምን ያህል ዝግጁ ነው ?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፡- በአካባቢያችን፣ በሁሉም አካባቢ ትርምስ የበዛበት፣ በጂኦፖለቲካ እርግጠኛ መሆን የማይቻልበት፣ መቼ ምን ይሆናል የማይባልበት ነው። አሁን እየገነባን ያለነው አቅምም ለዚህ ተመጣጣኝ ይሆናል ብለን ነው። በምሥራቅም ቢመጣ፣ በምዕራብ ቢመጣ እንዴት አድርገን መልስ መስጠት እንችላለን የሚል ነው እንጂ ዝም ብሎ አውሮፕላን መሰብሰብ፣ ምናምን አይደለም።
ለምሳሌ አሁን በምዕራብ የሆነ ችግር ቢፈጠር እንዴት አድርገን ነው ምዕራብ ላይ የምንዋጋው የሚል የውጊያ ጽንሰ ሀሳብ ይኖረናል። ከመሬቱ፣ ከመሠረተ ልማቱ፣ ከአየሩ፣ ከርቀቱ እንዴት አድርገን ነው የምንዋጋው የሚል ጽንሰ ሀሳብ።
በምሥራቅስ? በምሥራቅ ደግሞ በመሠረቱ መሬቱ የተለየ ነው። መሠረተ ልማቱ ይለያል። ብዙ ሀገሮች የተኮለኮለበት ቦታ ነው። የባሕር ላይ ውንብድና አለ። እኛ ደግሞ ብሔራዊ ፍላጎት አለን። ትጥቆቻችን ሁሉም በሚገቡበት ባሕር ላይ የራሳችን ፍላጎት አለን። በሰሜን ደግሞ በሰሜን ደግሞ ሌላ ነገር አለ። መሬቱ ይለያል። ኃይል ስትገነባ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ታደርጋለህ።
ስትራቴጂክ ቲንኪንግ /የወደፊት እይታ/ እቅድ ነው። የቱ ጋ መሠረተ ልማት ይኖራል? ምንጊዜ የምንጠቀምበት? ለየትኛው ጊዜ ምን አይነት ትጥቅ ይኖረናል? ምንዓይነት የሰው ኃይልስ ይኖረናል? ብለን ማሰብ ይኖርብናል። በነገራችን ላይ አንዱ የእኛ ተልዕኮ በሆነ ጊዜም ቢሆን የአየር ክልላችን መከላከል ነው። ሁሉንም ነገር የምናስበው ይሄን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ነው፤ በመሠረተ ልማቱም በሰውም በትጥቅም በቴክኖሎጂም ይህንን እያሰብን ነው የምንገነባው።
ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ አየር ኃይል የኢትዮጵያ አየር ክልልን በአስተማማኝ ሁኔታ ከመጠበቅ ባለፈ በቀጣናዊ እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ያለው ሚና ምንድነው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- በነገራችን ላይ አሁን አይደለም አየር ኃይል ሰላም ማስከበር የጀመረው። የመጀመሪያው በ1960 ኮንጎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተዋጊ አውሮፕላኖችን ይዘን ሔደን ተሳትፈናል። ታሪኩ ተጽፎ በትክክል ተሰንዷል ። እሱ ብቻ አይደለም በ60ዎቹ የታንዛኒያን የአየር ክልል ጠብቀናል። በነገራችን ላይ የዚያን ጊዜ የታንዛኒያ የአየር ክልል ሲጠብቁ የነበሩት ብርጋዴር ጀኔራል ተጫነ መስፍን በሕይወት አሉ።
በዳርፉር፣ በአብዬ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በርካታ ችግሮች አሉ፤ አንዱ በተልዕኳችን ግልጽ ያደረግነው ምንድነው? ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ላይ፤ በብቃት መሳተፍ የሚል አለ። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት አሁን በቅርብ ጊዜም ወደ ሶማሊያ እየገባን ነው። በምድር ኃይልም ልምድ ያለን ስለሆንን ይሄንንም በብቃት ለመሳተፍ ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ነው።
ጥያቄ፡- ሰማዩ የኛ ነው በትክክል አየር ኃይልን ይገልጸዋል እያሉኝ ነው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ ፡- ለምሳሌ ምድር ኃይል ብትሄጂ ምድር ኃይል ስናሠለጥን አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት የሚል ነው። ለምንድነው ይሄንን የምታስተምሪው? ሠራዊቱ ወይም ወታደሩ ሠላሳውን ጥይት አንድ ጊዜ ጨርሶ ጨረስኩ እንዳይል ነው። በጥንቃቄ እንዲጠቀም ነው፤ የተሰጠውን ጥይት በጥንቃቄ እንዲጠቀም ነው። በተለያየ የመከላከያ ሰርቪሶች ውስጥ እንደዚህ አይነት ዕሳቤዎች አሉ።
ወደ አየር ኃይል ስንመጣ ግን በጣም ወሳኝ የሆኑ በራሪዎች ወደ በረራ ሲሄዱ ስለ ሰማዩ ነው ማሰብ ያለባቸው፤ ሰማዩ የኔ ነው። ‹‹አይ ካን ኦን ዘ ስካይ›› በምድር ላይ ወይም የምድር ኃይል የኔ ነው ምድሩ፣ ቦርደሩን እቆጣጠራለሁ፣ ማንም ጥሶ አይገባም፣ እኔ እስካለሁ፣ ይላል ። ለእኛም ተመሳሳይ ነው ማለት ነው።
እኛ እያለን ሰማዩ አይጣስም ነው፤ ሰማዩም የኢትዮጵያ ሀብት ነው ፤ አየር ኃይል እያለ ሰማዩ አይጣስም የኛ ነው ሰማዩ። በእርግጥ ስንጀምር እንደ ቀልድ ነበር የጀመርነው ግን አድጎ አድጎ ሄዶ ወደ ፊልምም ተቀይሮ ጥሩ ደረጃ ላይ ደርሷል።
እሱ ብቻ አይደለም፤ እያንዳንዱ ዲፓርትመንት ደግሞ የራሱ ‹‹ሞቶ›› አለው። ለምሳሌ አካዳሚ በረራ ትምህርት ቤት ከሄዳችሁ ‹‹ዜሮ ቱ ሄሮ››፤ ምን ማለት ነው ይሄ? በቃ ቅድም እንዳልኩት ነው። አንድ ጥይት ለአንድ ጠላት እንደምንለው ለበረራ ትምህርት ቤት የተሰጠው ከበረራ ዜሮ የበረራ ሰዓት ያለው ስለአቪየሽን ምንም ዕውቀት የሌለውን ተቀብለህ ግዳጁን የሚወጣ ጀግና አርገህ ሀገሩን የሚጠብቅ አርግ ማለት ነው።
አየር ኃይል የሚዋጋበት የራሱ ዓውድ አለው። እንዳያችሁት ሰማይ ላይ ነው የሚዋጋው። ወይ ከሰማዩ ወደ ምድር ነው የሚተኩሰው ወይ ከሰማይ ወደ ሰማይ ነው የሚተኩሰው። ለዚያ ነው ሰማዩ የኔ ነው። ‹‹አይ ካን ኦን፣ አይ ካን ኮንትሮል፣ አይ ካን ዶሚኔት ዘ ስካይ›› ማለት መቻል አለበት። አንዱ ሠራዊቱን የምንገነባበት፣ ሞራል የምንሰጥበት፣ የምናበረታታበት ስለሆነ ነው እንዲህ አይነት ሞቶዎች የምናመጣው።
ጥያቄ፡- አየር ኃይሉን ለ88 ዓመታት ያገለገሉ ጀግኖች አሉ፤ የእነዚህ የቀድሞ አየር ኃይል አባላትና አመራሮች ታሪክ ለትውልድ እንዲተላለፍ ተቋሙ ምን እየሠራ ነው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፡- ሪፎርም ብለን መጀመሪያ የጀመርነው የሀገርም ይሁን የተቋም የአንድ ትውልድ ግንባታ አይደለም። የአንድ ትውልድ አድርጎ ማቅረብ፣ መሳል ትክክል አይደለም ብለን እናስባለን። ለምሳሌ እያንዳንዱ አዛዥ የራሱ ጠንካራ ጎን አለው፣ የራሱ ታለንት አለው፣ የራሱ አስተሳሰብ አለው። ግን ከመጀመሪያ ጀምሮ እየተገነባ ባይመጣ ኖሮ እኛ ዛሬ ላይ ይሄንን አናየውም ነበር ማለት ነው።
ለዚያ ነው አየር ኃይል የአንድ ትውልድ የአንድ ዘመን ግንባታ አይደለም ብለን የተነሳነው። ስለዚህ ይህንን ለማስተካከል የእያንዳንዱ አዛዥ የእያንዳንዱ ግለሰብ እንዲሰነድ አድርገናል። ለዚህ የመጀመሪያ ሥራችን ያደረግነው አየር ኃይልን በአዛዥነት የመሩት እነ ማን ናቸው? ከሚለው በመነሳትና የእነሱን ታሪክና ሥራዎች ማዘጋጀት ነው።
ታሪክን የማስተሳሰር ሥራ ነው የሠራነውና እየሠራን ያለነው። ከዛ ቀጥሎ እየተዘጋጀንበት ያለነው የሙዚየም ጉዳይ ነው። ገብታችሁ እንዳያችሁት፣ እስካሁን ተቋሙን ለመሩት ሰዎች፣ ለጀግኖቻችን ሙዚየም የማዘጋጀት ሥራን ለመሥራት በዝግጅት ላይ ነን። በኮቪድ፣ እና በጦርነት ምክንያት ትንሽ ዘገየን እንጂ ወደ ሥራው ከገባን ትንሽ ቆይተናል።
አሁን ዲዛይን አድርገን እየጨረስን ነው። በ1928 ምን ነበር፤ በ1935 ምን ነበር፣ በ1945 ምን ነበር፣ ምን ተሠርቶ ነበር፣ የታሪኩ ባለቤት ማን ነው፣ ማን ምን ሠራ፣ እነ ማን አዛዥ ነበሩ፣ አዛዡ ማን ነበር የሚለውን በምስልም፣ በፎቶ ጋለሪዎችም፣ በኦዲዮም ሰው ገብቶ እንዲያይ የማድረግ ሥራን እየሠራን ነው። በቅርብ ጊዜ እንጨርሳለን ብለን እናስባለን።
ጥያቄ፡- የአየር ኃይልን በፖል ለማክበር ኅዳር 20 የተመረጠበት ምክንያት ምንድን ነው፤ የበዓሉ ዓላማስ ምንድን ነው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፡- ኅዳር 20 የተመረጠበት ምክንያት፣ ከዓለም ተሞክሮ ስንነሳ ብዙ ሀገሮች የእያንዳንዶቻቸውን ተቋም የልደት ቀን ያከብራሉ። መቼ ተመሠረተ፣ በእነማን ተመሠረተ፣ እንዴት ተመሠረተ የሚለውን መሠረት በማድረግ ያከብራሉ። አሜሪካ ብንሄድ ይሄ አለ። እያንዳንዱ ዩኒት የተመሠረተበትን ያከብራል።
እያንዳንዱ ዩኒት በሠራው ጀብድ፣ በሠራው ጀግንነት እንዲኮራ ነው የሚያደርገው። ጀግኖች የሚታወሱበት፣ የተቋሙ ታሪክ የሚታወስበት፣ ታሪኩ ለትውልድ የሚተላለፍበት፣ ትውልዱ አየር ኃይልን፣ ተቋሙን የሚያውቅበት ነው የሚሆነው። በዓለም አቀፍ ደረጃም ልምዶች እና ተሞክሮዎች አሉ።
ይህንን ሲወስኑ ውሳኔው እንደየሀገሩ ይለያያል። ለምሳሌ አንዳንዶቹ ከፍተኛ ውጊያ አድርገው ያሸነፉበትን እንደ ተቋሙ ምሥረታ ቀን አድርገው ይወስዳሉ፤ ያከብሩታልም። አንዳንዶቹ የመጀመሪያው አዛዥ የተሾመበትን እለት ወስደው ያከብራሉ። ሁኔታው እንደየሀገሩ ይለያያል።
የእኛ ኅዳር 20 የተባለበት ምክንያት፣ በነገራችን ላይ ከዛ በፊት አክብረናል፤ ለምሳሌ እኔ የተመረቅሁት መጋቢት 26 ቀን 1990 ዓ/ም ነው። መጋቢት 26 በኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ ምንድን ነው? ብለሽ ብትጠይቂኝ አላውቅም። አንዳንዶቹ እንደውም ሲቀልዱ የእንትና የልደት ቀን ነው ብለው ይጨዋወታሉ።
ከዛ ቆየት አለና ደግሞ ሚያዝያ 11 ተባለና ሚያዝያ 11 አከበርን። ምንድን ነው ሚያዝያ 11 ብለን ስንጠይቅ ምንም የሚያግባባ መልስ የለም። በአየር ኃይል በዓል ቀን አከባበር ላይ እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ በእኛ፣ በአየር ኃይል ባለነው አባላት መካከልም አንግባባም ማለት ነው።
በመሆኑም በመከላከያም፣ በአየር ኃይልም በሪፎርሙ እንደ አንድ ተግባር አድርገን የወሰድነው የተዛቡ ታሪኮችን የማስተካከል ሥራን ነው። በስሜታዊነት የተወሰኑ፣ ያልተፃፉ ውሳኔዎችን የማስተካከል ሥራን መሥራት አለብን ከሚል ነው። እንደምታውቁት በመከላከያም ከፍተኛ ጥናት ተደርጎ 1900 ዓ.ም ጦር ሚኒስቴር የተቋቋመበት ነው ተብሎ ተወሰነ፤ በዛ ጀምረናል፤ ባለፈውም 116ኛውን ዓመት አክብረናል።
አየር ኃይልም በተመሳሳይ ልምድ በማሰባሰብ፣ በሕይወት ያሉትን በመጠየቅ፣ መረጃ በማሰባሰብ ምን ይሻላል ብለን ጥናት አካሄድን። በዚህ ጥናት ላይ ብዙ አማራጮች ነበሩ። አንደኛው አውሮፕላን መጀመሪያ ወደ ኢትዮጵያ የገባበት ቢሆንስ? ሁለተኛው አማራጭ አውሮፕላኑ በጦርነት የተሳተፈበት ቢሆንስ? የሚል ነበር። ሦስተኛው ደግሞ አውሮፕላኑ ሾው (ትርኢት) ያሳየበት ቢሆንስ? የሚሉ አማራጮች በሥርዓትና በቅደም ተከተል ተቀመጡ። በእነዚህ ላይ ከፍተኛ ውይይትና ክርክር ተደረገ።
ኅዳር 20 የተባለበት ምክንያት፣ ከዛ በፊት አየር ኃይል የሚል ቃል ፈልገን አጣን ። ምንድነው የሚባለው የሰማይ ባቡር እና ሌሎች ሌሎች ስሞች ይሰጡት ነበር። አየር ኃይል የሚል አልነበረም። ጣሊያን ሁለተኛ ወረራ ሲያውጅ እነዚህ አውሮፕላኖችን ሲያበሩ የነበሩ የውጪ ዜጎች ስለነበሩ አይ እኛ አንበርም ወደ ሀገራችን ነው የምንሄደው አሉ። ከዛ ተነስተው ንጉሡ ሚሽካ ባቢቼ የሚባል ኢትዮጵያዊን ከዛሬ ኅዳር 20 ጀምሮ የአየር ኃይል አዛዥና አስተባባሪ ሆነህ ተመድበሃል የሚል ደብዳቤ ተገኘ። ስለዚህም ይህንን መነሻ በማድረግ የአየር ኃይል ቀን ተወሰነ።
አንደኛ አየር ኃይል የሚል ቃሉ መጣ። ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ አዛዥ የመጀመሪያ የተሾመበት ነው። ይሄ ጥሩ ነው፤ ትክክለኛ ነው ብለን ተግባብተን ይሄን ደግሞ ለክቡር ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አቅርበን ብሪፍ አድርገን እሳቸውም አፅድቀው ከአሁን በኋላ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ምሥረታ ኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም እንደሆነና ከዚያ ዓመቱን እየቆጠረ እንዲከበር ተወሰነ። ዋናው በአጭሩ ይሄን ነው የሚመስለው።
ጥያቄ፡- በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰው አየር ኃይል ለአዲሱ ትውልድ ለማስተላለፍ፤
የአየር ኃይላችንን ታሪክ ለሕዝቡ ቅርብ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር መሥራት ያለብን እና ያልሠራነው የምትሉት ነገር አለ ?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ ፡- የማንኛውም ተቋም ግንባታ የዜጎች ቅብብሎሽ ነው። ከዚህ አንጻር በርካታ ሥራዎችን እየሠራን ነው። የዚህ በዓል ዋና ዓላማ፤ እንደ ግብ አድርገን የተነሳነው፣ ተቋሙን ሳቢና ተመራጭ በማድረግ በተለይ በአካዳሚ ብቃት ያላቸውን ወጣቶች እንዲቀላቀሉ ማድረግ ነው። ይሄ ደግሞ ዝም ብሎ በቅስቀሳ ብቻ ሳይሆን በተግባር ተቋሙን አይቶ ተገንዝቦ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ያስፈልጋል፤ እኛ ሰልችቶን ይበቃናል፤ ጊዜ የለንም፤ ሥራ አለን እያልን ነው እንጂ ከተለያዩ ትምህርት ቤቶች፣ ከክልሎች፣ ከፌደራል ተቋሞች፣ የጉብኝት ጥያቄዎች እያቀረቡልን ነው ።
ሌላው ያለፈውን የተቋሙ ታሪክ ነው፣ ታሪክ ላይ ሰው በጣም ይሳባል፤ እኔም ብሆን ጥሩ ታሪክ ላይ ያለ ተቋም እንዲሆን አስባለሁ። የተቋሙ የተጠሉ ታሪኮች አሉ፣ ለምሳሌ በሱማሌ ውጊያ አየር በአየር ተዋግቶ የሱማሌን አውሮፕላን አየር ላይ ያነደዱ ጀግኖች አሉ፤ እንደነባጫ ሁንዴ፣ በዛብህ ጴጥሮስ ለገሠ ተፈራ ያሉ ጀግኖች። ታሪኩ ልብ የሚነካ ነው፤ ለወደፊት እናወጣለን።
እነሱ ብቻ አይደለም በርካታ የአየር ኃይል መሪዎች የሠሩት ገድል፤ የአየር ኃይል አብራሪዎች የፈጸሙት ጀብዱ፤ ቴክኒሽያኑ ጥገና ክፍሉ የፈጠራቸው ሥራዎች፤ እነዚህን ሰብሰብ አድርገን በዶክመንታሪ ፣ በጉብኝት መልክ ለሕዝቡ እያቀረብን ነው ። በዚህም ተቋሙን መቀላቀል የገንዘብ ጉዳይ ሳይሆን የክብር ጉዳይ መሆኑን፤ የሀገር ጉዳይ መሆኑን ማስገንዘብ ይቻላል ። ይሄን ቱታ ለብሶ ወይም የአየር ኃይልን ዪኒፎርም ለብሶ የአየር ኃይል ወታደር መሆን ክብር ነው ብሎ ዜጋ እንዲመኝ ለማድረግ እየሠራን ነው።
ጥያቄ፡- ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ሲፈጠሩ ደግሞ ያው እነዛን አደጋዎች ለመቆጣጠር እንደ ሀገር የሚደረግ ጥረት አለ በነዚህ ጥረቶች ውስጥ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አበርክቶ ምን ይመስላል?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- የኢትዮጵያ አየር ኃይል አምስተኛ ተልዕኮ ለሰው ሠራሽ እና ለተፈጥሮ አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት ነው። ሰው ስናሠለጥንም ከዚህ አንጻር ነው ማለት ነው። በነገራችን ላይ ሠራዊት የምታሠለጥነው ተልዕኮ መሠረት በማድረግ ነው። ምንድነው የሚሠራው? ብለህ ነው ተልዕኮ ላይ ተመሥርተህ ነው እና አንዱ ተልዕኳችን እሱ ነው ። በምሳሌ ለማስደገፍ አሁን እንኳን እየሠራን ያለነው ሱማሌ ክልል ያጋጠመው የጎርፍ አደጋ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ያጋጠመ የጎርፍ አደጋ አንድም ዜጋ ሳይሞት ነው ያስወጣነው።
የእሳት አደጋ ሲያጋጥም፤ የጎርፍ አደጋ ሲጋጥም፤ የተለያየ ዜጎች ችግር ሲያጋጥማቸው ሄደን እናወጣለን። አሁንም እየሠራን ነው፤ ይሄ ከተልዕኳችን አንዱ ነው። ከተልዕእኳችን አንዱ ነው። በዚህም በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ። ለምሳሌ ወደ ጋምቤላ ክልል አከባቢ የሚያጋጥሙ ችግሮች አሉ እሱን ሄደን እንሠራለን። ስለሆነም በጥሩ ሁኔታ እየሠራን ነው።
ጥያቄ፡- በ2022 ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል የመሆን እቅድም አለ፤ ለዛ ምን እየተሠራ ነው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ናት። በታሪክም፣ በቆዳ ስፋትም፣ በሕዝብ ብዛትም፣ በባሕልም፣ በጀግንነትም በምኑም ትልቅ ሀገር ናት። ይህ ትልቅ ሀገር አየር ኃይል ብቻ አይደለም ትልቅ መከላከያ ያስፈልገናል። ትላንት ያልተገዛን ሰዎች ዛሬ ማንም የመንደር ጎረምሳ ሊጨፍርብን አይገባም። ስለዚህ አየር ኃይል ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያ ማንኛውም ተቋም ሲገነባ ትልቅ ተቋም ያስፈልጋታል። ይሄ ሲደመር ታላቅ ኢትዮጵያ ትሆናለች የሚል እምነት ነው ያለኝ።
ከዛ ውጭ አየር ኃይል ለምን ያስፈልጋል ላልከው አሁን ዘመኑ ተቀይሯል። ከላይ እንደገለጽኩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንም እንዳሉት፤ በአሁኑ ዘመን ምሽግ ቆፍረህ፣ ክላሽ ይዘህ፣ ብቻ አያዋጣም። ይሄ አያስፈልግም ለማለት አይደለም። እንደውም የሚደመስሰ፣ የሚጨርሰ፣ የሚያፀዳ ነው። ነገር ግን ሁኔታ ቀያሪ ኃይል ያስፈልጋል። አየር ኃይል ደግሞ በመሠረቱ ሁኔታ ቀያሪ ኃይል ነው። ምድር ላይ ያለውን ሁኔታ የሚቀይር ነው። ሁኔታዎችን ሁሉ የሚቀይር ስለሆነ ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ኃይል ያስፈልጋታል። ‹‹ለታላቅ ሀገር ታላቅ አየር ኃይል እንገነባለን›› ሌላኛው መሪ ቃላችን /ሞቷችን/ ነው። ስለዚህ ወሳኝ ነው ለማለት ነው።
አሁን አፍሪካ ውስጥ ከማን ነው የምንወዳደረው? ገና ራዕይ ስትቀርጽ እነማናቸው ከኛ በፊት ያሉት? በምንድነው? የሚል ነው። ይሄን ሁሉ እናውቃለን። ‹‹በጣም ግዙፍ አየር ኃይል አለን፣ እንዲህ አድርገናል›› የሚሉትንም እናውቃቸዋለን። ስለዚህ በምንድነው ነው የሚበልጡን? ለምንድነው እኛስ ይበልጡናል ብለን የምንገምታቸው? ወይም አጠገባቸው የማንደርሰው? ወይም የማናልፈው? የሚል እልህ ውስጣችን ያለው።
አሁን በትክክል አጠናን። በአካባቢያችን በአፍሪካ ውስጥ ያለው ምን አይነት አየር ኃይል ነው ያላቸው፤ ምን አይነት ፕላትፎርም እንዳላቸው፣ ምን አይነት የውጊያ ሲስተም እንደዘረጉ፣ ምን አይነት የሥልጠና ስልት እንደሚከተሉ፣ ምን አይነት የውጊያ ታሪክ እንዳላቸው በደንብ እናውቃለን። እንገነዘባለን። ይሄን ከተገነዘብን በኋላ ቅድሚያውን መውሰድ አለብን አልን።
እኛም ከዚህ ጎራ ውስጥ አለብን አልን። በነገራችን ላይ እንደ ተቋምም እንደ መከላከያም በምንም ተዓምር በሚቀጥለው ከስምንት እስከ አስር ባሉ ዓመት ውስጥ ቀዳሚ ሦስቱ ውስጥ መግባት አለባችሁ የሚል እቅድ ተቀምጧል። በተቋሙ ነው የተቀመጠው። እኛ ደግሞ ቀዳሚ ወይም የመጀመሪያው መሆን አለብን የሚል እቅድ አስቀምጠናል። ስለሆነም ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር ኃይል መሆን የግድ ነው።
ዱሮም ነበርን። ከላይ እንዳልኩት በውጣ ውረድ ነው የወረድነው። እኛ ስንታጠቅ አሁን የመጡት የአፍሪካ ሀገሮች ይቅርና ኤዥያኖች አውሮፕላን ምን እንደሚመስል አያውቁም ነበር። በ1921 እኛ ስንታጠቅ፣ እኛ ቴክኖሎጂውን ስናስመጣ፣ እኛ ስንበር፣ እኛ ስናሠለጥን እና አየር ላይ ስንበር ውጊያ ስንዋጋ አልነበራቸውም።
በነበረው ውጣ ውረድ አየር ኃይል ወርዶ ከሌሎች በታች የሆነው። ስለዚህ ይሄ ቁጭት ሊኖረን ይገባል። ሊጸጽተን ይገባል፤ ሊቆጨን ይገባል። ወደ ደረጃችን አሁን ዘመኑ ወደ ደረሰበትን ቀዳሚ የአየር ኃይል መገንባት አለብን። ቁጭቱ ነው ወደዛ የሚወስደን ደግሞ ማድረግም እንችላለን። እውነት ለመናገር እርሾዎች አሉ።
ወደዚህ የሚገፋ የሚያደርሱ፤ ከሰው ኃይልም፣ ከመሠረተ ልማትም ሆነ ከሌሎችም ያሉትን ይዘን የሚጨመረውን ቶሎ ጨምረን የመጀመሪያውን የአፍሪካ አየር ኃይል ለምን አንገነባም የሚል ነው። ምን ላይ ነው ያላችሁ ብለህ ብትለን ቀድመን እንደርሳለን፤ በእርግጠኝነት ቀድመን እንደርሳለን።
ጥያቄ ፡- አየር ኃይል ሠልጣኝ ወይም አባል ለመሆን ወስነው ይሄን ግቢ ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጡበት ቀን የሚያስታውሱት ከሆነና የዛን ቀን ምን እንደተሰማዎት ቢነግሩን?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ ፡- እውነት ለመናገር አላሰብኩበትም። ማለት እኔ የሆለታ ገነት የኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪክ ሦስተኛ ዓመት ተማሪ ነበርኩኝ። አየር ኃይል ለመቀላቀል ብዙም አላሰብኩም። አጋጣሚ ሆኖ ጥሩ የአካዳሚ ብቃት ስለነበረኝ ምልመላ ሲመጣ እንደማንኛውም ሰው ቀረብኩኝ። በውስጤ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም።
ልሞክር በሚል በመጀመሪያ የአካል ብቃት ምርመራ ነበር፤ ማለትም ቁመት፣ አይን፣ ጆሮ ወዘተ. ከጨረስኩኝ ከሳምንት በኋላ ወደዚህ ግቢ መጣሁ። ወደዚህ ግቢ ከመጣሁ በኋላ አላመንኩም። በርካታ የሜዲካል ምርመራዎች ተደረጉና መጨረሻ ላይ ‹‹ፊት ፎር ፍላይት ስኩል›› (FS) የሚል መዝገቤ ላይ ተጻፈ። ይሄ ሲጻፍ ደስ አለኝ፤ ደነገጥኩም። እኔ አብራሪ እሆናለሁ የሚል ሀሳብ አልነበረኝም።
የሆነ ታሪክ ትዝ አለኝ። እኔ የተወለድኩትና ያደኩት ገጠር ነው። ትምህርት የጀመርኩትም በጣም ገጠር ነው። አራተኛ ክፍል ሆኜ ትምህርት በሬዲዮ ትልቅ ግራር ስር ሆነን ተከታትለን ከጨረስን በኋላ እየተጫወትን ሳለን አሁንም በሕይወት አሉ ዳይሬክተራችን ለሚዬ ላምቢሶ ይባላሉ።
እያንዳንዳችንን እየዞሩ ይጠይቁናል። አንተ ምን መሆን ትፈልጋለህ አሉኝ፤ ዶክተር አልኳቸው። አንተ ዶክተር አትሆንም ፓይለት ነው የምትሆነው አሉኝ። ወደ በረራ ትምህርት ቤት ስገባ እሱ ትዝ አለኝና አስታወስኩ። ይሄንን አጋጣሚ እስከዛሬም አስታውሳለሁ። ፊዚክስና ሒሳብ በጣም ትወዳለህና አንተ ፓይለት ትሆናለህ አሉኝ። ፊዚክስና ሒሳብ በጣም እወዳለሁ።
ጥያቄ ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላን ይዘው ብቻዎትን ከምድር ከፍ ያሉባት ቀን ምን ነበር የምትመስለው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ ፡-ድሬዳዋ ነው፤ ነሐሴ 29 ቀን 1988 ዓ.ም. ነው ብቻዬን/ ሶሎ የበረርኩት። መዝግቤ ይዠዋለሁ። ከአስተማሪ ጋር ስትበሪ ጎን ለጎን ነው የምትቀመጭው። ተማሪ በቀኝ በኩል፣ አስተማሪ በግራ በኩል ይቀመጥና ያስተምራል፤ ያስተምራል፤ ያስተምራል፤ መጨረሻ ላይ ሲደርስ ይሄ ሠልጣኝ ብቻውን መብረር ይችላል ብሎ ሶሎ እንዲያደርግ ይፈርማል። እኔ እሠራለሁ ግን ብዙም ራሴን አላመንኩም፤ ገና መሥራት አለብኝ የሚል ነበረኝ። አስተማሪዎች በየጊዜው የየቀኑን ይገመግማሉ፤ማነው ሶሎ የሚወጣ የሚለውን ይወስናሉ።
አንድ ቀን አስተማሪዬ ነገ ጠዋት ሶሎ ትበራለህ አለኝ። የእውነት ደርሻለሁ ችያለሁ ስል ሳልተኛ ነው ያደርኩት። ለአንድ አብራሪ ሶሎ ማለት በሕይወቱ አብራሪ መሆን አለመሆን የሚወሰንበት ነው። ሌሎች ደረጃዎች አሉ። ከዛ በኋላ የሚቀጥሉ ናቸው። ምንም ሳልተኛ አደርኩኝ። ጠዋት መጣሁ እንደምንም ሻወር ወስጄ እራሴን አረጋጋሁ። ስሜታዊ መሆንም አለ። ምክንያቱም የሕይወት መጀመሪያ ነውና ። የመጀመሪያ ፔሬድ የሚባለው አብረን ካስተማሪዬ ጋር በረርኩ።
ከዛ ኖርማል መሆኔን እና በጣም የተረጋጋሁ መሆኔን ለማየት አሁንም ጦሩ ውስጥ ሥራ ሠራሁ። ከዛ በኋላ ሂድ አለኝ ። ከዛ ይዤ ተነሳሁ። ከዛ አስተማሪ የለም ብዬ ወንበሩን እነካካለሁ፣ አሁንም ዞሬ አያለሁ፤ አስተማሪው ይሄንን እንዲህ፤ ይሄንን እንዲህ አድርገሀል፤ ይሄንን አበላሽተሃል ይሄንን አጥፍተሃል የሚል የለም እንዴ? እያልኩ ዞሬ አያለሁ፤ ከዛ በኋላ አትቆይም ብዙ ‹‹ፓተርን ሶሎ›› ነው የሚባለው ሁለት ጊዜ ዞረሽ ተመልሶ ማረፍ ነው። ከዛ አረፍኩ፤ በኋላ ደግሞ፤ ውሃ መድፋት፣ አበባ መስጠት አለ ከዛ በጣም ደስ በሚል ሁኔታ ሶሎ ወጣሁ ማለት ነው።
ጥያቄ፡- በምን አይነት አውሮፕላን ነበር የበረሩት፤ ከዛ በኋላስ ምን አይነት አውሮፕላኖችን አብርረዋል?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- የኔ ጊዜ sf2 60 የምትባል የመጀመሪያ ደረጃ ማሠልጠኛ አውሮፕላን ነች። አሁን ለኦቨር ኦል ገብቶ ከባድ ጥገና ውስጥ ነው ያሉት። ቁጥሯንም አስታውሳለሁ ቴል ቁጥሯ 159 ነው። በሱ ነው የመጀመሪያ ሶሎ የበረርኩት ከዛ ቀጥሎ L39 ነው የሄድኩት የመጀመሪያ ዊንግ ያገኘሁበት አውሮፕላን ነው:: ቀጥሎ ሚግ 23 ነው የሄድኩት ቦንበር ነው። ለሁለት ዓመት ተኩል ቦንበር ወይም ሚግ 23 ተዋጊ አውሮፕላን ነው ያበረርኩት
ጥያቄ፡- በታሪክ ቅብብሎሽ እዚህ ደርሰው የዚህ ታላቅ አየር ኃይል አዛዥ ሆነዋል ይሄ ታሪካዊ አጋጣሚ እንደ ግለሰብ ለእርስዎ የሚፈጥርብዎት ነገር ምንድነው?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ ፡ በሁለት ነገር አንደኛ እንዳልሽው ይሄ ተቋም በጣም ትልቅ ተቋም ነው። እዚህ ተቋም ውስጥ ተማሪ ሆኜ ገብቼ ፤ አብራሪ ሆኜ፤ አሠልጣኝ ሆኜ እንደገና በአመራር ደረጃ መጥቼ አዛዥ ስሆን የሆነ ክብር ይሰማኛል። ከታች ጀምሬ ነው የመጣሁት። ክብር ነው የሚሰማኝ። እንደ ኃላፊነት ሲታይ ደግሞ በጣም ከባድ ነው።
የግል ሕይወት የሚባል የማይታሰብበት፤ ምክንያቱም ፍጥነቱ እንደዚህ ነው አየር ኃይል ማለት። የግል ሕይወት፣ የግል ኑሮ እውነት ለመናገር የማይታሰብበት የሥራ ሁኔታ ነው። እኔ ወደዚህ ቦታ ከመጣሁ ጀምሮ በጣም ጥሩ ሥራ ሠርቻለሁ፤ ነገር ግን በግል ሲታይ ደግሞ ዕረፍት አይኖርም። ሁሉም ነገሮች በጊዜው መሠራት አለባቸው፤ በጊዜው መስተካከል አለባቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ግዳጅ እና ተያያዥ ሁኔታዎች በየት በኩል እንደሚመጣ፣ መቼ እንደሚመጣ አታውቂም። የተፈጥሮ ሁኔታም ማለትም የምንበርባቸው አካባቢዎችና ቦታዎች ወዘተ. በእኔ ደግሞ እስከአሁን ባሳለፍኩት እንደምታዩት ግጭቶች የበዙበት ነው። በአንድ በኩል እዚህ መድረሴ ትልቅ ክብር ነው የሚሰማኝ በሌላ በኩል ትንሽ ጫና አለው።
የግል ሕይወት ቀርቶ ለሀገርና ለተቋም ካላልሽ አትወጪውም። መወጣት በጣም ከባድ ነው። ሁለቱን አንድ ላይ ማስኬድ አትችይም። ለወደፊቱም ከዚህ በላይ አየር ኃይልን ከሌሎች ጓዶቼ ጋር ሆነን ገንብተን፣ አስተምረን፣ አሳምረን፣ አስታጥቀንና አሠልጥነን ለሚቀጥለው ትውልድ የአማረ አየር ኃይል ለማስረከብ ዝግጅ ላይ ነን።
ጥያቄ – እጅግ ከተጣበበ ጊዜዎት ውስጥ እንደዚህ ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ ለማድረግና ቆይታ ለማድረግ ስለፈቀዱ እጅግ በጣም እናመሰግናለን?
ሌተናል ጀኔራል ይልማ፡- እኔም ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም