አካል ጉዳተኞች በመሠረተ ልማት ችግር፣ ትምህርት፣ በሥራ እና በሌሎች የአካታችነት እጦት ሳቢያ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተስፏቸው ሲገደብ በስፋት ይስተዋላል። ልዩ ችሎታቸውን ተጠቅሞ ከራሳቸው አልፈው ሀገር እንዲጠቅሙ የማድረጉ ሥራም የተቀዛቀዘ እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል። አካል ጉዳተኞች በትምህርትም ይሁን በሌሎች የሥራ መስኮች የመሠማራት መብት አላቸው። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች መብቶቻቸው ተግባራዊ አይሆኑም።
የሴቶች እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚነትን አስመልክተው እንደሚገልፁት ከአካል ጉዳተኞች ጋር የተያያዙ የተለያዩ ሕጎች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራቴጂዎች ቢኖሩም የተበታተኑ ናቸው። ከዚህ በመነሳት ሕጎቹን ሰብሰብ በማድረግ ‹‹የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግ›› አስገዳጅ ሆኖ ሁሉም ሊተገብረው በሚገባ መንገድ እየተዘጋጀ ይገኛል። አካል ጉዳተኞች ብቻቸውን ነገሮችን መቀየር አይችሉም፤ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትርጉም ያለው ትብብር ሲያደርጉ ውጤት ከማምጣት በሻገር ተሳትፏቸውን ለማረጋገጥ ያግዛል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍትሕ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ አቶ ፋሲካ አጌና እንደሚያስረዱት ሕግ መሠረታዊና ለሁሉም ኅብረተሰብ ክፍል ያስፈልጋል። ለአካል ጉዳተኞች ደግሞ አስፈላጊነቱ ከዚህም በላይ ነው። ለዚህም ዋናው ምክንያት አካል ጉዳተኞች ከሌላው ኅብረተሰብ በተለየ ለመብት ጥሰት የተጋለጡ በመሆናቸው ነው። ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር ብዙ ሕጎች አሉ ለማለት አያስደፍርም።
አሁን በሥራ ላይ ያሉ የተለያዩ ሕጎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ያፀደቀችው እንዲሁም የሀገሪቱ የሕግ አካል የሆነው የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቬንሽን በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ሕጉ ዘመናዊ ሕግ፣ የአካል ጉዳተኞች መብቶች ከሰብዓዊ መብቶች አንፃር በሰፊው የሚያትት ነው። በተጨማሪም ‹‹የአካል ጉዳተኞች የሥራ ስምሪት›› እና ‹‹የማራካሽ ስምምነት›› የሕትመት ሥራዎችን ለዓይነ ስውራን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ነው።
የአካል ጉዳተኞች ሥራ ስምሪት መብት አዋጅ ቁጥር 568 አካል ጉዳተኞች ያለመድሎ እና መገለል የሥራ ዕድል እንዲያገኙ የሚፈቀድና ረዳት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሲሆን የመብት ጥሰት ሲያጋጥማቸው ደግሞ ያለ ውጣ ውረድ ፍትሕ እንዲያገኙ የሚያስችል ሕግ ነው። ነገር ግን አሁን ያሉት ሕጎች በቂ አይደሉም። የአካል ጉዳተኞችን መብት ለማስከበር ገና በርካታ ሕጎች ያስፈልጋሉ። ‹‹የአካል ጉዳተኞች መብቶች ኮንቬንሽን›› የሚስገድደው መንግሥታት አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ሕጎችን እንዲያወጡ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም አሁን እንቅስቃሴ እየተደረገበት ያለው መንግሥት በሥራ ስምሪት፣ በትምህርት፣ በጤና፣ ከታክስ ጋር በተያያዙ እና ሁሉን አቀፍ የአካል ጉዳተኞች መብቶችን ያቀፈ ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል።
እንደ አቶ ፋሲካ ማብራሪያ፤ አካል ጉዳተኞችን ያማከሉ ሕጎች ጥቂቶች ናቸው። በአብዛኛውም ሕጎቹ የአፈፃፀም ችግር የሚታይባቸው ናቸው። እንደውም በመንግሥት በኩል የተሻለ ተፈፃሚነት አላቸው። አካል ጉዳተኞችን በመቅጠር ረገድ መንግሥት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል። ነገር ግን የግሉ ዘርፍ አካል ጉዳተኞችን ከመቅጠር ራሱን ያገለለ ነው። ስለዚህም አዋጁ በግል ዘርፉ ላይ በበቂ እየተተገበረ አይደለም። የተቀመጠው የአሠራር ሥርዓት ልል መሆን ደግሞ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ነው። ይህም በቂ ሕጎች አለመኖራቸውን ያመላክታል። ሕጎቹን ለማስፈጸም ደግሞ ሌሎች ሕጎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቷል። ሕጉ ተግባራዊ ሲሆን ሁሉም አካል ጉዳተኞች በቂ የሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከማድረጉ ባሻገር፤ የሚንጠባጠብ መብት አይኖርም። ለሁሉም የአካል ጉዳት ዓይነት ወይም በፆታ፣ በዕድሜ እና በመሳሰሉት ሳይከፋፈል በቂ ሽፋን ይሰጣል።
በኢትዮጵያ በስፋት የሚታየው ችግር የተጠያቂነት ሥርዓት የሚደነግግ ሕግ የለም። ከዚህ አኳያ የአካል ጉዳተኞችን መብቶች የሚጥሱ አካላት፤ ለድርጊታቸው ዋጋ መክፈል አለባቸው። ይህ ሳይሆን ሲቀር ግን መብቶችን በሚፈለገው መጠን ለማስከበር አዳጋች ይሆናል። ያደጉት ሀገራት ቀርተው ጎረቤት ሀገራት ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎች አካል ጉዳተኞች በቂ የሚባል የመብት ሽፋን አላቸው። በተጨማሪም መብቶችን መሬት ላይ አውርደው የሚያስፈጽሙበት የተጠያቂነት አሠራር ሥርዓት አላቸው።
ወደፊት ለመሄድ ወደ ኋላ ማየት ያስፈልጋል። ስለዚህ የደረስንባቸውን ስኬቶች ማበረታታት ይገባል። የአካል ጉዳተኞች መብት ስምምነት ኮንቬንሽን መብት መፅደቁ ትልቅ እርምጃ ነው። በዚህም ከአስተሳሰብ ጀምሮ ብዙ ለውጦችን ለማምጣት አስችሏል። በቁጥር ትንሽ ይሁኑ እንጂ የብዙ አካል ጉዳተኞችን ሕይወት የለወጡ ሕጎች አሉ። እነዚህን ማበረታታት እንዲሁም የተደረጉ ጥረቶች እውቅና መስጠት ይገባል።
ለመብቶች ጥበቃ የሚያደርገው ሕግ ነው። ‹‹የተጠቃለለ የአካል ጉዳተኞች ሕግን›› ጨምሮ በቂ ሕጎች መውጣት አለባቸው። የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተጣምሮ እና ተጨፍልቆ ወይም ማኅበራዊ ዘርፍ ውስጥ ተካቷል። ራሱን በቻለ ደረጃ የአካል ጉዳተኞችን ጉዳይ ብቻ የሚመለከት አንድ መንግሥታዊ ተቋም ቢቋቋም ችግሮችን ለመቅረፍ ያግዛል።
በተጨማሪም አካል ጉዳተኛው ላይም ይሁን ማኅበረሰቡ ላይ የግንዛቤ እና የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። አካል ጉዳተኝነት ምንድነው? አካል ጉዳተኛው ማነው? ምን መብቶች አሉት? የሚለውን ጉዳይ ማኅበረሰቡ እንዲገነዘበው ከተደረገ መብቶቻችንን መጠየቅ ሳያስፈልግ መብቶቻችንን ወደ ማክበር ሊኬድ ይችላል።
እኛ ዛሬ አካል ጉዳተኞች እንሁን እንጂ ሁሉም ሰው ‹‹ፖተንሻሊ›› አካል ጉዳተኛ ነው። የሚሉት አቶ ፋሲካ፤ ዓለምን ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ማድረግ ለሌሎች ኅብረተሰብ ክፍል ተብሎ የሚደረግ ሳይሆን ሁለም ሰው ለራሱ ሲል የሚያደርገው እንደሆነ ግንዛቤ መፍጠር ያሻል።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 4 ቀን 2016 ዓ.ም