ኢትዮጵያ የኩሩ ሕዝብና የጀግኖች ሀገር ነች ሲባል በግምት አይደለም። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረው የአርነትና ተጋድሎ ታሪካችን ምንጊዜም ስለሚዘከር ነው። ኢትዮጵያ ዘመናዊ የጦር ኃይል መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በዋንኛነት ከሚጠቀሱት የጦሩ ክፍሎች አንዱ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ነው። አየር ኃይሉ ከተመሠረተበት ከኅዳር 20 ቀን 1928 ዓ.ም. ጀምሮ የሀገርን የአየር ድንበር ከመጠበቅ አንስቶ በተለያዩ የውጊያ ዓውዶች ከፍተኛ ጀብዱዎችን በመፈጸም ለሀገርና ለሕዝብ የኩራት ምንጭ የሆነ ተቋም ነው።
ከምሥረታው እስከ 1942 ዓ.ም በንጉሡ ቀጥታ አመራር በሲዊዲናዊዎቹ ጄኔራል ሐርድና ካውንት ቮን ሮዛን (ኮሎኔል) አማካሪነት ሥራውን የጀመረው አየር ኃይሉ፤ ከምሥረታው ማግስት ጀምሮ በሙያው አንቱታ ባተረፉ እንደ ሜ/ጄ አሰፋ አያና፣ ሜ/ጄ አበራ ወ/ማርያም፣ ሜ/ጄ ፋንታ በላይ እና ሜ/ጄ አምሐ ደስታ የተመራ ባለብዙ ገድል ተቋም ነው።
እንደ እ.ኤ.አ. በ1935 በጣሊያን ወረራ ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የነበሩት አራት አብራሪዎች ብቻ ነበሩ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አሥራ ሦስት አውሮፕላኖችና ጥቂት የማጓጓዣ አውሮፕላኖችም ነበሩት። ከእ.ኤ.አ ከ1934 እስከ 35 አውሮፕላኖቹ ለአምቡላንስ ሥራ ጭምር ያገለግላሉ ነበር። አየር ኃይሉ እስከ 1935 በኮሎን ጆን ሮቢንሰን (አፍሪካዊ አሜሪካዊ) ነበር ይታዘዝ የነበረው።
ፋሺስት ኢጣሊያ በዳግም ወረራው ወቅት አየር ኃይሉን በኢትዮጵያውያን አርበኞች ላይ በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለን የጦር መሣሪያ ሳይቀር ተጠቅሞ በሀገሪቱ ላይ አደገኛ ተፅዕኖ ያለው የሰው እና የእንስሳት ሕይወት የቀጠፈ ጉዳት አስከትሏል። ንጉሥ ኃይለስላሴ ከስደት ከተመለሱ በኋላ ከጣሊያን ትምህርት በመውሰድ የአየር ኃይል በጦርነት ውስጥ ያለውን ጨዋታ ቀያሪ ሚና በመገንዘብ አየር ኃይሉን ደግም ለማደራጀት ጥረት አድርገዋል።
በወቅቱ ንጉሡ እኤአ በ1946 ከአሜሪካና ከታላቋ ብሪታንያ ባገኙት ወታደራዊ እርዳታ ጥቂት አውሮፕላኖችና የበረራ ትምህርት ቤት መቋቋም ችለው ነበር፡፡ በኋላ ግን አሜሪካም ሆነች ታላቋ ብሪታንያ የኢትዮጵያን አየር ኃይል ለመደገፍ ባለመፈለጋቸው ንጉሡ ፊታቸውን ወደ ስዊድን በማዞር ዘመናዊ አየር ኃይል ለመገንባት ጥረት ማድረግ ችለዋል።
የአየር ኃይሉ ከሀገር ውስጥ ግዳጅ ባለፈ በዓለም አቀፍ የሠላም ማስከበር ሥራዎች ላይ በመሳተፍ አንቱታን ያተረፈ ነው ። ለዚህም በ1960 ዓ.ም በአራት ኤፍ 86 አውሮፕላኖች በፍላይት ደረጃ ኮንጎ ዛየር በተደረገው የሠላም ማስከበር ሥራ ላይ በቀዳሚነት ተሳትፏል። 2000 ዓ.ም ዳርፉር ሱዳን (UNAMID) በአቭዬሽን የሰላም ማስከበር ዩኒት በአምስት ሚ- 35 ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ከተሟላ የጥገና አቅምና የድጋፍ መሣሪያዎች ጋር ተሰማርቷል። በአብየና ሩዋንዳ የሎጅስቲክና ጦር ማዘዋወር ግዳጆችን በብቃት መወጣቱን መጥቀስ ይቻላል።
የቀድሞው የሶማሊያ አምባገነናዊ መሪ ዚያድ ባሬ በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የከፈተውን የመስፋፋት ጦርነት በብቃት እና በታላቅ ተጋድሎ ለመከላከል በተደረገው ጦርነት አየር ኃይሉ ከፍ ባለ ብቃት የፈጸማቸው ጀብዱዎች የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ሂደት የጎላ ስፍራ ከመያዝ ባለፈ፣ ተቋሙና ባለሙያዎቹ የብዙ ጀብዱ ትርክቶች ባለቤት እንዲሆኑ አድርጎታል።
ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት ጊዜውና አጋጣሚውን መርጣና ተደራጅታ ነበር፡፡ ጃንሆይ ከሥልጣን እንደወረዱ ደርግም ገና ምኑን ልያዘው፤ ምኑን ልጨብጠው በሚልበት ጊዜ በአጠቃላይ በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ የነበራት አራት ክፍለ ጦር ብቻ ነበር።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዚያን ዘመን ለማጓጓዥ ዳኮታና ሲ-42 የተባሉ የአሜሪካን አውሮፕላኖች እንዲሁም ኤፍ-5 የተባለ ተዋጊ ጄት የታጠቀ ነበር። ከንጉሡ ከሥልጣን መውረድ በኋላ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ባለችበት ወቅት ነው የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬ ከሶቪየት ኅብረት እጅግ ዘመናዊ የተባሉትን ሚግ 21፣ ሚግ 23 የጦር ጄቶችን እና ሚ-17 የመሳሰሉትን ተዋጊ ሄሊኮፕተሮች ፤ ቲ-55-57 ታንኮችን፤ 120 ሚሜ መድፎችን ቢ ኤሞችን ብረት ለበሶችን ጊዜ ወስዶ፣ ታጥቆና ተደራጅቶ በሚገባም አሠልጥኖ፤ ነበር ወረራ የፈፀመው፡፡ በዚህ ጦርነት ታዲያ አየር ኃይሉ የፈፀመው ጀብዱ ታላቅ ነበር።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል በንጉሡ ዘመን ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገትና መሻሻል እያሳዬ ነበር። ለእዚህ ማሳያው የውጊያ ችሎታና የበረራ ትርዒት ላይ አስገራሚ ብቃት ያላቸው አብራሪዎች መታየታቸው ነበር። በ1960ዎቹ መጀመሪያ የነበሩ የንጉሠ ነገሥቱ አየር ኃይል አብራሪዎች ብዛት ባላቸው አውፕላኖች የአየር ትርዒት ማሳየት የተለመደ ነው። በአንድ ወቅት ንጉሡ በክብር እንግድነት ሲገኙ አብረዋቸው የነበሩት የኬንያው ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታ «የኢትዮጵያን ነፃነት በሚገባ የሚጠብቅና በቂ ዋስትና ያላችሁ ለመሆኑ ይህ ዓይነተኛ ምስክር ነው። ስለዚህም ዓይነ ሥውር ካልሆነ በቀር የኢትዮጵያን ነፃነት ለመድፈር የሚመጣ ይኖራል ብዬ አላምንም» ማለታቸውን ከአየር ኃይል የተገኙ ሰነዶች ያስረዳሉ።
የአየር ኃይል የአቭዬሽን ጥገና አቅሙ መጐልበትም በጥንካሬ የሚነሳ አቅም ነው። ምንም እንኳን የጥገና ተቋሙ ከ1921 ጀምሮ በውጭ ሀገር ዜጐች ጭምር አገልግሎት ሲሰጥ ቢቆይም 1970ዎቹ ገደማ መዳከም አሳይቷል። በተለይ «የሶቭዬት ኅብረት ትጥቆች ወደ ሀገራችን መግባታቸውን ተከትሎ አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች ብልሽት ሳያጋጥማቸው ውጭ ሀገር ልኮ ማሠራት የተለመደ ነበር።» ይላሉ ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል የሠሩ ኃላፊዎች።
ከአየር ኃይል የወጣ የጽሑፍ መረጃ እንደሚያስረዳውም በ1982 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ የውስጥ ጥገና አቅም በመዳከሙ የማይሠሩ አውሮፕላኖች በዝተው ነበር። ለምሳሌ ከነበሩት 48 ሚግ 21 አውሮፕላኖች መካከል ለውጊያ ዝግጁ የነበሩት 6 ብቻ ነበሩ።
ከደርግ መንግሥት ውድቀት በኋላ ሥልጣን የያዘው በሕወሓት የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት አየር ኃይሉን እንደገና ለማደራጀት በሚል አፍርሶ ብዙ አንጋፋ አብራሪዎች አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል። በ2010 ወደ ሥልጣን የመጣውና በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚመራው መንግሥት ለተቋሙ በሰጠው ልዩ ትኩረት አየር ኃይል እንደገና ተደራጅቶ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በአየር ለመጠበቅ ዝግጁ መሆን ችሏል።
በሂደት ሲዳከም ቆይቶ አየር ኃይል ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ትንሳኤውን አግኝቷል፡፡ ከአየር ኃይል የጥገና ማዕከል ባሻገር ዛሬ በደጀን አቭዬሽን የሚሠሩ (የሚጠገኑ) አውሮፕላኖችና ሄሊኮፕተሮች ከሀገር አልፈው እንደ ሱዳን አንጎላና ደቡብ ሱዳንን ጭምር እያገለገሉ ነው። በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የአውሮፕላንና ሄሊኮፕተር ሞተሮችና ክንፎችን እንዲሁም የውስጥ ክፍሎች በጥራት ይጠገናሉ። «የኦቨር ሆል» ጊዜ ገደብ የማራዘም ሥራ የሞዲፌኬሽንና የፈጠራ ሥራዎች ይከናወናሉ።
የኢፌዴሪ አየር ኃይል ሲቋቋም የነበሩት የአየር ምድቦች የማዕከሉን ደብረ ዘይት ምድብ ጨምሮ በአሥመራ በድሬዳዋና በሐረር ነበር። ከደርግ ውድቀት በኋላ መቀሌና ባሕርዳር ተጨምሮ አሁን በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫ የአየር ምድቦች ተቋቁመዋል። በእዚህም ሀገሪቱን ከማንኛውም የአየር ጥቃት የሚጠብቅ የ24 ሰዓት ተጠንቀቅ ያለው አቅም ስለመገንባቱ ከአየር ኃይል የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።
የአየር ኃይል የማዕከል ምድቡ ግቢ (ቢሾፍቱ) ሞቃታማ ቢሆንም አረንጓዴ የሞላበትና ፅዳት የማይለየው ነው። ይህንን አንጋፋ የሀገር ባለውለታ ተቋም የተለያዩ የሀገር መሪዎች ጎብኝተውታል፡፡ ከእንግሊዛዊቷ ንግሥት ኤልሳቤጥ ጀምሮ የቤልጅየሙ መሪ፤ የኩባው መሪ ፊደል ካስትሮ፣ የጋናው መሪ ጆሪ ሮሊንግ የኮንጐው ሞቡቱ ሴ ሴ ሴኮን ጨምሮ ሌሎችም በተለያየ ጊዜ የነበሩ የተለያዩ የሀገር መሪዎች ጎብኝተውታል። አድናቆታቸውንም ቸረውታል፡፡
በአንድ ወቅት ስመገናና የነበረው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በመሐል መዳከም ቢታይበትም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ድንቅ ግስጋሴ እያስመዘገበ ይገኛል። የበረራ አቅሙን ወቅቱ እስከደረሰበት ቴክኖሎጂ በማሳደግ ያለውን ነባር አቅም (ሀብት) በመጠንና በጥራት በማሻሻል የሰው ኃይሉን በስፋት በማልማት ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ሀገራዊና ሕገመንግሥታዊ ኃላፊነቶቹ ባሻገር በማኅበራዊ ዘርፍም ሰፊ ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል።
በስፖርቱ ዘርፍ አየር ኃይል አንጋፋው ሻምበል ምሩፅ ይፍጠርን ጨምሮ በርካታ አትሌቶችን አፍርቷል። በእግር ኳስ ስፖርትም አየር ኃይል ስም ያለው ክለብ የነበረውና(ንብ)የሚል ቅፅል ስያሜ የተሰጠው የእግርኳስ ቡድን እስከ አሁንም የቀጠለ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጥሩ ተፎካካሪ ሆኖ ይገኛል። ሌላው በአካባቢ ጥበቃና የልማት ሥራዎች ረገድ በተለይ የአየር ምድቦች በሚገኙበት አካባቢ ካለው ማኅበረሰብ ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ያለ ተቋም እንደሆነ ይነገራል።
በደብረዘይት (ቢሾፍቱ) አየር ኃይል አካባቢ የሚኖሩ የከተማዋ ነዋሪዎችም ለተቋሙ ያላቸው ፍቅር በተለያየ ጊዜ ይገልፃሉ «አየር ኃይልና ደብረዘይት ተነጣጥለው አይታዩም። እንዲሁ ደግሞ በአካባቢ ልማትም ሆነ በአደጋ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳት አየር ኃይል የተለያየ ተሳትፎ ያደርጋል።
ቀደም ሲል የአየር ምድቡ ከከተማ ዳርቻ የተሠራ ቢሆንም አሁን በከተማዋ መስፋፋት አንዳንድ መኖሪያ ቤቶች ተጠግተውታል። አንዳንዶች የአውሮፕላንና ሄሊኮፕተር ድምፆች ዘወትር ቢጮኽም ስለለመዱት የሚሰለቻቸው አይደለም። ከተቋሙ መስፋፋትና መጠናከር ጋር ተያይዞ በሚፈጠረው የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚጠቀሙ፣ በሚፈጠረው የሥራ ዕድል ሕይወታቸውን መምራት የጀመሩ የአካባቢው ነዋሪዎችም አየር ኃይልን ይበልጥ የኩራታቸው ምንጭ ማድረግ ችለዋል። በአጠቃላይ አንጋፋው የኢፌዴሪ አየር ኃይል ከትናንት እስከ ዛሬ ብዙ ውጣውረዶችን አልፎ እነሆ እዚህ ደርሷል።
የአንድ መከላከያ ኃይል እምቅ አቅምና ጥንካሬ፤ የመለኪያ መስፈርቶቹ፤ የሠራዊቱ ብቃትና የውጊያ ዝግጁነት የታጠቀው ዘመናዊ የጦር መሣሪያና በታጠቀውም መሣሪያ በየትኛውም የመሬት ገጽ ላይ ለመጠቀም ያለው ችሎታና ብቃት ሀገርን ለመከላከል በውስጥ በተለያዩ ዓውደ ውጊያዎች ተሰልፎ ያስመዘገበው ድልና ስኬት ከዚህም አልፎ ድንበር ዘለል ተልዕኮን በመወጣት ረገድ (ዓለም አቀፍ) ያሳየው ወይንም የሚያሳየው ብቃት የአቅሙን ልኬት ሊያሳዩ የሚችሉ ናቸው፡፡
አንድ የመከላከያ ኃይል ያለው የውጊያ ብቃትና ችሎታ የሚገነባው በሰላሙ ጊዜ በሚሰጠው ተደጋጋሚና የማያቋርጥ በተለያዩ ከግዳጅ አፈጻጸሙ ጋር ሊያጋጥሙት በሚችሉት ተመሳሳይ የመሬት ገጽታ ዓይነቶች ላይ በሚያደርገው ሥልጠና ከዚህም ባሻገር የተናጠል ሳይሆን የጣምራና የተቀናጀ የጦር ልምምዶችን በየሙያ መስኩ ያደርጋል፡፡
ጦርነት ሲቀሰቀስ አንድ በሰላሙ ጊዜ በሚገባ የተማረ የሠለጠነ የተደራጀ አሰላለፉን ጠንቅቆ የሚያውቅ ኃይል ሠርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ ዓይነት አይሆንበትም። ሌላው የመጎልበት መለኪያ የመከላከያ ኃይሉ በእጁ የያዛቸው የታጠቃቸው ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች ናቸው።
ኢትዮጵያ በተፈተነችበት ጊዜ ሁሉ ሉዓላዊነቷን ለማስከበር በጀግንነት ከተፋለሙ የሀገር መከላከያ ክፍሎች አየር ኃይል ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል ብንል ማጋነን አይሆንም። ይህ አንጋፋና የአፍሪካ ተምሳሌት የሆነው አየር ኃይል ከኅዳር 20 2016ዓ.ም ጀምሮ 88ኛ የምሥረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል። የምሥረታ በዓሉን በመጪው ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች በማጠቃለያ መርሐግብር እንደሚያከብር አስታውቋል።
የአየር ኃይል ምሥረታ በዓል ታሪካዊ አመጣጡን በጠበቀ መልኩ ይከበራል ያሉት የወቅቱ የአየር ኃይል አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ይህ ዝግጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ለግዳጅ ብቁ አብራሪዎችን ማስመረቅን ጨምሮ በፓናል ውይይት፣ ለሕዝብ ክፍት በሚሆኑ ጉብኝቶችና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚከበር ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አብራርተዋል።
የአዲስ ዘመን የዝግጅት ክፍልም መላው ኢትዮጵያውያንን ለዚህ የሀገር ባለውለታና መኩሪያ ለሆነ አንጋፋ ተቋም የ88ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ አደረሰን ይላል።
ክብረዓብ በላቸው
አዲስ ዘመን ታኀሣሥ 3 ቀን 2016 ዓ.ም