መሿለኪያ አካባቢ ከሚገኘው የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማህበር ስጋ ሲገዙ ያገኘኋቸው ወ/ሮ ሃና መስፍን የስጋ ዋጋ ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ ታይቶ እንደማይታወቅ ይገልጻሉ። ከማህበሩ ስጋ ቤት አንድ ኪሎ ስጋ በ160 ብር መግዛታቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ሃና “ለልጆቼ ብዬ እንጂ የስጋ ጉዳይ እኔን አያሳስበኝም፤ነገም ካልጨመረም ዕድለኛ ነኝ”ይላሉ ።
አያት መድሃኒዓለም አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ፍሬ ህይወት ብርሃኑ ደግሞ ኪሎ ስጋ 240 ብር መግዛታቸውን ይናገራሉ። ወደ መሃል ከተማ ገባ ላለ ደግሞ አንድ ኪሎ ከ300 ብር በላይ ሊሸጥ እንደሚችል የሚጠቁሙት ወይዘሮ ፍሬህይወት፣ ባለ ስጋ ቤቶቹ ምክንያት እየፈለጉ ዋጋ ሲቆልሉ የሚከላከልላቸው እንደሌለም ነው የሚገልጹት።
በኮተቤ አካባቢ የካራ ስጋቤት ባርና ሬስቶራንት ባለቤት አቶ ተስፋዬ ደስታ ከበዓል ወዲህ በአንድ የቁም ከብት ዋጋ ላይ ከ10ሺ ብር በላይ ጭማሪ መታየቱን ይጠቅሳሉ። በስጋ ዋጋ ላይ የተደረገውን ጭማሪ አሳሳቢ መሆኑን የሚጋሩት የኮልፌ ልኳንዳ አካባቢ ስጋ ነጋዴው አቶ ብርሃኑ አጃሞ በከብት ሻጩና ገዥው መካከል ያሉ ሰንሰለቶች መብዛት ለዋጋው መናር ምክንያት ሲሉ ይጠቁማሉ።
የአዲስ አበባ ልኳንዳ ነጋዴዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ አየለ ሳህሌ የስጋ ዋጋ ናረ የሚለው ቅሬታ ተገቢ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከፋሲካ ጀምሮ ለታየው ችግር በከብቶች ግብይት ያሉ ሕገወጥ ደላሎች መብዛት አንዱ ምክንያት መሆኑን በመጥቀስ የአቶ ብርሃኑን ሀሳብ ያጠናክራሉ።የመኖ እጥረት እና በሽያጭ ላይ የሚከፈለው ታክስም ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን ነው የሚጠቅሱት። ደላሎች በከብት ግብይት ውስጥ ገብተው የደለቡ ከብቶችን በ‹‹ኪስ ስልክ›› ፎቶ እያነሱ ዋጋ እየሰቀሉ ከብቶቹ ሳይንቀሳቀሱ ከገዢዎች ጋር የሚደራደሩበት ሁኔታም ሌላው የግብይቱ ችግር እንደሆነም ይጠቅሳሉ።
ሥራ አስኪያጁ መንግሥት የቁም እንስሳት የሚያደልበውን አካል መደገፍ፣ በማኅበር በማደራጀት የሕግ ከለላ መስጠት፣ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ሳይገባ ስጋ ነጋዴዎችና ሸማቾች የሚገበያዩበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን መንገድ በማመቻቸት ችግሩን መፍታት እንዳለበት ያብራራሉ።
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አረጋ በከተማዋ በሚገኙ 210 የሸማቾች ሱቆች ላይ የስጋ ሽያጭ እንደሚካሄድ ይገልጻሉ። ስጋ ቤቶቹን ግለሰብ ነጋዴዎች በጣም ባነሰ ዋጋ እንዲከራይዋቸው ተደርጎ ለሸማቹ አማራጭ ሆነው በመቅረብ የገበያ ውጥረትንና የዋጋ ንረትን በማርገብ እያገበያዩ መሆኑን ይናገራሉ።
ስጋ በሸማቾች ሱቆች ከ130 እስከ 170 ብር እየተሸጠ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሲሳይ፣ የበሬ ዋጋ ባልተጠበቀ ሁኔታ መናሩንም ይጠቅሳሉ።በዚህ ምክንያትም የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን ጠቁመው፣ የከብት የመኖ እጥረትም ለዋጋው መናር ሌላው ምክንያት ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደበሌ ለማ መፍትሔው ሕገወጥ የቁም እንስሳት ዝውውርን መከላከል፣ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የመኖ ልማቱን ማስፋፋት፣ የመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላትን ማጠናከር ነው ይላሉ። ለቁም ከብት ለውጪ ግብይት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ/ ወለል/ ተቀምጦለት እንደሚሸጥ ጠቅሰው፣ ለሀገር ውስጥ ግን አለመተግበሩን ይናገራሉ።
በተነሱት ጉዳዮች የሚስማሙት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ በየቦታው ሲፈጠሩ የነበሩ ሁከቶችና መንገድ መዝጋት በተወሰነ መልኩ ምርት ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ያደረገበት ሁኔታም በሀገር ውስጥና የውጪ የቁም እንስሳት እና ስጋ ዋጋና ግብይት ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይጠቅሳሉ። ዜጎች ለሰላም ዘብ ከመቆሙ አምራቹም ሸማቹም ተጠቃሚ እንደሚሆንም ይገልጻሉ።
ለሀገር ውስጥ የቁም ከብት ግብይት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ጣሪያ ማስቀመጡ ግን ነፃ ገበያውን እንደሚፃረር ይገልጻሉ።የውጪው የቁም ከብት ግብይት ግን የውጪ ምንዛሬን ለማስገኘት ካለ ፍላጎት አንፃር የግብይት ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ/ ወለል/ መቀመጡ ተገቢ መሆኑን ያስረዳሉ።
ለሀገር ውስጥ ሽያጭ ዋጋ መናር አንዱ ምክንያት የቁም እንስሳት ግብይትን ለማሳለጥ የወጡ መመሪያዎች እና ደንቦች በትክክል አለመተግበር ነው አቶ ወንድሙ፣የቁም እንስሳት ኮንትሮባንድ ግብይትም ሌላው ትልቁ ችግር ነው ይላሉ። ‹‹የኢትዮጵያን የቁም እንስሳት ማንነቱና አድራሻው የማይታወቅ ነጋዴ በድንበር ወደ ጎረቤት ሀገሮች ይዞ ይወጣል። የቁም እንስሳቱ የኛ ቢሆኑም ሌላ ሀገር እንዲገቡ ተደርገው በሌላ ሀገር ስም ይሸጣሉ።›› ሲሉ ያስገንባሉ።
ሕግ አስከባሪው፣ ሕግ አስፈፃሚው፣ሕግ አውጪውና ኅብረተሰቡም በጋራ ሕገወጥነትን ኮንትሮባንድ ንግድን መቆጣጠር መቻል አለበት። የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የፖሊስና የፍትሕ አካላት ጥምረት ወሳኝነት አለው ብለዋል።
የግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ጌትነት በበኩላቸው በስጋ ዋጋ ላይ የተፈጠረውን ንረት ለማርገብ ክልሎች ከከተሞች ጋራ የመጀመሪያ ደረጃ ግብይት ማዕከላትን ማጠናከርና ማኅበራት ዩኒየኖች ባለሀብቶችና ሌሎችም በመቀናጀት ሕጋዊ የግብይት ሥርዓቱ እንዲኖር የጋራ ርብርብ ማድረግ ይኖርባቸዋል ይላሉ።
የሕገ ወጥ የቁም እንስሳት ቁጥጥርን የማከናወኑ ሥራ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረግ ከፍተኛ ሥራ ይጠይቃል ያሉት አቶ ፍቃዱ፤‹‹ችግሩ ታይቷል ፤ያንን ለመፍታት ከሚመለከታቸው ጋራ በተለይ በድንበር በኩል የሚወጡትንም ሆነ በተለያየ መንገድ የሚንቀሳቀሰውን የቁም እንስሳት ዝውውር መከላከል ይገባል››ይላሉ።
ግብአቱን በተለይ የመኖ አቅርቦትና ፍጆታቸውን አጠቃላይ የእንስሳት አረባቡን ዘመናዊ ማድረግ ሌላው መፍትሔው መሆኑም ይጠቅሳሉ።‹‹የመኖ ልማት ራሱን የቻለ ሥራ ነው፤ ይህን ችግር በራሱ ለመፍታት በአርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ የመኖ ልማቱን በስፋት ለማምረት የተጀማመሩ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል›› ይላሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ