አዲስ ዘመን ትናንት፤ ዛሬና ነገም ጭምር ነው። ታሪክና ክስተት ሁነትና አጋጣሚዎች ሁሉም ከአዲስ ዘመን ትናንቶች ይቀዳሉ። አዲስ ዘመን ድሮ ዛሬም የሚነግረን ይህንኑ ነው። 1960ዎቹ በተለይም 1966 የዛሬው ምንጫችን ግዙፍ ኩሬ ነው። ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የፋኦ ምክር ቤት አባል የሆነችበትን የመጀመሪያው ዘገባ፤ የኢትዮጵያን ፊደላት ወደ አንድነት… የሐረር ጋሪዎች ሠልፍ አሳይተዋል። ጥቁሮችን በዕባብ? በዘረኝነት ናላው የዞረው ዲን ባርበር… እንዲሁም ከጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎችም ታክለው ለዛሬው ትውስታ ተሠናድተዋል።
ኢትዮጵያ የፋኦ ምክር ቤት አባል ሆነች
ኢትዮጵያ 27 አባሎች የሚገኙበት የተባበሩት መንግሥታት ምግብና የእርሻ ድርጅት(ፋኦ) ምክር ቤት አባል ሆና የተመረጠች መሆኗን ክቡር አቶ በለጠ ገብረጻድቅ የእርሻ ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ኅዳር 29 ቀን በነበረው የጋዜጠኞች ጉባዔ ላይ አስታውቀዋል።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 1966ዓ.ም)
የሐረር ጋሪዎች ሠልፍ አሳዩ
በሐረር ከተማ የሚገኙ ጋሪ ነጂዎች ከሐረር ማዘጋጃ ቤት በተሰጣቸው ምክር መሠረት በገንዘባቸው የተለየ የመታወቂያ ልብስ በማሰፋት መስከረም 12 ቀን 1966ዓ.ም ከቀትር በላይ ከነፈረስ ጋሪዎቻቸው ሰልፍ በመውጣት፤ የተሰጣቸውን ምክር በመፈጸም በጎ ተግባራቸውን አሳይተዋል።
አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 1966ዓ.ም)
233ቱ ፊደላት በ33 ብቻ ተቻቻሉ
233 የሆኑት የኢትዮጵያ ፊደላት፤ በ33 ብቻ ለመጻፍ የሚያስችል አዲስ የፊደል ቅርጽ ማውጫ ተሠርቶ ወጥቷል።
አዲሱን የፊደል ቅርጽ ማውጫ የሠሩት በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በቁም ጽሕፈት ክፍል ውስጥ የሚሠሩት አቶ ኃይሉ ጌታሁን ናቸው።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 13 ቀን 1966ዓ.ም)
ሂሊኮፕተሩ ጠፍቶ ተገኘ
ጎንደር፡- በእርሻ ሚኒስቴር የአዝዕርትና የተክል ክፍል ንብረት የሆነው ሂሊኮፕተር ጥቅምት 4 ቀን 1966ዓ.ም ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ የመቶ አለቃ ሽብሩ አያና የተባለው ፓይሌት ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር እየነዳ ሲሔድ የሞተሩ ዘይት ስለፈሰሰበት ተሰናክሎ በበጌምድር ሰሜን ጠቅላይ ግዛት ቋርሳ በተባለው ቀበሌ ወድቋል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 1966ዓ.ም)
ጥቁሮችን በዕባብ?
ከሲልማ፡- የአላባማ ፖሊስ ኃይል ባለፈው ሐሙስ አንድ ነጭ በአንድ ጥቁር አሜሪካዊ አፍ ውስጥ ነፍስ ያለው ዕባብ ለመክተት ሲታገል አግኝቶ በመያዝ እንዲታሠር ያደረገ መሆኑን ተገልጿል።
ጄምስ ክላርክ የተባለ አንድ የሲልማ ቀበሌ ሹም እንዳስረዳው ይህ 27 ዓመት የሆነው ዲን ባርበር የተባለው ወንጀለኛ ነጭ የብጥብጥ አስነሺ በመሆንና ድንገተኛ አደጋም በመጣል በተጨማሪ የተከሰሰ መሆኑን አስታውቋል።
የቀበሌውም ሹም ከዚህ በማያያዝ ሲያመለክት ተከሳሹ ዲን ባርበር ከዚህ ከፈጸመው ወንጀል ሌላ በሲልማ ቀበሌ በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የዘር ልዩነትን ለማስወገድ ስብሰባ በተደረገበት ዕለት አራት የሚሆኑ ጥቁር አሜሪካውያንን በዕባብ ያስነከሰ መሆኑን ደግሞ ገልጿል።
ይህም የቀበሌ ሹም ጉዳዩን በመዘርዘር አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች የነከሳቸውን ዕባብ ለመበቀል በተነሱ ሰዓት ብጥብጥ ተደርጎ እንደነበር አስረድቷል (ኤ.ኤፍ.ፒ)
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 10 ቀን 1966ዓ.ም)
ጥያቄ አለኝ ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
* ባለቤቴ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ከቤታችን ጋብዞ አመጣና ከቤት የተቀመጠውን አበባ አይቶ አደነቀን። ግን ከዚያው ከሳሎን ሆነው ከባለቤቴ ጋር ሲያወሩ ፈረንጁ ሲጃራ እያጨሰ አመዱን ወይም ኩስታሪውን ከአበባው ማስቀመጫ ውስጥ ይጨምር ጀመረ። በዚህ አደራረጉ አልተናገርንም እንጂ ባለቤቴም እኔም በጣም ተናደናል። ፈረንጁ እንደሔደም አበባውን ከነአመዱ አውጥተን ጣልነው። ፈረንጁ አበባውን አድንቆ የሲጃራውን አመድ ከውስጡ መኮስተሩ እኛን ለመናቅ ነው? ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?
ወይዘሮ ጸ.ደ
ትልቁ ነገር እንደተናደዳችሁ ያለመናገራችሁ ነው። ፈረንጁ ያን ያደረገው አበባው ቶሎ እንዳይደርቅ ብሎ ምግብ መስጠቱ ነው እንጂ እናንተን ለመናቅ ወይም ለሌላ ጉዳይ ብሎ አይደለም። እሜትዬ! ለወደፊቱም እንግዶች ሲወጡሎት በሲጃራ መኮስተሪያ ላይ ያጠራቀሙትን አመድ እውጭ ከማፍሰስ በአበባ ማስቀመጫው ላይ ይጨምሩት። ግን እንዳይበዛ። ያበባውን ዕድሜ ያረዝመዋል። ለመሆኑ ምን አይነት አበባ ነው የሚወዱት?
(አዲስ ዘመን ጥር 13 ቀን 1965ዓ.ም)
* ከዚህ በፊት በሀገራችን ውስጥ የሕንድ ፊልም በብዛት ይታይ ነበር። አሁን እስከአንዱም ጠፍቷል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው?
– መታየቱ ይታያል። በዚህ ላይ የምነግራችሁ ዳግመኛ ስለሕንድ ፊልም የምትጽፉልኝ ሰዎች እንዳትጽፉልኝ። ምክንያቱም በብዛት እየደረሱኝ እንደማያቸው ከመጠን በላይ የሚያሞግስና ሌላም ሌላም አድርጋችሁ ስለምትጽፉ እየታዘብኳችሁ ጥያቄያችሁን ጥዬዋለሁና ዳግመኛ እንዳትጽፉልኝ።
(አዲስ ዘመን የካቲት 16ቀን 1964ዓ.ም)
* አንድ የተፈረደበት ሰው ሊገረፍ በሚተኛበት ጊዜ ሰውየው ከመገረፉ በፊት መሬቲቱን ሁለት ጊዜ ገራፊው የሚገርፈው ለምንድነው?
ወታደር ሞገስ እሸቱ (ከመቱ)
ድሮ አንድ አስተሳሰብ ነበር። አንድ ሰው በሚመታበት ወይም በሚገረፍበት ጊዜ ሰይጣን አብሮ ይመታል ወይም ይገረፋል ይባል ነበር። ስለዚህ ሰይጣኑ ቸኩሎ ሰውየውን ከጅራፍ ጋር ሊገርፈው ስለሚፈልግ፤ ሰይጣኑን ለማታለል መጀመሪያ መሬቷን ሲገርፍ ሰይጣኑም የሚገርፈው መጀመሪያ ስለሆነ የሰይጣኑ ምት ከመሬት ላይ እንዲያርፍ ብለው ነው። ለምሳሌ አንዱ አንዱን ሰው ዦሮ ግንዱን ሲያንጋጋው ዦሮው እንዳጋጣሚ ሊደነቁር ይችላል። ይህም የሚባለው ሰይጣኑ አብሮት ስለመታው ነውና ምነው መጀመሪያ ከሌላ ዘንድ በመታው ይባላል። የሚደፈነው ግን ከጥፊው ጋር ከዦሮው ውስጥ የሚገባው አየር የጆሮውን ከበሮ ስለሚቀድደው ነው።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 1966ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ታኅሳስ 2 ቀን 2016 ዓ.ም