– ‹‹እኔም አለኝ ቁስል ያንተን የሚመስል››
– ‹‹አቁሳይ ገዥዎች እንጂ አቁሳይ ህዝብ የለም››
አዲስ አበባ፡– የግንቦት ሀያ በዓል በሀገራችን ታሪክ ተፈጥረው በነበሩ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ መዛነፎች ምክንያት በህዝቦቻችን ላይ የደረሱ በደሎች ትተው ያለፏቸውን ቁስሎች የምናክምበት ሊሆን ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ፡፡.
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግንቦት ሃያ 28ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸው እንዳስታ ወቁት፡ ግንቦት ሀያ ኢትዮጵያ በታሪኳ ያለፈችባቸው አበይት የታሪክ ምእራፎች ሲታሰቡ ከሚታወሱት ቀናት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ይህ ዕለት የኢትዮጵያን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ መልካአምድር የቀየረ ታሪካዊ ዕለት ነው፡፡
ይህን በዓል ዛሬ ካለችውና ለወደፊትም እንገነባታለን ብለን ከምናስባት ኢትዮጵያ አንጻር ማክበር የተሻለ ብቻ ሳይሆን ለሁላችንም የሚበጅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣በሀገራችን ‹‹እኔም አለኝ ቁስል ያንተን የሚመስል ››የሚል ታላቅ አባባል እንዳለም ጠቅሰዋል፡፡ይህ አባባል ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የሚጠቅሙ ሁለት ሀሳቦችን አቅፎ መያዙን ተናግረው ፣የመጀመሪያው ሀሳብ ቁስል የመኖሩን እውነት እንደያዘ ሁለተኛው ደግሞ የእኛን ቁስል ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ቁስል ማየት እንዳለብን ማስረገጡ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በሀገራችን ላይ የደረሱ በደሎች በህዝቦች ጠባሳዎችን ትተው ማለፋቸውን አስታውሰው፣ እነዚህ ቁስሎች በሚገባ ባለመታወቃቸው ታውቀውም ባለመታከማቸው በየጊዜው እንዳዲስ እያገረሹ ሀገራችንን ጤና እየነሷት መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ይህ በዓልም እነዚህን ቁስሎች የምናክምበት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 20/2011