“ፍላጎት ብቻውን የትም አያደርስም”ተስፋዬ ማሞ

በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ሁለገብነት ይሉት ካለ እሱ የዛሬ የዝነኞች ገጽ እንግዳችን ተስፋዬ ማሞን ይገልጸዋል። የግጥም፣ የልብወለድ፣ የሬዲዮና የቲቪ ድራማ ብሎም የፊልም ደራሲ ነው። ግሩም አዘጋጅ፤ የማስታወቂያ ባለሙያ፣ የመድረክ መሪ፣ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ፣ ፕሮዲዩሰር ከፊቱ የሚቀድሙ መጠሪያዎቹ ናቸው።

ለየትኛው ሙያ ልብህ ያደላል ሲባል ‹‹ሁሉም የአንድ ዛፍ ቅርንጫፎች ናቸው›› ይላል። ድንገት የማስታወቂያ ሥራው ለየት ብሎ ወደ ንግዱ ከሄደ እንጂ ሌሎቹ በሙሉ ግንዳቸው ኪነ-ጥበብ ሆኖ እነሱ ቅርንጫፎች ናቸው። ተስፋዬ ሥነ-ጽሑፉ፣ ፊልም ዝግጅቱ፣ ግጥሙና፣ መድረክ መምራቱ ሁሉ የጥበብ ሥራዎች ስለሆኑ እራሴን እንደ አንድ የጥበብ ሰው አያለሁ ይላል።

አንዱን ከአንዱ ብዙም አላበላልጥም ይበል እንጂ ውስጠቱ ለድርሰት እንደሚያደላ ይናገራል። ወደ ኪነ-ጥበብ ዓለም ሲቀላቀልም የመጀመሪያ በር መክፈቻው ሥነ-ጽሑፍ መሆኑን ያስታውሰል። በሬዲዮ ለድምጽ፣ በቴሌቭዥን ለዓይን፣ እንዲሁም ለንባብ የሚሆኑ ነገሮችን መሥራት የጀመርኩት በሥነ-ጽሑፍ ነው ይላል።

የሁሉ ነገር ጅማሬው ወሎ ኮምቦልቻ ላይ ነው። የቤተሰቡ የበኩር ልጅ በመሆን ይህችን ምድር የተቀላቀለው መጋቢት 23 ቀን 1949 ዓ.ም ነው። እድሜው ከፍ ሲል በአቅራቢያቸው ከነበሩት መሪጌታ ከበደ ይመር ዘንድ የቄስ ትምህርቱን ተከታትሏል። የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ መንደሩ በኮምቦልቻ ተምሯል።

ያኔ በዘመኑ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ኮምቦልቻ ላይ አልነበረምና ስንቁን ቋጥሮ ከጎረቤት ደሴ ዘልቆ በሥመ ጥሩ የወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት በመከታተል ላይ ነበር። አባቱ የአውሯ ጎዳና ሠራተኛ ነበሩ። አባት ጡረታ በወጡ ጊዜ ቀድሞ የነበረ የድሎት ኑሮ ቀረ።

ይህ አጋጣሚ ተስፋዬን እራስን ከቤተሰብ ሸክምነት አላቆ ለቤተሰብ ስለመትረፍ ያሳስበው ያዘ። እናም ከወይዘሮ ስህን ትምህርት ቤት እንደወጣ አቅጣጫው ወደ ጎንደር የጤና ኮሌጅ ሆነ። ከልጅነቱ ሰዓሊ፣ ጋዜጠኛ ወይም የሥነ-ጽሑፍ ሰው እሆናለሁ እያለ ቢያድግም ሕይወት ማረፊያውን የጤና ሙያ ላይ አደረገችው።

ተስፋዬ “ሕክምና የሕይወት ማምለጫዬ ነበር” ይላል። ለፈተና ከተቀመጡ 400 ሰዎች ጋር ተቀላቅሎ ቢፈተንም ፈተናውን አልፎ ለትምህርቱ ተጠራ። ትምህርቱን ሲጨርስ በኪነጥበብ ብዙ እንደሚደርስ የተተነበየለት ሰው ሙያው በጤናው ዘርፍ ተፈረጀ። በወቅቱ አጠራር በኤርትራ ክፍለ ሀገር፣ አሰብና አስመራ ከተማ በሚገኙ የሕክምና ተቋማት ተቀጥሮ አገልግሏል።

ተስፋዬ ከልጅነቱ ይጽፋል፣ ሃሳቡን በግጥም ይገልጻል። የአራተኛ ክፍለ ተማሪ እያለ አንስቶ ትልልቅ ድርሰቶች ውስጥ ያሉ ገጸ ባህሪዎችን ተጫውቷል። ሃሳቡን ለመግለጽ ወደ ኋላ አይልም፤ ለዚህም ይመስላል ከድሮም ከሌሎች በተለየ ሃሳቦች ሲኖሩ ‹‹ተስፋዬ ይናገር›› የሚባለው። ወደኪነ-ጥበቡ ዓለም ተጠቃሎ ከመግባቱ በፊትም ባገኘው አጋጣሚ በብዕሩ ይጭራል።

አስመራ እያለ ‹‹ሕብረትና ኢትዮጵያ›› የሚሰኝ ጋዜጣ ላይ ይጽፍ ነበር። የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እና ዛሬ ታሪኩን ላጋራበት አዲስ ዘመን ጋዜጣም ጽሑፎችን ይልክ እንደነበር ያስታውሳል።

ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ስሙን በሕትመት ውጤቶች ላይ ማየቱ ብቻ በቂ እንዳልሆነ ተረድቶታል። በዚህም ሳቢያ ከቀናት በአንዱ ‹‹እንጀራዬ መተዳደሪያዬ›› ሳይል ሥራውን ለቀቀ። በዚህም ብዙ ዋጋ ከፍያለሁ ይላል። በወቅቱ ተስፋዬ በ24 ሰዓት ሁለት ዳቦ እየበላ 11 ወራት ቆይቷል። ኑሮ ቢከብደውም ከአሁን በኋላ ሕይወቴን የምመራው በሥነ-ጽሑፍ ነው ብሎ ለራሱ የገባውን ቃል ላለማጠፍ ጥሯል። ይህ ዓይነቱ ውሳኔው ዋጋ አስከፍሎታል። መራብን መጠማትን በተግባር አይቷል። “መፈለግ ብቻውን የትም አያደርስም” የሚለው ተስፋዬ ዋጋ ሲከፈል የሚፈለገው ነገር ጋር እንደሚያደርስ ይናገራል ።

በኢትዮጵያ ላይ ባለው እውነታ በሥነ-ጽሑፍ ብቻ መተዳደር ከባድ መሆኑን ያምናል። በተለይ ቤተሰብ ከመሠረተ በኋላ ጎጆውን በሁለት እግር ለማቆም የማስታወቂያ ሥራ ውስጥ መግባቱን ይናገራል። በዚህም በርካታ ተጠቃሽ ማስታወቂያዎችን ለመሥራት ችሏል። በማስታወቂያ ሥራው ተስፋዬን ማየት አይታሰብም። በአካል በታየ ቁጥር ነፃነት እየተገደበ እንደልብ መቆየት ያለበት ቦታ ሳይቆይ ውስንነት ይመጣል።

የእሱ ሃሳብ ከዚህ መሰሉ ውስንነት መራቅ ነው። ‹‹እኔ በቋንቋዬ በዳይሬክቲንግ ችሎታዬ ሃሳብ በማመንጨት አቅሜ የማስተዋውቀውን ምርት ወይም ሃሳብ እሸጣለሁ እንጂ እራሴን መሸጥ አልፈልግም›› የሚል መመሪያ አለው። በዚህም የትም ቦታ ሰዎች አዩኝ አላዩኝ ሳይል፣ ሳይደባበቅ እንደልቡ የትም ቦታ የመገኘት ነጻነት እንዳለው ይናገራል። በዚህም ሃሳቦችን በቀላሉ ለማግኘት ይችላል።

በሕይወቱ የሚፈልገውን ነገር ጠንቅቆ በመሆኑም እራሱን በራሱ ማስተማሩን ይናገራል። ለሥራው የሚያስፈልገው እውቀት ሲጎድለው መልሱን ከመጻሕፍት ይሽታል። ‹‹ቢሮዬም ይሁን ቤቴ ሀብቴ መጻሕፍት ነው›› ይላል። ከመጻሕፍት በተጨማሪ ሰዎችን መጠየቅና መወያየት ሌላው ክፍተቱን የሞላበት መንገድ ነው።

ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ሥነ-ጽሑፍ ባለመማሩ ምክንያት “የጎደለኝ ምንድነው?” በማለት ክፍተቱን ይፈልጋል። ክፍተቱን ለይቶ ሲያበቃ እሱን ለመሙላት የማይፈነቅለው ድንጋይ. የማይወጣው ተራራ አይኖርም። የቤተሰቡ የበኩር ልጅ ነውና የሚያገኘውን ገቢ ከእራሱ ቀንሶ ለቤተሰቡ ማቃመስ የሚጠበቅበት የውዴታ ግዴታ ነው። ሁሌም ቢሆን ደስ እያለው የሚፈጽመው ተግባር ነበር።

ዋጋ ያለው ሰው ለመሆን ዋጋ መክፈል ያስፈልጋል የሚለው ተስፋዬ አባቱን በሞት ካጣ በኋላ እንደበኩር ልጅነቱ የመጀመሪያ ኃላፊነት ይጠበቅበት ነበር። በወቅቱ እናቱ በጥንካሬ እየሰሩ ቤተሰቡን በመደገፋቸው እሱ በነጻነት ጥሪውን ሊከተል እንደቻለ ይናገራል።

‹‹እራስን የመፈለግ ጉዞ›› ሲል በጠራው የመጀመሪያ መጽሐፉ ዕጸ-በለስን ‹‹የመጀመሪያ ልጄን ሳሚልኝ›› ከሚል ማስታወሻ ጋር ለእናቱ ላከላቸው። ያኔ እናቱ ከሰው በፊት አስተምሬ የት ይደርሳል ያልኩት ልጅ ሲሉ የኔን ጉድ እዩልኝ ማለታቸውን ያስታውሳል። ሆኖም ውጤቱን ካዩ በኋላ ‹‹አንተማ ታውቅ ነበር ስለምታውቅ ነው ሁሉንም ታደርግ የነበረው ››እንዳሉት ዛሬም ድረስ ያስታውሳል። ተስፋዬ ለሚፈልገው ነገር ዋጋ መክፈልን አሁን ድረስ እንደመርህ የያዘው እውነት ነው።

ተስፋዬ ከጥበብ አድናቂዎች ጋር የተዋወቀው በ1982 ዓ.ም “ዕጸ-በለስ” የተሰኘ የልብወለድ መጽሐፉ መውጣቱን ተከትሎ ነበር። ብዙም ሳይቆይ “የጨረቃ ጥሪ” የልብ ወለድ መጽሐፉ ተከተለ። ከዛ በኋላ እሱን በመጻሕፍት ማግኘት ሩቅ ሆነ። ተስፋዬ ከነዚህ ጊዚያት በኋላ በቴሌቭዥን ድራማዎች እንዲሁም በፊልሞች ብቅ ማለቱን ይናገራል።

ይህ ሥራ የይዘት ለውጥ እንጂ ድርሰት ናቸውና ከድርሰቱ ዓለም እምብዛም አላራቀውም። ትዳር መያዙን ተከትሎ ግን ሕይወቱ ሙሉ በሙሉ መለወጡን ይናገራል። ተስፋዬ የመጀመሪያ አላማው ትዳሩን በሁለት እግሩ ማቆምና ልጆቹን በሚገባቸው ልክ ማሳደግ ሆነ። ይህን ተከትሎም አብዛኛውን ጊዜ ማስታወቂያዎችን መሥራት ጀመረ።

እንደ አጀማመሩ በየዓመቱ መጽሐፍ የመጻፍ ሂደት ነበረው። በወቅቱ ብዙ መጽሐፍ ሊኖረው ሲገባ እንደሃሳቡ አለመግፋቱን ያምናል። ይሁን እንጂ ለቁጥር የሚታክቱ ዶክመንተሪዎችን፣ አዘጋጅቷል። ዕጣ ፈንታን የመሰሉ ፊልሞች፣ የቴሌቭዥን ድራማዎች፣ እንዲሁም አሁን ድረስ በሸገር 102.1 ኤፍ ኤም ላይ በሚተላለፈው የጥበብ ውሎ የተሰኘ ሳምንታዊ መሰናዶ ላይ እንደቀጠለ ነው።

በየሳምንቱ “የድባቤ ውሎ” በሚል እሱ ጽፎት በሚተውንበት ተከታታይ የሬዲዮ ድራማ ላይ እየጻፈ መሆኑንም ይናገራል። ተስፋዬ ‹‹በመጽሐፍ መልክ ካልሆነ በስተቀር ሃሳቤን በተለያየ መልኩ በማውጣት አላረፍኩም›› ይላል።

ተስፋዬ በሕይወቱ በቀን ሁለት ደረቅ ዳቦ ከመብላት ተነስቶ እራሱ በሠራው ፎቅ ቤት ወደመኖር ተሸጋግሯል። ባስ አለመለጠኝ ብሎ ከመሯሯጥ የራሱን መኪና ያሽከረክራል። የቅርብ ወዳጆቹ የተስፋዬ ጸባይ በማግኘትና በማጣት የማይቀየር የትላንቱ ያው ተስፋዬ መሆኑን ይመሰክራሉ።

እንዴት ሳትቀየር በድሮ ማንነትህ ቆየህ ሲባል “የእያንዳንዳችን ሙያ እኮ ሰውን ማገልገል ነው። ለሰው ከሰው ውጭ ሌላ የተሰጠው ምን አለ?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል።

ተስፋዬ በእሱ አምሳል የተፈጠረ ሰው ሊያገኝ የሚገባውን አክብሮት መስጠት እንዳለበት ያምናል። ‹‹በወዳጅነት አንድ ጊዜ የተጠጋነውን ሰው ጉድለቱን እየሞላንለት መሄድ ይገናባል›› የሚል አቋም አለው። የእሱ ጥንካሬ ተብሎ የሚነሳው ጓደኞቹን ወዳጆቹን መፈለጉ ለእሱ ምልአት ተብሎ የተሰጠው ሊሆን ይችላል ብሎ ይገምታል። “ለሌላ ሰው ደግሞ ሌላ ስጦታ ይኖረው ይሆናል፤ እንዲህ በመሞላላት ሙሉ መሆን ይቻላል። ሰውን ካልፈለግሽ ምን ትፈልጊያለሽ?” ጥያቄው ነው።

“የመጣው ሰው ለምን ይቀነሳል መጨመር እንጂ። ” በሚለው ሃሳቡ የጸና ነው። ወዳጆቹን በየጊዜው ባይሆንም በስልክ እየደወለ ‹‹ጠፍታችኋል፣ በሰላም ነው የማለት ልማድ አለው። በዚህም አንዳንድ ወዳጆቹ ጋር ሲደውል ባጋጣሚ ታመው ሊያገኛቸው ይችላልና በድንገት የጠየቀበትን አጋጣሚዎች ያስታውሳል። እሱ በአካል ሄዶ ‹‹አይዞህ ማለት ብቻውን ውስጥን እንደሚያበረታ ያምናል። ሁሌም “ሰው የሚታከመው በሰው ነው” ሲል ያስባል።

“እኔ በወዳጅ እድለኛ ነን ያልወለድኳቸው የልቤ ልጆች አሉ” የሚለው ተስፋዬ፤ እናቴ ያልሰጠችኝ ወንድሞችና እህቶች አሉኝ ሲል ይመካል። ተስፋዬን ‹‹ጋሼ እያሉ የሚፈልጉት ብዙ ወዳጆች አሉት። ይህ በሰው መውደድ ከአባቱ ያገኘው ወርስ ነው። አባቱ ኮፍያ ያደርጉ እንደነበር የሚያስታውሰው ተስፋዬ፤ ይሁን እንጂ ኮፍያውን እጃቸው ላይ እንጂ ራሳቸው ላይ አይቶት እንደማያውቅ ይናገራል። የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በየሄዱበት ለሰላምታ ኮፍያቸውን ማውረዳቸው ነበር። ምናልባት እንደሳቸው ባይሆንም በመጠኑ ባህርያቸውን ስለመውረሱ ይጠረጥራል።

ተስፋዬ ስኬታማ ከሆነው የኪነ-ጥበብ ሕይወቱ ባሻገር ስኬታማ የሆነ የትዳር ሕይወት አለው። ይህ ሕይወቱ ለበርካቶች አርአያ ሆኗልና በተለያየ ጊዜ ከባለቤቱ ጋር በመቅረብ ስኬታማ የትዳር ተሞክሮአቸውን ለሚዲያ አካፍለዋል። ተስፋዬ ባለቤቱ የውብዳር አንበሴን ጽዮን ሆቴል ሌላ ሴት ቀጥሮ ሄዶ ያገኛት ግራ ጎኑ ነች። ‹‹ ፈጣሪ ለኔ ያዘጋጃት ስጦታ ናት ይላል። በወቅቱ እሱ የቀጠራት ሴት ቀርታ የአሁን የትዳር አጋሩ ከውጭ ሀገር መጥታ ከጓደኞቿ ጋር ልትዝናና በወጣችበት አጋጣሚ ነበር የተገናኙት። በዚህ አጋጣሚም ወደ ትዳር ማምራታቸውን ያስታውሳል።

ተስፋዬና ባለቤቱ ሁለት ወንድና አንዲት ሴት ልጅ አፍርተዋል። “ሁለት የተለያዩ ሰዎች መሀል አለመግባባት አይኖርም ማለት ውሸት ነው፤” የሚለው ተስፋዬ አለመግባባት ሲኖር እንዴት አለመግባባቱን እንፍታው ማለት ተገቢ እንደሆነ ይናገራል።

‹‹ትዳር ስመሰርት 40 ዓመት ሞልቶኛል›› የሚለው ተስፋዬ ሌላውን መንገድ ሁሉ ጨርሼ የቀረኝ የሕይወት መንገድ ትዳር ስለነበርና እሱንም ጥሩ አድርጌ ልሄደው እፈልግ ስለነበር በቻልኩት አቅም ሁሉ ለትዳሬ የሚገባውን አክብሮት እሰጣለሁ›› ይላል። ‹‹ባለቤቴን 16 ዓመት እበልጣታለሁ ስለዚህ ከባለቤቴ የወሰድኩባት እድሜ አለ፤ ያን እድሜዋን መልሼ ልሰጣት እፈልጋለሁ›› ለዚህም በቤትና በቢሮ መሃል ስብሰባ ካልሆነና የሥራ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ብዙ ቦታ አይገኝም።

ሁሌም የቤት ሰላም ለቤት በተሰጠው ዋጋ ልክ እንደሚገኝ ያምናል። “እኔ ሚስቴንና ልጆቼን ካላከበርኩ ማንን ላከብር ነው?” የሚለው ተስፋዬ እያንዳንዳችን ውስጥ ያለውን ጉድለት በመሞላለት ትዳርን ሰላማዊ ማድረግ ይገባል ባይ ነው።

ለቃለ መጠይቅ የተገኘንበት ቢሮው እስኪደንቅን ድረስ በበርካታ የምስጋናና የእውቅና ሽልማቶች ተሞልቷል። ከፊሉ በነጻ ለሰጠው የበጎነት ግልጋሎት ሲሆን የተቀሩት በሙያው ላበረከተው አገልግሎት የተሰጡ እውቅናዎች ናቸው።

እኛ በብዛታቸው ብንገረምም እሱ ግን እኛ ያየነው ከሽልማቶቼ አንድ አምስተኛው እንኳን አይሆንም ብሎ ይበልጥ አስገርሞናል። ተስፋዬ ከሽልማቶቹ ሁሉ ከኢትዮጵያ ልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል የተበረከተለትን ያህል የሚያስደስተው የለም።

ማዕከሉ ከመመስረቱ አስቀድሞም ከዶክተር በላይ አበጋዝ ጋር በዘውዲቱ ሆስፒታል በኮንቴነር ደረጃ ካለበት ጊዜ አንስቶ አሁን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያለው ሆስፒታል እስኪገነባ አብሮ መኖሩን ያስታውሳል። በዚህም ፈንድ ሬይዚንግ ስትራቴጂ (ገቢ የማግኛ ዘዴ) በማዘጋጀት፣ መድረኮችን በመምራት አብሮ መሆኑን ያኮራዋል።

“ዛሬ በእዛ ቤት ሕፃናት ይድናሉ፤ ሕይወታቸው ይተርፋል የሚለውን በማሰብ በጥቁር አንበሳ ጎን ሲያልፍና የተሰራውን ማዕከል ሲያይ ልቡ ይረካል። ‹‹እኔ ባደረኩት ትንሽ አስተዋጽኦ የአንድ ሕፃን ሕይወት ይተርፋል” በሚል ደስ ይለዋል። ተስፋዬ ከተሰጠው ከሁሉም ክብሮች ሁሉ ከማዕከሉ የተበረከተለት እውቅና እንደሚበልጥበት ይናገራል።

ተስፋዬ ቢሮ እንደገባ ለራሱ የመረጋጊያ ጊዜ ይወስዳል። ክላሲካል ሙዚቃ ከፍቶ ይመሰጣል። ሰው ተንደርድሮ ሁሉንም ነገር ወዲያው ማድረግ አለበት ብሎ አያምንም። ለብዙ ነገሮች አስቀድሞ መንፈስን ማረጋጋትና ማሰብ ጥሩ ስለመሆኑ ይመክራል።

እሱ ሁሌም ለስላሳ ሙዚቃ ውስጥ ቆይቶና እራሱንም ስሜቱንም ሰብስቦ ወደ ሥራ መግባት ምርጫው ነው። ሙዚቃ ያነቃዋል፤ ብቻውን ሲሆንም ባዶነት እንዳይሰማው ያግዘዋል። ‹‹ሙዚቃ ካለ አካባቢዬ በሰዎች የተሞላ ነው›› ይላል። መኪና ውስጥና፣ ቢሮ ሲሆን ከሙዚቃ ጋር መዛመድ ምርጫው ነው።

ሀገር ሰላም ቢሆን ‹‹ፍቅር መጨረሻ›› የተሰኘውንና በዋናነት መቼቱን ጣና ሐይቅ ላይ አድርጎ በቪዲዮ የወጣውን ፊልሙን ዳግም የመሥራት እቅድ አለው። መጋቢት ላይ 65ኛ ዓመቱን የሚደፍነው ተስፋዬ “ሕይወቴን መለስ ብዬ ስጽፈው እውነት እኔ በዚህ ውስጥ አልፌያለሁ ብዬ የሚገርሙኝን ሁኔታዎች አልፌያለሁ” ይላል።

በእስር፣ በሞትና በአደጋ ፍራቻ በረሀብ ውስጥ ተራምጃለሁ የሚለው ተስፋዬ እነዚህ የኢትዮጵያን መልክ የሚያሳዩ የሚላቸው ዋና ዋና የሕይወት መንገዶቹ በመጽሐፍ መልክ ማዘጋጀቱን ይናገራል። ፈጣሪ ቢፈቅድለት መጋቢት ላይ የማውጣት እቅድን ይዟል።

በተመሳሳይ የአጫጭር ልብወለድና የወግ መድብል አዘጋጅቶ ያጠናቀቀ ሲሆን ከልጅነት እስከ እውቀት ከተጻፉ ከ260 በላይ ግጥሞች ውስጥ የተወሰኑትን መርጦ የግጥም መጽሐፍ የማሳተም ሃሳብም ሰንቋል። ወደፊት የበዛ ትኩረቱን መጻሕፍት ላይ ማድረግን ይሻል። እንደእሱ ዕቅድ ቢያንስ በዓመት አንድ መጽሐፍ የማሳተም ውጥን አለው። ያቀደው ሁሉ ይሳካለት ዘንድ ተመኝተናል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You