ሀገራችን ሰሞኑንም አንድ የማይዳሰስ ቅርስ በዓለም ቅርስነት አስመዝግባለች። የዚህ ቅርስ በዩኔስኮ መመዝገብ ሀገሪቱ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸውን ቅርሶች ቁጥር 16 አድርሶታል። በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ቅርስ በሀረሪ ብሔረሰብ ዘንድ በየዓመቱ ለሶስት ቀናት በደማቅ ሥነ ሥርዓት የሚከበረው የሸዋል ኢድ በዓል ነው።
በሐረሪ ብሔረሰብ ዘንድ ከሚከበሩ ቱባ ባህሎች ውስጥ የሚጠቀሰው ይህ የሸዋል ኢድ በዓል ዩኔስኮ በቅርቡ በቦትስዋና ባካሄደው 18ተኛው ዓለም አቀፍ ጉባኤው ላይ ነው በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ያደረገው።
የቅርሱን መመዝገብ ተከትሎ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክቶች ተላለፈዋል፤ የቅርሱ በዩኔስኮ መመዝገብ ፋይዳው ብዙ መሆኑም ተጠቁሟል።
የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የሸዋል ኢድ በዓል በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። ብልጽግና በትኩረት እና በልህቀት እፈፅማቸዋለሁ ብሎ ከያዛቸው አምስት የልማት መስኮች የቱሪዝም ዘርፍ አንዱ መሆኑን የገለጹት የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት፣ “በኢትዮጵያ የሚገኙ ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ መስህቦች በይበልጥ እንዲያድጉና ለሀገራችን የብልጽግና ጉዞ ተጨማሪ አቅም መፍጠር እንዲችሉ ፓርቲው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል›› ብለዋል።
የሸዋል ኢድ በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ መመዝገቡ በቱሪዝም ዘርፍ የምናደርገው እንቅስቃሴ እንዲጠናከርና አድማሱን እንዲያሰፋ ያደርገዋል ሲሉም ገልጸዋል። ይህ ታሪካዊ ውሳኔ ሀረር ከተማን በዩኔስኮ ሁለት ቅርሶችን ያስመዘገበች ብቸኛዋ ከተማ፣ ኢትዮጵያን ደግሞ በርካታ ቅርሶችን በዓለም ቅርስነት በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ስፍራን እንድትይዝ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሪት ሌንሳ መኮንን በዩኔስኮ መመዝገቡ በሀገሪቱ የቱሪስት ፍሰት እንዲጨምር እንደሚያደርግ፣ የሀገር ገጽታን በመገንባት በኩልም የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። የክልሉን የቱሪስት ማዕከልነት በማጎልበት የሕዝቡን ተጠቃሚነት እንደሚያሳድግም ገልጸዋል።
በዓሉ ለቀጣዩ ትውልድ በረከት የሚሰጥበት መድረክ መሆኑንም ሚኒስትር ዴኤታዋ ጠቅሰው፣ በተለይ ወጣቶች ባህላዊ እሴቶችን ወጎችን ለመማር እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው የሸዋል ኢድ በዓል አከባበር በማይዳሰስ የዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈው፣ የክልሉ መንግሥትም የዓለም ቅርስ የሆነውን ሸዋል ኢድ በዓል ለመጠበቅ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል። ሸዋል ኢድ በዓል የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የሀረር ከተማ ነዋሪዎችም “የሸዋል-ኢድ በዓል በዓለም ቅርስነት መመዝገቡ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል። ‹‹ለመላው ኢትዮጵያውያን ትልቅ ኩራት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ከሀረሪ ክልል ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው፤ የሐረሪ ሕዝብ ክልል ሕገ መንግሥትም የሐረሪ ብሔረሰብ ታሪኩንና ባህሉን የማልማትና የማበልፀግ እንዲሁም በቋንቋው የመጠቀምና የማሳደግ ሕጋዊ መብቱን በመጠቀም በአዋጅ ቁጥር 61/1999 የሹዋሊድ በዓል የሚከበርበት ዕለት በክልሉ የበዓል ቀን ሆኖ እንዲከበር በአዋጅ ደንግጓል። ይህም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው በየዓመቱ በዓሉ በድምቀት የሚከበርበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል። ክብረ በዓሉም በብሔረሰቡ አባላትና በሌሎችም አካባቢ ማኅበረሰቦች ዘንድም እንዲታወቅ ምክንያት ሆኗል።
በዚህም ቅርሱ የተለያዩ የዓለም ሕዝቦች የመነጋገሪያ እና የመወያያ ርዕስ እንዲሆን ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ከሹዋሊድ በዓል እሴቶች ሌሎች ሕዝቦችም ልምድ መቅሰም እንዲችሉ ቅርሱን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማስመዝገብ አስፈላጊ ሆኖ ሲሰራ መቆየቱን የክልሉ ባህል፣ ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ይገልጻሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ቅርሱ በዩኔስኮ የማይዳሰሱ ቅርሶች እንዲመዘገብ በቅድሚያ በሐረሪ ክልል በዓሉን ልዩ የሚያደርጉት ነገሮች እንዲሁም በዓሉ በምን መልኩ እንደሚከበር ጥናት ተደርጎ ተለይቷል፤ ከዚያም ጉዳዩ በፌዴራል ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን እውቅና ተሰጥቶታል። ቅርሱን ለማስመዝገብ ዩኔስኮ የሚጠይቀው መስፈርት ተሞልቶ በባለሥልጣኑ በኩል መቅረቡንና ለመመዝገብ መብቃቱን ይገልጻሉ። ቅርሱን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ጥናት ማድረግ ከተጀመረ አንስቶ በማይዳሰስ ቅርስነት እስከተመዘገበበት ድረስም ከአምስት ዓመት በላይ መውሰዱን ገልጸዋል።
የቢሮ ኃላፊው ስለሸዋል ኢድ በዓል ምንነትና አከባበር ሲያብራሩም እንዳሉት፤ በእስልምና ሃይማኖት ካሉ አጽዋማት መካከል ዋናው የጾም ወቅት የረመዳን ወር ጾም ከተጠናቀቀ በኋላ የሹዋል ፆም ይጀመራል። በሹዋል ወር የመጀመሪያው ቀን የዒድ አልፈጥር በዓል ይከበራል።
የዒድ አልፈጥር በዓል ከተከበረ በኋላ ባሉት ተከታታይ ስድስት ቀናት ደግሞ የሹዋል ጾም ይጾማል። ይህ ጾም በሹዋል ወር የሚጾም በመሆኑ ስያሜውን ከወሩ አግኝቷል። የሹዋል ጾምን ነብዩ መሀመድ (ሰ.ዐ.ወ) በሕይወት ዘመናቸው ሲጾሙት የነበረ ጾም ሲሆን፣ እሳቸው በሹዋል ወር ስድስት ቀናትን የጾመ ዓመቱን በሙሉ እንደጾመ ይቆጠራል የሚል አስተምህሮት ያላቸው በመሆኑ የሹዋል ጾም በዚሁ መነሻነት በሐረሪዎች ዘንድ ከጥንት ጀምሮ መጾም እንደተጀመረ ይነገራል።
ይህ የስድስት ቀናት ጾም ካበቃ በኋላ የሸዋል ኢድ በዓል ያለምንም የእድሜ፣ የጾታና የማህበራዊ ደረጃ ገደብ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ በደመቀ ሁኔታና ባህላዊ እሴቶችን በሚያንጸባርቅ መልኩ ከጥንት እየተከበረ እንደሚገኝም ነው የቢሮ ኃላፊው የገለጹት።
የሹዋሊድ በዓል በሐረር የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላት ብቻ ሳይሆኑ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሐረሪዎች ጭምር ከያሉበት በመሰባሰብ ያከብሩታል። ክብረ በዓሉ በድሬዳዋ፣ በጉርሱም በተለይ ካለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባም በብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ እየተከበረ ነው። የሹዋል ጾምን የእስልምና እምነት ተከታዮችም የሚጾሙት ቢሆንም፣ የሹዋሊድ በዓልን ግን እንደ ሐረሪዎች አያከብሩትም።
በዓሉን ታዳጊዎች እንጨት ካሰባሰቡ በኋላ ወደ አዋቹ እንዲገባ ይደረጋል። ከዚያም ለበዓሉ የተዘጋጁትን ከበሮዎች በእሳት የማሞቅ ሥራ ይከናወናል። ፡ አስሱም በሪ ወይም ፈላና በር በሚገኘው አዋች ላይ የሹዋሊድ ክብረ በዓል ዋዜማው ላይ በአዋቹ አካባቢ የበዓል ማክበሪያ መድረክ በማዘጋጀት ሥነ-ሥርዓቱ ይጀመራል።
የበዓሉ እድምተኞች ወደ አዋቹ ገብተው በተዘጋጀላቸው ቦታ እንዲቀመጡ ይደረጋል። ከበሮውንም የሚመቱት የዓመታት ዕውቀት ልምድና ክህሎት ያካበቱ አዛውንቶች እና ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣውን ዕውቀት የቀሰሙ ወጣቶች ናቸው። ከበሮ መቺዎቹ መጀመሪያ ድምጹን በመቃኘት የተስተካከለ መሆኑን ያረጋግጡና ለበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ዝግጁ ያደርጋሉ።
በሹዋሊድ በዓል በየቤቱ ለበዓሉ ተብለው የተለያዩ ባህላዊ ምግቦች ይዘጋጃሉ። ከእነዚህም መካከል ስሪዋ ኢሺሽ፣ ሩዝ፣ አቅሌል፣ ጡፍ ጡፍ (ከስንዴ የሚጋገር ቂጣ)፣ እንደሙሸበክ፣ ሀላዋ፣ ሳምቡሳ፣ ሙጠበቅ (በሰሊጥ የሚሰራ ብስኩት)፣ የመሳሰሉ ብስኩቶች ለአዋቂዎች፣ ወጣቶችና ሕፃናት ይቀርባሉ። ሑልበት መረኽ (የአብሽ ወጥ)፣ የብሔረሰቡ መለያ ከሆኑ ምግቦች አንዱ ቢሆንም የበዓሉ ዕለት ግን ከላይ የተጠቀሱት የምግብ ዓይነቶች ተመራጭ እንደሆኑ ይገለጻል።
በእነዚህ የበዓል ዋዜማዎች ወጣቶች ‹‹ሀንዶፍሊ›› የተባለ ጨዋታ ይጫወታሉ። ሀንዶፍሊ በሹዋሊድ የጾም ወቅት በአብዛኛው በአው አባድር የሚዘወተር እና አልፎ አልፎ በየሰፈሩ የሚከወን የእሳት ላይ ዝላይ ጨዋታ ነው። በዚህ ጨዋታ ታዳጊዎች ለዝግጅቱ የሚሆነውን እንጨት እና ቅጠላ ቅጠል ያሰባስባሉ፤ ይህም በዘፈን ታጅበው ይፈጸማል።
በበዓሉ ላይ በዛኪሮችና በአዛውንቶች መሪነት የተለያዩ ሃይማኖታዊ ውዳሴዎች ወይም ዝክሪዎች ይቀርባሉ። ይህንንም የአላህ ወይም ፈጣሪ አንድ መሆንና ታላቅነትን በመጥቀስ አላህንና ነብዩ መሀመድን በማወደስ ይጀምራሉ።
በበዓል አከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በየደረጃው ያሉ የሐረሪ ብሔረሰብ አባላት የየራሳቸው ድርሻ እና ኃላፊነት አላቸው። በዚህም መሠረት ሙሪዶች ሥርዓቱን በማስተባበርና በመምራት፣ ለተለያዩ የዝክሪ አውጪዎች ዕድል በመስጠት በቅደም ተከተል እንዲያቀርቡ ያደርጋሉ። አዛውንቶች ዝክሪ በመቀበል፣ በማጨብጨብና በመጨፈር ይሳተፋሉ። እናቶችና ወጣት ሴቶች በበኩላቸው የበዓል ሥነ ሥርዓቱን ለሚመሩና ለሚያስተባብሩት እንደ ሐሸር ቃሕዋ፣ ቡን ቃሕዋ የመሳሰሉ ባህላዊ ትኩስ መጠጦችን በማዘጋጀትና በማቅረብ ተሳትፎ ያደርጋሉ።
የምሽቱ የበዓል ሥነ-ሥርዓት የሚጀመረው በአባቶች ምር ቃት ነው። የበዓል ሥነ-ሥርዓቱ አንድ ጊዜ በምርቃት ከተጀመረ በኋላ በቅደም ተከተል በሚቀርቡ ዝክሪዎች ወይም የምስጋና ዜማዎች እየታጀበ ይደምቃል።
በዓሉ ‹‹ዋሐቺ ዋ ደርማ ዒድ››/ የወጣቶችና የልጃገረዶች ዒድ በመባልም ይታወቃል። በበዓሉ ላይ ያገቡና ያላገቡ ሴቶች የሚለዩት በአለባበሳቸውና በጸጉር አሰራራቸው ነው። በብሔረሰቡ አንዲት ልጃገረድ እጮኛ ያላት ከሆነች ከእጮኛዋ ቤተሰቦች በስጦታ መልክ የመጣላትን በእጅ የተጠለፈ የታጨችበት ልብስ ‹‹ኩሻ ቡሩቅ›› የተባለ ባህላዊ ቀሚስ ትለብሳለች። በዚህ አለባበሷ ስለምትለይም ማንም ወንድ ለወደፊት የትዳር ጓደኛ አይመኛትም። ጸጉሯን ደግሞ ‹‹ገማሪ›› በመባል የሚታወቀውን ባህላዊ የጸጉር ስሪት በመሠራት ትለያለች። በዚህ መልኩ አለባበሳቸውን ካስተካከሉና ካሳመሩ በአጠቃላይ ባላቸው አቅም አጊጠው፣ ተውበውና ተሸቀርቅረው ከጨረሱ በኋላ በቡድን በመሆን ወደ ክብረ በዓሉ ያመራሉ።
ወጣት ወንዶችም በተመሳሳይ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የወደፊት የትዳር አጋራቸውን ለመምረጥ በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ ይሄዳሉ። በቦታው እንደደረሱም አመቺ ቦታ በመምረጥ ጨዋታውን ይከታተላሉ። በሹዋሊድ በዓል የእጮኛ አመራረጥ ሂደቱ በሁለት መልኩ ይከናወናል። የመጀመሪያው በዓሉ በሚከበርበት አው ሹሉም አህመድ እና አው ዋቅበራ አዋቾች ላይ ጨዋታውን ለመመልከት ከሚመጡ ልጃገረዶች መካከል ዓይናቸው ያረፈባትን በመምረጥ የሚያጩበት ሥርዓት ሲሆን፣ ሁለተኛው በዓሉ የሚከበርባቸውን ሁለቱን አዋቾች በቀጥታ የሚያገናኝ ‹‹አሚር ኡጋ›› ወይም የሐረር ኢሚሬት መሪ (አሚር) መንገድ ላይ የሚከወን ነው።
በሐረሪዎች በሹዋሊድ የበዓል ቀን ተያይቶ፣ ተመራርጦና ተዋውቆ ለጋብቻ መብቃት ዛሬም ህያው የሆነ የብሔረሰቡ ትልቅ እሴት ነው። በዚህ ዕለት አንድ ወጣት በበዓሉ ላይ መሳተፍ ካልቻለ ወይም በበዓሉ ላይ ተገኝቶ ‹ዓይን አዋጅ ሆኖበት ሳይሳካለትና ሳይመርጥ ከቀረ ‹‹ሹዋሊድ አመለጤኽ›› ይሉታል። ይህም ማለት የማታ ማታ የበዓሉ ድምቀት አሞኝቶህ ሳትመርጥ ቀረህ እንደማለት ነው። በሌላ በኩል በበዓሉ ላይ ተገኝቶ መምረጥ የቻለ እና የተሳካለት ወጣት ደግሞ ‹‹ሹዋል ዒድ ማረኼኝ›› እንደሚባል ይነገራል።
የሹዋሊድ በዓል ከብሔረሰቡ ተወላጆች ባለፈ ሌሎች ሕዝቦች በነጻነት የሚያሳተፍ በመሆኑ ለባህል ልውውጥና እድገት፣ ለሕዝቦች ትስስርና ግንኙነት መጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የቢሮ ኃላፊው ይጠቅሳሉ። እሳቸው እንዳብራሩት፤ በበዓሉ ላይ የብሔረሰቡን ባህልና ወግ የጠበቁ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች የብሔረሰቡ አባላትም የባህል ልብሱን እና ጌጣጌጦቹን ለብሰው ወደ በዓሉ ሲመጡ አንዱ የሌላኛውን ባህል እንዲያውቅ ያደርጋል ።
የአደባባይ በዓል እንደመሆኑ በሥራ፣ በትዳር ሕይወት፣ በሌላም ምክንያት ለተራራቁ ቤተሰቦች፣ ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛማቾች የመገናኛና የመሰባሰቢያ መድረክ ነው። የተራራቁ የሚቀራረቡበት፣ የተቸገሩ ተመልካች የሚያገኙበትና የሚረዱበት በመሆኑ ማህበራዊ ፋዳው የጎላ ነው ሲሉም ይገልጻሉ።
አቶ ተወለዳ እንዳብራሩት፤ ይህ በዓል ከዓመት ዓመት በከፍተኛ የተሳታፊዎች ቁጥር የሚከበር ሲሆን፣ በበዓሉ ላይ የብሔረሰቡ ተወላጆች በብሔረሰቡ ባህላዊ አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቀውና አሸብርቀው የሚታደሙበት ነው፤ ይህም በአልባሳትና በጌጣጌጦች የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎችን ለአዳዲስ የፈጠራና የዲዛይን ሥራ በማነሳሳት አዳዲስ ሥራዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ የሚያደርጋቸውን የገበያ እድል ፈጥሯል። በበዓሉ ላይ የብሔረሰቡ ተወላጆች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሌሎችም ተወላጅ ያልሆኑትም ጭምር የብሔረሰቡን አልባሳት እና ጌጣጌጦች ለብሰው ከመታደም ባሻገር በማስታወሻነት የሚገዙበት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል። ለዚህም ሲባል በስፋት የማዘጋጀቱና የማምረቱ ሁኔታ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መጥቷል።
በዓሉ በዩኔስኮ ከመመዝገቡ አስቀድሞ ክልሉ በየዓመቱ ለበዓሉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በተለይም ወጣቶች ባህላቸውን እና ማንነታቸውን እንዲያውቁ እየተሰራ መቆየቱን የቢሮ ኃላፊው ጠቅሰው፣ በተጨማሪም ሌሎች አጎራባች ክልሎች ከኦሮሚያ፣ አርጎባና ስልጤ ወደበዓሉ በመጋበዝ እንዲሳተፉ መደረጉንም ገልጸዋል። በሸዋል ኢድ በዓል የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ፣ የገጽታ ግንባታ እንዲጎለብት ማድረጉንም ተናግረዋል።
በሀገራችን በዩኔስኮ የተመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች አራት የነበሩ ሲሆን፣ የሸዋልኢድ በዓልን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና የባህል ተቋም በማይዳሰሱ ቅርሶች የተመዘገበ አምስተኛው ቅርስ ያደርገዋል። ይህ በዓል በዩኔስኮ መመዝገቡ ብዙሃነትንን ከማስተናገድ በተጨማሪ የሀገር ገጽታ በበጎ መልኩ እንዲገነባ ያደርጋል። በቱሪዝም ዘርፍም እንዲሁ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተመዘገቡ ቅርሶች እየተበራከቱ መምጣት ለቱሪዝም ዘርፉ ትልቅ አቅምን ይፈጥራል። የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል።
ሰሚራ በርሀ
አዲስ ዘመን ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም