ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባህላቸውና ማንነታቸው ተከብሮ በአንድነት የሚኖሩባት ሕብረ ብሔራዊት ሀገር ናት፡፡
ይህንኑ መነሻ በማድረግም ኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የጸደቀበት ህዳር 29 የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ተብሎ በአገርአቀፍ ደረጃ በድምቀት እንዲከበር የተወሰነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚያዚያ 21 ቀን 1998 ዓ.ም ባካሄደውሶስተኛው የፓርላማ ዘመን አንደኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ነበር።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በየዓመቱ ህዳር 29 ቀን እንዲከበርና በዋነኝነት የወሰነው የአገራችን ህዝቦችም ተመካክረውና ፈቅደው የጸደቁት ህገ-መንግስት ያስገኘላቸውን ጥቅሞች እንዲያስቧቸው ለማድረግና በቀጣይ ማከናወን የሚገባቸውን ተግባሮች ላይም መምከር እንዲችሉ ለማድረግ ታቅዶ ነው፡፡
በአገራችን የመጀመሪያው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በ1999 ዓ.ም በፌዴሬሽን ምክር ቤት
አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሲከበር መሪ ቃሉም “ሕገ-መንግስታዊ ቃል ኪዳን የአብሮነታችን መገለጫ ነው”የሚል ነበር። ሁለተኛው በዓል ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መዓከል በሆነችው ሀዋሳ ላይ በድምቀት ሲከበር መሪ ቃሉም “ልዩነታችን ውበታችን ውበታችን አንድነታችንና ጥንካሬያችን ነው” በሚል ተከብሯል።
እንዲህ እንዲህ እያለ ላለፉት 17 ዓመታት በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በልዩ ልዩ መሪ መልዕክቶች ሲከበር ቆይቷልⵆ በዚህ በዓል አከባበር ደግሞ በርካታ የአገራችን ብሔር ብሔረሰቦች ማንነታቸውን ባህላቸውን አለባበሳቸውን ብሎም አመጋገባቸውን ለቀሪው ወገናቸው የማሳየት እድልን አግኝተውበታልⵆ በሌላ በኩልም እነዚህ ዓመታት በዓሉ እንዲከበር ከተወሠነባቸው ዓላማዎች አንፃር ብዙ ጥቅሞችን አስገኝተዋል ማለትም ይቻላል።
ይህ በዓል እንደ አገር አንድነታችን የሚጠናከርበት በመካከላችን ያሉ ልዩነቶችን ጠብቀን ወደ አንድ የምንመጣበት ይሆን ዘንድም ብዙ አስተዋጽኦ አበርክቷልⵆ ነገር ግን አሁንም ብዙ አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች እንደሚቀሩም አመላካች ነገሮች በመኖራቸው የዘንድሮው በዓል በዚህ በኩል የሚታየውን ክፍተት ይሞላል የሚልም ተስፋ ተጥሎበታልⵆ
ብዝሀነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ መልዕክት የሚከበረው 18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት እንደሚከበር ይጠበቃልⵆ
በዓሉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ልምዳቸውን፣ ተሞክሯቸውን እና ባህላቸውን የሚለዋወጡበት፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለፈጣን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የሚነሳሱበት እንደሚሆንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ገልጿል ፡፡
ባለፉት 17 ዓመታት በዓሉ ሲከበር ሕዝቦች ለረዥም ዘመናት ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያፀኑ፣ ከልዩነት ይልቅ አንድነት እንዲያጎለብቱ እና በሕገ መንግሥቱ እና በፌዴራል ሥርዓቱ ዙሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠሩ የሚያስችሉ ሰፋፊ ሥራዎች እንደተሠሩ እና በነዚህም ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ጨምሮ ገልጿል።
18ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በፌዴሬሽን ምክር ቤት አሥተባባሪነት በሶማሌ ክልላዊ መንግሥት አስተናጋጅነት «ብዝኃነት እና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት» በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይቶች፣ በጎዳና ላይ ትዕይንቶችና ልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል ፡፡
የዘንድሮው በዓል ሲከበር ብዝኃነትን በማስተናገድ እና ሕብረ ብሔራዊ ኢትዮጵያን በማጠናከር ሀገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ለማድረግ አንድነትን የሚያስጠብቁ አንኳር ተግባራት ቅድሚያ የሚሠጣቸው ሆኖ በተለይም ለሀገር ሕልውና መከበር ሲባል አማራጭ የሰላም መንገዶችን ሁሉ መጠቀም ለምርጫ የማይቀርብ ተደርጎ እንደሚሠራም ነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዓሉን አስመልክቶ ያስተላለፈው መልዕክት የሚያሳየው፡፡
በዓሉ ከኅዳር 1ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች፣ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች፣ በፌደራልና የክልል ተቋማት በተለያዩ ኹነቶች የሚከበር ሲሆን ዋናው በዓል በጅግጅጋ ከተማ ከኅዳር 25ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ያሉት አምስቱ ቀናት የወንድማማችነት ቀን፣ የብዝኀነት ቀን፣ የአብሮነት ቀን፣ የመደመር ቀን፣ የኢትዮጵያ ቀን በሚል ስያሜ ይከበራሉ ፡፡
እኛም በዓሉን አስመልክተን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ከሆኑት ወይዘሮ ዘሃራ ኡሙድ ጋር ቆይታን አድርገናልⵆ
አዲስ ዘመን፦ እስከ አሁን በተከበረው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የተገኙ ዋና ዋና ስኬቶችን እንዴት መግለጽ ይቻላል?
ወይዘሮ ዘሃራ፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ላለፉት 17 ዓመታት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር ቆይቷልⵆ ሲከበርባቸው የመጡት የበዓል አከባበር ሂደቶችም አንድ አይነት ናቸውⵆ ነገር ግን በዓሉ በመከበሩ ውጤት ያመጣል ተብሎ የሚታሰበው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦችን አንድነትና ህብረ ብሔራዊነትን ማምጣት ነውⵆ ህብረ ብሔራዊነት ሲባል እንግዲህ ኢትዮጵያ 76 ብሔር ብሔረሰብ ነው ያላት እነዚህ ደግሞ የማያውቅ ዜጋም ያለ በመሆኑ እንዲሁም ኢትዮጵያ ሲባል እራሱ ብቻ የሚመስለው ሰው ስላለ እንዲሁም ህብረ ብሔራዊነቱን ዘንግቶ ኢትዮጵያዊነትን ጨፍልቆ አንድ ማድረግ የሚመስለውም ስላለ እነዚህን ጽንፍ የረገጡ አመለካከቶችን ወደመካከል አምጥቶ ልዩነቶቻችንን ተቀብለን በልዩነቶቻችን ውስጥ አንድነታችን ፈጥረን የሁላችን የሆነች ኢትዮጵያ በመፍጠርና በመገንባት በኩል ትልቅ ሚናን ተጫውቷልⵆ
በሌላ በኩል ደግሞ አገራችን ለሁላችንም የምትበቃ ከመሆኗ አንጻር እርስ በእርሳችን ተዋውቀን አንድነታችንን በመጣን ልክ አገራችን ላይ ተፋቅረን ተስማምተን ለመኖር ያስችለናል በዓሉ ደግሞ ይህንን ነገር በመፍጠር በኩል ሚናው ከባድ ነበርⵆ ከዚህ ከዚህ አንጻር በተለይም በዓሉ ባለፉት 17 ዓመታት በተጠናከረ ሁኔታ መከበሩ ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን ብሔር ብሔረሰቦች የማያውቅ ዜጋ እንዳይኖርም ትልቅ ሚና ተጫውቷልⵆ
በአሁኑ ወቅት በአለባበሱ የየትኛው ብሔር አባል መሆኑን ማወቅ የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናልⵆ በስያሜውም( በመጠሪያ ስሙ) ከየት እንደሆነ እንለያለንⵆ ይህ ደግሞ እኛ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ከእኛ ውጪ የሆኑ ዜጎችም በዚህ መልኩ ማን ከየት ነው የሚለውን ለመግለጽ መቻላቸው የተገኘው ውጤት ማሳያ ነውⵆ
በዓሉ ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ አንድነትን ከማምጣት በተጨማሪ እርስ በእርስ መደጋገፍን አብሮ እያስተማረ የመጣ ነው ፡፡በዚህም ብዙ ውጤቶች ተገኝተዋልⵆ ለምሳሌ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ሲያጋጥሙ ወንድም ለወንድሙ ቀድሞ ደርሷል፤ ሀዘኑን ሀዘን ፤ጉዳቱን ጉዳቱ አድርጎ በቦታው በመገኘት አጋርነቱን አሳይቷል ⵆ
ፌደራሊዝም ዋና መርሁ ዴሞክራሲ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ላይ ተመስርቶ ነው ፌደራሊዝም ተግባራዊ የሚሆነው፤ ከዚህ አንጻር ፌደራሊዝማችንን እውነተኛ ለማድረግ ደግሞ የባለፉት አመታት ጉዟችን አግዞናል ለዚህ ማሳያው ደግሞ ዘንድሮ ላይ 12ተኛ ክልል ምስረታ ለማብሰር እድል ፈጥሮልናልⵆ
አዲስ ዘመን ፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ከለውጡ በፊትና በኋላ ምን መልክ አለው ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ዘሃራ፦ ከለውጡ በፊት የነበረው አከባበር በሁለት ነገሮች ላይ የተመሰረተ ብቻ ነበርⵆ ይህ ሲባል በወቅቱ በዓሉ ይከበር የነበረው በጭፈራና በአመጋገብ ብቻ ነበርⵆ ሁሉጊዜም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል የሚለው ነገር ሲነሳ በአብዛኞቻችን አእምሮ የሚመጣው ጭፈራና ባህላዊ አመጋገባቸው ነበርⵆ በባህል ልብስ የተዋቡ ሰዎች ይገልጸናል የሚሉትን ዘፈንን ጭፈራ ሲያሳዩ መመልከት ነበር ሲከበርበት የነበረው ሂደትⵆ
በሌላ በኩልም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ከልማትና ዴሞክራሲ ጋር በተገናኘ መልኩ እንዲከበር ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸው የሚካድ አይደለምⵆ በዚህም ዕለቱን በማስመልከት የተሰሩ የልማት ስራዎች የሚጎበኙበት አጋጣሚም ብዙ ነበር ፤ ነገር ግን ከዴሞክራሲ አንጻር ምንም ሳይሰራበት ቆይቷልⵆ
ከለውጡ በኋላ ባሉት ጊዜያት እለቱ እውነተኛ ዴሞክራሲን ከማስረጽ ህብረ ብሔራዊነትንም ከአንደበት በዘለለ መልኩ ወደ መሬት እንዲወርድ በማድረግና ህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚያስችል መልኩ እየተከበረ ይገኛልⵆ ለዚህ አንዱ ማሳያው ደግሞ ከለውጡ በኋላ የተመሰረቱት አራቱ ክልሎች ናቸውⵆ በእነዚህ አራቱ ክልሎች መመስረት ውስጥ ደግሞ የተለያዩ የህዝብ ጥያቄዎች ተመልሰዋል፡፡ ለምሳሌ ከመካለል ከፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጥያቄዎች ሁሉ ምላሽ እንዲያገኙ መሆኑ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት የፈጠረ የበዓል አከባበር ነውⵆ
ዘንድሮ እየተከበረ ያለው 18ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ኢትዮጵያዊነትን ፤ወንድማማችነትንና አብሮነትን በሚጎላ መልኩ እየተከበረ ነው፡፡በዓሉ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ አሰባሳቢ እና ብሔራዊነት ትርክት መገንባት በሚያስችል መልኩ በመከበር ላይ ነው።የበዓሉ መከበርም አንድነቷ የተጠበቀ፣ ሕብረ ብሔራዊትና የተረጋጋች ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ያስችላል፡፡
አዲስ ዘመን፦ አሁንም ድረስ ማንነታችን አልታወቀም ድምጻችን አልተሰማም የሚሉ ጥያቄዎች አሉና በዓሉ የእነዚህን ወገኖች ችግር በመፍታቱ በኩል የሚኖረው ሚና እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ዘሃራ፦ እውነት ነው አሁንም ቢሆን የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎች ይነሳሉ፤ የማንነት ጥያቄዎች ግን ስለተነሱ ብቻ ምላሽ የሚያገኙ ሳይሆን የእውነትም እነዚህ ጥያቄዎች ተገቢነት አላቸው ወይ?ለሚለው ራሱን የቻለ መሟላት የሚገባው ሂደት አለⵆ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ይህንን ጉዳይ ብቻ የሚያይ በዳይሬክተር ደረጃ የተቋቋመ የስራ ክፍል አዋቅሯልⵆ ነገር ግን አሁንም ማንነታችን አልታወቀም ብለው ድምጻቸው እንዲሰማ የሚፈልጉ አካላት በማንኛውም ሰዓት ምናልባትም ከበዓሉ ጋር ተያይዞም ሆነ ሳይያያዝ ድምጻቸውን ያሰማሉ እግረ መንገዳቸውንም የሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓል በሆነው በዓል ላይም የራሳቸውን ሚና ይጫወታሉⵆ
በዓሉ እንግዲህ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ በሚያደርግ ደረጃ የሚከበር በመሆኑ ማንነቴ ተከብሮልኛል የሚልም አልተከበረልኝም የሚል ጥያቄ ያለውም ዜጋ አብሮ የሚያከብረው ነውⵆ ነገር ግን የማንነት ጥያቄን በተመለከተ አሁንም የማያቋርጡ ጥያቄዎች አሉ እነሱንም ለመፍታት ምክር ቤቱ በዘረጋው አሰራር መሰረት እያስተናገደ ነውⵆ
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል ሲከበር ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት ብዙ የአገር ሃብትም የሚባክንበት ሁኔታ ይስተዋል ነበርና ይህንን በማስወገዱ በኩል ምን አይነት ዝግጅቶች ተደርገው ነው ወደ በዓሉ የገባው?
ወይዘሮ ዘሃራ፦ በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያውያን በዓል ከመሆኑ አንጻር ወጪዎች መውጣታቸው አይቀርም ⵆ ነገር ግን የአገር ሃብት ለበዓሉ ተብሎ ሊባክን አይገባምⵆ ቀደም ሲል በነበረው ሂደት ክልሎች የበዓሉ አክባሪ ሲሆኑ ስታዲየም የመገንባት መንገድ የመስራት የእንግዶች ማረፊያ የማዘጋጀት ነገር ነበርⵆ አሁን ላይ ግን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ ሁሉም ዜጋ የራሱን ድርሻ የሚያበረክትበት ሲሆን እንግዶችን ደግሞ የማስተናገድ ሃላፊነቱ የህዝቡ ይሆናል ማለት ነውⵆ ለምሳሌ ዘንድሮ ጅግጅጋ ላይ በዓሉ ይከበራል በዚህ የበዓል አከባበር እንግዶች ከያሉበት መጥተው ከተማው ላይ ከደረሱ በኋላ እንግድነታቸው የመላው ሶማሌ ነው የሚሆነው የሚያበላው የሚያጠጣው የሚያሳርፈው ህዝቡ ይሆናልⵆ በዚህ ውስጥ ደግሞ የበዓሉ ዓላማ የሆነው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት በጣም ይጠናከራል ማለት ነውⵆ
በሌላ ጎን ግን ከጸጥታ ከመሰረተ ልማትና ከመስትንግዶ ጋር የተያያዙ የተወሰኑ ወጪዎች ሊኖሩ ይችላሉⵆ ይህ ወጪ ግን አዘጋጁን ከተማ ጨምሮ ፌዴሬሽን ምክር ቤትና ወኪሎቹን የሚልክ ክልል ሁሉ የሚጋራው በመሆኑ ማንንም የሚጎዳ በጀትም የሚባክንበት አይደለምⵆ
አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል እስከ አሁን ካለው ተሞክሮ የምንፈልገውን ፌደራሊዝም አምጥቷል ማለትስ ይቻላል?
ወይዘሮ ዘሃራ ፦ ፌደራሊዝም በዚህ በዓል ብቻ አይደለም የሚገነባው የዚህ በዓል ዋናው ዓላማ ደግሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ማጠናከር ነውⵆ ህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ከማጠናከር አንጸር የሚጠበቅበትን ውጤት አስገኝቷልⵆ በዛ ውስጥ ደግሞ ሌሎች ተደብቀው የቆዩ የማንነት የዴሞክራሲ የፍትሃዊነትና የመካለል ጥያቄዎች በየጊዜው ይመጣሉⵆ ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያውያን በፌዴራሊዝሙ ያላቸው እምነት የተጠናከረ መሆኑን ነውⵆ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ትክክለኛ የሆኑ የማንነትና የፍትሃዊነት ጥያቄዎች አሉ እንዲሁም ደግሞ የተለያዩ አጀንዳ ያላቸው ጥያቄዎች አሉ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ፌደራሊዝሙን የሚያጠናክር ተግባራት እየተከናወኑ ነውⵆ
የመጀመሪያው እምነት ሲሆን በዚህም ጥያቄዬ ይመለስልኛል ብሎ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄን ለምክር ቤቱ ማቅረብ በራሱ የፌደራሊዝሙን ውጤት ያሳያልⵆ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጥያቄዎች መጠየቃቸው ብቻ የፌደራሉዝሙን ውጤታማነት ያሳያሉ ማለት ስላይደለ ምክር ቤቱ ምላሽ ለመስጠት እየሰራው ያለው ስራ ጥሩ ነውⵆ
ሌላውና ዋናው ነገር ፌደራሊዝም የተጠናከረ ልንል የምኝንችለው የምናስባትንና የምንፈልጋትን ኢትዮጵያ በትክክል ማስረጽ ስለምንችል ነውⵆ ያቺ ኢትዮጵያ ደግሞ ህብረ ብሔራዊቷ ናትⵆ
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን በማስታረቅ በኩል በዓሉ የሚኖረውን ሚና እርስዎ እንዴት ይገልጹታል?
ወይዘሮ ዘሃራ፦ በተለያየ ሁኔታ ሊገለጹ የሚችሉ ጥያቄዎች አሉ ⵆአንዳንዱ ጸረ ሰላም በሆነ ሃሳብ ሌላው ደግሞ በመሳሪያ ተደግፎ የሚቀርቡ ጥያቄዎች አሉⵆ በነገራችን ላይ የተለያየን መሆናችንን ተቀብለን ማስተናገድ ባልቻልን መጠን አሁንም ችግሮች መከሰታቸው አይቀርምⵆ እንደ ምክር ቤትም ሁሉንም ጥያቄዎች የምናስተናግድባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸውⵆ ነገር ግን ጥያቄዬ አልተመለሰም እኔ አልተካለልኩም በሚል ግን ጠመንጃ እንስቶ የሚዋጋን መንገድ ዘግቶ ሰው የሚያግትን አካል በፌደራሊዝም ሳይሆን የሚመለሰው ራሱ በመጣበት መንገድ በልኩና በአግባቡ ነውⵆ
ሰላማዊ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ምላሽ የሚያገኙ ሲሆን አመጽ የተቀላቀለባቸው ደግሞ በአገሪቱ የጸጥታ ሀይሎች አማካይነት ምላሽ የሚሰጣቸው ይሆናልⵆ በመሆኑም ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ ህዝቡ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ ሰርቶ እንዳይበላ እንቅፋት የሚሆኑ ህገ መንግስታዊ መብትን የሚያፍኑ በመናቸው በመጡበት አግባብ የሚመለሱ ናቸውⵆ
ኢትዮጵያውያን ደግሞ በፌደራሊዝም በህብረ ብሔራዊነት አብሮ በመኖር ላቅ ያለ ልምድና አቅም ያላቸው እንደሆኑ ሁሉ በጸብ የመጣባቸውን ደግሞ እንዴት አድርገው አሳፍረው መመለስ እንደሚችሉ ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው ህዝቡ የጋራ ጥላቱን በጋራ አደብ የሚያስገዛ ይሆናልⵆ
አዲስ ዘመን ፦ በዓሉን አስመልክተው ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ወይዘሮ ዘሃራ ፦ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሄሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች አገር ናት፤ የብዙ ቋንቋዎች እና ባህል(ሎች) መገኛም፡፡ ሁሉም ብሄሮች እና ብሄረሰቦች እኩል መሆናቸዉንም ህገመንግስቱ አረጋግጧል፤ የባህልና የቋንቋ እኩልነትንም አረጋግጧል፡፡ በዚህም ሁሉም ብሄሮችና ብሄረሰቦች ባህላቸዉን የሚያሳዉቁበትና ቋንቋቸዉን ተጠቅመዉ እንዲማሩ እና እንዲዳኙበትም መደረጉ ለዚህ ማሳያ ነዉ፡፡
ቋንቋ መግባቢያ እንደመሆኑ የሀገርንና የዜጎችን የሚገልፅ ሲሆን ባህል ደግሞ የሰዎችን ማንነት እና የአኗኗር ዘይቤ የምንለይበት ነው፤ ሁለቱም መሰረታዊ የማንነት መገለጫዎች ናቸው፡፡ የኢፌዲሪ ህገመንግስትም ማንኛዉም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰብ እና ህዝብ በቋንቋዉ የመናገር፣ የመጻፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉን የመግለጽ፣ የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለዉ በህገመንግስቱ መደንገጉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ባህላቸዉን ለቀጣይ ትዉልድ ለማስተላለፍ እና በመከባበር ጸንቶ እንዲቆይ አንዱ የሌላዉን ተገንዝቦ በልዩነት ዉስጥ ተቻችለዉ እንዲኖሩ ያስችላል፡፡
የኢፌዲሪ ህገመንግስት ከመጽደቁ በፊት የቋንቋ እና የባህል እኩልነትም ሆኑ ሌሎች መብቶች በህገመንግስቱ የተደነገጉ ቢሆንም እኩልነት በስፋት ሰፍኖ ይታይ እንዳልነበር አንዳንድ ጽሁፎች ያመለክታሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ ዘመን የተለያዩ እና ብዙ ሆነዉ አንድነት በመፍጠራቸዉ ዉበት የተላበሱ እና የሌሎችን ቀልብ የሳቡ ህዝቦች የሚኖሩባት አገር መሆኗንም በተለያዩ ክልሎች ላይ የሚከበሩ ብሄራዊ በአላት ምሳሌ ኢሬቻ-በኦሮሚያ፣ ጨምባላላ-በደቡብ፣ አሸንዳ-በትግራይ፣ ሻደይ-አማራ ክልል ሰቆጣ ወዘተ የሚከናወኑ መንፈሳዊ ክበረ በአላት ላይ የሚታደሙ የዉጭ ሀገር ዜጎች ምስክር ናቸዉ፡፡ ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም የጸደቀዉ የኢፌዴሪ ህገመንግስትም የኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄሮች እና ህዝቦች በተወካዮቻቸዉ አማካኝነት ባጸደቁት ህገመንግስት ዋስትናቸዉን እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ሁለቱን አቻችሎ አንዱ የሌላዉን ባህልና ቋንቋ አክብሮ ለመጓዝ እንዲችል የሚረዳዉም ህዝቦች ልዩነታቸዉን እንደ ዉበት ቆጥረዉ መኖር ነዉ፡፡ ከ1999 ዓ.ም ጀምሮ ‘ሀ’ ብሎ ህዳረ 29 ቀን መከበር የጀመረዉ የብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀንም በህገመንግስቱ የተገኘዉ የዲሞክራሲ ስርአት ዉጤት በህዝቦች መረጋገጡን ያሳያል፡፡ ህገመንግስቱ በሰጣቸዉ መብት መሰረትም ዴሞክራሲያዊ መብታቸዉን፣ ቋንቋ እና ባህላቸዉን ጠብቀዉ ታሪካቸዉን እያቆዩ መሆኑን ያንጸባርቃል፡፡
በአጠቃላይ የአገራችነ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እስከአሁን ያከናወኗቸዉ የልማትና የዲሞክራሲ ስርአት ግንባተ ተግባረት ዋነኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑም ያስቻለዉ የእኩልነታቸዉ ነጸብራቅ ነዉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በአልን ስናስብ ካለፈዉ የጋራ ታሪካችን የገነባነዉን አዎንታዊ እሴቶች በጋረ ለመጠበቅና ይበልጥ ለመገንባት ቢሆንና ለነዚህ አላማዎችና መርሆዎች እዉን መሆን የጸና እምነት በመያዝ መሆን ይገባል፡፡
በመጨረሻም ሁሉም ኢትዮጵያውያንንና በዓሉን ለሚያከብሩ በሙሉ እንኳን ለ18 ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በሰላም አደረሳችሁⵆ ብዝሃነታችን አንድነታችን ነው፤ ብዝሃነታችንን ተጠቅመን አንድነታችንን ደግሞ ለአገራዊ አንድነትና እድገት እንድናውለው ሁላችንም የበኩላችንን እንወጣⵆ
አዲስ ዘመን ፦ ለነበረን ቆይት በጣም አመሰግናለሁⵆ
ወይዘሮ ዘሃራ፦ እኔም አመሰግናለሁ
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 29 ቀን 2016 ዓ.ም