ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ሰሜን ምዕራብ የሶሪያ ክፍል ከባድ ጦርነትን አስተናግዷል:: የሩስያና የሶሪያ መንግስት ጥምር ጦር በኢድሊብ፣ በአፖሎ እና በሀማ ቦታዎች ከባድ የሆነ ጦርነት ከሃይት ታሂር አል ሻም ከተባለ ታጣቂ ቡድን ጋር ውጊያ አድርጓል፡፡ ታጣቂ ቡድኑ ከአልቃይዳ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሲሆን እአአ 2019 ሚያዚያ 27 በሶሪያ መንግስት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ማድረሱ ይታወሳል፡፡
በቅርቡ የተከሰተው ጦርነት በሩስያና በቱርክ መካከል ተደርሶ የነበረው ጊዜያዊ የተኩስ ስምምነት በተለይ በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ አካባቢዎች የጣሰ ነበር፡፡ ባለፉት ወራትም የተወሰኑ የስምምነቱ አንቀፆች በተደጋጋሚ ሲጣሱ ነበር፡፡ እንደ ሶሪያ ሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሪፖርት በተከሰተው ጦርነት 500 ንፁሃን ዜጎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በተያዘው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር የቱርክ ወታደሮች ሁለት ግጭቶች ላይ ተሳታፊ ነበሩ::
የሶሪያ መንግስት ከቱርክ ሰራዊት ጋር ተዳብሎ የነበረ ሲሆን በተለይ በሰሜናዊ ሀማ የኩርዱሽ ታጣቂዎች ከህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) ጋር በመሆን በታል ሪፋትና በሰሜናዊ አፖሎ በሰነዘሩት ጥቃት አንድ የቱርክ ወታደር ተገድሏል:: ይሕ ጥቃት እያደገ በመምጣቱ ምክንያት በሩስያና በቱርክ መካከል ከፍተኛ የሆነ ክፍተት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የጠነከረ ግንኙነት ለማስቀጠል የገቡትን ስምምነት ለመፈፀም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
ምንም ሆነ ምን ሩስያና ቱርክ በሶሪያ ጉዳይ ያላቸውን መተባበር የሚቀጥሉት ለራሳቸው ፍላጎት ሲሆን በይበልጥ ግን በሶሪያ ጉዳይ የአሜሪካን ግፊት ለመቀነስ ነው፡፡ ነገር ግን ወሳኝ የሆኑ ልዩነቶቻቸውን ማስወገድ አልቻሉም፡፡ ሩስያ ቱርክ የገባችውን የተኩስ አቁም ስምምነት እያከበረች ባለመሆኗ ያላት ትግስት ያለቀ ይመስላል፡፡ ቱርክ በበኩሏ ደግሞ ሩስያ የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ)ን ከቴል ሪፋት ለማስወጣት የገባችውን ቃል ላትጠብቅ ትችላለች ብላ ፈርታለች፡፡
ሁለቱ አገራት በሶሪያ ጉዳይ የተስማሙ አይመስሉም፡፡ ቱርክ ከሩስያና ከአሜሪካ ጋር በመተባበር በምስራቅና በምዕራብ በኩል ጥቅሟን ለማስጠበቅ እየሰራች ትገኛለች:: በቅርቡ የተደገረው ወታደራዊ ጦርነት በሁለቱ አገራት መካከል ያለው አለመተማመን ምን ያክል እያደገ እንደሚገኝ ማሳያ ነው፡፡ እአአ 2019 ሚያዚያ 25 እና 26 በሩስያ፣ በቱርክና በኢራን መካከል ሰፊ ውይይት ተደርጓል::
በውይይቱ ሩስያ ቱርክ በሶሪያ መንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል ሰላም ሰፍኖ የህገ መንግስት አውጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም ግፊት ታደርጋለች ብላ ተስፋ ጥላ ነበር፡፡ ነገር ግን ቱርክ ስምምነቱን ልታስፈፅም አልቻለችም:: በመቀጠል በተያዘው የፈረንጆቹ ወር መጀመሪያ የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መቭሉት ቻቩሶግሉ ቱርክና አሜሪካ በሶሪያ ቱርክ ድንበር በሚገኘው በምስራቅ ኤፍራጠስ ወንዝ አካባቢ ሰላማዊ ዞን ለመፍጠር ጫፍ መደረሱን አበሰሩ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ንግግር ሩስያን ያበሳጨ ሲሆን በዚህም ቱርክ በምትፈልጋቸው በቴል ራፋትና በኢድሊብ ስፍራዎች ግፊቷን አጠናክራለች፡፡ ቴል ሪፋት በሰሜን አፖሎ የሚገኝ አነስተኛ ስፍራ ሲሆን የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) እአአ 2018 ቱርክ በከፍተኛ ወታደራዊ ጦርነት ከተሸነፈች በኋላ አካባቢውን እያስተዳደረው ይገኛል፡፡
ነገር ግን የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) ሁሉንም ስፍራ እያስተዳደረ አይደለም:: በአሁኑወቅት የቱርክ ወታደሮችና ቱርክ የምትደግፈው የሶሪያ ነፃ ወታደሮች ሰሜን ክፍሉን፣ ኢራን የምትደግፈው ጦር ደቡብ አካባቢውን እና የሶሪያ መንግስት ወታደሮችና የሩስያ ወታደሮች ደቡብ ምስራቁን እያስተዳደሩ ይገኛሉ፡፡
እአአ 2018 የካቲት ወር የኩርድ ታጣቂ ቡድን ከሩስያና ከሶሪያ ጋር ስምምነት አድርጎ ነበር፡፡ ስምምነቱ በአካባቢው የሩስያ ወታደሮችና የሶሪያ መንግስት ጦር እንዲሰማሩ ነበር፡፡ ይህ ስምምነት ቱርክን አስፈርቷታል፡፡ ሩስያና ኢራን ቴል ሪፋትን የማቋረጫ ዞን በማድረግ ቱርክና የሶሪያ ተባባሪ ሀይሎችን ለመጠበቅ ይፈልጋሉ፡፡
ቱርክ በበኩሏ አጠቃላይ ቦታውን በመቆጣጠር በአፍሪን ያጣችውን ድል ለማግኘት እና ማንቢጂን ለመቆጣጠር እንዲሁም የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) የያዛቸውን ቦታዎች በመውሰድ ቡድኑ ሽብርተኛ ነው ተብሎ እንዲፈረጅ ፍላጎት አላት፡፡ የቱርክ አጭር ጊዜ እቅድ አጠቃላይ የሶሪያ ቱርክ ድንበርን ለመቆጣጠር እና በምዕራብ ኤፍራጠስ ወንዝ እና በጋዛቲፕ አፖሎ መንገድ በመያዝ የቱርክ ምርቶችን ለሶሪያ ገበያ ማቅረብ ነው፡፡ ኢድሊብ ለቱርክ ወሳኝ የሆነ ስፍራ ነው::
የቱርክ ዋነኛ ፍራቻዋ የሶሪያ መንግስት አካባቢውንና በአማፅያኖች የተያዙ ስፍራዎችን ከተቆጣጠረ በሶሪያ ጦርነት ምክንያት ልታገኘው የነበረውን ትልቅ ጥቅም ልታጣ ትችላለች:: በዚህም ከፍተኛ የሆኑ የሶሪያ ስደተኞች ወደ ድንበሩ ሊሰደዱ ይችላሉ:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በቱርክ ሶሪያ ድንበር አካባቢና በምዕራብ ኤፍራጠስ ያላትን ቁጥጥር ሊገድብባት ይችላል:: በአጠቃላይ የሩስያና የኢራን ጫና እና የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) እንዲሁም በአሜሪካ የሚደገፈው የሶሪያ ዴሞክራቲክ ሀይል ቱርክን ከበዋታል፡፡
ኢድሊብ ለሩስያ በተመሳሳይ ወሳኝ የሆነችበት ምክንያት ሁለት ሶስተኛው ኤም 4 እና ኤም 5 ሀይ ዌይ መንገድ ከላካታ እስከ አፖሎ እና ከአፖሎ ወደ ደማስቆ ለማለፍ የሚያስችል ስፍራ በመሆኑ ነው፡፡ ይህንን ስፍራ መቆጣጠር የሶሪያን ኢኮኖሚ መልሶ ለማቋቋም ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ ሩስያ በተጨማሪም ሌሎች ስፍራዎችን መቆጣጠር ትፈልጋለች፡፡ በተለይ ምዕራብ ኢድሊብን የምትፈልገው በአካባቢው የሚገኙትን አማፂ ቡድኖች ለመደብደብ እንዲመቻት ነው፡፡
ይህን ፍላጎቷን ለማሟላት ሩስያ ለቱርክ ቀጥተኛ የሆነ አማራጭ አቅርባላታለች፡፡ ቱርክ ወደ ቴል ሪፋት እንድትስፋፋና በማድረግ ደቡብ ኢድሊብን እንድትለቅ ነው፡፡ እንደዚህ አይነት ስምምነቶች ለድርድር ማቅረብ አስቸጋሪ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉት፡፡ በመጀመሪያ ሩስያ የቱርክ አየር ሀይል ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት በአፍሪን ላይ ጥቃት እንዳያደርስ ከልክላ ነበር፡፡
በሁለተኛነት ደግሞ በኢድሊብ የቱርክ እግረኛ ወታደሮች ጦርነት እንዳያካሂዱ በመከልከላቸው ቱርክ ወደ አሜሪካ እንድታዘነብል አድርጓል፡፡ ሶስተኛ ደግሞ ኢራን፣ ሶሪያና የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) የሩስያና የቱርክ በቴል ሪፋት ስምምነት ላይ ተቃውሞ ስላላቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ እንደሚያሳየው የተገደበ ሰጥቶ መቀበል በሁለቱ ተስማሚ አገራት መካከል ሊፈጠር የሚችል ነገር ነው፡፡
ሩስያና ቱርክ በሁለቱ መካከል ያለው ፍላጎት እንዳይጋጭ ለማድረግ ሌሎችን በማይስብ መልኩ የማድረግ እድሎች አሏቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁለት ጉዳዮች በቱርክ ላይ ከፍተኛ የሆነ መወሳሰብ ያመጣባታል:: የመጀመሪያው ቱርክ ሩስያ ሰራሹን ኤስ 400 ሚሳይል ግዥ እንድታረዝም አሜሪካ ጠይቃታለች:: ይህን ማድረግ ከቻለች ምስራቅ ኤፍራጠስ አካባቢን እንደምትለቅላት ነግራታለች፡፡ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በቱርክና የህዝብ ጥበቃ ማህበር (ዋይ ፒ ጂ) መካከል ስምምነት ለመፍጠር እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡
ይህ አካሄድ ደግሞ ቱርክን ከአስታና እንቅስቃሴ የሚያስወጣት ሲሆን ከሩስያ ጋር ያላት ግንኙነትም ይሻክርባታል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቱርኮች ሩስያ በተቆጣጠረችው የኢድሊብ ይዞታ ምንም አይነት መብት ስለሌላት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሩስያዎች ከሶሪያ ተቃዋሚዎች ጋር የቆሙ በመሆኑ ዋነኛ የሶሪያ አማፅያን በኢድሊብ አካባቢ ይዞታቸውን በማጠናከር የቱርክ ይዞታን ሊቆጣጠሩ ይችላሉ::
ኢራን በቱርክና በሶሪያ መካከል የጀመረችው ድርድር ደካማ በመሆኑ ቱርክ በሶሪያ አማፅያን እየተጠቃች ትገኛለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁሉንም ለማግኘት መሞከር ለቱርክ ትክክለኛ ስትራቴጂ አይደለም፡፡ ለወደፊቱ የሚሻለው ነገር የምስራቅ ወይም የምዕራብ ኤፍራጠስ ወንዝ አካባቢዎች አንዱን መምረጥ አለባት፡፡ ለዚህ ደግሞ ቴል ሪፋት፣ ማንቢጅ ወይም ኢድሊብን ምንም ዋጋ ቢያስከፍልም አንዱን መልቀቅ ይጠበቅባታል፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካ በኤስ 400 ሚሳይል ግዥ ላይ ባሳየችው አቋም ቱርክ ኢኖሚዋን ከሚጎዳው የአሜሪካ ማዕቀብና ሩስያ ኢድሊብን በመቀማት ቱርክ በሶሪያ ተፅዕኖዋ እንዲቀንስ ከማድረግ ሁኔታዎች አንዱን መምረጥ ይጠበቅባታል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በቱርክና በሩስያ መካከል ያለውን ግንኙነት አሻሚ ያደርጉታል፡፡ በዚህ ምክንያት በሰሜን ምዕራብ ሶሪያ ተጨማሪ ጦርነቶች ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ብርሃን ፈይሳ